Saturday, 14 January 2023 10:47

ሴት ካለማህጸን ልትፈጠር ትችላለች፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

  በአለም ላይ በየወሩ ለመውለጃ እድሜ የሚጠጉ 1.8 ቢሊዮን የሚሆኑ ሴቶች የወር አበባ  ያያሉ።
የወር አበባን በተመለከተ ከብዙ ሴቶች የተለያዩ ገጠመኞች ይሰነዘራሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል፤
የወር አበባ መምጫው የተስተካከለ አይደለም፡፡
አንዳንዴ በሁለት ወር እና ከዚያ በላይ ቆይቶ ይመጣል የሚሉ አሉ፡፡
በየአስራ አምስት ቀኑ ይመላለሳል የሚሉም አሉ፡፡
የወር አበባ ሲመጣ ከባድ የሆነ የእራስ ምታት እና ሌላም ሕመም ይሰማኛል የሚል አስተያየትም ይሰነዘራል፡፡
ይሄ ነገር በተደጋጋሚ የዘገብነው ቢሆንም ምንጊዜም ለገጠመኙ እድሜአቸው ደርሶ የሚያስተናግዱ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ስለሚተኩ፤ እንዲሁም መረጃን ለማግኘት የሚቸገሩ ስለሚኖሩ ዛሬም እናነሳዋለን፡፡ ለዚህ እትም የጋበዝናቸው ባለሙያ ዶ/ር እዮብ አስናቀ ይባላሉ፡፡ ዶክተር እዮብ በአበበች ጎበና የእናቶችና ህጻናት ሆስፒታል የማህጸንና ጽንስ ህክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡
ለዶ/ር እዮብ የመጀመሪያ ያደረግነው ጥያቄ የወር አበባን ተፈጥሮአዊ ሁኔታ የሚመለከት ነበር፡፡ እሳቸውም እንዳሉት የወር አበባ በሴቶች ላይ አንዱ ተፈጥሮአዊ ኡደት ሲሆን በአለም ላይ በየወሩ ለመውለጃ እድሜ የሚጠጉ 1.8 ቢሊዮን የሚሆኑ ሴቶች የወር አበባ  ያያሉ፡፡ የወር አበባን የሚቆጣጠሩ ሆርሞኖች የሚመነጩት ከአንጎል ሲሆን ከአንጎል የሚመነጩት ሆርሞኖች ወደ እንቁላል ማምረቻ በመሄድ በየወሩ እንቁላል እንዲዘጋጅና እንዲለቀቅ ያደረጋሉ፡፡ ይህ እንቁላል ሲለቀቅ ጽንስ ይፈጠራል በሚል የማህጸን ግድግዳ እራሱን ያዘጋጃል፡፡ ይህ ክፍል ዋናው መሰረት ደም ቢሆንም እንደ ፕሮጄስትሮን (progesterone) ሰውነትን ከኢንፌክሽን የሚከላከሉ እንደ የነጭ የደም ሴል ዘሮች እና የመሳሰሉ ከደሙ ጋር እየተቀላቀሉ የሚወጡ ንጥረ ነገሮች አሉት፡፡ ከደሙ ጋር እየተቀላቀሉ የሚወጡት ንጥረ ነገሮች ከውስጠኛው ማህጸን ክፍል ተቀርፎ ከሚወጣው አካል ጋር ተቀላቅሎ ሲወርድ የወር አበባ ይባላል፡፡ ማህጸን ሶስት ክፍሎች አሉት እነርሱም ውስጠኛው የማህጸን ክፍል (ኢንዶሜትርየም) ማህከለኛውና ዋናው (ማዮሜትር) እና የማሀከለኛውን የሚሸፍነው የውጨኛው ክፍል ሴሮሳ ይባላል፡፡
ጥያቄ፦ በወር አበባ ወቅት ከማህጸን እየተቀረፈ ከደም ጋር እየተቀላቀለ የሚወጣው ንጥረ ነገር በዚህ መልክ ከሰውነት መወገዱ ጉዳት አያስከትልምን?
መልስ፦ የሚጎዳ ነገር አይደለም፡፡ በየወሩ እየተቀረፈ የሚወጣው የማህጸን ግድግዳ ሆኖ የላይኛው 2/3ኛው ክፍል ነው፡፡ እርግዝና ባለመፈጠሩ ምክንያት የላይኛው 2/3ኛው ተቀርፎ ከወጣ በሁዋላ ከታች ያሉት 1/3ኛው ክፍል የማህጸን ግድግዳ ሴሎች እየተራቡ ያንን ተቀርፎ የወጣውን የማህጸን ግድግዳ ይተኩታል፡፡  ለቀጣዩ ጊዜ ደግሞ ተተኪውን የማህጸን ክፍል ሴሎች ተራብተው ይተኩታል፡፡ እርግዝና ሳይካሄድ ከቀረ እነዚያ ይቆጣጠሩ የነበሩ ሆርሞኖች ይቀንሳሉ፡፡ እነዚህ ሆርሞኖች በየወሩ የሚጨምሩበት የሚቀንሱበት የእራሳቸው አካሄድ አላቸው፡፡ እርግዝና ሳይካሄድ ቀርቶ እነዚህ ሆርሞኖች ሲቀንሱ ከውስጥ ሆኖ ድጋፍ የሚያደርግለት ስለሚጠፋ ተቀርፎ ከማህጸን ይወጣል፡፡የንጥረ ነገሮቹ አወጋገድ በዚህ መልክ ስለሆነ ሴትየዋን የሚጎዳት ምንም ነገር አይኖርም። ይህ የንጥረ ነገር ከደም ጋር ተቀላቅሎ የመውጣት ሁኔታ  ከተለያዩ ነገሮች ጋር ከተገናኘ ግን ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ ደም ለረዥም ጊዜ ሲፈስ ሴትየዋን ሊጎዳት ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ በጤና ላይ ምንም የሚያስከትለው ጉዳት የለም። እርግዝና ባለመፈጠሩ ምክንያት መወገድ ያለበት ይወገዳል፡፡
ጥያቄ፦ የወር አበባ የማይታይበት ምክንያት ይኖር ይሆን?
መልስ፦ የወር አበባ የማይታይበት ምክንያት አለ፡፡ የወር አበባ አለማየት ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው፡፡ በህይወት ዘመናቸው ሙሉ በሙሉ የወር አበባ አይተው የማያውቁ አሉ፡፡ (Primary Amenorrhea) አንዳንዶች ደግሞ የወር አበባ ማየት ከጀመሩ በሁዋላ በተለያዩ ምንያቶች የሚቋረጥበት አጋጣሚ አለ፡፡ ይህ ደግሞ (Secondly Amenorrhea)  ይባላል፡፡
በህይወት ዘመናቸው የወር አበባ ሳያዩ የሚኖሩ (Primary Amenorrhea) ምክንያቶቹ የተለያዩ ናቸው፡፡
የማህጸን አለመፈጠር ሊኖር ይችላል፡፡
የሆርሞን በተገቢው ሁኔታ አለመመንጨት ሊኖር ይችላል፡፡
(Secondly Amenorrhea) ሰከንደሪ አሚኖሪያ) የሚባለው ደግሞ በመውለጃ እድሜ ላይ ያለች ሴት ምናልባት በእርግዝና ላይ ካለች፤
ጭንቀት፤ የክብደት መዋዠቅ ካለባት፤
የአመጋገብ ችግር …የመሳሰሉት ለወር አበባ በጊዜው አለመታየት ምክንያት ይሆናሉ፡፡
ጥያቄ፦ ማህጸን ላይፈጠር ይችላል ሲባል ምን ማለት ነው?
መልስ፦ እንግዲህ ሴት ሆኖ መፈጠርን የሚያመለክቱ ነገሮች ይታያሉ፡፡ ክሮሞዘፐም ሲታይ xx ስለሆነ ሴትነትን ያሳያል፡፡ ፀጉር አለ፤ የጡት ማጎጥጎጥ ይታያል፡፡ ነገር ግን ከጉርምስና ምልክቶች የወር አበባ መታየት አይስተዋልም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ማህጸን ጭርሱንም ስላልተፈጠረ ነው፡፡ ይህ በጣም በተደጋጋሚ የሚታይ ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ ይከሰታል፡፡ ይህ በኛም አገር አንዳንድ ሴቶች ላይ የሚታይ ነው፡፡ እነዚህ ሴቶች ወደህክምናው የሚቀርቡት ልጅ መውለድ አልቻልኩም፤ የወር አበባም አላይም ብለው ነው። እነዚህ ሴቶች ማህጸን ባይኖራቸውም እንቁላል ማምረቻው ግን አላቸው፡፡ ምክንያቱም ልጅ ሲጸነስ የሚቀመጥበት ማቀፊያው አይኖርም እንጂ በግራና በቀኝ ያሉት የእንቁላል ማምረቻዎች አሉ፡፡ የዘር ፍሬ አላቸው፡፡ ሆርሞንም በየጊዜው ይመነጫል፡፡  እዚህ ላይ መታሰብ ያለበት እነዚህ ሴቶች የዘር ፍሬ ቢኖራቸውም ማጸን ስለሌላቸው እና እርግዝናው ስለማይታሰብ እንደ ከማህጸን በላይ ያለ እርግዝና የመሳሰለ ችግር አይገጥማቸውም፡፡ በሰለጠነው አለም የራሳቸው እንቁላልና የባሎቻቸውን የዘር ፈሳሽ በማዳቀል በሚከራዩት ማለትም በሌላ ሴት ማህጸን ውስጥ ተቀምጦ የራሳቸውን ልጅ ሌላ ሴት እንድትወልድላቸው ይደረጋል፡፡ በኢትዮጵያ ይህ የማህጸን ኪራይ ህግ ስላልወጣለት አይተገበርም፡፡  
ጥያቄ፦ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የወር አበባን ለማታይ ሴት የሚሰጥ ህክምና አለ?
መልስ፦ የወር አበባ የማይታይበት ምክንያት ምንድነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡
ለምሳሌ…..
ሲፈጠሩ ማህጸናቸው ያልተፈጠረ ከሆነ ለእሱ የሚደረግ ምንም የህክምና እርዳታ የለም፡፡ በማህጸን ኪራይ ልጅ ለመውለድ ሲፈልጉ ያንን ከመርዳት ባሻገር ሌላ ምንም አይደረግም፡፡ ይህም በእኛ አገር አይተገበርም፡፡
ድንግልናቸው ድፍን ሆኖ የሚወለዱ እና ለወር አበባ መፍሰስ ምንም ክፍተት የማይኖራቸው ሴቶችም አሉ፡፡ ይሄንን በቀላሉ ማከም እና ማስተካከል ይቻላል፡፡ ስለዚህ እንደምክንያቱ ህክምናውም ይለያያል፡፡ ሊስተካከል የሚችል እንደመኖሩ የማይስተካከልም አለ፡፡
ጥያቄ፦ የወር አበባው ከተመረተ በሁዋላ በተለያዩ ምክንያቶች ላይወርድ ወይንም በሰውነት ውስጥ  ይቆያል ሲባል እንዴት ነው ሁኔታው?
መልስ፦ የወር አበባቸው ተፈጥሮአዊ ሂደቱን ጠብቆ በየወሩ ይመረታል፡፡ ነገር ግን
ስለማይፈስ ወሩን  ጠብቆ የሚመጣ ህመም ይኖራቸዋል፡፡
በተጨማሪም ደሙ በተጠራቀመ ቁጥር ከእንብርት በታች እብጠት ይኖራቸዋል፡፡ እብጠቱም ሽንትን የመዝጋት፤ድርቀት የማምጣት ባህርይ አለው፡፡
ሌላው ነገር ማህጸኑ በወር አበባ ደም ከተሞላ በሁዋላ በማህጽን ቱቦ ሄዶ እንቁላል ማምረቻው ላይ ጉዳት አምጥቶ የመሀንነት ችግር ሊያመጣ ይችላል፡፡
ስለዚህ እንደነዚህ ያሉ ችግሮች ያሉባቸው ሴቶች ወደህክምናው በጊዜው በመቅረብ መፍትሔውን ማግኘት ይገባቸዋል፡፡
ጥያቄ፡- የወር አበባ ሲፈስ መጠኑ ምን ያህል ነው? ጊዜውስ?
መልስ፡- አንዲት ሴት የወር አበባዋ በየወሩ መምጣት አለበት ፡፡ በአማካኝ በ28 ቀን ይመጣል ቢባልም ብዙ ጊዜ ከሃያ አንድ እስከ ሰላሳ አምስት (21-35) ባሉት ቀናት ከመጣ እና ከ2-7 ቀን ከፈሰሰ መጠኑም ከ30-60 ሚሊ ሊትር ወይንም ከ30-60 ሲሲ ከሆነ ትክክል ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ወይም 50% ደም ሲሆን 50% ከማህጸን ተቀርፈው የሚወጡ ህዋሶች እንዲሁም የተለያዩ ፈሳሾች ናቸው፡፡
ጥያቄ፡- ወር አበባ መዛባትን ማለትም መብዛት ወይም ማነስን እንደችግር ማየት ይቻላልን
መልስ፡- እንደ ችግር የሚታየው ፍሰቱ ከሁለት ቀን ያነሰ ከሆነ ፤ወይንም የወር አበባው ከሰባት ቀን በላይ ከቆየ እንዲሁም ብዛቱ ከጨመረ እና በተለይም የረጋ ደም አብሮት የሚወጣ ከሆነ፤ እንዲሁም ከሀያ አንድ ቀን ባነሰ ጊዜ ውስጥ የሚመጣ ከሆነ፤ ወይም ከሰላሳ አምስት ቀን በላይ የወር አበባ ሳይታይ ከቀረ፤ በተጨማሪም የወር አበባ ሲታይ ከእንቅስቃሴ የሚያግድ ከባድ ሕመም የሚያስከትል ከሆነ ችግር ያለበት የወር አበባ ይባላል፡፡    

Read 972 times