Saturday, 14 January 2023 10:43

ፍቅር ያላት አገር፣ ሽለ - ሙቅ ናት!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 በጥንት ዘመን የነበረ አንድ ንጉሥ ታላላቅ ጠበብት፣ መኳንንት፣ መሣፍንት እንዲሁም የጦር ኃይል አባላትን ጨምሮ ህዝቡን ሰበሰበና አገር ለማዳንና ህልውናዋ ተጠብቆ እንድትቆይ “ወሳኝ እኔ ነኝ” የሚል እጁን ያውጣና ምክንያቱን ያስረዳኝ አሉ፡፡
በመጀመሪያ የጦር አበጋዙ ተነስቶ፤
“አገር የማድን፣ የአገርን ህልውና የማስጠብቅ እኔ ነኝ” አለ፡፡
ሁለተኛ የተነሳው ምሁሩ ነበር፤
“ያለ እኔ ዕውቀት አገር ደህንነቷና ህልውናዋ አይጠበቅም፡፡ ምንም ነገር ስትሰሩ፣ እኔን ያማክሩ አለ፡፡ ስለ ጦር መሳሪያም ቢሆን መሰረቱ የእኔ እውቀት ነው!” አለ፡፡
ሦስተኛው ገበሬው ነው፤
“እኔ ካላመረትኩ ሁሉም ከንቱ ነው ንጉሥ ሆይ።
 ስለዚህ በልተው ካላደሩ፣ ምንም አይሰሩ!” አለ፡፡
ነጋዴው ተነሳ፤
“የጦር መሳሪያውንም፣ የምሁራኑንም የምርምር ዕቃ፣ የገበሬውንም ምርት የሚያንቀሳቅሰው የእኔው የንግድ ሥራ ነው! በእኔ ኃይል ነው የአገርን ደህንነትና ህልውና የሚያቆዩት ንጉሥ ሆይ!” አለና ተቀመጠ፡፡
የቢሮ ኃላፊው እጁን አውጥቶ ተነሳና፤
“ንጉሥ ሆይ! የተናገሩት ሁሉ ዕውነት ነው፡፡ ነገር ግን የጽህፈት ሥራና የቢሮክራሲ ደም - ሥር ካልታከለበት ከንቱ ነው፡፡ የእኔን ቢሮክራሲ የማያከብር ዋጋ አይኖረውም!”
የጥበብ ሰው ተነስቶ፤
 “አገርን የሚያሽር የጥበብ ሥራ ነው! ምንም ነገር ተነስቶ ጥበብ ካልተጨመረበት ዐይን አይገባም፡፡ ህይወት አይኖረውም!” አለ፡፡
የፋይናንስ ሃላፊው፤
“ንጉሥ ሆይ! ምንም አያሳስብም፡፡ ያለ ሂሳብ፣ ያለ ፋይናንስ ማንም የትም አይንቀሳቀስም! እኔ ሂሳብ ከተቆጣጠርኩ፤ አገር አማን ናት!” አለ፡፡
በመጨረሻ አንዲት ምስኪን ሴት ተነስታ፤
 “ንጉሥ ሆይ! ምንም ተባለ ምን፣ ወሳኙ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ነው ገዢው!” አለች፡፡
ንጉሡ አሰቡ አሰቡና፤ “ያለ ፍቅር ምንም ነገር ከንቱ ነው፡፡ አንቺ አማካሪዬ ትሆኛለሽ” አሉና ደመደሙ፡፡
***
“እስከ ዛሬ ጥሩ ጦርነት አልነበረም፡፡ መጥፎ ሰላምም ታይቶ አያውቅም!” ይላል ፍራንክሊን፡፡ ታላቅ ጦርነት አንድ አገር ላይ ሦስት አሻራ ትቶ ያልፋል፡-
ሀ. የአካል ጉዳተኞች ሠራዊት
ለ. የሐዘንተኞች ሠራዊት
እና    ሐ. የሌቦች ሠራዊት
ይሄ ሁሉ የፍቅር መጎናፀፊያ በሌላት አገር የሚከሰት ነው፡፡ ከቤተሰብ እስከ ህብረተሰብና እስከ ጎረቤት አገር ድረስ  ፍቅር ከሌለ የሚከሰት ብዙ ጎዶሎ ሥፍራ አለ፡፡ ያንን ለመሙላት የሞቀ ፍቅር ያስፈልጋል፡፡ ጦር፣ ትምህርት፣ ምርት፣ ንግድ፣ ቢሮክራሲ፣ ጥበብ፣ ፋይናንስ ወዘተ … ሁሉም የፍቅር ተገዢ መሆን አለባቸው - አለዛ ሰላም አይኖርም!
የዓለም ኢንፎርሜሽን ቀን እናከብራን፡፡
የፍትሕ ቀን እናከብራለን፡፡
የፕሬስ ቀን እናከብራለን፡፡
የአረጋውያን ቀን እናከብራለን፡፡
የወጣቶች ቀን እናከብራለን፡፡
የቫላንታይን ቀንም እናከብራን፡፡
የእጅ መታጠብ ቀንም እናከብራለን!
ምኑ ቅጡ! አያሌ የምናከብራቸው ቀናት አሉ፤ ይኖራሉም። ወደንም ይሁን ሳንወድም! የዓለምም ይሁን የአገር! ወጣም ወረደ፤ ሁሉም ፍቅር ይፈልጋሉ፡፡ ፍቅሩን በዛ አድርጎ ይስጠን!
ክፉ ክፉውን በማሰብ አገር አናድንም፡፡ መግባባት፣ መናበብ፣ መቀራረብ፣ ውዝግብን ከየሆዳችን ማውጣት፣ ለመፋቀር መዘጋጀት … የአገር ፍቅር መሰረት ነው፡፡ የጀግንነት ምልክት ፍቅርን መላበስ ነው!
ለወታደሩ ፍቅር ይስጠው፡፡ ለፖለቲከኛው ፍቅር ይስጠው፡፡ ለምሁሩ ፍቅር ይስጠው፡፡ ለሂሳብ አዋቂው ፍቅር ይስጠው፡፡ ለነጋዴው ፍቅር ይስጠው! ለጥበብ ሰው ፍቅር ይስጠው! አገር በፍቅር ትድን ዘንድ ለሁላችንም ፍቅር ይስጠን፣ ብርታት እና ፅናቱን ይስጠን!
ኮስተር ብለን ካሰብን ምርት ያለ ፍቅር አይመጣም፡፡ ዕድገት ያለፍቅር አይመጣም። የመንፈስ ተሐድሶ ፍቅርን ይሻል፡፡ ለውጥ ፍቅርን ይሻል፡፡ A change is equal to rest የሚለው የአይንስታይን አባባል መለወጥ ማረፍ ነው እንደማለት ነው፤ ትርጉሙ እያደር ሊገባን ግድ ነው። እረፍት የሰላም መደላድል ነው፡፡ ለውጥ ለአዲሱ ሁኔታ ተገዢ መሆንን ይጠይቃል! Resist conservatism! እንደሚሉት ነው ፈረንጆቹ፡፡ “ወግ - አጥባቂነት ይውደም” የሚለው የዱሮ መፈክር ይበልጥ ይገልጠው ይሆናል! መንገዶች ሁሉ ወደ ለውጥ ያመሩ ዘንድ ዐይናችንን እንግለጥ!!
ለውጥ ፍቅር ይፈልጋል፡፡ ምነው ቢሉ? ፍቅር ያላት አገር ሽለ-ሙቅ ናት፤ (Fertile) ወላድ ናትና! ምርታማ ናትና! ለዚያ ያብቃን!



Read 2224 times