Saturday, 07 January 2023 00:00

የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ወደ ኢትዮጵያ መሳብ ያስፈልጋል

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ለ44ኛ ጊዜ በአውስትራሊያ ባቱረስት ይካሄዳል

44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በአውስትራሊያዋ ባቱረስት ከተማ  ከወር በኋላ ይካሄዳል፡፡  በሻምፒዮናው ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ  ቡድን ምርጫ ለማከናወን  ከሳምንት በፊት አትሌቲክስ ፌደሬሽን  40ኛውን የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በሱሉልታ አካሂዷል።  በሁለቱም ፆታዎች በአጭርና ረጅም ርቀት በተዘጋጁ አምስት የውድድር መደቦች ላይ  ክለቦች፤ ክልሎችና  የግል ተሳታፊዎች ተወዳድረዋል፡፡  በ10 ኪ.ሜ ሴቶች  ለተሰንበት ግደይ፣ ጌጤ ዓለማየሁና መቅደስ አበበ እንዲሁም በወንዶች ደግሞ በሪሁ አረጋዊ ፤ታደሰ ወርቁና ጌታነህ ሞላ ከ1 እስከ 3 ደረጃ አግኝተዋል፡፡ በጃንሜዳው ውድድር በአጭርና በረጅም ርቀት ውድድሮች እስከ ስድስተኛ ደረጃ ያገኙት አትሌቶች በአውስትራሊያ  በሚካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ይሳተፋሉ።
የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ከ3 ዓመት በፊት ለ43ኛ ጊዜ በዴንማርክ  አሩህስ ከተካሄደ በኋላ 44ኛው በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በጉዞ ገደቦች ለሁለት ጊዚያት ተራዝሞ ነበር፡፡ ሻምፒዮናው ከወር በኋላ በባቱረስት ሲካሄድ ከ65 በላይ አገራትን የሚወከሉ ከ500 በላይ አትሌቶች እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል፡፡ በዴንማርክ አርሁስ ከተማ በተካሄደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ኢትዮጵያ በውድድሩ 5 የወርቅ፣ 3 የብርና 3 የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 11 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም አገራት አንደኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ለሻምፒዮናው በድምሩ ከ310 ሺ ዶላር  በላይ የሽልማት ገንዘብ ያዘጋጃል፡፡  በግልና በቡድን  ከ1ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች የሽልማት ገንዘቡ ይከፋፈላል፡፡ በአዋቂ አትሌቶች የሁለቱም ፆታዎች የውድድር መደቦች በግል  ውጤት ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ለ1ኛ 30ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 15ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 10ሺ ዶላር፣ ለ4ኛ 7ሺ ዶላር፣ ለ5ኛ 5ሺ ዶላር እንዲሁም ለ6ኛ ደረጃ 3ሺ ዶላር ይበረከታል፡፡ በቡድን ውጤት ለሚያሸንፉ አገራት ደግሞ ለ1ኛ 20ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 16ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 12ሺ ዶላር፣ ለ4ኛ 10ሺ ዶላር፣ ለ5ኛ 8ሺ ዶላር እንዲሁም ለ6ኛ ደረጃ 4ሺ ዶላር የሚታሰብ ሲሆን በሁለቱም ፆታዎች ድብልቅ የዱላ ቅብብል ውድድር ለ1ኛ 12ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 8ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 6ሺ ዶላር፣ እንዲሁም ለ4ኛ 4ሺ ዶላር እንደሚሸለም ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ለ4ኛ ጊዜ በአፍሪካ አህጉር ለማዘጋጀት የኢትዮጵያ  አትሌቲክ ፌደሬሽን ጥረት ማድረግ እንዳለበት መጠቆም ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ  ባለፉት 43 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ያስመዘገበችውን ከፍተኛ ውጤት በመንተራስና በሻምፒዮናው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ታላላቅ አትሌቶቿን በአምባሳደርነት በመጠቀም ዘመቻ መስራቱ ስኬታማ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ዓለም አቀፍ ውድድሩን ማዘጋጀት ለአትሌቲክሱ እና ለአገር ገፅታ ከሚፈጥረው ውጤት ባሻገር በአገር ውስጥ እንደጃንሜዳ፤ ሱልልታ አካባቢ ያሉ የውድድር ስፍራዎችን በቋሚነት ለመገልገልና በተሟላ የስፖርት መሰረተልማት ለማጠናከር ያስችላል።
የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው በዓለም አትሌቲክስ ማህበር ስር ከሚካሄዱ ውድድሮች በአንጋፋነቱ ይጠቀሳል፡፡ ከ1973 እኤአ ጀምሮ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ለ38 ጊዜያት በየዓመቱ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ከ2011 እ.ኤ.አ ወዲህ ግን በየሁለት ዓመቱ የሚደረግ ሆኗል፡፡ በተለይ ባለፉት 30 አመታት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በየውድድር መደቡ እስከ 10 ያለውን ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ በመቆጣጠር ያሳዩት የበላይነት  ባስከተለው ጫና ሻምፒዮናው የተዳከመ ቢመስልም ከዓለም አትሌቲክስ ዋና ውድድሮች ተርታ የሚጠቀስ ሆኗል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በተሳትፎ ታሪኳ  ታላላቅ ውጤቶችን አስመዝግባለች። በኦሎምፒኮችና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ታላላቅ ስኬት ያገኙ አትሌቶቿም መገኛቸው  የአገር አቋራጭ ሩጫ እንደሆነም ይታወቃል፡፡ የአፍሪካ እህጉር ሻምፒዮናውን ለሶስት ጊዜያት አዘጋጅታለች፡፡ ከ5 ዓመት በፊት የሻምፒዮናውን አዘጋጅነት የምስራቅ አፍሪካዋ ኡጋንዳ አግኝታ በተሳካ ሁኔታ ማስተናገዷ የሚታወስ ሲሆን ከዚያ በፊት በ1998 በማራካሽ ሞሮኮ እንዲሁም በ2007 እኤአ በሞምባሳ ኬንያ ሻምፒዮናውን አዘጋጅተዋል፡፡ በባቱረስት ከሚካሄደው 44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በኋላ 45ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በ2024 የሚካሄደው በክሮሽያ ሜዱሊንና ፓውላ ነው፡፡በአፍሪካ አህጉር ለ4ኛ ጊዜ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን በ2026 ወይንም በ2028 ለማዘጋጀት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን መስራት ይኖርበታል፡፡
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ከፍተኛ የሜዳልያ ስብስብ  በግል እና ከቡድን ጋር በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ በአጠቃላይ 27 ሜዳሊያዎችን በመውሰድ  እንዲሁም በሴቶች ደግሞ  ወርቅነሽ ኪዳኔ በ21 ሜዳሊያዎች በመቀዳጀት በሁለቱም ፆታዎች ከዓለም አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

Read 280 times