Monday, 09 January 2023 10:08

አንዴ ከመወርወር ሁለቴ ማሰብ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንኳን ለብርሀነ ልደቱ አደረሳችሁማ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- እንዴ ምስኪኑ ሀበሻ! ምን ጉድ ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ምን አጠፋሁ?
አንድዬ፡- በበዓል ቀን እኔ ዘንድ የመጣኸው እውነት አንተ መሆንህን ለማመን በጣም ቸገረኝ እኮ! ምነው ምስኪኑ ሀበሻ፣ በበዓሉ ቀን  ቤቱ ባዶ ሆነ እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ የአቅማችንን ያህል ተዘጋጅተናል፡፡
አንድዬ፡- ጎሽ፣ ጎሽ፣ በነገራችን ላይ ምስኪኑ ሀበሻ እንኳን አደረሰህ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን! እንኳን አብሮ አ...አ...ይቅርታ አንድዬ!
አንድዬ፡- ለምኑ ነው ይቅርታ የምትጠይቀኝ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እንዴ አንድዬ፣ እኛ እኮ እንኳን አደረሰህ፣ አደረሰሽ የምንባባለው አንተ ለበዓሉ ስላደረስከን ነው፡፡ እኛ እንደገና አንተን እንዴት...እንዴት...
አንድዬ፡- ቆይማ፣ እኔ እንኳን አደረሰህ መባል ይበዛብኛል ያላችሁ ማነው!  ደግሞ ስማ አንድ ሰሞን “እንኳን አደረሰህ ስትባባሉ፣ የደረሳችሁት ራሳችሁ ናችሁ እንጂ ማንም አላደረሳችሁም፣” ትባባሉ ነበር እኮ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ምን መሰለህ...
አንድዬ፡- ግዴለም ምስኪኑ ሀበሻ፣ ይህን ጉዳይ የሆነ ኮሚቴ አቋቁመን እናየዋለን፡፡ መቼስ እኮ ከትናንት ወዲያም፣ ትናንትም፣ ዛሬም እንደ እናንተ ከኮሚቴ ጋር የወደቀው ፍቅር አልለቅ ያለው ዓለም ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡ ብቻ ምን አገባኝ! ግን ምስኪኑ ሀበሻ ቅድም የአቅማችንን ያህል ተዘጋጅተናል ያልካትን አሁን አሁን ጭራሽ የተረሳች ነገር ማለትህን ወድጄልሀለሁ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አመሰግናለሁ፣  አንድዬ!
አንድዬ፡- አቅምን ማወቅን የመሰለ ነገር የለም እኮ! አየህ እዚህ ዓለም ላይ በተሳካላቸውና ባልተሳካላቸው መሀል ካሉት ልዩነቶች አንዱ አቅምን የማወቅና ያለማወቅ ነው፡፡ አየህ ምስኪኑ ሀበሻ፣ አቅምህን ስታውቅ መሥራት ያለብህንና መሥራት የሌለብህን፣ ሊሳካ የሚችለውንና ሊሳካ የማይችለውን ታውቃለህ፡፡ አቅምህን ካላወቅህ ደግሞ...ያው እንግዲህ ይህን ለአንተ አልነግርህም! በአጭሩ ሁሉ ነገር ውሀ ቅዳ፣ ውሀ መልስ ነው የሚሆነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱስ ልክ ነው አንድዬ፡
አንድዬ፡- ቆይ ምስኪኑ ሀበሻ... ቆየኝማ፡፡ አንድ ነገር አስታወስከኝ፡፡ የአቅማችንን ያህል ተዘጋጅተናል አይደል ያልከኝ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አዎ አንድዬ፤ ከአቅማችን በላይማ ብንንጠራራ የት እንደርሳለን ብለህ ነው!
አንድዬ፡- የትም፣ የትም የማትደርሱ ነው የሚመስለኝ፡፡ ግን እኮ ምስኪኑ ሀበሻ ከአቅማችሁ በላይ እየተንጠራራችሁ ነገሩ እንደማይሆን እስኪገባችሁ ድረስ ራሳችሁንም፣ ሌላውንም ትበጠብጣላችሁ፣ አሁን ሀገራችሁ ብዙ ቦታ እንደሚታየው ማለት ነው፡፡ አትስማማም ምስኪኑ  ሀበሻ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አ...አ...አንተ ብለኸውማ እንዴት አልስማማም አንድዬ!
አንድዬ፡- አሀ... ሀሳቡን ወደኸው ሳይሆን እኔ ስላልኩት ብቻ ነው የምትስማማበት ማለት ነው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ፣ እንደሱ አስቤ አይደለም!
አንድዬ፡- ወዴት ሸሸት፣ ሸሸት! አንዳንዴ ምናለበት አዎ፣ እዚህ ላይ ተሳስቻለሁ፣ እዚሀ ላይ አጥፍቻለሁ ምናምን ማለት ቢለምድባችሁ።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንደእሱ ቢሆንም ጥሩ ነበር፡፡
አንድዬ፡- ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ሁሉም ሰው፣ በሁሉም ጊዜ፣  በሁሉም ነገር ትክክልና አዋቂ የሆነባት ሀገር የእናንተዋ ብቻ ትመስለኛለች። አንዳንዴ በሁሉም ነገር የለየላችሁ አዋቂዎች ከሆናችሁት ጋር ምንም የማያውቁ ጥቂቶችን ጨምሩ አንጂ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱስ ልክ ነህ፣ አንድዬ....
አንድዬ፡- እሺ፣ ይሁንም አይሁንም እኔ ስላልኩት ብቻ ደገፍከው እንበል፡፡ ግን እኮ ምስኪኑ ሀበሻ....ብቻ በበዓል ቀን ወቀሳ አብዝቼ እንዳላስከፋህ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ ምን ሆንኩኝ ብዬ ነው የሚከፋኝ! በጭራሽ አይከፋኝም፡፡ እንደውም አንድዬ በዛሬው የበዓል ቀን እቤት ብውል የተወሰኑ ሰዓቶች መከፋቴ አይቀርም፡፡
አንድዬ፡- ምነው ዶሮና በጉ ዘንድሮ የሉም እንዴ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ለአንተ ምስጋና ይግባህና ሁሉም ሙሉ ነው፡፡ እንደውም ዘንድሮ አልፎልኝ በበግ ፈንታ ወይፈን የሚያክል ፍየል ነው ያስገባሁት፡፡
አንድዬ፡- ኧረግ ኧረግ! ምስኪኑ ሀበሻ አሁን በደንብ አኮራኸኝ፡፡ በቃ ምቀኞቼ የምትላቸው ዓይናቸው ቀልቷላ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ ቀልቷል ብቻ ሳይሆን ቀይ ስር መስሏል፡፡ እኔም ከየት ከየትም ያለችኝን ሰብስቤ ፍየል የገዛሁት ለእነሱ እልህ ብዬ ነው፡፡.....አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡- እ...ም... ምን አልከኝ ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ሳወራህ ዝም አልከኝ እኮ አንድዬ!
አንድዬ፡- ዝም አልኩህ አይደል፣ ምን ታደርገዋለህ አይደል የምትባባሉት! ስማኝማ...ለእነሱ እልህ ብዬ ነው ያልከኝ ይሄን ያህል ደመኛ የሚባሉ ጠላቶች አሉብህ እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እንደሱ ሳይሆን አንድዬ፣ ብቻ ሸሚዝና ጫማ እንኳን የለወጥኩ ጊዜ በንዴት ድብን ይላሉ፡፡
አንድዬ፡- አፍ አውጥተው ያሉህ ነገር የለም፣ አይደል!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አፍ አውጥተውማ ያሉኝ ነገር የለም፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ታዲያ በንዴት ድብን ማለታቸውን በምን ታውቃለህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ፊታቸው ላይ አይባቸዋለኋ!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ እኔ አንዱ ችግር የሆነብኝ የምትናገሩትን በመስማትና ፊታችሁን በማየት ምን እንደምታስቡ ልለያችሁ  የቸገረኝ ለካስ ያንን ችሎታዬን እናንተ ወስዳችሁት...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!...
አንድዬ፡- ቆይማ ምስኪኑ ሀበሻ! ዲሞክራሲያዊ መብቴን ጠብቅልኛ! ስማ ቅድም የሆነ ነገር ልልህ ፈልጌ ሌላ ጉዳይ ውስጥ አስገባኸኝ እኮ፡፡ እናማ...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ...
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ እንዲህ በየመሀሉ አስሬ የምታቋርጠኝ ከሆነ የተቃውሞ ሰልፍ እወጣለሁ፡፡ ምን ልልህ ነበር መሰለህ...የሆነ ነገር ሲነገር ያለውን ግለሰብ ወይም ቡድን በማየት ብቻ የእውር ድንብራችሁን የምትደግፉትንና የምትቃወሙትን ነገር ትታችሁ አንዴ ከመወርወራችሁ በፊት ሁለቴ ማሰብ ስትጀምሩ፣ ያኔ እኔ ነኝ ከዳር እዳር በፍየል ቁርጥ የማንበሸብሻችሁ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- በል ምስኪኑ ሀበሻ መልካም በዓል ይሁንላችሁ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!
እንደገና እንኳን ለብርሀነ ልደቱ አደረሳችሁ!

Read 1231 times