Saturday, 14 January 2023 10:44

ኢትዮጵያውያኑ በቦስተን ማራቶን ላይ ተጠብቀዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)


       በ127ኛው የቦስተን ማራቶን ላይ በምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች መካከል ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግ ሲሆን ኢትዮጵያውያኑ በወቅታዊ ብቃታቸው ውጤታማና ለአሸናፊነት ተጠብቀዋል፡፡  በወንዶች ምድብ 21 አገራትን የሚወክሉ ምርጥ የማራቶን አትሌቶች ይሳተፋሉ፡፡ ከመካከላቸውም  ከ2 ሰዓት ከሰባት ደቂቃ በታች  የሚገቡ 15 አትሌቶች መኖራቸው አስደናቂ ፉክክር የሚፈጥር ይሆናል፡፡ በወንዶች ምድብ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የዓለም ሪከርድን የያዘው ኤሊውድ ኪፕቾጌ መሳተፉ ነው። ሄርፓሳ ነጋሳ፤  ሹራ ኪታታ፤ አንዱአለም በላይና አንድአምላክ በሃይሉ  ኢትዮጵያን በመወከል የሚሮጡ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በቦስተን ማራቶን ላይ በሴቶች  ምድብ  ልዩ ትኩረት የሳበችው ደግሞ የኢትዮጵያዋ አማኔ በሬሶ ናት፡፡ በ2022 የቫሌንሽያ ማራቶን ላይ ያሸነፈችው አማኔ በወቅቱ  ያስመዘገበችው 2 ሰዐት ከ14 ደቂቃዎች ከ58 ሴኮንድ  በማራቶን የኢትዮጲያ ክብረወሰን  እንደሆነ ይታወቃል። በማራቶን የዓለም ሻምፒዮን የሆነችውና  በቶኪዮ ማራቶን በሶስተኛ ደረጃ የጨረሰችው ጎይተቶም ገብረስላሴ፤ በ2021 በበርሊን ማራቶን ሁለተኛ የነበረችውና በ2022 ቶኪዮ ማራቶን በ5ኛ ደረጃ የጨረሰችው ህይወት ገብረማርያም፤ በ2019 በቺካጎ ማራቶን 2ኛ፤ በ2021 ኒውዮርክ ማራቶን 3ኛ እንዲሁም በ2022 ቦስተን ማራቶን ሁለተኛ ደረጃ የወሰደች አባቤል የሻነህ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው።  ኬንያን በመወከል ደግሞ የዓለም ክብረወሰን የያዘችው ብሪጂድ ኮሴጊ፤ ያለፈው የቦስተን ማራቶን አሸናፊ ፔሬስ ጄፕቺሪር፤ ሁለት ጊዜ የቦስተን ማራቶን ሻምፒዮን የሆነችው ኤድና ኪፕላጋት ይጠቀሳሉ፡፡
የቦስተን ማራቶን አሸናፊዎች በሁለቱም ፆታዎች 150ሺ ዶላር በአዘጋጆቹ የሚሸለሙ ሲሆን ለሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ  75ሺ ዶላርና 40ሺ ዶላር ሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡  የቦታውን ሪከርድ ለሚያስመዘግብ አትሌት ደግሞ 50ሺ ዶላር ቦነስ ይበረከታል፡፡
ባለፉት 126 የቦስተን ማራቶኖች ከ27 በላይ አገራትን የወከሉ አሸናፊዎች ተገኝተዋል። 108 አሸናፊዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚዋ አሜሪካ ስትሆን፤ ኬንያውያን 34 እንዲሁም ካናዳ 21 አሸናፊዎችን አስመዝግበዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑም በወንዶች 6 ጊዜ እንዲሁም በሴቶች 8 ጊዜ ቦስተን ማራቶንን አሸንፈዋል፡፡ በወንዶች በ1989 ላይ አበበ መኮንን፤ በ2005 ላይ ሃይሉ ንጉሴ፤ በ2009 ድሪባ መርጋ፤ በ2013ና በ2015 ሌሊሳ ዴሲሳ እንዲሁም በ2015 ለሚ ብርሃኑ አሸንፈዋል፡፡ በሴቶች ደግሞ በ1997 በ1998 እና በ1999 ለሶስት ተከታታይ ግዜያት ፋጡማ ሮባ፤፤ በ2008 ድሬ ቱኔ፤ በ2010 ጠይባ ኤርኬሶ፤ በ2014 ብዙነሽ ዳባ፤ በ2016 አፀደ ባይሳ እንዲሁም በ2019 ወርቅነሽ ደገፋ አሸንፈዋል፡፡

Read 1517 times