Saturday, 14 January 2023 10:25

ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ለሀገር ውስጥ የቤት ተመዝጋቢዎች የጎጆ ሮስካ እጣ አወጣ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙና ቤት የመገንባት አቅማቸው አነስተኛ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ያዘጋጀውን “ጎጆ ሮስካ” የተሰኘ የቤት ዕቁብ የአገር ውስጥ ሞዴል እጣ ማወጣት ሥነ-ስርዓት አከናወነ።
ሥነ-ስርዓቱ ባለፈው ማክሰኞ ጥር 2 ከሰዓት በኋላ በግራንድ ኤሊያና ሆቴል የተከናወነ ሲሆን ዕጣው ለ105 ሰዎች ወጥቷል።
ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ከዚህ ቀደም በወዳጅነት አደባባይ የእጣ ማውጣት ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም በቴክኖሎጂው ብልሽትና በአንዳንድ የቴክኒክ ችግሮች ሳቢያ የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓቱ ሳይተገበር መቅረቱ ይታወሳል። ኩባንያው ከዚህ ቀደም የተፈጠሩ ስህተቶችን በማጤንና በማረም ይሄኛው የእጣ አወጣጥ እንከን እንዳይገጥመው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጉን የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አልማው ጋሪ ተናግረዋል።
በዚህ እጣ ውስጥ የተካተቱት ተመዝጋቢዎች እስከ መስከረም 6 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የተመዘገቡት ብቻ ሲሆኑ ፤ከዚህ ቀን በኋላ ተመዘገቡት በቀጣዩ ዙር ዕጣ ውስጥ እንደሚካተቱ ዋና ስራ አስያጁ ጨምረው ገልጸዋል።
ለ105ቱ ዕድለኞች ሁለት ሳይቶች ላይ የቤት ግንባታ የሚካሄድ ሲሆን፤ አንዱ ብሄረጽጌ አካባቢ ሌላው ደግሞ ሀያት መቄዶኒያ አካባቢ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። በእነዚህ ሳይቶች በድምሩ 118 ቤቶች የሚገነቡ ሲሆን በብሄረፅጌ አካባቢ 42 ቤቶች፤ በሀያት መቄዶኒያ  ደግሞ 63 ቤቶች በድምሩ የ105  ቤቶች ዕጣ ይፋ ተደርጓል። በዚህ እጣ ለመሳተፍ ከተመዘገቡና ለእጣው ብቁ ከሆኑ 8 ሺህ 127 ተመዝጋቢዎች መካከል ነው የ105 ቤቶች ዕጣ በይፋ የወጣው፡፡
 የእጣ ማውጫ መተግበሪያው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴክኖሎጂ ፋኩሊቲ የበለጸገ ሲሆን የእጣ አወጣጡን ያለምንም ችግር በስኬት ማከናወን መቻሉን ሀላፊዎቹ ተናግረዋል።
በእለቱ የእጣ አወጣጥ ሥነ-ስርዓት ላይ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የዳሸን ባንክ ከፍተኛ አመራሮች፣ የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ የቦርድ አመራሮች፣ በርካታ የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ደንበኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ታድመዋል።

Read 2217 times