Saturday, 07 January 2023 00:00

በዓል ሲደርስ

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(1 Vote)

 ማታ፣ ጭር ሲል የሚሰማው የሽታዬ ድምፅ ጠፍቷል። የእንቁራሪቶች ሲርሲርታ፣ የሽታዬ ኡኡታ የለም። ምን ዋጣቸው? ብዬ አሰብኩ። ሲኖር ዝም ያሉት ሲሞት እንደሚታወስ ሁሉ ፣ስትጮህ የማልረዳት ዝም ስትል ጨነቀኝ። ከምሽቱ 1:00 አካባቢ አዛን፣ ከምሽቱ  3:00 አካባቢ የሽታዬን ኡኡታ ክፉኛ ለምጄ ኖሯል።
[የቀይ ጤፍ እንጀራ፡ሽሮ ወጥ ከጎኑ ጎመን፡በአንድ ሞሶብ ቀረበ_እራት በላን።]
ባለቤቴ ዓይኔን እየቃኘች ነው የፍቅር ያልሆነ፣ የጥላቻም ያልሆነ፣ የመደነጋገር ዓይነት እይታ። እራቱ ከፍ ከማለቱ የእኔ ለመነሳት መጣደፍ አሳሰባት። ወሬ ትርጉም አልባነቱን ያወቅኩት አኳኋኗ (ድርጊቷ) ሲቆጣጠረኝና ስጨነቅ ነው። ምንም ሳትለኝ “አልጮኸችም” አልኳት ።
[ትንሽ ፈገግታ ፊቷ ላይ። ነጋች አልኩ በልቤ።]
«ታዲያ በዚህ ምሽት የት ልትሄድ ነው?»[እያማጠች ተናገረች]
«አልጮኸችምኮ»
«እና ኼደህ ዛሬ ለምን አልጮህሽም ልትላት ነው?»
ደነገጥኩ። ቁጭ_ብድግ_ቁጭ አደረገኝ ጭንቀት። ድጋሚ ተፋጠጥኳት_ባለቤቴን። ሰው ዝም ሲል ይጨንቀኛል። አጼ ሚኒሊክ የሕዝቡን ጉርምርምታ ከመጤፍ ሳይቆጥሩ ዝምታውን እንደፈሩ ሁሉ እኔም የሚስቴን ዝምታ ፈራሁ። ተሳዳቢ ሚስቴ ደርሳ ዝም ብትለኝ ተርበደበድኩ_እገባበት ቀዳዳ ፣እሾልክበት ውሉ ጠፋኝ።
«ቀልድ ላውራሽ?» [ድንገት ነበር የተነፈስኩት፤ የጨነቀው እርጉዝ ያገባልና]
«ቀጥል» [አመላለሷን አልወደድኩትም። ግን ቀጠልኩ ...]
 አምና ነው አሉ።
«አሉ ሳትል አውራኝ»
“እሺ። ቤቲ ያቺ ዳሌያሟ አወቅሻት? [በአዎንታ እራሷን ነቀነቀች]። ለበዓለ እግዚአብሔር ስለት ተስላ ኖሮ፣ ስለቷም ደርሶላት ኖሮ፣ ተደስታም ኖሮ፣ ደስታዋንም ለመግለፅ ፈልጋ ኖሮ..”
አቋረጠችኝ። “ኖሮ ...ኖሮ አትበል። ዝም ብለህ አውራ!”
«ዝም ተብሎ ይወራል እንዴ?»
«አይ እንግዲህ!...ቀጥል»
“እሺ። እናልሽ የባል ማግባት ስለቷን እና ደስ መሰኘቷን ለመግለጽ “ለእኔ የደረሰለኝ ነገር ለእናንተም ይድረስላችሁ” ብላ ተናገረች። ይሄን የሰሙ ጎረቤቶቿ ቀና ሴት እያሉ አሞገሷት። ቆይቶ..ባሏ መንደር ለመንደር ጥንብ እንደሸተተው አሞራ ይዞር ጀመር። ቀስ በቀስ ቀና ሴት ብለው ያሞገሷትን ሴቶች በተራ ተኛቸው። እነሱም የተቀማ ወንድ ይወዳሉና ደስታ ውስጥ ሆኑ። ቤቲ የባሏን ማመንዘር ባወቀች ሰዓት ሰፈሩን ቀወጠችው። ከመንደሩ ሴቶች ጋር ወገቧን ይዛ ስድድብ ገጠመች። ከንግግራቸው መሐል  አንዷ ሴት “ለእኔ የደረሰ ለእናንተም ይድረስ” ብለሽ መርቀሽን አልነበር? ዛሬ ለአንቺ የሆነው ባል ለእኛ ቢሆን ምንድን ነው ነውሩ”  አለቻት። አያስቅም?
[ከንፈሯን አጣመመችብኝ። ነገሬን አልወደደችውም።]
በዓል ደርሷል አለች።
ይድረሳ አልኩ በልቤ። ለእርሷ የሚታይ አመጼ ሳይሆን ዝምታዬ ነው። በጣቷ ጠቁማ አስቀመጠችኝ። መፋጠጡን ተያያዝነው። በመሐከላችን ረጅም ፀጥታ ሰፈነ። ደስ ሲል። ሁለታችንም በሐሳብ መባዘን ጀመርን።
ድንገት ሣቅሁ።
«ምን አሣቀህ?» [ተኮሳተረች]
«ትናንት የነገሩኝ ቀልድ ትዝ ብሎኝ »
አሁንም ነገሬ አልጣማትም። አንገቷን አቀረቀረች። እራሷ በእግሮቿ መሐል ሆነ። አድራሻው የሚገመት ውኃ መሬት ላይ ጠብ ሲል ይታያል - እንባዋ ነው።
ሰውነቴን ድንጋጤ ተዋረረኝ። ምን በደልኳት? ምን አጠፋሁ? እራሴን በጸጸት አለንጋ ገረፍኩት። ነፍሴ ስትደማ ታወቀኝ። በዓል ሲደርስ ለቅሶ ? በዓል ሲደርስ ኩርፊያ? ምን ይሆን ጥፋቴ?
ድንገት ቀና አለች። እንባዎቿ በሁለት በኩል ይፈሳሉ። የአፍንጫዋን ተራራ እየታከኩ፣ ኩሬ ስርጉዶቿን እየሞሉ፣ የከንፈሯን ጠርዞች አካለው፣ ግማሾቹ ወደ መሬት፣ ግማሾቹ ወደ አፏ ይገባሉ።
«ለአንተ ሁሉም ነገር ግድህ አይደለም» [እንባዋን እየጠረገች]
«እውነት ነው ደንታዬ አይደለም።ግን ምን በደልኩሽ?»
«የሌላው ባል ...በዓል ሲደርስ ቤቱን በአዲስ ዕቃ ይተካል..አዲስ ቴሌቪዥን፣ አዲስ ሶፋ፣ አዲስ ብፌ... ለልጆች ልብስ፣ ለሚስቱ ልብስ፣ ምን የማይቀይሩት አለ?.. አንተ ግን.. ጨመቆት!»
«አየሽ እነሱ ኢንቨስት የሚያደርጉት ዕቃ ላይ ነው። ውስጣቸው ላይ ኢንቨስት ቢያደርጉ የት በደረሱ?»
«ወሬማ ታውቃለህ...»
ጠጋ አልኳት። የሴት ልጅ ቁጣ እስከምትታቀፍ ነው። ያ የጋለው ስሜቷ እቅፌ ውስጥ በረዶ ሆነ። ተመልሳ እንደምትናደድ ሳስብ ሰውማ የውኃነት ባህርይው በገሃድ አለ አልኩ። ውኃ ፍሪጅ ውስጥ ሲገባ ጠጣር በረዶ፣ በረዶው ከፍሪጅ ሲወጣ ፈሳሽ ውኃ ሰውም እንደዚያ ነው። ጠጣር፤ፈሳሽ።
ውስጤ ቃል ያቀባብል፣ አፌም ይተኩስ ጀመር። በዓሉን በደስታ ነው የምናሳልፍ። ቀንዱ የዞረ በግ እገዛለሁ፣ አሟላ የምትይኝን ዕቃ አሟላለሁ። ምንጣፍ፣ አልጋ፣..ወዘተ እንቀይራለን። ይኼ ደስታ የሚሰጥሽ ከሆነ አደርገዋለሁ።
በስሱ ትተነፍስ ጀመር።
እጇ በወገቤ ጥምጥም ዞሯል። አካሏን ከአካሌ በጥብቅ ሰፍተዋለች። «እንዲህ ቀና ስትሆን ሲያምርብህ» የሚል ቃል እንደጸነሰች ገመትኩ ።
«ሽታዬ ያልጮኸች’ኮ በዓል ስለደረሰ ነው። በዓል ሲደርስ ባሏ ያቀብጣታል። ያ ተደባዳቢ ባሏ ገር የሚሆነው የበዓል ሰሞን ነው»
ሣቅሁባት።
«ይህች በዓል ሲደርስ ጽድቅ..ጽድቅ ጨዋታ መች እወዳታለሁ»
«አንተማ ...» [አቋረጠችኝ]
ንግግሯን አልጠበቅኩም። ከተወጣጠረ የደም ሥሯ፣በፊቷ ከተደፉት የላብ ዘለላዎች ሐሳቧን አነበብኩ። በዓል ሲደርስ የሚያሸበሽበው ሳይጾም የከረመው ነው ልላት አስቤ ተውኩት። በግ ሊገዛ የሚሮጠው፣ አልባሳትን በውድ የሚሸምተው፣ ቤቱን በአዲስ ዕቃ የሚያጥለቀልቀው ማን ነው? ብዬ ልጠይቃትም አሰብኩ_ያው ያልጾመ ነው ብዬ ተውኩት። ብዙ ወቀሳ ነበረኝ፤ በይደር ያዝኩት።
«ቃል ገባህ አደል ልታደርግልኝ?»
«አዎ! አዎና»
ደስ አላት። ስማ ለቀቀችኝ። ማምሸዋን ስታንቆለጳጵሰኝ አደረች። እኔም«ይቺ ጠጋ ጠጋ ነገር ፍለጋ ነው» እያልኩ ነጋ።
ብዙ የታሸጉ ብሮች ይዤ ወጣሁ። ከሶፋ ልጀምር ከምንጣፍ? ከቡፌ ልጀምር ከአልጋ? ግራ ገባኝ።
ወደ ሶፋ ቤት ኼድኩ ።
ሶፋ የሚሰሩ አናጢዎች በሥራ ተጠምደዋል። ተዘጋጅተው የተኮለኮሉ አብረቅራቂ ሶፋዎች አሉ። በጅምር ላይ ያሉ ሶፋዎችንም እየጨረሱ ነው። ዋጋው ድሮ ቤት ከእነ ቦታው የሚገዛበትን ከፍዬ አስጫንኩ። ደስ አላት። ሌሎቹንም ዕቃዎች በተራ አስገባሁ። ጎረቤቶቻቸን በነጠላ አፋቸውን ለጉመው እንኳን ደስ አለሽ የሚል ቅናት ይዘው መጡ።
ያን ቀን ቤቱ ፍስሃ ሆነ። አጥባኝ የማታውቀውን እግሬን አጠበች፣ በደንብ የተከሸነ ምግብ ሰራች፣ ምን ጎደለብህ? ምን ይሟላልህ? በየት ልዙርልህ? ያልተባልኹት አልነበረም...
ልጆቻችን የመሰላል ቅርፅ ሰርተው ተኝተዋል፤ ኬክሮስ እና ኬንትሮስ ሆነዋል። የባለቤቴ ፊት ያለወትሮው ነግቷል። የሽታዬ ድምፅ ድራሽ አባቱ ጠፍቷል። አይ በዓል! አልኩ በልቤ። አንተን ጠብቆ ሰው መደሰቱ ቢያስገርመኝም፤ በአንተ ሰበብ የተከፉት መነቃቃታቸው ደስ ያስብለኛል እያልኩ አጉተመተምኩ።
ገና ነው። ታኀሣሥ 29። የክርስቲያን በዓል። የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት።
ባለቤቴ ለበዓሉ የተዘገጃጀውን በሙሉ ለሆድ እንዲመጥን አድርጋ ሰራች። የፈጣሪን ልደት ለማስዋብ ደፋ ቀና እያለች ነው። የገና አባት ይሉትንም ልጄ ገዝታ አምጥታለች [ጥቅሙ ባይገባኝም]። ቤቱን ቄጤማ ወርሶታል። የማይጨስ ጭስ፣ የማይጠጣ መጠጥ የለም። የምግብ ትሪዎች አብረቅርቀዋል። በግራ እጅ የተቀረቀረው ሁሉ ወጥቷል። ለበዓሉ ካልሆነ የተባለው ቀሚስም ተለብሷል። ሁሌ በዓል በሆነ የሚያስብል ድባብ፣ በአላፊ አግዳሚዎች ፊት ላይ ሁሉ የደስታ ብርኀን ዘንግ ይታያል ።
[ሥጋ፣ ወይን፣ ቄጤማ
ጭስ፣ ውበት፣ ሸማ
ሁሉም ሁሉም የፈካ። ደስ አለኝ፤ ደስም አላለኝም።]
የሰው ልጆች ደስታ በበዓላት ቀን ብቻ መታየታቸው ገረመኝ። የበዓል ሆድ የሚቀበለው ብዙ ፣የአዘቦቱ ግን ሽሮ የሚያርበት መሆኑ ደነቀኝ። የበዓል ጊዜ የሚሰባሰበው ዘመድ አዝማድ ለዓመት ያህል ሳይጠያየቅ መክረሙም ታወሰኝ። በዓል ታክኮ የሚመጣ ደስታ በዓል ሲሸሽ ይሸሻል አለኝ ውስጤ። ለበዓል ብዙም የተነሳሳሁ አይደለሁም። ለሚነሳሱት ግን ወጥመድ መሆንን አልሻም። ዕቃ ብቀይር ለሚስቴ ደስታ እንጂ ለእኔ አልነበረም።
በዓሉ አለፈ። በማግሥቱ ሁሉም ትዝታ ሆነ።
ዋለ አደረ። ዕቃ ለመግዛት የተበደርናቸው ሰዎች በነጋ በጠባ ከደጃፋችን ይሰየሙ ያዙ። የገዛነው አዲስ አልጋ ይጎረብጠን ጀመር። የበላነው ምግብ ቁርጠትን አትርፎልን ሄደ። ኦ በዓል!
ዋለ አደረ። የሚስቴ ፊት ተመልሶ ጭጋግ ዋጠው። የሽታዬም ኡኡታ እየጨመረ መጣ። ይባስ ብሎ ለበዓሉ በግ ሰርቆ ኖሯል ያረደላት፤ ታሰረ። ኦ በዓል!
ዋለ አደረ። ዘመድ በሞረሽ አልገኝ አለ። ሲጮኹ የሚረዳ፣ ሲቸገሩ የሚያግዝ ጠፋ። የመብሉ ጊዜ የመጡ እግሮች ድራሻቸው ጠፋ። ኦ በዓል!
የፈራሁት ቀን ደረሰ፣ የጠላሁት ቀን ደስታዬን ወረሰ። በዓልን የምወደው በምሥጢሩ እንጂ በግርግሩ አልነበረም፤ በዓልን የምወደው በመታሠቢያነቱ እንጂ በሌላ ውበቱ አልነበረም። ቢሆንም ፈጣሪ ለሰው ልጆች እንዳዘነ አርዕያዬን ተከትዬ ለሚስቴ ስል በዓል አክባሪ ሆንኩ። ለዕቃ ኢንቨስት አደረግሁ። እስከዛሬ ለተከበሩ በዓላት የዕቃ ሸመታ ላይ ኢንቨስት ከማደርግ፣ ማንነቴ ላይ ኢንቨስት ባደርግ የት በደረስኩ? ኦ በዓል በአንተ ሁሉ ሆነ።

Read 321 times