Saturday, 07 January 2023 00:00

“የሰላም ስምምነቱ አተገባበር ግልፅነት ይጎድለዋል”

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

ህውሓት ሙሉ በሙሉ ትጥቁን ሲፈታ የአሸባሪነት ፍረጃው ይነሳለታል።
የህውሓት ከፍተኛ አመራሮችን ያካተተ የልዑካን ቡድን ሰሞኑን አዲስ አበባ ይገባል
በትግራይ በጥቂት ቀናት ውስጥ ጊዜያዊ አስተዳደር ይመሰረታል


  በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካው ፕሪቶሪያ የተደረገውና በህውሓት ታጣቂ ሃይሎችና በመንግስት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት አተገባበር ግልፅነት የጎደለውና ህዝቡን ያላሳተፈ ነው ተባለ፡፡ ስምምነቱ ዘላቂነት እንዲኖረው የአተገባበር ሂደቱ ይበልጥ ግልፅ ሊደረግ ይገባልም ተብሏል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ራሄል ባፊ እንደገለፁት የሰላም ስምምነቱ ጅማሮ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ሰላሙ ዘላቂነት እንዲኖረው ትግበራው አካታችና ግልፅ ሊደረግ ይገባዋል፡፡
ጦርነቱ በአፍሪካ ህብረት ዋና አደራዳሪነት ሲቆም መንግስትና ህውሓት ካደረጓቸው ስምምነቶች መካከል የህውሓት ትጥቅ መፈታት ዋንኛው ሲሆን የፌደራል መንግስቱም ትግራይ ክልልን በመቆጣጠር በአሸባሪነት በተፈረጀው ህውሓት ምትክ አዲስ አስተዳደር እንደሚተካ በግልፅ ሰፍሯል፡፡ ከስምምነቱ በኋላ በኬኒያ ናይሮቢ በተካሄዱ ውይይቶች በተደረሰው ስምምነት መሰረትም፤ በሁለቱም ወገኖች ስምምነቱን ተግባራዊ የማድረግ እርምጃዎች ተጀምረዋል፡፡
ከስምምነቱ በኋላ በትግራይ ክልል መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን ሰብአዊ እርዳታዎች በስፋት ለህዝቡ መዳረስ የሚችልበት መንገድ እንዲመቻች ተደርጓል። የፌዴራል መንግስቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያካተተ የልዑካን ቡድን ወደ መቀሌ በማምራት ከህውሓት አመራሮች ጋር ውይይት ያካሄዱ ሲሆን የሰላም አደራዳሪዎቹ የአፍሪካ ህብረት ልዑካን ቡድንም ወደ መቀሌ በማምራት የሰላም ስምምነቱን አተገባበር ሲታዘቡ ሰንብተዋል፡፡
በሰላም ስምምነቱ በተገለፀው መሰረትም የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት ወደ ክልሉ በመግባት መንግስታዊ ተቋማትን መቆጣጠር የጀመሩ ሲሆን የህውሓት ሃይሎችም ከባድ መሳሪያዎችን በመፍታት ለመከላከያ ሰራዊት ማስረከባቸው ተሰምቷል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌና ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ በረራዎችን ታህሣስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም የጀመረ ሲሆን በ10 ቀናት ውስጥ ከ10ሺህ በላይ መንገደኞችን ማጓጓዝ መቻሉም ተጠቁሟል፡፡
በሰላም ስምምነቱ የአተገባበር ሂደት የጊዜ ሰሌዳ መሰረትም በቀጣጦቹ ጥቂት ቀናት የህውሓት ከፍተኛ አመራሮችን ያካተተ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅና ቡድኑ በቆይታውም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ታስረው የሚገኙትን የህውሓት አመራሮች እንደሚያነጋግር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በመንግስትና በህውሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ በተደረገው የሰላም ስምምነት መሰረት፤ የህውሓት ሃይሎች ትጥቅ መፍታት መጀመራቸውን ምንጮች የጠቆሙ ሲሆን ታጣቂ ሃይሎቹ ሙሉ በሙሉ ትጥቃቸውን ፈተው ሲያጠናቅቁ በህውሓት ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፈው የአሸባሪነት ውሳኔ እንደሚነሳና በህውሓት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተከፈተው የወንጀል ክስ እንዲቋረጥ እንደሚደረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ስለ ስምምነቱ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች ገለፃ ባደረጉበት ወቅት ተናግረዋል፡፡ “የትጥቅ መፍታት ሂደቱ ጫፍ ሲደርስ ለፖለቲካ ሂደቱ በር መክፈት ስለሚያስፈልግ ፓርላማው የሽብር ፍረጃውን ሊያነሳ ይችላል፡፡ የተመሰረተ የወንጀል ክስ ሂደትም እንዲቋረጥ የሚደረግበት ሁኔታም ይኖራል” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ ይህ የሚደረገው ሰላም ለማምጣት ሲባል እንደሆነና ለሰላም ሲባል አንዳንድ መራራ አካሄዶችም እንደሚኖሩ ተናግረዋል።
የህውሓት ታጣቂ ሃይሎች በአሁኑ ወቅት ከባድ የጦር መሳሪያዎቻቸውን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያስረከቡ ሲሆን የመከላከያ ሰራዊት አንድ ሻለቃ ጦር ከባድ መሳሪያውን ተረክቦ በጥበቃ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት አባላት የትግራይ ክልል ዋና ከተማን መቀሌን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሰላም በማስከበርና የፌዴራል ተቋማትን በመጠበቅ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል፡፡
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረትም፣ ተፈፃሚ ከሚሆኑ ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው የኤርትራ ሃይሎችን ከክልሉ የማስወጣቱ ተግባር መጀመሩንና የኤርትራ ሃይሎች ከትግራይ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ለቀው መውጣት መጀመራቸውን ባለፈው ሳምንት ሮይተርስ የአይን እማኞችን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት በትግራይ አዲስ ጊዜያዊ አስተዳደር እደሚመሰረት ምንጮች ጠቁመዋል።

Read 2208 times