Saturday, 14 January 2023 10:49

የእኛ ሰው በኳታር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  (የሰብለ ነጋሽ ሌላኛው ገጽታ)
             
       (ካለፈው ሳምንት የቀጠለ)
“አባቴ ልብሱን አውልቆ ለድሃ የሚሰጥ ነው”
ሰው ቤት ሆኜ ተቀጥሬ ስሰራ ሰው እንዴት እንደሚናፍቅ፣ ምን ያህል በችግር ውስጥ ሆነህ ችግርህን የምታወራለት እንደምታጣ አውቀዋለሁ፡፡ ሰው ማገዝ የሚለው ነገር ከእንዲህ አይነት የስሜት መጎዳት የሚመነጭ ነው፡፡ በራሴ መኖር ስጀምር ሌሎችን ማገዝ እንዳለብኝ ተሰማኝ፡፡ ከጅምሩ በአስተዳደጌም ይኸው ነው፡፡ አባቴም እናቴም ደግ ሰዎች ናቸው፡፡ ሰዎች ሲያግዙ ሰዎች ሲረዱ ነው የማስታውሰው፡፡ በእኛ ቤት አንድም ቀን ሃብታም ሰው የተጋበዘበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። አባታችን በዓል ሲሆን እንግዳ አለ ተዘጋጁ ይለናል፡፡ ስንጠብቅ አስር አስራ አምስት ሰራተኞችን ሰብስቦ ነው ወደ ቤት ይዞ የሚመጣው፡፡ እንግዶቼ እነዚህ ናቸው ብሎ አባቴ በሳሎን ያስተናግዳቸዋል፡፡ ልብሱን አውልቆ ለድሃ የሚሰጥ ነው አባቴ፡፡ ይህ ተግባሩ ውስጤን እየነካው ነው ያደግሁት፡፡ በህይወትሽ ምንድነው የሚያስደስትሽ ካልከኝ፣ የሆነ ሰው የእኔን እርዳታ ፈልጎ ከእኔ አግኝቶ ተሳክቶለት ማየት በጣም ያስደስተኛል፡፡ ፀጋዬ እንደሆነ ነው የማስበው፡፡ ባለኝ አቅም ሰው እረዳለሁ።  ባይኖረኝም ተበድሬ መርዳት ያስደስተኛል፡፡ ዋጋን የማያሳጣው አምላክ፣ የልቦናዬን መሻት አይቶ ይመልሰልኛል፡፡ ስጠኝና ልስጥ ብዬ እለምነዋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ይመስገን ምንም አላሳጣኝም፡፡ ሰዎችን ሆስፒታል ሄጄ መጠየቅ እወዳለሁ፡፡ እስር ቤት ያሉትን አዘውትሬ እጠይቃለሁ፡፡ የተቸገሩ ሰዎች ካሉ ለመርዳት ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ሰው ማገዝ ደሜ ውስጥ ነው፡፡
ኳታር ምርጥ አገር ናት
 ኳታር በእኔ እይታ  ትንሽ አገር ናት፡፡ ይህን ዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ ስትነሳ፣ ከውስጥም ከውጭም፤ ከቅርብም ከሩቅም ብዙ ፈተናዎችና ጫናዎች ገጥመዋታል፡፡ ያለ ስሟ ብዙ ስም ተሰጥቷታል፡፡ ኳታር ሁለተኛ አገሬ ናት፤ በጣም ነው የምወዳት፡፡ በሰብዓዊ  መብት ስትከሰስ፤ ለሰራተኞች ደሞዝ አትከፍልም ተብሎ ስትወገዝ ቆይታለች፡፡ እንደ እኔ ግን ኳታር ምርጥ አገር ናት ብዬ መመስከር እፈልጋለሁ፡፡ የአገሪቱ መንግስት የሚያወጣውን ህግና  ስርዓት አክብረህ ከኖርክ፣ ከአገሩ ዜጋ እኩል መብትህ ይጠበቃል።  ሆስፒታል ገብተህ ሙሉ ህክምና አግኝተህ (ኦፕራሲዮን ጭምር) ሁለት መቶና ሦስት መቶ ሪያል ብቻ ነው የምትከፍለው፡፡  ፍርድ ቤት ስትሄድ እኩል ነው ፍትህ  የምታገኘው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙዎቻችን ክርስትያኖች ነን፤ መቶ ፐርሰንት ሙስሊም በሆነ አገር ላይ ተከብረን ነው የምንኖረው። ሃይማኖትን ማራመድ ብቻ ሳይሆን መሬት ሰጥተው ቤተ ክርስቲያን (ካቴድራል) እንድንገነባ ፈቅደውልናል፡፡
የጽርሐ ማርያም ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ግንባታ በዶሃ  
 ኳታር ሙሉ ለሙሉ የእስልምና እምነት የምትከተል አገር ብትሆንም ካቴድራል እንድንገነባ መፈቀዱ ትልቅ የዲፕሎማሲ ውጤት ነው፡፡ ድሮ ወደዚህ አገር ስንመጣ ስማችንን  ቀይረን፣ ማህተባችንን በጥሰን ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ የትም ስንሄድ መስቀላችንን አድርገን ነው፡፡ በሃይማኖታችን ምንም የሚደርስብን ጫና የለም፡፡ መገፋት የለም፡፡ በጣም ሰው ያከብራሉ፡፡ ስለ ኳታር መጥፎ ነገር የሚያወራው በህግ አግባብ ሳይሄድ ቀርቶ ችግር ውስጥ የገባ ሰው ነው፡፡ ኳታር ምርጥ አገር፣ ኳታሮች ምርጥ ህዝቦች ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እየተከራየን ከግብጾች ጋር ነበር የምናካሂደው። ኋላ ላይ ግብፆችን እንዴት ቦታ አገኛችሁ ብለን ስንጠይቅ፤ ብዛታችን 500 እና ከዚያ በላይ ከሆነ፣ መሬት እንደሚሰጥ ነገሩን፡፡ ከ10 ዓመት በፊት ነው፡፡ በፅዋ ማህበር ጀምረን ስም ዝርዝርና ፊርማ አሰባስበን አዘጋጀን፡፡ ከዚያም አመለከትን፡፡ በወቅቱ ድጋፍ ያደረጉልን ግብፃዊ የሃይማኖት አባት፣ የነበረውን ትኩሳትና ችግር ከምንም ሳይቆጥሩ ተባብረውናል፤ አንድም ቀን ፊታቸውን አላዞሩብንም፡፡ በእሳቸው እገዛ የኳታር መንግሥትን ቦታ ጠየቅንና ቦታውም ተሰጠን፡፡ ቦታውን ካገኘን በኋላ ግን የግንባታ ፈቃድ ለማግኘት ሰባት አመት ነው የፈጀብን፡፡ የግንባታ ፈቃድ ለማግኘት ብዙ መከራ ገጥሞናል፡፡ ከመንግስት መሥርያ ቤት ወረቀት አልደረሰንም የሚል ነበር ምክንያቱ፡፡ ጥያቄያችንን ያቀረብነው በግብፅ በኩል ነበር፡፡ በኋላ ላይ ኤምባሲ ስላለን ጉዳዩን ለምን ወደዚያ ወስደን፣ ከአምባሳደሩ ድጋፍ አንጠይቅም ብለን ተነሳን፡፡ በወቅቱ አምባሳደር ወደነበሩት አምባሳደር ምስጋናው ሄደን አማከርናቸው። አምባሳደር ምስጋናው ቤተ ክርስቲያን እንድንገነባበት የተፈቀደውን ቦታ መጥቶ ጎበኘ፡፡ ጉዳዩን ወደ ኤምባሲ በመውሰዳችን ግብፃውያን ደስተኞች አልነበሩም፡፡ አምባሳደሩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለኳታር የውጭ ጉዳይ ደብዳቤ ፃፉ፡፡ ከዚያ ደብዳቤ በኋላ የግንባታውን ፈቃድ አገኘንና  ግንባታውም ተጀመረ፡፡ አሁን ግንባታው ከተጀመረ ከአንድ አመት በላይ ሆኖታል፡፡ 75 በመቶ ግንባታው የተከናወነ ሲሆን የጉልላት ስራውም ተጠናቅቆ ይገኛል፡፡
ሁሌ በአረብ አገር ስለምትገኝ ሴት ኢትዮጵያ ውስጥ የተዛባ አመለካከት አለ። የአረብ አገር ሴት ኃይማኖቷን የተወች፤ ስለ አገሯ ምንም የማይመለከታት፤ ዝም ብላ የምትኖር ተደርጎ ነው የሚታሰበው፡፡ እንደ አረብ አገር ኢትዮጵያዊት ሴት ግን ጀግና የለም። በሃይማኖቷ የማትደራደር፤ በአገራዊ ጉዳይ  ግንባር ቀደም ሆና የምትሰለፍ አረብ አገር ያለች ሴት ናት፡፡ ከእያንዳንዷ የቤት ሰራተኛ አንስቶ የቤተሰቦቻቸውን ጉሮሮ ዘግተው ከወር ደሞዛቸውና ከገቢያቸው  እያዋጡ  ነው ቤተክርስቲያኑ  የተገነባው፡፡  ቤተክርስቲያኑ እዚህ ደረጃ የደረሰው እያንዳንዳችን የወር ገቢያችንን አዋጥተን ነው፡፡ ቤተክርስቲያን  ተቋም ናት፡፡ እንደ ሃገርም ቅርስ ሆኖ ሊታይ ይገባል፡፡ ቤተክርስቲያን ሃኪም ቤት ናት። ተከፍተው ቢመጡ አልቅሰው እንባቸውን አፍስሰው ተፅናንተው የሚመለሱባት ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን መኖሩ ለእርስ በእርስ ግንኙነት  ይጠቅማል፤ አገርህን እንድታከብር፤ ብሄራዊ በዓሎቻችንን ሰብሰብ ብለን እንድናከብር ያስችለናል፡፡ ሊቃነ-ጳጳሳት ሲመጡ እናስተናግዳቸዋለን፡፡ በቤተክርስቲያኑ ግንባታ እጅግ የሚመሰገኑት ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ ይባላሉ፡፡ እኝህ የአገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ  ከእኛ ጋር ሲሚንቶ እያቦኩ፤ ድንጋይ እየተሸከሙ፣ ይሄ የልጆቼ ርስት ነው እያሉ አበርትተውናል፡፡  
የቤተክርስቲያኑ ግንባታ ከዓመት በፊት ሲጀመር ግንባታው በሦስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ ነበር፡፡ በመጀመርያው ምዕራፍ የቤተክርስቲያኑ የጉልላት ስራ ተጠናቅቋል። የቤተክርስቲያኑ ግንባታ በአጠቃላይ 15 ሚሊዮን የኳታር ሪያል ይፈጃል፡፡ በውስጡ በጣም ብዙ ክፍሎች አሉት፡፡ የህፃናት መማርያ፤ የአባቶች ማረፊያ፤ መሰብሰቢያ አዳራሽ ሁሉ ያለው ነው፡፡ እስካሁን ወደ 4.5 ሚሊዮን  ሪያል ወጭ ሆኖበታል፡፡ አሁን የቀረውን ለማስቀጠል ወደ 10 ሚሊዮን  ሪያል ያስፈልገናል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ገቢ ለማድረግ ደግሞ በኢትዮጵያ በአዋሽ ባንክ፤ በንግድ ባንክ፤ በአቢሲኒያ፤ በኦሮሚያ ባንክ አካውንቶችን በመክፈት፤ በአሜሪካ በዜል አካውንት እና በጎ ፈንድሚ የገቢ ማሰባሰቢያዎች ጀምረናል፡፡ በተባበሩት አረብ ኢምሬት የሚገኙ ቤተክርስቲያኖችን ኮሚቴ በማቋቋም  እዚያ ያሉ ምዕመናን የሚረዱበትን መንገድ አዘጋጅተናል፡፡ በተለያየ ጊዜ በቲክቶክ ብዙ ተከታዮች ካላቸው ሰዎች ጋር በመተባበር ድጋፍ እንጠይቃለን፡፡ ከመላው ዓለም  እጃቸውን እየዘረጉልን ነው፡፡
በኢትዮጵያ በከፈትነው አካውንት ሰዎች የራሳቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው ያሉት። ምናልባት አሜሪካን አገር ወይም አውሮፓ ውስጥ ቤተክርስቲያን  ማነፅ ወይም መግዛት አይገርም ይሆናል፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ መቶ በመቶ ሙስሊም በሆነበት አገር ላይ ሙሉ ፈቃድ ሰጥተውን ይህን ቤተክርስቲያን እንድንገነባ ሲፈቅዱልን በጣም ትልቅ እድልና ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ ለሁሉም ኩራት ነው። የኢትዮጵያ ርስት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ለባለማህተቦች ልዩ ስሜት የሚፈጥር ነው፡፡ ይህን ጋዜጣ  የሚያነቡ የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ በእግዚአብሄር ስም እጠይቃለሁ፡፡ ገቢ ለማሰባሰብ  ህንፃ አሰሪ ኮሚቴው እንቅልፍ የለውም፡፡ ሰባካ  ጉባኤው፤ የባህል ኮሚቴው፤ ሰንበት ትምህርት ቤቱ፤ ልማት ክፍሉ በየራሱ መንገድ እየለፋ እየጣረ ነው፡፡ በኳታርና በሌሎች የዓለም ክፍሎች በርካታ ተከታይ ያላቸው ቲክቶከሮች በዚህ ጉዳይ ላይ እየተሳተፉ በመሆኑ በእጅጉ እናመሰግናለን፡፡
በዶሐ ይህ ቤተክርስቲያን እንዲታነፅ ለፈቀዱት ለኳታሩ ንጉስ ሼክ ተሚም፣ ለአባታቸው ለሼክ አህመድ፣ ለሼክ ሃሙዛ በጣም ከፍተኛ አክብሮትና ፍቅር እንዳለኝ መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ ከፍተኛ ምስጋናዬን ለማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ስለ ሁሉም ነገር ክብሩን ሁሉ እግዚአብሄር ይውሰድ፡፡ ይሄ ሁሉ የእሱ ፈቃድ፤ የሱ ቸርነትና የሱ መልካምነት ስለሆነ ነው፡፡ አገራችንን ሰላም ያድርግልን። ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፡፡ የተጀመረውን ሰላም እግዚአብሄር ያጽናልን። ዞሮ መግቢያችን አገር ነውና፤ አገራችንን እግዚአብሄር ሰላም ያድርግልን፡፡

Read 955 times