Saturday, 31 December 2022 13:15

የመሐል ነገር

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(1 Vote)

  ጨለማን በጥቁረቱ የምጠላውን ያህል፡ብርኀንን በፍካቱ እጠለዋለሁ። ሁለቱም ለእኔ ምቾት የላቸውም። ጨለማ እንዳልታይ በመጋረዱ አይመቸኝም፤ ብርኀንም ፍጹም እንድጋለጥ በመፍቀዱ ሰላም አይሰጠኝም። አምላክ ለምን በቀንና በጨለማ መካከል ያለ ሰዓት አልፈጠረም? ደብዘዝ ፈዘዝ ያለ፤ አይጋለጡበት አይጋረዱበት ዓይነት።
ሌሊት።
ከሽቦ አልጋዬ ላይ ተጋድሜ ሐሳብ በአእምሮዬ ውስጥ ድሪሳ ሲመታ እባትታለሁ። ሐሳብ ሳሳ፣ ሐሳብ ስዳምጥ፣ ሐሳብ ስነድፍ፣ ሐሳብ ሳባዝት፣ ሐሳብ ስፈትል... ቆይቼ ወደ አልጋዬ ጀርባዬን ሳስጠጋው ምቾት አጣለሁ። ከቡጭቅጫቂ ጨርቅ የሰራሁት ድሪቶ የቀድሞ ምቹዬ ለአሁኔ አጋም፤ ጥጥ በኬሻ ከትቼ ያበጀሁት ምቹ ትራሴለአሁን ጉመሮዬ ሆነዋል።
ዕለቱ ማክሰኞ ከጠዋቱ 12:00።
አበባዬ በእጇ ጆግ ይዛ ከቤቷ ወጣች። አወጣጧ በምሥራቅ ነው። ፀሐይን ልትመስላት ፤ልታክላትም።
በእጇ የበር ውኃ ይዛለች።
አበባዬ እስላም ጎረቤቴ አላህን ስታመሰግን አድራ ዓይኗ ጨው መስሏል። ማክሰኞ አዳሯን ስትቅም “አሚን”ስትል ነው የምታድረው። የቡና ተርቢተኞቿም አብረዋት ያነጉታል።
«አንተ በእልሁ ሁሌ እጠቡኝ የሚል ዕቃ አይስጥህ» (ጆጓን ይዛ ወደ ሽንት ቤት እየገባች ነበር)
አፈርኳት።
«ወየው የሚታጠብ ዕቃ ሰጥቶ የሚጎረብጥ መኝታ በነሳኝ» (ደፍሬ መልሼ አሳቅኳት)
“ዕቃ የለኝም ከማለት የማይተናነስ መልስ”እያለች ጆጓን ይዛ ወደ ጉዳይዋ ገባች። ከገባችበት ክፍል “ጯ” የሚል ድምፅ በተደጋጋሚ ይወጣል፣ ወደ እኔም ይመጣል፣ ወንድነቴንም  ይቀሰቅሳል። አሁን ጠለቀች... አሁን “ጯ”አረገች የሚል መቃተት በልቤ ውስጥ ተንሰራፋ። ጭኔ ውስጥ ግለት ሲፈጠር፣ ዓይኔ እያዬ ሰውነቴ ሲቀጣጠል ይታወቀኛል። ኦ! የእሳትነት ባሕሪ እንዳለኝ አውቅ ዘንድ የክብሪት እንጨቱን በጭኔ መሐል አስቀመጧል፤ አልኩት ለእራሴ፡፡
[ብዙ፡ መቁነጥነጥ፤ የማይበሉትን፡ መቧጠጥ፤
ካ’ረገ፡ የተመኘ፡ ወደ፡ ሚሉት፡ መረብ፡መውደቅ ቅጽበት]
የአበባዬን ቀይ ጎረቤት አልወዳትም በመልኳ። ጥሩ ቁመና ሰጥቶ የፊት ቀለሟን ቀይ ያደረገባት ሴት ነች። እንዴት ቀይ መሆን አልከበዳትም? ሌላኛዋ ጎረቤቷን ፋጤንም አልወዳትም። መልኳ የጀበና ቂጥ ነው ሚመስል። ጥቁር። እንዴት ጥቁርነቷን ወደደችው? የምወደው ጠይም ነው። ቀይ እና ጥቁርን የሆነ። ከሁለቱም ለአመል ያለበት። ፈካ ያለ ጥቁረት ጠቆር ያለ ቅላት። ጠይም። ጠይም ሳይ እሆነውን አላውቅም። እግሬን እንቅፋት ቢመታው አይሰማኝም። ከነዘፈኑስ “ጠይም ዓሣ መሳይ “አይደል። ጠይም ነው የኔ ምርጫ፤ አዎ ደብዘዝ ያለ ቀይ... ደብዘዝ ያለ ጥቁር።
ሌላ ቀን።
ድሪቶ ያቆሰለው ገላዬን ይዤ ወጣሁ። ጣትን አር ቢነካው ቆረጦ አይጥሉትና፤ የእኔውም ገላ በስል ጥፍሬ የታከከው ደም እየዘነበው ቢሆንም አልጣልኩትም። ገላ ገላ ነው። ቁስሌን ገልጬ መንገድ ዳር ብቀመጥ ሰው ሳንቲም ይጥልልኝ ይሆናል። መቼም ሰው ቁስል ካላዬ አይጥልም። ቁስል ወዳዶች። የአእምሮ የውስጥ ቁስልን ማን ያያል? በውጭ ገጽታ ብቻ እንደተፈረጅን፣ እንደተረዳን፣ እንደተመጸወትን እንኖራለን አይቀርና ደግሞ እንሞታለንም። “ገፅታ ግንባታ” ይላል መንግስት እውነቱን ነው። ለዘመኑ ይበጀውን አውቋል። በገፅ አማኝ በገፅ ኮናኝ፤ “እኔ ከዚህ ትውልድ አይደለሁም” ልል ያምረኛል እንደ ሠዎች።
መንገድ ዳር።
እከካም ገላዬን ይዤ ለምጽዋት እጄን ዘረጋሁ። በእርግጥ ገንዘብ አላጣሁም። እንደ አብዛኛው ለማኝ ባንክ ቤት አስቀምጨው ነው። ከባንክ ሄጄ ከማወጣ የታቦት ስም እየጠራሁ ብለምን ችግሬን እቀርፋለሁ።
ጀመርኩ።
ስለ ማርያም  አለፉኝ።
ስለ ሚካኤል አለፉኝ።
ስለ መንግስቱ ኃ/ማርያም እጄ ጋ ድፍኑ ሁለት መቶ ብር ተቀምጠልኝ። ቀና ብዬ የሰጠኝን አየሁት። ፊቱ ጥግናኔ ነው። አረመኔነት ይነበብበታል። ትንሽ ፈገግታው ፊቱን ለማንጋት አልበቃችም። በቀኝ በኩል ያለች የወርቅ ጥርሱ ፈልቃብኛለች። ቢሰጠኝ እወድ ነበር ለማኝኮ ነኝ።
በተፈጥሮዬ የሚሰጥ አልወድም።
በተፈጥሮዬ የሚነሳ አልወድም።
የምወደው የሚሰጥ የሚነሳ ሰው ነው። ሁሌ መስጠት ስንፈትን ከመስበክ አይተናነስም። ሁሌ መንፈግም ግፍ ከመስራት አያንስም። ሰጣ  ነሳ... ሰጣ ነሳ፣ እንደ ነሐሴ ጀንበር ወጣ ገባ እንደምትለዋ የሚያደርገው ይግደለኝ።
ዛሬ ንፁሕ ገላ ይዣለሁ።
በአጠራቀምኩት ገንዘብ የገዛሁት ሳሙና እድፌን በላብኝ። እድፌን ...እድፌን እቆርብበት እነግስበት የሚመስለኝን። እድፌን_ የገቢ ምንጬን።
ለአላፊ አግዳሚው መዓዛዬ ደረሰው። ጠጅ ሳር፣ አርቴ ፣አዝሙድ ቅልቅል። ከሽቱም ሽቱ ፣ከቅባትም ቅባት የተመረጠለት መሰለ አካሌ። መንገደኛው ከሽታዬ ተስፋ ሲቀዳ አየሁ።
«በአገሪቷ ክርፋት በዛ?»(በድፍረት ጠየቅኩት)
«ድሮ የሞተ ነበር የሚሸት ፤ዘንድሮ የቆመም ይሸታል» አለኝ።
oran ትዝ አለችኝ የthe plague ዋ። የሞተ ዓይጥ የከተማዋን ጠረን እንደቀየረው። ኢትዮጵያ ምነዋ በቁሙ በሞተ ሠው ሽታ ጠረንሽ ተቀየረ? አልኩኝ።
ቆንጆ መዓዛ አልወድም።
ክርፋትም እጠላለሁ።
 መካከለኛውን እወደዋለሁ። ከራሴ በላይ ኮፍያ፣ ከእግሮቼም ግርጌ ጥላ፣ ሁሉም ቢቀር ተመኘሁ መሐል ላይ ልብን ስላየሁ። መሐሉ ለቄስ ነው። መሐሉ አይነገርም የሚወደድ የማይሰለች ነው።
ሳምንታት ተቆጠሩ።
ቀኖቹ በጨመሩ ቁጥር ሞት በሆነ ያህክል ጋት እየቀረበኝ እንደሆነ አውቃለሁ። ኑሮም በሆነ ጋት ያህክል እየሸሸኝ እንደሆነ እረዳለሁ። የሚጨመሩት ጊዜያቶች ያስፈሩኛል። ወደፊትን ማሰብ አልሻም። ከትዝታ ጋርም ትክሻ መለካካት አይሆንልኝም። እኔ የአሁን ሰው  ነኝ። አሁን እኖራለሁ፣ አሁንን አስባለሁ። ወደ ነገም አልንጠራራ፣ ወደ ትናንትም አልንሰራራ፣ የምፈልገው በዛሬ እንድጠራ ነው።
መንግስት ማነው? አልኳቸው።
ሰፈርተኞቼ ተሰብስበው ሲያሙት ነው የደረስኩ። ወደ ድሪቶዬ ልመለስ ባልኩበት ሰዓት ነው ሐሜቱን የሰማሁ። “መንግሥት ሆይ የእጅህን ይስጥህ” እያሉ ይረግሙታል። እነሱ መጉዳታቸው ነው። እግዜር ፍካሬውን ካልሰማቸው በቀር በእማሬው የእጁን ሰጥቶ መከራቸውን ነው የሚያበዛው። በእጁ ያለው ብር፣ ወርቅ፣ ታንክ፣ ባንክ ነውና።
አያርፉለትም ለሞቱም ሲሳሉ ሰማሁ።
ለሰው ሞት የሚመኝ ሰው ያሳዝነኛል። ሰው ለሰው ሞት በተመኘ ሰዓት ራሱ መሞቱን ለምን አያስብም? ከመንግስት ጋር ግብግብ ምን ጥቅም አለው ድሮስ። “ጩኸታችንን አይሰማም” ይላሉ ደግሞ ‘የልቤ ዜማ’ን የመሰለ ጣፋጭ  ነጠላ ዜማ እያለለት ምን ሊያደርግ የእነሱን ጩኸት ይስማ?
እርሜን ፀዳ ብዬ ቢያዩኝ የመንግስት እጅ አለበት ብለው አዋከቡኝ። ቤቴ ገብቼ የምወድቅበትን አልጋ ሸቀን አላዩምና።
“እጅግም ስለት ይቀዳል አፎት
እጅግም ብልሃት ያደርሳል ከሞት"
እጅግም ማማር ያማርራል ብዬ መቀጠል ያምረኛል። ስቆሽሽ መከራ፣ ስነጣ መከራ፤ ስወፍር መከራ፣ ስከሳ፣ መከራ፤ ዝም ስል መከራ፣ ሳወራ መከራ_ኧሯ! ሲመረኝ፣ ደብዘዝ አድርገኝ [ቆሸሽ ያለ ፅዱ ፣መጠነኛ ወፍራም] እለዋለሁ አምላኬን። ደብዝዘህ አጋለጥካቸው የምትል ነጠላ ዘፋኝ ትገጥመኝ እንደሁ።
“ኢትዮጵያ ትፈተናለች ግን ትሻገራለች” የሚለው ዓ.ነገር ከቀረጥ ነፃ ከሆነ ወደ ልቤ ላስገባው ፈቀድኩ። እኔ እፈተናለሁ ግን እሻገራለሁ። የመኝታዬ አለመመቸት፣ የሰዎች የሐሜት ሱስ፣ የቦዘኔዎች አልቧልታ፣ የመጽዋቾች ሁኔታ ሁሉም ሰላም አይሰጡኝም። እፈተናለሁ። ግን ደግሞ እሻገራለሁ። እንደምን ቢሉኝ ለዘብ ...ደብዘዝ ብዬ።
ዳግም ወደ አልጋዬ።
አልጋን የማይወድ የለም። የሁሉም ሰው ታሪክ ቢታሰስ በአልጋ ዙሪያ መገኛው ነው። እንደ dead sea scroll የታሪክ ጥቅልሎች፣ የኑሮው እንክብሎች መታጨቂያ ነው አልጋ። ሁሉም ሰው ትጥቅ የሚፈታው ለሞት ነው፤ ከዛ በፊት ግን ለአልጋ ትጥቅ ይፈታል። አልጋን መጻዕጉ ታሞ ተኛበት፣ እታጉ ወልዳ ተኛችበት፣ እኔ በእልሁስ?
ጀርባዬን ወረወርኩት በቀስታ።
ጃርት እሾኋን የበተነችበት ይመስል ጎኔን የሚወጋው በዛ። አልጋዬ ደረቅ ነው። በተፈጥሮዬ ደረቅ አልወድም፤ እርጥብም እንዲሁ። ለዘዝ ያለ  እሱ ይምጣብኝ። ከተተከለ እንጨት እና ከወለቀ እንጨት ብባል ከሁለቱም ውጪ ተተክሎ የሚንቀሳቀስ ማለቴ አይቅርም። መሐል ነገር ነው ጥሩ። ምክንያቱስ...የሚነቃነቅ እንጨት እና የምትስቅ ሴት ልባቸው አይገኝም ስለሚሉ። አዎ!ደረቅ ይሰበራል፤እርጥብ ግን ይታጠፋል። የተሰበረ ወደ መጀመሪያው አይመለስም የታጠፈ ግን ይችላል።
ታደረና ተሞተ።
በቆንጆ አልጋ ለተኙት፣ እንደ’ኔም ሲያ’ኩ ለአደሩት እኩል ነጋ። በሰፌድ ያሰጣም፤ በሸራ ያሰጣም እኩል ክረምቱን እንደሚወጣ። ድህነትን አልወደውም ሲያኩ መኖር ነው። ሀብት ሲበዛም አልወድም ብወድስ የት አግኝቸው?  መሐል ነገር ይመቻል።
ሰውነቴ በጥፍሬ ታርሷል፤ መች እንደሚዘራ አላውቅም። የምበላው ጮርናቄ ሆዴ ውስጥ ድምፅ እየፈጠረ ይረብሸኛል። የምለብሰው ልብስ ቅማል እያፈራ spontaneous generationን እንዳስታውስ እየገፋፋኝ ነው።
ቁስል አለብኝ ከጣቴ።
ሌላውም ሰው ቆስሏል።
በቁስል ደረጃ የእኔ ይቀላል በህመም ግን ከሁሉም ይልቃል። የታመምኩት ጣቴን ነው። የጣት ቁስል እና የዘመድ ምቀኛ ነዝናዞች ናቸው። እንቅልፍ አያስተኙም። ጤና ይነሳሉ። ሙሉ ጤነኛ መሆንን አልሻም (የህመም መርፌ ጠቆም ሲያደርግ እዝነት በልብ ውስጥ ያድጋል)፤ ሙሉ የአልጋ ቁራኛ መሆንም አልሻም (የሰው እጅ የእግዜር ደጅ ነው፤ ዓይን ዓይን ማየቱ ያሳቅቃል)። መሐል ነገር ይመቻል። የሚታመሙት ደግሞም የሚቻል።
ቀኔን ላገባድደው ስል “ይውረድ” የሚል መፈክር ሰማሁ። ማንን ነው? አልኩ እንደለመደብኝ መንግሥትን።
አፈርኩ።
እንደኔ አይሆኑም? መንግሥት ገዛሁ ይበል እንጅ እኔ መች አምኜ በእራሴ ላይ ሾምኩት። ለእራሴ መንግሥት እራሴ ነኝ፤ ለምን ለእራሳቸው እራሳቸው መንግሥት አይሆኑም? ግራ ገባኝ...
ጠጋ አልኩኝ ወደ ሰልፉ።
ወርዶስ? አልኩት አንዱን ሸበላ ወጣት። ላብ በፊቱ ያሻርታል። ዘገሩን ነቅንቆ ሊነርተኝ ቃጣው። እኔም ከፊቱ ሸሸሁ። ሌላኛውን ተመልካች ጠጋ ብዬ “ወርዶስ ግን?” አልኩት፡፡ አይመለከተኝም ብሎ ዘጋኝ። ይመለከተኛልንም አይመለከተኝንም አልወድም። መሐል ነገር ይመቻል። የደረቀ እንዲሰበር ፣የለዘዘ እንዲታጠፍ አውቃለሁ።
ደግሞ መሸ። የቀን ዑደቱ ክብ ሆነ። ተመልሶ እዛው። የለቀቅኩትን አልጋ ተመልሼ ልተኛበት ነው። አለፈ ባልነውን ሥርዓት ዳግም እየተገዛን አይደል? ታዲያ ምን አዲስ?... ሲያ’ኩ መኖር።
ለካ አንዳንዴ መሐልም ይሰለቻል።
መሐል ሰፋሪ ይሉትን ባይ መሐል ጠላሁ። የሁለት ጥይት ማረፊያ እሆን ዘንድ አልፈቅድም። የጠላኋቸው ቀይዋም፣ ጥቁሯም፣ ጨለማም ብርኀንም፣ ነገም ትናንትም፣ ይመለከተኛልም አይመለከተኝምም፣ ደረቅም እርጥብም፣ ጤናም ህመም ይምጡብኝ ይምጡብኝ። ጥቃታቸው በአንድ ጎን ነው መሐል ግን...!!

Read 283 times