Saturday, 07 January 2023 00:00

ዋልያዎቹ ለ3ኛ ጊዜ በቻን ይሳተፋሉ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

በአልጀርያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 7ኛው የቻን ውድድር (የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ) ከሳምንት በኋላ ይጀመራል፡፡ በሻምፒዮናው ለ3ኛ ጊዜ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  የመጨረሻ ዝግጅቱን በሞሮኮ እያካሄደ ነው።
ዋልያዎቹ በምድብ 1 ከአዘጋጇ አገር አልጀሪያ፤ ሊቢያና ሞዛምቢክ ጋር የተደለደሉ ሲሆን፤  በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታው ከሞዛምቢክ ጋር፤ ሁለተኛውን ጨዋታ ከአልጀርያ እንዲሁም የመጨረሻውን የምድብ ጨዋታ ከሊቢያ ጋር ያደርጋሉ፡፡ ከሞዛምቢክና ከአልጀርያ  በአልጀርስ ከተማ በሚገኘው ኔልሰን ማንዴላ ስታድዬም የሚጫወቱ ሲሆን ከሊቢያ ጋር የሚጫወተው ደግሞ በአናባ በሚገኘው 19 ሜይ 1986 ስታድዬም ነው፡፡ሶከር ኢትዮጵያ  እንደዘገበው ብሄራዊ ቡድኑ በሞሮኮ የሚያደርገው የሳምንት ዝግጅት በሻምፒዮናው ለሚያስመዘግበው የተሻለ ውጤት ምክንያት ይሆናል፡፡ ሻምፒዮናው ከመጀመሩ በፊት በሁለት ቀናት ልዩነት ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን  ከሞሮኮ አቻው ጋር እንደሚያደርግ ደግሞ የፌደሬሽን ፅህፈት ቤት ሃላፊ በቲውተር ገፃቸው አስታውቀዋል፡፡ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በአገር ውስጥ ሊግ ከሚጫወቱ ክለቦች የሰበሰቧቸውን 26 ተጨዋቾች በመያዝ በሰሜን አፍሪካ መጫወታቸው በቀጣይ አህጉራዊ ውድድሮች የሚኖራቸውን ተፎካካሪነት ያሳድገዋል፡፡  እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከቻን ውድድር ጋር በተያያዘ ለቅድመ ዝግጅትና  ሌሎች ወጭዎች ከመንግስት እስከ 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ጠይቆ በጎ ምላሽ ማግኘቱ ይታወቃል፡፡
 ከ14 ዓመታት በፊት የተጀመረው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሽፕ ቻን ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሲሳተፍ ለ3ኛ ጊዜ ነው። በ2014 ደቡብ አፍሪካ ላይ እንዲሁም በ2016 በሩዋንዳ በተዘጋጁት የቻን ውድድሮች ላይ  ብሔራዊ ቡድኑ ከምድቡ ማለፍ አልቻለም።
አልጀሪያ የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንን በ4 ከተሞች  በሚገኙት 4 ስታድየሞች የምታስተናግድ ሲሆን ሱፕር ስፖርትና ስታር ታይምስ በመላው ዓለም በቲቪ ያሰራጩታል፡፡ ኢትዮጵያ ከምትገኝበት  ምድብ 1 ባሻገር በምድብ 2  ዲሪ ኮንጎ፤ አይቬሪኮስት፤ ሴኔጋልና ኡጋንዳ፤ በምድብ 3 ሞሮኮ፤ ሱዳን፤ ጋናና ማዳጋስካር፤ በምድብ 4 ማሊ፤ አንጎላና ሞሪታኒያ እንዲሁም በምድብ 5 ካሜሮን፤ ኮንጎና ኒጀር ተደልድለዋል፡፡ በሻምፒዮናው ታሪክ ከፍተኛውን  ውጤት ያስመዘገቡ አገራት  እያንዳንዳቸው ለሁለት ጊዜያት ሻምፒዮን ለመሆን የበቁት ሞሮኮና ዲ.ሪ.ኮንጎ ናቸው።

Read 874 times