Saturday, 07 January 2023 00:00

አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን (old Wine in a new bottle)

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ከእለታት አንድ ቀን ፣ አንድ ክፉ ሚስት የነበረችው ደግ ባልና ሚስቱ በአንድ መንደር ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ ሚስቲቱ የፈሰሰ ውሃ የማታቀና ፣ ሁሉንም ነገር ገበሬ ቧላ ከእርሻ ሲመለስ ጠብቃ “ይሄን አድርግ፤ ይሄን አታድርግ” እያለች አልጋዋ ላይ ተጋድማ የምታዝዝ ቅምጥል ነበረች፡፡
ባል ደሞ ሁሉንም እሺ ባይ፣ ገርና ታዛዥ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ የሚያውቅ የሰፈሩ ሰው ሁሉ ከመጠን በላይ ለዚያ ባል ያዝንለታል፡፡
ከፊሉ ሰው፤
“ምነው እንደ ባል ሁን እንጂ" እያለ ይመክረዋል፡፡ ይገስፀዋል፡፡
ከፊሉ ሰው ደግሞ፤
 “እኛንም አሳፈርከን  እኮ፤ እንደ ባል ኮስተርተር በል እንጂ" ይለዋል፡፡
አንዳንዱ ደሞ፤
“እሷ ጌታህ አንተ ሎሌዋ ነው የምትመስሉት፤ እንዲህ አገር እስከሚያውቅ እስከሚሳለቅብህ ድረስ ለምን መጫወቻ ትሆናለህ!"   ይለዋል፡፡
አክስቱ እማማ ጀማዬ ግን ቀልድ አያውቁም፤
 “እረዲያ ወይ ትክክለኛ ባልና ሚስት ሁኑ አልያ ተፋቱ፤  ወለም ዘለም ይብቃችሁ” ይሉታል፡፡
ይሄ ሁሉ ሆኖም ባል አመሉ ሳይቀየር ብዙ አመት ቆዩ፡፡ የፈጣሪ ስራ ታከለበትና ሚስት በጠና ታመመች፡፡ ብዙም ሳትሰነብት ህይወቷ አለፈ፡፡
ምስኪኑ ባል ሚስቱን ቀብሮ ተኮማትሮ እቤት መቀመጥ ሆነ ስራው፡፡ አመታት ካለፉ በኋላ አንድ ቀን የሰፈር አዛውንት ወደ ባል ቤት መጥተው፤
“ልጄ እስከ መቼ እንደዚህ ተኮማትረህ ትችለዋለህ፤ እኛ የሰፈር ሽማግሌዎች መክረን ዘክረን መፅናኛ የምትሆንህ ጨዋ ፀባይ ያላት ሴት ልጅ መርጠን እንድርልሀለን፤ እሺ በልና  ሀዘኑንም እርሳው“ ብለው ተማፀኑት፡፡
ይሁን ብሎ ተዋወቃትና አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ ይቺኛዋን ሚስት የፊተኛዋን ተቃራኒ ሆና አገኛት፡፡ እጅግ ደስተኛ አደረገችው፡፡ ሸክም ያለበት እንደሆነ እርሻው ቦታ ድረስ ተከትላ ሸክሙን ታግዘዋለች፡፡ ማታ ደክሞት ሲመለስም ውሃ አሙቃ እግሩን አጥባ፣ ጀርባውን በቅባት አሽታ፣ እራቱን አብልታ ታስተኛዋለች፡፡ ጠዋትም ገና ከአልጋው ሳይነሳ ፊቱን አስታጥባ ቁርስ አቅርባ ታጎርሰዋለች፡፡
መቼም የሰው ልጅ ነገር አስገራሚ አይደል ፤ ጠዋት ማለዳ ከእንቅልፉ ነቅቶ ፀሎት ሲያደርስ፤
“አምላኬ ሆይ፤ ያቺን ክፉ ሚስቴን ወስደህ ይቺኛይቱን ስለሰጠኸኝ አመሰግንሀለሁ፤ ጌታዬ የተሻለች የምትመጣ ከሆነ ምነው እቺም በሞተች ” አለ ይባላል፡፡
***
ከእንስሳት ይልቅ በልቶ የማይጠግብ የሰው ልጅ ነው፡፡ እድሜ ልኩን የተሻለ ፍለጋ ሲዳክር ይኖራል፡፡ የሀገራችን ነገር አሳሳቢነቱ የሰው ልጅን ፍላጎት ያህል እንደቀጠለ ነው፡፡ የማይጠግቡ ሰዎች ስላሉን ነው፡፡
ዋና ዋናዎቹንና ተደጋጋሚዎቹን እንነቁጣቸው፡-
አዳዲስ ፓርቲዎች እንደ እጭ ይፈለፈላሉ፤ አዳዲስ መሪዎችም ድንገት ብቅ ይሉና እንደ ድመት ኮርማ ይንጎማለላሉ፤ ዛሬ የተጣሉ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ነገ ይታረቃሉ፤
ወዳጅና ወዳጅ የተጣሉ እንደሆን
መታረቅም  እንደ ጥንትም  አይሆን
--እንደተባለው ነው፡፡ አንዱ አንዱን አጥፍቶ መጠበቁ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም
ገዴ ዞራ ዞራ በእንቁላሏ ላይ
ጊዜ የሚጠብቅ ሰው ጅል ሊባል ነው ወይ!
በኢኮኖሚውም ረገድ፡-
አሁን ኑሮ ነው ወይ የሸማኔ ኑሮ
ከጉልበቱ በታች መሬት ተቀብሮ
ሲል ይውላል፡፡
አሻግራቸውና ከብቶቹ ሳር ይብሉ
ያ ሳር አይደለም ወይ የምናየው ሁሉ
 ምሬት የገባው ለታ ደግሞ
እረ ምረር ምረር ምረር  እንደ ቅል
አልመርም ብሎ ነው ዱባ እሚቀቀል
ከዚህ ወዲያ ወደ ጫካ ባሰበ ሰዓት ደሞ
መሳሪያው ሳያብል ጥይቱ ሳያንሰው
እንዴት ልሙት ብሎ እጁን ይሰጣል ሰው
ቀጣዩ የፖለቲካ ጨዋታ ደግሞ የካሮትና የአርጩሜ ነው (carrot and stick) ሲፋጅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ እንደሚሉት ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ስጋታችን የስታሊን በትር እንዳይመጣና እንደገና ቀይ ሽብር እንዳይደገም ነው፡፡ እንደ ዘመኑ አባባል በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል እንዳይባል ነው፡፡ አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን ማለት ይሄው ነው፡፡
መልካም የገና በዓል ይሁንልን!

Read 2188 times