Saturday, 31 December 2022 13:16

“የሌኒን የገና በዓል”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

  ሁላችንንም ሰብስቦ ስለ ገና በዐል አከባበርና በቴሌቪዥን ጣቢያችን ስለሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ውይይት እንዳለ ከነገረን ሣምንት አልፎታል፡፡ የዚህ ዐይነት ስብሰባና ውይይቶች ሌላም ጊዜ ቢኖሩ ያሁኑ ግን የተለየ እንደሚሆን ገምተናል፡፡ አለቃችን በብዙ ነገሩ ለየት ያለ ሲሆን ነገሮችን ውስጥ ድረስ ገብቶ ለማየት የሚመኝና ከሚያምንበት ርዕዮተ ዓለም ጋር ለማጣጣም መከራ የሚያይ ነው፡፡ በዚህ ፀባዩ ብዙዎች ደስተኛ የሆኑ አይመስሉም። እንዲያውም ቅፅል ስም ያወጡለት አያሌ  ናቸው፡፡ ከሁሉም ይልቅ ጎልቶ የተለመደው ቅጽል ስሙ “ሌኒን” የሚለው ነው፡፡ ሁሌም፤ “ሌኒን ምን አለ?.... ሌኒን…ምን ተፈላሰፈ?...” እየተባለ ይወራል፡፡ አለቃችን ስሙ ሰለሞን ይባላል፡፡
ዐይኑን እያንዳንዳችን ላይ እያሳረፈ፤ “..እስቲ የገናን በዓል  ልታከብሩ ያሰባችሁበትን ምክንያት ንገሩኝ!...”
ሲል ጠየቀ፡፡
ሁሉም ሰው እርስ በርሱ ተያየ፡፡
“እኛ መች ጀመርነው?...ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲከበር የቆየ በዓል!” አንዱ ጋዜጠኛ የሰጠው መልስ ነው፡፡
“አሃ! ማንም የፖለቲካ መሥመር የሌለው ሰው ያከበረውን ሁሉ ልታከብሩ ነው ታዲያ?....” አለ አለቃችን፡፡
“መቸም እኛ ባናከብርም ዓለም ያከብረዋል ጌታዬ!”  አለ፤  ደራሲው ጋዜጠኛ ወዳጄ ፈገግ ብሎ፡፡  
“እሺ ክርስቶስ ለምን ተወለደ?”
“እርሱን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እናገኘዋለን፤ ይልቅ እኛ ይህንን በዐል በየትኛው መንገድ፣ በምን ቅርፅ ልናዘጋጀው እንችላለን፤ የሚለው ላይ ብንወያይ ይሻላል አቶ ሰለሞን--” ሌላ ጋዜጠኛ የሰነዘረው አስተያየት ነበር፡፡
ኮስተር አለ አቶ ሰለሞን፤ “…ለምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ በበረት ውስጥ ለምን ተወለደ? ... ለምን ወደ ጭቁኖች ቤት ገባ? …ለምን ከባለጠጎች ጋር አልኖረም?....”
ብዙ ሰው ወንበሩ ላይ ተሻሸ፡፡ ሁላችንም ይህ ሰውዬ ደግሞ ኢየሱስንም ፖለቲከኛ ሊያደርገው አስቦ እንዳይሆን ሲል መስጋቱ አልቀረም፡፡ አለቃችን ቀጠለ፡፡
“አያችሁ!... ኢየሱስን ማየት ያለብን ከሃይማኖቱ አንጻር ብቻ አይደለም፤ ከልማቱ አንፃር እንዴት ሊታይ ይችላል?... ለነበረበት ማህበረሰብ የፈጠረው ፋይዳ ምንድን ነው? በጊዜው የነበረው ገቢዎችና ጉምሩክ ገቢውን እንዲሰበስብ ያስተማራቸው ትምህርቶች ቀላል አልነበሩም፡፡ ሰዎች ግብር እንዲከፍሉ በአደባባይ ያበረታታ ነበር፡፡ ይህንን ወደ ሚዲያው ልናመጣ ይገባል---”
ድንገተኛ  ሣቅ የስብሰባውን መንፈስ ቀየረው፡፡
“እኛ ልማታዊ ጋዜጠኞች ነን፤ ነገሮችን የምናይበት ዓይን፣ መዝናኛን ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ፋይዳውን መጨመር አለበት፡፡… የሀገር ገፅታ ግንባታንም ሊያካትት ይገባል!”
ከመካከላችን አንዱ እጁን አወጣና፤ “…እኛን ወደ ነገረ መለኮት ውስጥ የሚያስገባን ምንም ነገር የለም፤ ይህ የሃይማኖት አባቶች ሥራ ነው። ለምን በዓሉ እንደሚከበር፣ ፋይዳው ምን እንደሆነ… መናገር ያለባቸው እነሱ ናቸው፡፡”
ሰለሞን ወዲያው ተቀበለውና፤ “…ጥሩ ብለሃል፤ … እኛ ግን የሃይማኖት አባቶችን ሀሳብ አይደለም የምናስተጋባው፡፡ በራሳችን አቅጣጫ በዓሉ፣ ለህዝቡ ያለውን ጠቀሜታና ልማታዊ  ገፅታ እናሳያለን፡፡… ለምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ ለዘነጋናቸው እርብቶ አደሮች የነበረውን ፍቅር የምናይበት አጋጣሚ አለ። ለምንድን ነው ትልቅ ሆቴል ውስጥ ገብቶ ያልተወለደው?... ለምን በከብቶች በረት ውስጥ ተወለደ? ይህ ራሱ ለአርብቶ አደሮች ያለውን ወገንተኝነት ማሳያ ነው---!”
አሁንም ብዙዎቻችን ሣቅን፡፡
“አትርሱ እንጂ በኋላም ወደ ኢየሩሳሌም የገባው በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ነበር፡፡…. ይህ ነው የህዝብ ወገንተኝነት መሆን--! እሺ እናቱ ማርያምና ዮሴፍ ለምን ወደ ቤቴልሄም ሄዱ?... መቼም ለህዝብ ቆጠራ አይደለም። ይህስ ከልማት አንጻር ተባባሪነታቸውን አያሣይም?... ይህን ሁሉ መገምገም አለብን። ዝም ብለን የፈረንጅ ዛፍ ተክለን፤ መብራት ብልጭ ድርግም ማድረግ አይደለም፡፡ ጋዜጠኞች ይህንን ማስተጋባት ይጠበቅብናል። ልዩ ዓይን ሊኖረን ይገባል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የክርስቶስ ልደት መከበሩ ፋይዳው ምንድን ነው?... ወደ መሬት ሲወርድ የሕዝቡ ተጠቃሚነት ምን ያህል ነበር?”
አንደኛው ጋዜጠኛ እጁን አወጣ፡፡
“ምንድን ነው? ነገሩን ፖለቲካ አደረግነዋ?... ይህ እኮ የእምነት በዓል ነው!”
“በእምነት ውስጥ ፖለቲካ መኖሩን የምናጣው አይመሥለኝም!”..ሰለሞን መለሰ፡፡
“በደንብ ከመረመርነው እኮ ኢየሱስ የጭቁኑ ህዝብ አጋር እንደነበረ የሚያሣይ የልደት በዓል ነው፡፡ ዮሴፍ አናጢ ነበር፤ ኢየሱስም  በልማቱ ተሣታፊ ሆኗል፡፡ እንደ ዛሬ በማህበር ባይደራጅም ሠራተኛና ሥራ ፈጠራን የሚያበረታታ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ሙስናን ተቃዋሚ ነበር፡፡ ኪራይ ሰብሳቢዎች ቤተ መቅደስ ገብተው ምንዛሬ ሲሠሩ፣ ቀረጥ ያልተከፈለበትና ህገ ወጥ ንግድ ሲነግዱ ተመጣጣኝ እርምጃዎችን የወሰደ የህዝብ ወገን ነው፡፡ ይህን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ ልዩ የገና በዓል የቴሌቪዥን ፕሮግራም ነው መሰራት ያለበት፡፡
“አያችሁ -- ለለውጥ፣ ለብልፅግናና ለልማት ነው መሥራት ያለብን፡፡ የኛ ሀገር ደራሲ ስለ ድህነት ከማውራት ያለፈ ከድህነት ስለምንወጣበት መንገድ አያሣይም፡፡…በዛብህና ሰብለ ሳይጋቡ ሞቱ፤ አበራ ወርቁ ታሠረ፣ አደፍርስ ለውጥ እንዳማረው ተገደለ-- ወዘተ፡፡ ስኬት ያሥፈልገናል --- ሰዎች፡፡ የሚጨበጥ ተስፋ--- ተስፋ --”
ይህ ንግግሩ ትንሽ ልባችንን ቆንጠጥ አደረገው። ፖለቲካውን እየሸሸንም ቢሆን ውስጡ ያለው አንዳንድ ጥዝጣዜ አሳከከን፡፡ እጄን አወጣሁ። ትክ ብሎ አየኝና መነፅሩን ከአፍንጫው ወደ ላይ ከፍ እያደረገ ዕድሉን ሰጠኝ፡፡  
“ደራሲያኑ አይደሉም መንገድና መልካም ህይወት የከለከሏቸው ---- መሪዎቻቸው ናቸው፡፡ ሁሉም በጨቋኝ ገዢዎች ሥር ተስፋቸው ተዳፍኖ፣ ህይወታቸውን በእንባና በሥቃይ ያሳለፉ ናቸው። ደራሲያኑ እውነቱን ነው የጻፉት!” ብዬ ሃሳቤን ሰነዘርኩት፡፡
በማፌዝና በንቀት ዓይነት ፈገግ ብሎ ሲያየኝ፣ አንዳች ነገር ሊጥልብኝ እንደሆነ ገብቶኛል፡፡
“ግን ከዚያ ያለፈ ሀቅ አለ፡፡ ለምሳሌ ስለ ልደት በዐል ስታስብ ሞትንም አትረሣም…ግን ከዚህ ባለፈ ከእምነታችን ውስጥ ለፖለቲካችን የምናመጣው ሀቅ አለ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶ ሞተ፤ ነገር ግን ተነሳና ሌሎችንም ከሞት አስነሳ፤ ለምን ይሄን ተስፋ ወደ ሌላው  አናጋባም? ለምን አንቆጭም?”
ደሞ ምን ሊያመጣ ነው? ብዬ አፈጠጥኩ፡፡
“የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎች መዋጋት እንዳለብን ኢየሱስ አሣይቷል፤ ዮሴፍና ማርያም ብዙ መንገድ ጥለውት ከሄዱ በኋላ ሲመለሱ ያገኙት፣ ርዕዮተ ዓለሙን ሲያሰርፅ ነው፡፡ መጀመሪያ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት በህዝቡ ውስጥ ያለውን መርዝ መንቀል ነበረበት፡፡ ይህ  የኛን ሥራ ይመለከታል። ኢየሱስ እንደ ጋዜጠኛና እንደ ኮሙኒኬሽን ባለሙያ ነው ሲሰራ የነበረው፡፡ የፀረ ህዝብ ሃሳቦችን አሥወግዶ፤ ህገ መንግሥቱን በህዝቡ ውስጥ እንዲሰርፅ አድርጓል!”
ሳናውቅ አጨበጨብንለት፡፡
“በየሰፈሩ ሌኒን እንዲህ አለ፣ እምትሉ አንዳንዴ ምን ቁም ነገር ተናገረ? ብላችሁ ፈትሹ!”
ሁሉችንም ሳቅን፡፡ ራሱን “ሌኒን” ብሎ  መጥራቱ ነበር  ያሣቀን፡፡
“ጨቋኙ ሄሮድስ፤ ኢየሱስን ለማግኘት ህፃናትን ሲጨፈጭፍ፣ ኢየሱስ ግን በራሱ ዘመን ያደረገውን አሥታውሱ፡፡ ህፃናትን ተንከባካቢ ነበር፡፡ ለህፃናት መብት ተሟጋች!... ለሴቶች መብት የታገለበት ጊዜ ብዙ ነው። ሣምራዊቷ ሴት በብሔርዋ ተገልላ ነበር፡፡ ኢየሱስ ግን ዴሞክራት ስለነበር ሊያገላት አልሞከረም፡፡ ሰዎችን በማስወገድ ሣይሆን በማሣመን ያምናል፡፡ “አመንዝራ” የተባለችውን ሴት ማየት እንችላለን። ከነፍሰ ገዳዮች ታድጎ ጠላቶቿን በማሳመንና ትጥቃቸውን በማስጣል በውይይት ችግሩን ፈትቷል፡፡ ብዙ ነገር ላወራላችሁ እችላለሁ። ስለዚህ የበዓል ፕሮግራማችንን ወደተሻለና ለህዝብ ወደሚጠቅም አቅጣጫ እንመልሰው። በያመቱ ለገና በዓል ከበሮ ከመደለቅ፣ አልኮል ጠጥቶ ከመዝለል ልማቱን ለማሳካት እንስራ!”
ስብሰባው ተጠናቆ ጋዜጠኛው ከተቀመጠበት ሲነሳ፣ አንዳንድ የገና ሥጦታ እንደተዘጋጀልን አበሰረን፡፡ ስጦታው ምን ይሆን? ስንል ማውጣት ማውረድ ያዝን፡፡
“የቄስ መስቀል ይሆናል!” አለ አንዱ፡፡
“ፖስት ካርድ!” አለ ሌላው፡፡
እኔ፤ “ምናልባት የሌኒን መጽሐፍ ይሆናል!” ብዬ ቀለድኩ፡፡
የተበረከተልንን ስጦታ ስንከፍተው፤ “በዓላትና ልማታዊነት” የሚል ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ነው፡፡ የደራሲው ስም “ሌኒን” ይላል።


Read 617 times