Saturday, 14 January 2023 11:16

“ካፒታል” የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን እያከበረ ነው

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  - ሚዲያው ራሱን ከዘመኑ ጋር ማራመድ አለበት
                       - በሚዲያው ማርኬት ምርጥ ልጆች ነው ያሉን

         በኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ታሪክ ከአስር ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ የህትመት ውጤቶች ማግኘት እጅጉን ብርቅ ነው። በ1990ዎቹ በመቶዎቸ ይቆጠሩ የነበሩት የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች እየተመናመኑ ዛሬ ላይ በአጠቃላይ ያሉት የህትመት ውጤቶች አስር  አይዘሉም፡፡
በህትመት ላይ ያሉትም ቢሆኑ ከፍተኛ የህልውና አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በእጅጉ የናረው የህትመት ዋጋ ከእነ አካቴው ከገበያ እንዳያወጣቸው ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለቤቶች ክፉኛ ይሰጋሉ፡፡ መንግስት ጣልቃ ገብቶ የግል ፕሬሱን እንዲታደግ የሚጠይቁም ብዙዎች ናቸው፡፡
በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድና የህልውና ስጋት ውስጥ የሚገኘው ካፒታል፤ ለሩብ ክፍለ ዘመን በጥንካሬ ተጉዞ ለ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓሉ ደርሷል። በቢዝነስና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገው ጋዜጣው፤  ሰሞኑን  ክብረ በዓሉን ማክበር ጀምሯል። ለ25 ዓመታት አንዴም ሳይቋረጥ በየሳምንቱ እሁድ እየታተመ ለአንባቢያን የሚደርሰው “ካፒታል”፤ የስኬት ምስጢሩ ምን ይሆን?
ምን ዓይነት ተግዳሮቶችን አሳልፎ ለዛሬው ክብረ በዓሉ ደረሰ? ወደፊትስ ምን አቅዷል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛዋ ናፍቆት ዮሴፍ የካፒታል ጋዜጣ መሥራችና ማኔጂንግ ኤዲተር ከሆኑት  ትዕግስት ይልማ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-

          እንኳን ለ25ኛ ዓመት ክብረ በዓላችሁ አደረሳችሁ። 1ሺህ 255 እትሞችን ለአንባቢ ማድረስ ቀላል አይደለም…
እውነት ነው፤ እናመሰግናለን፤ እንኳን አብሮ አደረሰን። እኛ እንደ ጋዜጣ እንግዲህ 25 ዓመታትን ስንዘልቅ ለህዝብ መረጃ ከማድረስና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እውቀት ከማስጨበጥ በተጨማሪ ማህበራዊ ሃላፊነታችንን ለመወጣትም በጤና፣ በትምህርትና በአካባቢ ጉዳዮች ዙሪያ ሥራዎችን ስንሰራም ቆይተናል። ከዚህ ቀደም ጋዜጣችን የተመሰረተበትን በዓል ስናከብር ለህብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ አገልግሎቶችን ሰጥተን ማለፍ ስለምንፈልግ ነው ዓመቱን ሙሉ የምናከብረው።
ለምሳሌ በችግኝ ተከላ፣ በአካባቢ ጥበቃ ላይ እንሳተፋለን፤ በጤናው ደግሞ በክትባት ዙሪያ ህዝቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ስንቀሰቅስ ስናነቃ ነበር። በኤች አይቪ የተያዙ ህጻናት ያሉበት ድረስ ሄደን አብረናቸው እንውላን፣ የተለያዩ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርገን ደስ ብሏቸው እንዲውሉ እናደርጋለን። በዚህ መልኩ መረጃ ከመስጠት በተጨማሪ በርካታ ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ እንቅስቃሴዎችን ስናደርግ ቆይተናል። አሁን በጥንካሬ 25ኛ ዓመታችን ላይ ደርሰን ይኸው ክብረ በዓላችንን እያከበርን ነው።
የዘንድሮውን የ25 ዓመት ኢዮቤልዩ በዓል በምን መርሃ ግብሮች ለማክበር ነው ያቀዳችሁት?
እንግዲህ አከባበሩን የጀመርነው ባለፈው ማክሰኞ አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ በተዘጋጀ ትልቅ የፓናል ውይይት ነበር። በዚህ የፓናል ውይይት ላይ በህትመት ሚዲያውም ሆነ በአጠቃላይ በሜይንስትሪም ሚዲያው ከፍተኛ እውቀት ያላቸው ሰዎችን ነው የጋበዝነው። እነዚህ እውቅ ባለሙያዎች እንግዲህ ሶሻል ሚዲያው በህትመት ሚዲያው ላይ ያሳረፈውን ጥላ እንደ ተግዳሮት ቢያነሱም፣ ማህበራዊ ሚዲያ ለመረጃ በስፋትና በፍጥነት መዳረስ ያለውን በጎ ሚናም አንስተው ግንዛቤ ሰጥተዋል። ከህግ ማዕቀፍ አኳያ ሜይኒስትሪም በህግ የሚታወቅ፣ አድራሻ ያለው፣ በአካል የሚጠየቅ ተቋም ሆኖ ሳለ በሶሻል ሚዲያው በኩል የሚሰራጩት መረጃዎች ችግር ቢፈጥሩ በአድራሻቸው ሄዶ ለመያዝም ሆነ ለመጠየቅ አስቸጋሪ እንደሚሆንም በብዙ መልኩ ተነስቷል። ይሄ የ25ኛ ዓመት ክብረ በዓላችን እስከ ዓመቱ መጨረሻም ድረስ የምናከብረው፡፡ መጨረሻ ላይ አንባቢዎቻችንን ማስታወቂያ የሚያወጡ ደንበኞቻችንንና ሌሎች አጋሮችን የምናመሰግንበት የመዝጊያ ፕሮግራም ይኖረናል፡፡
በእርግጥም የዲጅታል ሚዲያው መስፋፋት ለህትመት ሚዲያው ከፍተኛ የሕልውና አደጋ ጋርጧል። እርስዎ እንደ አንድ የሚዲያ መሪ የፕሬሱ በተለይ የግል የወደፊት ዕጣ ፈንታ  ምን የሚሆን ይመስለዎታል?
የህትመት ሚዲያው ላይ አንድ መስማማት ያለብን ጉዳይ ምን መሰለሽ? እራሱን እየቀየረ ዓለም ወደሚጓዝበት መንገድ መግባት አለበት። ራሱን ወደ ዲጅታል እየቀየረና እየዘመነ መሄድ አለበት። ይህ ማለት ህትመቱ ሙሉ በሙሉ ይቅር ማለት አይደለም። አሁን ላይ በሌላውም ዓለም የህትመቱ እየቀነሰ የዲጂታል ሚዲያው እየጨመረና ተደራሽነቱም እየሰፋ ነው። ስለዚህ የህትመት ሚዲያው እንዳለ ሆኖ ዲጂታሉ ተደራሽነቱን ማሳደግ አለበት። በፓናል ውይይቱም ላይ በደንብ እንደተብራራው፤ በአሁኑ ወቅት ዲጂታል ሚዲያው የገቢ ምንጭም ነው። ስለዚህ ህትመት ሚዲያው በተለያየ መልኩ የገቢ ምንጭ እየሆነና አንባቢ ወደሚፈልገው አቅጣጫ እየተቀየረ መምጣት አለበት።
በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ቶሎ ቶሎ መረጃ እንዲደርሰው ነው የሚፈልገው እንጂ ገና ሳምንት ጠብቆ ጋዜጣ ገዝቶ የማንበብ ፍላጎቱ እየቀነሰ መጥቷል። መረጃ በየሰዓቱ እንዲደርሰው ወደመፈለግ እያመዘነ ነው ያለው። በሌላ በኩል፤ ለረጅም ዓመታት ከእኛ ጋር የዘለቁ አንባብያን አሉ። ትልቅ ካፒታል ነው ያለን። ትልቅ እምነት ነው ያዳበርነው። ይህንን ካፒታል ላለማጣትና አንባቢያን ከእኛው ጋር እንዲዘልቁ፣ እኛ ከዘመኑ ጋር ልንራመድላቸው ይገባል። ፓናል ውይይቱም ላይ ይሄ ጉዳይ በስፋት ተነስቶ ነበር። እኛም እንደ ካፒታል ጋዜጣ ወደዚሁ መሄድ አለብን ብለን ነው የምናስበው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የኮቪድ 19 ወረርሽኝና የሰሜኑ የሀገራችን ጦርነት። የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማዳከሙ ይታወቃል። እኒህ ተግዳሮቶች በቢዝነሳችሁ ላይ ያሳደረው ጫና እንዴት ይገለጻል?
ጫናው በጣም ከባድ ነበር።  ኮቪድ 19 ሀገራችን ላይ ሲከሰት ከጤና ባለሙያዎችና ጤና ላይ ከሚሰሩ የህብረተሰቡ ክፍሎች ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ተጠቂው ጋዜጠኛው ነበር። ምክንያቱም ጋዜጠኛው ነው ስለ በሽታው ምንነት፣ ስለሚወሰዱ ጥንቃቄዎችና ስለ አጠቃላይ ሁኔታው ፊት ለፊት ተጋፍጦ ለማህበረሰቡ መረጃ የሚያቀብለው። ስለዚህ ጋዜጠኛው በወቅቱ በጣም ተጎድቶ ነበር። ጋዜጦችን ማለትም ተቋማትን በተመለከተ ደግሞ የወረርሽኙ ባህሪ ንክኪን፣ ግንኙነትን የሚገድብ በመሆኑ ማንም ሰው ጋዜጣን መንካትና ከሌላው ተቀብሎ ማንበብ ስለማይፈልግ፣ ከሌላው ሚዲያ በበለጠ የህትመት ሚዲያው ላይ ጫና አሳድሮ ነበረ። በአጠቃላይ ጊዜው ከባድ ነበር።
ያን ጊዜ ካፒታል ምንድነው ያደረግነው… እንግሊዝኛ ጋዜጣ እንደ መሆናችንና ብዙ አለም አቀፍ ሁነቶችን እንደ መዳሰሳችን በቅድሚያ ይህ ጉዳይ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ፣ የውጪ ሃገራት እንዴት እየያዙት እንደሆነ ማጤን ጀመርን። በተለይ አውሮፓ ላይ ከኮቪድ በኋላ ምን ሲከሰት እንደነበረ በደንብ ነው የተከታተልነው። ከዚያ ወዲያውኑ ራሳችንን አዘጋጀን።
በምን መልኩ ነው ራሳችሁን ያአዘጋጃችሁት?
አንደኛ በየቤታችን ሆነን  ከያለንበት ልንሰራ የምንችልበትን መንገድ ተመካከርንና ማን ምን ማድረግ አለበት የሚለውን ጉዳይ ማፑን ሰርተን ሥራ ላይ አዋልነው። ሁለተኛ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማለትም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክም) ሆነ የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር አልነበረም። እነዚህን ቁሳቁሶች የምናገኝበትንና የእኛ የሥራ ባልደረቦች አካላዊ ጥንቃቄ  የሚያደርጉበትን መንገድ አመቻቸን። ከዚያ ቀጠልንና ጋዜጣውን በየሳምንቱ ለአንባቢዎቻችን ለማድረስ ከባድ እንደሚሆን ስለተረዳን፣ ወዲያው በኢሜይል በፒዲኤፍ ፎርማት ለአንባቢዎቻችን ማድረስን አስተዋወቅን። “ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ካፒታል ጋዜጣን በዚህ ፎርማት በኢ-ሜይላችሁ ታገኛላችሁ” እያልን ገለጽን። ለአንባቢዎች ብቻ ሳይሆን ማስታወቂያ ለሚያወጡ ሁሉ ነገርን። ዓመታዊው ማስታወቂያዎች ካልሆኑ ሌሎች ማስታወቂያዎች ለምሳሌ የስራ ማስታወቂያና መሰሎች ይቆማሉ ማለት ነው። እነሱ ቢቆሙም ለሌሎቹ ግን ጋዜጣው ሳይቋረጥ ለሁሉም አንባቢ በኢሜይል እንዲደርስ አደረግን። ሌላው ትልቁ ጉዳይ ምንድን ነበር… በወቅቱ በሚዲያዎችም ሆነ በመንግስት ትኩረት ተደርጎ የሚሰራበት በሽታው እንዳይስፋፋ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ የሚያደርግበት መንገድ ላይ ነበር። ከተያዙ የሆስፒታል አልጋዎች እንዳይጨናነቁ ምን መደረግ አለበት የሚለው ነበር ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራበት። እኛ አንድ ተለየ ጉዳይ አየን። ይህም ኮቪድ የሚያስከትለው የስነ-ልቦና ጫናና  ተያያዥ ጉዳዩ ትኩረት አልተሰጠውም ነበር። ስለዚህ ምን አደረግን? በዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ የተፈጠረው ኔትወርክ ሰፊ ነውና ኢትዮጵያዊት ዶክተር አነጋገርን። በዓለም ዙሪያ በዚህ ደረጃ ስልጠና መስጠት ከሚችሉ ሁለት አፍሪካዊያን አንዷ ኢትዮጵያዊት ናት፤ ዶ/ር የኔ አሰግድ ትባላለች። እሷን አገኘን። ከዚያ ለካፒታል የስራ ባልደረቦች ስልጠና እንድትሰጥልን አነጋገርናት። እሷ በዚያ ወቅት ለተመድ መስሪያ ቤቶች ዓለም አቀፍ ስልጠና ትሰጥ ነበር።  በሽታው ከየት ተነስቶ ወዴት ይሄዳል? ሌሎች ሀገራት ምን እያደረጉ ነው? እኛስ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን በቅጡ እንድንረዳ ስልጠናውን ሰጠችን። ያን ስልጠና ከወሰድን በኋላ በቢሯችን ላይ ትልቅ ለውጥ አየን። ባልደረቦቻችን መረጋጋት አመጡ። ስልጠናው አዕምሯችን ላይ ያመጣውን እረፍት ስንረዳ፣ ይህን ስልጠና ለምን ለአንባቢዎቻችንስ አናካፍላቸውም ወደሚል ሀሳብ ከፍ አደረግነው። ምክንያቱም ብዙ አንባቢዎች አሉ፤ በየቤታቸው በጭንቀትና በድብርት የሚያሳልፉ። አውሮፓ ደግሞ ይሄ ነገር ደርሶባቸው መፍትሄ አግኝተው፣ ከበሽታው ጋር የሚኖሩበትን ዘዴ ፈጥረው ነበርና፣ እኛስ ስልጠናውን ስንወስድ የተሰማን መረጋጋት ልክ ነው ወይ ብለን  ስልጠና አዘጋጀንና በጋዜጣችንም በኦንላይንም አስተዋወቅነው። ለ3 ጊዜ እንዲሆን አድርገን ነው ያዘጋጀነው። በመጀመሪያው ሳምንት ዶክተር የኔ፣ ውጪ ሆና በኦንላይን ነው፤ እኛም ከዚህ አንባቢዎቻችን በኦንላይን ነበር ሊንክ እንዲያደርጉ ያደረግነው፤ እጅግ በጣም ጥሩ ስልጠና ተካሄደ። ብዙ አንባቢዎቻችን ከዚህም ከኢትዮጵያ ውጪም ተሳተፉ፤ በጣም ተደሰቱ። ጥሩ ቁምነገር አግኝተንበታል ብለው አመሰገኑን። በቀጣዩ ላይ እዚህ ኢንተርኔት ችግር ስለነበር የኢትዮጵያ አንባቢያንን መድረስ ባንችልም፣ የውጪዎቹ ግን በጥሩ ሁኔታ ስልጠናውን ወሰዱ። ይህ ትልቅ ጉዳይ ነበር።
ይሄም ራሱ ማህበራዊ ሃላፊነትን  መወጣት ነው አይደለም?
ትክክል ነው። እኛ ምን እንላለን… ዜናና መረጃ ዕለት ተዕለት ከማቅረብም ባሻገር የምንሰጣቸው የህዝብ አገልግሎቶች ናቸው ትኩረቶቻችን በሚዲያ ላይ ስንኖር ዋና አላማችን ዜና መጻፍ ብቻ አይደለም። የእውነት ህብረተሰቡን ማገልገል ነው። እርግጥ ነው ዜና መጻፍና ህብረተሰቡ ኑሮውን ወደተሻለ አቅጣጫ የሚመራበትን መረጃ መስጠትም አገልግሎት ነው። ነገር ግን እንደዚህ አይነት አገልግሎቶችም እንሰጣለን። ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ በአካል እየተገኘን በትምህርት፣ በጤና እና በአካባቢ ጥበቃ ላይ እንሳተፋለን፤ እናገለግላለን። ስለዚህ ኮቪድ ሲመጣ ብዙ ጫና አሳድሯል። ነገር ግን እጅ ላለመስጠትና ከወቅቱ ጋር ተጣጥመን ችግሩን ለመሻገር ከላይ የገለጽኩልሽን ተግባራት አከናውነን አልፈናል።
የግል ፕሬሱን ለመታደግ ከመንግስት ምን ይጠበቃል? ከራሱ ከግል ፕሬሱስ?
አሁን ላይ ሀገራችን ከፍተኛ ለውጦችን እያካሄደች ነው። በኢኮኖሚውና በፖለቲካው ዙሪያ ብዙ ለውጦችን እያካሄደች ነው። እነዚህን ለውጦች ያለ ሚዲያ ማስቀጠል ከባድ ነው። ሚዲያው እነዚህን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን በመደገፍ በኩል ካለው ሚና አንጻር፣ በመንግስት በኩል የሚዲያውን ሚና ተገንዝቦ መደገፍ አለበት። ምክንያቱም ሜይንስትሪም ሚዲያው ነው መሟላት ያለበትን የሙያ ብቃት አክብሮ፣ ፈቃድ ይዞና መሰረታዊ መስፈርቶችን አሟልቶ ተጠያቂነትንም ወስዶ የሚሰራው።
ስለዚህ መንግስት ይህንን ሚዲያ መደገፍ አለበት። የትኩረት ማነስ በመንግስት በኩል ያለ ይመስለኛል። ትኩረት ተሰጥቶትና ተደግፎ ቢቀጥል የሚዲያው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም።
በራሳችን በኩል ስላለውና መደረግ ስላለበት ጉዳይ በፓናል ውይይቱም ላይ ተነስቶ ጥሩ ሃሳብ ቀርቦበታል። ሚዲያ ቤጊዜው በርካታ ተግዳሮቶች ይገጥሙታል። ለምሳሌ መጀመሪያ ላይ ሬዲዮ ሲመጣ ጋዜጣ በቃ አለቀለት ተብሎ ነበር። ከዚያ ቴሌቪዥንንም ሲመጣ እንደዚሁ ተብሎ ነበር። ተግዳሮቶች አሉ። ስለዚህ ጋዜጣው ራሱን ከሁኔታዎች ጋር እያጣጣመ እያሻሻለ ነው የቀጠለው። አሁንም አለም ወደ ዲጂታል ሚዲያ እየሄደ ነው። በዓለም ላይ መረጃ ብቻ ሳይሆን ስራ ኦን ላይን እየሆነ ነውኮ! ሰርቪስ አውትሶርሲንግ እኮ ተጀምሯል። ለምሳሌ ለህክምና ፈረንሳይ አገር ቢደወል ስልኩን የሚያነሳው ህንድ አገር ያለ ኤጀንት ሊሆን ይችላል። አሁን አሰራሩ ሁሉ እየተቀየረ ስለሆነ ሚዲያውም ራሱን ከዘመኑ ጋር በሚያምድበት መስመር ላይ መቆም አለበት። ከግሉ ፕሬስ የሚጠበቀው ይሄ ነው ብዬ አምናለሁ።
ካፒታል በህዝብ ውስጥ የቆየበት እድሜ የአንድ ትውልድ እድሜ ነው። ይህንን ትልቅ ሚዲያ መምራት ቀላል አይደለም፤ ብቃት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። በዚህ አድናቆት ይገባዎታል። በዚሁ የአመራር ብቃትም ከፈረንሳይ መንግስትና ከሌሎችም የተቀበሏቸው ሽልማቶች መኖራቸውን አውቃለሁ። በነዚህ ሽልማቶች ዙሪያ ትንሽ ያጫውቱኝ?
ስለ አድናቆቱ በጣም አመሰግናለሁ። እንደ አመራር ጋዜጣን መምራት ከባድ ነው። በአጠቃላይ ገበያው ቀላል ገበያ አይደለም። በየጊዜው የተለያዩ አዳዲስ አምዶችን መክፈት ግድ ይለን ነበር፣ ቅድም እንዳልኩሽ የተለያዩ ሰርቪሶችን መስጠት ነበረብን፣ ለምሳሌ የኮቪዱ እንዳደረግነው በቀጥታ በመሄድና በመሳተፍ ብዙ ስንሰራ ነበር። ለአንባቢዎቻን ዜናውን ሰርተን እናቀርብላቸዋለን። እንደገና ደግሞ “ኑና ዜናው ላይ ያለውን እውነት ኑሩት” እንላቸዋለን። ይህ ብዙ ድካምና ስራን ጠይቃል። ግን አንባቢዎቻችን ደስ ብሏቸው ከእኛ ጋር እንዲዘልቁና ሁልጊዜም እሁድን እንዲናፍቁ ያደርጋቸዋል። ምን ለማለት ነው… የተለያዩ የአመራር ጥበቦችን ተጠቅመን ነው እዚህ የደረስነው።
ነገር ግን ጥሩ የስራ ቡድን ከሌለ  አመራሩ ብቻ የትም አያደርሰውም። በእውነቱ እኛም በሚዲያው ማርኬት ላይ ምርጥ ምርጥ ልጆች ነው ያለን። ካፒታል ውስጥ  ለምሳሌ ዋና አዘጋጁ አቶ ግሩም አባተ፣ ምክትል ዋና አዘጋጁ አቶ ሙሉቀን ወንድወሰን፣ ፎቶግራፈራችን አንተነህ አክሊሉ፣ ዲዛይነራችን እነብርሃ ዳንኤል… በጣም ጎበዝ ጎበዝ ልጆች ናቸው ያሉን። አጠቃላይ ቲሙ ጥሩ መንፈስ ያለው ቲም ነው። በዚህ አጋጣሚ ይህን ቲም ማመስገን እፈልጋለሁ። ጋዜጣው እዚህ መድረሱ የነሱም ውጤት ነው። በተለያየ ጊዜ ካፒታል ውስጥ የነበሩና በተለያየ ምክንያት ከካፒታል የለቀቁትም ጥሩ ጥሩ ነገር ጥለውልን ነው የሄዱትና መመስገን ይገባቸዋል። ይሄ በስልጠና ሲደገፍ ደግሞ የበለጠ ያማረ ውጤት ያመጣል። በየጊዜው ራሳችንን በስልጠና እንደግፋለን። ይሄ ይሄ ሁሉ ነው ለዚህ ያደረሰንና ለመወደድ ያበቃን።
ሽልማትን በተመለከተ የፈረንሳይ መንግስት ሁለት ጊዜ ሽልማት ሰጥቶኛል። የመጀመሪያው እ.ኤ.አ በ2008 የተቀበልኩት “ኦርደር ናሽናል ሜሪት” የተሰኘ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም የተቀበልኩት “ሌዥዋም ዶነር” የተሰኘ ትልቅ ሽልማት ነው። ሽልማቱ የተሰጠኝ በሀገሬ የምሰራው ስራ ለህብረተሰቡ ያለው ፋይዳና አስተዋጽኦ ተገምግሞ ነው።  ሽልማቶቹ በዓለም ዙሪያ ያሉ ፕሮፌሽናሎች በሚሰሩት ስራ ሀገራቸውንና ወገናቸውን በማገልገል ያበረከቱት አስተዋጽኦ ታይቶ የሚሰጡ ናቸው። ሌላው ሽልማት በ2020 ከሮተሪ ኢንተርናሽናል የተበረከተልኝ ሲሆን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ባበረከትኩት አስተዋጽኦ ያገኘሁት ነው። ይህ ሽልማት ከዓለም ዙሪያ 6 ሰዎች ተመርጠው የተተሸለሙት ነው። እኔ አንዷ ተሸላሚ ነበርኩ።
 በመጨረሻ ወደፊት ምን አቅዳችኋል?
እቅዳችን እንደ ካፒታል ራሳችንን አዘምነን የዲጂታል ተደራሽነታችንን ከፍ ማድረግ ነው። ካፒታልን ሙሉ በሙሉ ከህትመት መዝጋት ሳይሆን ከህትመቱ እየቀነሱ ወደ ዲጂታሉ እያደሉ ማጠናከር ነው ዓላማችን። የዲጂታል ተደራሽነታችን ህትመቱን የሚደግፍበት ዘዴ መፍጠር ነው እቅዳችን። ዲጂታል ተደራሽነታችን ገቢ እያመነጨ መስራት መቀጠል አለብን የሚል እምነት ነው ያለን። የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በየጊዜው እየተፈጠሩ ስላሉ ራሳችንን በዚያ መስመር አስገብተን መቀጠሉ አስፈላጊ ነው። በአሁኑ ወቅት በሁሉም ፕላትፎርም ላይ ማለትም ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ኢንስታግራም፣ ዌብሳይት ትዊተር ላይ እንገኛለን። እሱን ግን አስፍተንና አጠናክረን፤ አንባቢዎቻችን ምንድን ነው የሚፈልጉት የሚለውን አጢነን በዚያው ልክ ነው ለመቀጠል ያቀድነው።
ለ50ኛ ዓመታችሁ እንዲያደርሳችሁ እንመኛለን…
 በእጅጉ አመሰግናለሁ።


Read 1178 times