Saturday, 31 December 2022 13:09

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    
              “ሟችም የሚሞተው ለዓላማ፤ ገዳይም የሚገድለው ለዓላማ”
                  ሌንጮ በዳዳ

       ለምን ዓላማ እና ለማን ዓላማ ለመሞት ዝግጁ ናችሁ? ለአላማ መሞት አሪፍ ነገር ነው አይደል? አዎ! አሪፍ ነው ለብዙኀኑ፤ .... በግሌ ለኔ ግን አይደለም፡፡
በያዝኩት ነገር ምክንያት ሞት ከመጣብኝ፣ ምላሴን አውጥቼበት ላሽ እላለሁ እንጂ፣ የሞኝ ጀብደኛ ሞት አልሞትም፡፡
በመሰረቱ አላማ የለኝም፣ ቢኖረኝም ሙትልኝ የሚል አይደለም፡፡ እንዲያ ካለማ ጠላቴ እንጂ አላማዬ ስላልሆነ ዶሮ እስኪጮህ ሳልጠብቅ እክደዋለሁ፡፡ ሃይማኖትም ለጊዜው የለኝም፣ ለነገሩ እንዲያው ለጊዜው፣ ለጊዜው ብዬ ልለፈው እንጂ ለዘላቂውም አይኖረኝም፡፡ ሃይማኖትና እምነት ይለያያል አይደል ግን? ….ሀገር አለኝ በእርግጥ፡፡ ለሀገሬ ግን አልሞትላትም፡፡ ብችል እኖርላታለሁ፣ እኖርባታለሁ እንጂ ለምን ስል እሞትላታለሁ፡፡ እሷስ ምን ቆርጧት ሞቴን ትሻለች? አንድ ደረጄ ዓለማየሁ የተባለ የዛ ዘመን ሰው (የመኢሶን አባል የነበረ)፣ በእፎይታ መፅሄት ላይ ለአንድ የሕወሓት ሰው በፃፈው የመልስ ደብዳቤ ውስጥ እንዲህ ይላል፤
“ወንጀሉ የሚጀመረው መግደል ላይ ሳይሆን፣ ለመሞት ዝግጁ መሆን ላይ ነው፡፡ ለቅዱስ ዓላማ መሞት ቅዱስ ይሆንና እርኩስ የተባለን ዓላማ ተከታይ መግደል ወንጀል መሆኑ ይቀራል” ይላል፡፡ ዝቅ ብሎም፤ “እየፎከረ የሚሞት፣ እየዘፈነ ቢገድል ምን ይገርማል?”
ምስለ- ሴጣን የሆነችው ደርግ በዘመኗ ሀገሩን፣ ህይወትን እየተኛ ሞትን እንዲያልም` አድርጋው ነበር … “አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት!፣ አብዮት ልጆቿን ትበላለች፣ ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር፣ አረንጓዴ፣ ቡራቡሬ….. ሽብር… ሞት! … ካካካ ጥይት ዷዷዷ… ጠብመንጃ!
ስንቱ ለሀገሩ ሞተ፣ ስንቱ በሀገሩ ሞተ? ስንቱ ለዓላማው ሲል ስንቱን ገደለ? ስንቱ ዓላማውን እየዘመረ ደረቱን ነፍቶ ወደ መቃብሩ ነጎደ? የስንቱ ዓላማ ትክክል ነበር? ከሞታቸው ሀገራቸው ምን አተረፈች?
በርግጥ ሞታቸውን እያቃለልኩ አይደለም። ከውድ ህይወታቸው አንፃር ግን ሞታቸው የቀለለ ነው፡፡ (ለነገሩ ስለ ህይወት ውድነት እርግጠኛ መሆንም አይቻልም)
መቼም ያ ዘመን፣ ሞት በዓላማ ወለል ላይ የሚደንስበት እየዘፈኑ መሞት የበዛበት ነበር፡፡
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በግለ ታሪክ መፅሐፋቸው እንዲህ ይላሉ፤...
“ለዓላማችን ነው ብለን የገባንበት የፓለቲካ ዓለም ምን እንደነበርና ከሞት ጋር ስንጫወት የነበረውን የዥዋዥዌ ጨዋታ አስታውሼ በጣም አዘንኩ” (ገፅ 72)
….ብዙ ሰው “ለሃይማኖቴ እሞታለሁ፣ ለሀገሬ እሞታለሁ” ሲል ይገርመኛል፡፡
የሃይማኖት አላማ ህይወትን መስጠት እንጂ ህይወትን ማጥፋት ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው። ሀገር የሚኖሩባት እንጂ ማገዶ የሚሆኑባት ከሆነችም ነገር ተበላሽቷል፡፡ በመሰረቱ ማንም ለማንም አይሞትም፡፡ ማንም ለማንም በመሞቱ ለማንም የተሻለ አለም አያመጣም፡፡ ለሁሉ ነገር እራሳቸውን የመስዋት በግ አድርገው ማቅረብ የሚወዱ ሰዎች የነብሳቸውን ሰንካላነት በሞታቸው ሊያቀኑ የሚሞክሩ ሰነፎች ነው የሚመስሉኝ፡፡
የሚገርመው፣ ሟችም የሚሞተው ለዓላማ፤ ገዳይም የሚገድለው ለዓላማ መሆኑ ነው!
ወዳጄ፣ ዓለም ከምናየው እጅግ የሰፋ ነው። እና በዚህ ሰፊ ዓለም ውስጥ ዓላማ በሚባል ጠባብ በረት ውስጥ የተከረቸምን መጋጃ መሆን አለብን? ... መሆን አለብን ወይ ነው እምለው?
ኧረ ለጠላቴም አልመኝም ... ለነገሩ እኔ ጠላት የለኝም
Moral of the story:- ሁልሽም ውኃ እንዳገኘች እንቁራሪት ትንሽ ነገር (ጠብታ ውኃ) ስታገኝ ትልቅ ነገር የሰራሽ ወይም ያገኘሽ መስሎሽ ከተግባርሽ በላይ ድምፅሽን ስታሰሚ ጠላትሽን በራስሽ ላይ አታንቂ፣ ጠንቀቅ በይ!

_________________________________________________

                    በእንተ ትግራይ
                        በእውቀቱ ስዩም


       የሚከተለውን ልጥፍ፥ አምና  በፈረንጅ አቆጣጠር ፌብሯሪ 28፥ 2021 ጽፌ ያጋራሁት ነው፤ ያኔ ጦርነት የተጧጧፈበት ወቅት  የተጻፈ ቢሆንም፥ ዛሬም ትርጉም ይኖረዋል ብዬ በድጋሚ አምጥቸዋለሁ፡፡
ስለትግራይ ሲነሳ ብዙ ይነሳል ፤ እኔ ጭሮ አዳሪ ስለሆንሁ መጀመርያ የማስታውሰው የጽሁፍ ሰዎችን ነው፤ አለቃ ተወልደ መድህን፥ ደብተራ ፍስሀ ወልደጊዮርጊስ፥ ገብረህይወት ባይከዳኝ እና ስብሀት ገብረእግዚአብሄር፥ ከትግራይ ምድር የተሰጡኝ የኢትዮጵያ ገጸበረከቶች ናቸው::
 የዛሬ ሶስት መቶ አመት ገደማ የተጻፈ የታሪክ ድርሳን አግኝተህ ብታነብ፥ ትግራይ በእርሻ፥ በቀንድ ከብት እና በሌላው ምርት የበለጸገች እንደነበረች ትረዳለህ:: ከዚያ ያ ሁሉ አዱኛ ምን ሆነ? ጂኦግራፊ እና ታሪክ ከኛ ምርጫ በላይ የሆኑ ነገሮች ናቸው፤ የትግራይ ምድር የኢትዮጵያ ዋናው በር ነው:: የውጭ ወራሪ የወረወረው ሁሉ ቀድሞ እዚህ በር ላይ ይወድቃል፤ በውስጥም የሀያላን መደባደቢያ መድረክ ሆኖ ቆይቷል:: በቴዎድሮስ ዘመን (1861) አገው ንጉሴ የሚባለው ሸፈተና ወደ አክሱም አፈገፈገ፤ ንጉሱ ከሸዋ ተነስተው አክሱም ድረስ ገስግሰው ገጠሙት፤ ከቴዎድሮስ ህልፈት በሁዋላ፥ የላስታው ጎበዜ፥ ተክለጊዮርጊስ ተብለው ነገሱ፤ ካሳ ምርጫ የተባለው ወደረኛቸው አልገዛም አለ፤ አድዋ ላይ ተቀጣጥረው ተፈሳፈሱ፤ ከሁለቱም ወገን ብዙ ሰው አልቆ ተክለጊዮርጊስ ቆስለው ተማረኩ፤ ካሳ ምርጫም” ዮሀንስ አራተኛ” ሆነው ነገሱ::
ዮሀንስ ሞተው አጼ ምኒልክ ሲነግሱ እነ መንጌ አሻፈረኝ አሉ፤ ደሞ በዚያ ዘመን መንጌ ምን ይሰራል ለሚለኝ አንባቢ መንጌ ያልኩት  የአጼ ዮሀንስን ወራሽ ራስ መንገሻን ነው፤ አጤ ምኒልክ ወደ ትግራይ ወጡና ውጊያ ገጠሙ፤ ከአመታት በሁዋላ ደግሞ ጣልያን በጀልባ አቆራርጦ መጣና “በራሳችሁ ሜዳ ይዋጣልን” አለ፤  በአምባላጄ በመቀለ እና በአድዋ ጥይት ዘነበ፤ ከቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዘመን ጀምሮ የነበረውን የጦርነት ታሪክ ብዙ ሰው ስለሚያውቀው ልግደፈው::
ይሄ ሁሉ በአረር ሲለበለብ፥ በመድፍ ሲታረስ የኖረ መሬት ሳር ማብቀሉም ይደንቃል፤ ባጠቃላይ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ፥ በህይወት መቆየትና ወልዶ መሳም በራሱ ቶንቦላ ነው፡፡
ለማንኛውም፥
ለአጥቂዎች የእጃቸውን ይስጣቸው፤ ጌቶችም ስራቸው ያውጣቸው፤ አርሶ ነግዶ፥ ከሞላ ጎደል ቡና እየተጠራራ የመከራና ተድላ ኑሮ እየተጋራ የሚኖር ህዝብ፥ ግፍ ሊፈጸምበት አይገባም::
በቁም ነገር የጀመርኩትን ጽሁፍ በቁጭ-ነገር እንድዘጋው ይፈቀድልኝ፥ ከአሜን  ባሻገር “የተባለውን መጽሀፌን ለመጻፍ በየከተሞች ስዞር አድዋን አዲግራትን አክሱምን እና መቀለን ጎበኘሁ፤ አንድ ቀን ወዳጄ መሀመድ ሳልማን መቀለ ዩኒቨርሲቲ ጋብዞኝ፥ ውዬ ሳበቃ ወደ ሆቴሌ የሚመልሰኝን ባጃጅ ተሳፈርሁ፤ “አብርሀ ካስል“ የተባለው ሆቴል ስደርስ ወረድኩና “ሂሳብ ስንት ነው?" አልኩት ባለ ባጃጁን፤
“ዙ ብለህ ደስ ያለህን ስጠኝ” ሲል መለሰልኝ፤ ከዚያ  በፊት ሌላ ባጃጅ ያስከፈለኝ አስር ብር ነው፤ ይሁን እንጂ የዚህኛው ልጅ ትህትና ልቤን ስለነካው፥ መልኩም ኪሮስ አለማየሁን ስለሚመስል፥ ከባንክ የወጣ ትኩስ አምሳ ብር አውጥቼ ሰጠሁት፤ ልጁ እሳት ለብሶ፥ እሳት ተንተርሶ እንዲህ አለኝ፥ “ዋይይይ! ብር ከሌለህ የለኝም አትልም እንዴ?”

__________________________________________________________

                    የኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ የመኪና ሙዚየም
                      ዋሲሁን ተስፋዬ



           ማልደው መነሳትን የለመዱት ከልጅነታቸው ነው፤ በጠዋት ይነሱና የተለመደ ፀሎታቸውን አድርሰው ፡ ከተቋቋመ ከአርባ አመታት በላይ ወዳስቆጠረውና ፡ አራት መቶ ሺህ ዶሮዎች ወዳሉበት ፡ የዶሮ እርባታቸው ፡ ወይም ወደ ትልቁ ሰው ሰራሽ የአሳ እርባታ ጣቢያ ..... ወይ ደግሞ. ... ከሰፋፊ የእርሻ ስፍራቸው መሀከል ወደ አንደኛው ሄደው ፡ ግብርናው እንዴት እየሄደ እንደሆነ ጎብኝተው ፡ በማሳው ውስጥ ወዲያ ወዲህ ሲሉ ይቆዩና..... በናይጄሪያ ውስጥ አርባ ሰዎች ብቻ በሚነዱት .. ዘመናዊ ሞዴል ሮልስ ሮይስ ፋንቶም መኪናቸው ፡ ወይም በግል ሄሊኮፕተር ....... ካሏቸው ከ18 በላይ ዘመናዊ ቪላዎች ወደ አንዱ ሄደው እረፍት ያደርጋሉ። በነገራችን ላይ እኚህ አዛውንት ከዚህ ፋርም ብቻ በቀን ከሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ያገኛሉ።
ይህ የቀን ገቢ የዛሬ ሀያ አመት አካባቢ የከፈቱትን እና በየእለቱ 10 ቶን የፓልም ዘይት የሚያመርተውን ግዙፍ ካምፓኒ ገቢን አይጨምርም። በነዚህ እና በሌሎች የገቢ ምንጫቸው በሚያገኙት ፡ ፎርብስ፡ ከአፍሪካውያን ቢሊየነሮች መሀከል መዝግቧቸዋል።
ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ ፡ ወይም በሀገሬው አጠራር “ባባ” ....አሁን አሁን ፡ ከእድሜ ጋር በተያያዘ ፡ የከሰአቱን ጊዜ የሚያሳልፉት ፡ ብዙ ሚሊዮኖችን አውጥተው፡ ከስልጣን ከተሰናበቱ በኋላ በገነቡት እጅግ እጅግ እጅግ በጣም ትልቅ በሆነው ፕሬዝደንሽያል ቤተ-መጻህፍታቸው ውስጥ ነው። ይህ በስማቸው ያሰሩት ግዙፍ ቤተ መጻህፍት ፡ በውስጡ ፡ የስብሰባ ማእከላት ፡ የወጣቶችና የህፃናት መዝናኛዎች. . እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ያካተተ ሲሆን በውስጡም 42 ሚሊየን የሚሆኑ መጻህፍትና መዛግብት ተሰባስበውበታል። ( 42 ሚሊየን)
ይህ ትልቅ ቤተ መጻህፍት ካካተታቸው ነገሮች መሃል አንደኛው ፡ በእድሜ የገፉ አዛውንቶች ተሰባስበው ፡ ትዝታቸውን ልምዳቸውን ፡ የሚያወጉበት ፡ ብቸኝነት ሳይሰማቸው ፡ የአዛውንትነት እድሜያቸውን ያለድብርት እንዲያሳልፉ ለማድረግ ታስቦ የተሰራ ክበብ ነው ። ሌላው በዚሁ ላይብረሪ የሚገኘው ደግሞ ፡ የመኪና ሙዚየም ነው። ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ በተለያዩ ጊዜያት ከገዟቸው መኪናዎች ብዛት የተነሳ. .. የመኪና ሙዚየም ለመክፈት ተገደዋል።
በዚህ የመኪና ሙዚየም ውስጥም ፡ ካሉት ስብስቦች መሀከል. . በልጅነታቸው ይነዱት የነበረው ፡ ብስክሌት ፡ የመጀመሪያ መኪናቸው የሆነችው ቮልስዋገን .... የድሮ ሞዴል ፔዦ 504 ን ጨምሮ ፡ ዘመናዊዎቹ ላንድክሩዘር ፕራዶ .... መርሰዲስ S-550 .... ሌክሰስ LX570 ... የተለያየ ሞዴል ያላቸው ሮልስ ሮይስ መኪኖችና ሌሎች ብዛት ያላቸው ተሽከርካሪዎች እና ሁለት የግል ሄሊኮፕተሮች ይገኙበታል። ከነዚህ ሙዚየም ውስጥ ካሉ ብዛት ያላቸው ተሽከርካሪዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ፡ በመርሰዲስ እና በሮልስ ሮይስ ኩባንያ ፡ ለኚህ ሰው ተብለው በልዩ ትእዛዝ የተሰሩ ናቸው።
የሰማንያ አምስት አመቱ አዛውንት ፡ .የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ፡ የአሁኑ አደራዳሪያችን ፡ ናይጄሪያዊው ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ ላለፉት አርባ አመታት በትላልቅ የግብርና ስራዎች ላይ ተሰማርተው ፡ ሀብት ማፍራት የቻሉ ፡ ሀገራቸውን በቅንነት አገልግለው የስልጣን ዘመናቸው ሲያበቃ ፡ ያላንዳች ኮሽታ ስልጣናቸውን በሰላም ያስረከቡ ፡ ከዛም በኋላ በተለያዩ ሰብአዊ አገልግሎት እየተሰማሩ ያሉ ፡ ከባለፈው አመት ጀምሮ ደግሞ ፡ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ ለማድረግ የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ እስከዛሬዋ እለት ድረስ የዘለቁ  ሰው ናቸው።

________________________________________________

                   ከቅዠት ወደ መራራ ሀቅ
                       ሙሼ ሰሙ


         ሁለት ዓመት ከፈጀ እጅግ አሰቃቂና ከፍተኛ ዋጋ ካስከፈለ አውዳሚ የቀቢጸ ተስፋ ጦርነት በኋላ በማን አህሎኝነት ተወጥሮ ማብቂያ በሌለው የጦርነት አዙሪት ውስጥ በመዳከር ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ዜጎችን ሕይወት ከመቅጠፍና ንብረት ከማውደው በስተቀር አንዳችም ትርፍ እንደማይኖረው መረዳት ከቻልክ፣ በሕዝብ ላይ ተስፋ የሚያጭርን የሰላም በር የማንኳኳት እድል እንዳለህ የመቀሌውን ጉዞና ሂደቱን ለታዘበው ትልቅ ትምህርት ነው።
መነሻው ከየትኛውም ወገን መንጭቶ ወይም አንዳንዶች እንደሚገምቱት በሃያላን መንግስታት ተጽእኖ የተተገበረ ሊሆን ይችላል። ተወደደም ተጠላ የሰላም ድርድሩ፣ የመቀሌው ጉዞና በመቀሌ ከተማ የተደረገላቸው አቀባበል ለድምዳሜ እንጭጭ ቢሆንም ውጤቱ ያልተጠበቀና እያደገ ሊሄድ የሚችል አስደማሚ ክስተት መሆኑ አያጠራጥርም ።
የተንጸባረቀው የይቅር ባይነት መንፈስም ለሀገሬና ለሕዝቤ ደህንነትና ሰላም እቆረቆራለሁ የሚል ዜጋ ላይ ሁላ መጋባት የሚችልና መጋባት ያለበት ዘመን ተሻጋሪ ውሳኔ ከመሆኑም በላይ ጦር ሰባቂነትና ሟርተኝነትም ሰላም በመሻት ሊሟሽሹ የሚችሉ ስለመሆናቸው ፍንጭ የሰጠ ሂደት ነው።
በእርግጥ የጦርነቱ ሰበብም ሆነ መዘዘኞቹ ፖለቲከኞች እንጂ ሕዝቦች አልነበሩም፣ ወደፊትም ሊሆኑ አይችሉም። ዛሬ ላይ ፖለቲከኞቹ ስለታረቁ የጦርነቱ ታሪክና የቀውሱ ምዕራፍ አይዘጉም።
በፖለቲከኞች ሰበብና ቆስቋሽነት ወደ ጦርነት የተማገደና ለእርስ በእርስ ጥላቻ የተዳረገ ሕዝብ ሞልቶ ስለተረፈ በፖለቲከኞች የተጀመረው ሰላምና ይቅር ባይነት ወደ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አድጎና ጎልብቶ ማየት ያስፈልጋል። ከገጠመን ሀገራዊ ቀውስ ለመሻርም ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ህዝብም መፈወስ መቻል አለበት።
ጦርነት ከሚፈጥረው ሰብአዊ ቀውስ፣ ከሚያደርሰው ቁሳዊ ውድመትና ከሚፈጥርብህ የማይጨበጥ የአሸናፊነት ቅዠት በኋላ ምኞትህ አለመሳካቱን ስትረዳ የምትማረው መራራ ሀቅ ቢኖር፣ ጦርነት በደረሰበት ላለመድረስ በፍርሃት በመሸሽ፣ የትኛውንም ዓይነት ግለሰባዊ ክብርህን ተራምደህ ሰላምን መናፈቅና እርቅን መሻት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውም ይኸው ነበር። ከቅዠት ወደ መራራ ሀቅ መሸጋገር።
በመጨረሻ ማለት የምፈልገው ነገር፣ አምላካችን በከንቱ ጦርነት የሞቱ ወገኖቻችንን ነፍስ በገነት ይቀበል። በስነልቦና ለተጎዱትንና በማህበራዊ ቀውስ ለተመቱ፣ ሀብት ንብረታቸውን ላጡት ወገኖች መጽናኛን ይላክ። የሰላም ጅማሮውንም በጸና መሰረት ላይ ያቁምልን። አሜን።


Read 1536 times