Saturday, 14 January 2023 11:30

አሞሮቹ

Written by  ትዕግስት ታፈረ ሞላ
Rate this item
(8 votes)

  ማታ ማታ ስለሚያፍነኝ የቤቱን ማሞቂያ አጠፋዋለሁ።  ጀርመን  ፍራንክፈርት አካባቢ በሚገኝ ሩሰልሳይም በሚባል ትንሽ ከተማ መኖር ከጀመርኩ ሰባት ዓመታት ቢያልፉም፣ ብርድ በመጣ ቁጥር አዲስ ነኝ፡፡ ማታ በአግባቡ ባልጋረድኩት የመኝታ ቤቴ መስኮት ወደ ውጭ እያየሁ ከሰውነቴ ተለይቶ የበደነ እግሬን ማሻሸቱን ተያይዤዋለሁ::  
የማትሞቅ የፍሪጅ መብራት የመሰለች ፀሐይ በስሱ ወጥታለች፡፡ በጠዋቱ በብርዱ ምክንያት የወየቡ የዛፎቹ ቅጠል ላይ አርፋ ቀኑ ቢጫ ሆኖ ጀምሯል፡፡ ጨለማው ወቅት ሊጀምር ዛሬ ዋዜማው ላይ ነን። ከባዱ የአውሮፓ ክረምት ከመግባቱ በፊት ንፋሱ ያይላል፡፡ በቅዝቃዜ የወየቡ ቅጠሎች ይረግፋሉ፡፡ መሬቱ ወርቅማ ምንጣፍ የተነጠፈበት ይመስላል፡፡ ይኼ ለዓይን ውብ ነው፡፡ እያባባ የሚያምር ነገር!
ክረምቱ ሊገባ ሲል በፀደይ ወቅት ከየቦታው ወደዚህ ሀገር የሚመጡ ነጫጭ አሞራዎች ብርዱንና መጭውን የበረዶ ዘመን መቋቋም እንደማይችሉ ስለሚያውቁት በሰልፍ እጅብ ብለው ወደ ደቡብ አቅጣጫ ይተማሉ፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ሆኖ ይህን የተፈጥሮ ዑደት መመልከት ልብ ያሸብራል። ምናልባት ይኼ ስሜት የእኔ ብቻ ይሆን? ወቅት ሲለዋወጥ ቶሎ አለምድም፡፡ ዓይኖቼን አፍጥጬ ሰማይ ምድሩን እያየሁ እባባለሁ፡፡
የቤቴ ደወል ሰበሰበኝ፡፡ በማፍጠጥ የዛሉ ዓይኖቼን አርገብግቤ አነቃቃኋቸው፡፡ “በጠዋት ከቤቴ በር የቆመው ማነው?”
እንደገና ደወሉ ጮኸ፡፡ ተነስቼ ወደ በሩ አመራሁ። በሩን ስከፍት ለሶስተኛ ጊዜ ደወሉን ለመጫን የተዘረጋው የቢያዝን እጅ አስግጎ ነበር። ገርሞኝ በዝምታ አየሁት፡፡
እጁን በፍጥነት ሰብስቦ፤ “በጣም ይቅርታ በጣም…” ተንተባተበ፡፡ ቤት ውስጥ ተኝቶ ያደረ አይመስልም፡፡ ዓይኖቹ ደፍርሰዋል፡፡ እጆቹ የሚንቀጠቀጡ መሰለኝ፡፡
“ግባ ወደ ቤት ብርድ ነው፡፡” ደረቴን ከቅዝቃዜው ለመሰወር በእጆቼ ሸፍኜ  ከበሩ ላይ ገለል አልኩለት።   
“ምንም አልተኛሁም፡፡ እንዴት የአንዳቸው ስልክ አይሰራም? ሥራ ከመሄድሽ በፊት እንድትደውይልኝ ላስቸግርሽ ነው” በሩን እየዘጋ ከላይ ከላይ ያወራል፡፡
“የሀገራችን ኔትወርክ ገጠር ላይ ያስቸግር የለም፤ እንዲሁ ነው እንቅልፍ ያጣኸው” ብዬ ነገሩን ቀለል ላደርግለት ፈለግሁ፡፡
“አይ አይመስለኝም፡፡ ሰውነቴ የሚነግረኝ ነገር አለ፡፡ ለምን እንደሆን አላውቅም መረበሼን ማቆም አልቻልኩም፡፡ ሀገራችን አሁን እንደ ድሮው መሰለሽ፤ ጥጋበኛው በዝቷል፡፡ ዜና አትሰሚም የወለጋ መሬት ቀን በቀን ደም አምጡ እያለች ነው፡፡” ከበሩ ሳይርቅ ባለ ወንበር ላይ ከነጭንቀቱ ቁጭ አለ፡፡
ወደ መኝታ ቤቴ ተመልሼ ስልኬን እያመጣሁ፤ ‹በየቀኑ እንደምንሰማው የእሱ ቤተሰቦችም በጥጋበኞች ታርደው ይሆን?› ብዬ አሰብኩና ሆዴ ተላወሰ፡፡
ስልኬን ሰጥቼው ሶፋ ላይ ያገኘሁትን ጋቢ ደርቤ ቁጭ አልኩ፡፡ ከኪሱ አነስተኛ ማስታወሻ አውጥቶ እያነበበ፣ አቤት ባይ እስኪያገኝ ይደውላል፡፡
ጀርመን ከገባ ሁለት ሳምንት አልፎታል፡፡ በሰሃራ በረሃ የተጎሳቆለ ሰውነቱ ገና አላገገመም። ከእኔ ቤት በላይ የተደረበ የስደተኞች መኖሪያ ኮንቴነር ላይ እንዲኖር ካመጡት አራት ቀን ይሆነዋል፡፡ በዚህ በዚህ አውሮፓውያንን አለማመስገን እንዴት ይቻላል? እንደ እኔ አይነት የሰው ቋንቋ የማይሰርፀው፣ ተምሮ የተሻለ ሥራ መያዝ ያልቻለን ሰው እንኳን መጠለያ ሰጥተው ቀለብ እየሰፈሩ ያኖራሉ፡፡ ይቺን መጠለያ ላለማጣት በድብቅ የምሰራው አድካሚ የቤት ውስጥ ሥራም ቤተሰቦቼን በብዙ መንገድ እያገዘልኝ ነው፡፡
“ቀለም ቀለም ቀለም…” ይልና ቢያዝን ትንሽ ቆይቶ “የቀለምም አይሰራም፡፡” ይላል፡፡
“ግርማ ግርማ ግርማ…” እያለ ቁጥሮቹን ከማስታወሻው ወደ ስልኬ ይገለብጣል፡፡ ይደውልና በተስፋ ይቁነጠነጣል፡፡
ትንሽ ጠብቆ፤ “የግርማም አይሰራም” ይላል።
“እትዬ ብርቄ እትዬ ብርቄ…” ዓይኖቹ ከማስታወሻው ወደ ስልኬ ይሯሯጣሉ፡፡ እጆቹ ለመጻፍ ይፈጥናሉ፡፡ የስልኩን ድምፅ ከፍታ ላይ ማድረጉን ረስቶ ጆሮው ላይ ይለጥፈዋል፡፡
“Der Teilnehmer ist im Moment nicht erreichbar,versuchen siees spatter noch einmal” ትላለች ስልኳ በጀርመንኛ፡፡ (ለማግኘት የሞከሩት ሰው አሁን አልተገኙም በኋላ ይሞክሩ፤ ማለቷ ነው፡፡)
“በቃ እህቴ አሁንም አልሆነም፡፡ ከሥራ ስትመለሽ ማታ ደግሞ ልሞክር፤ የራሴን ስልክ እስክይዝ መቼም ላስቸግርሽ ነው፡፡” አለኝ፡፡
“ዛሬ እረፍት ነኝ አያሳስብህ፡፡ እየቆየህ መሞከር ትችላለህ፡፡ ይልቅ ቆይ ቡና ላፍላና ቁርስ ልጋብዝህ” ጋቢውን ከላዬ ላይ ገፍፌ ተነሳሁ፡፡ አዲስ ሰው ሲመጣ ስለ ሀገር ቤት ሲያወራኝ ደስ ስለሚለኝ በቶሎ እንዲሄድ አልፈለኩም። ለነገሩ የሚያዋራስ የት ተጘኝቶ።
“እሰይ እረፍት ነሽ” አለና ወደ ማስታወሻ ደብተሩ ተመለሰ፡፡ “ከድር ከድር ከድር….” የከድር ቁጥር እየተፈለገ ነው፡፡
ትንሽ ድርቆሽ እንጀራ አለችኝ፤ ለእኔና ለቢያዝን ለአንድ ጊዜ ትሆናለች፡፡ ሽንኩርት እየላጥኩ፤ “የከድርም ስልክ አይሰራም” ሲል ሰማሁ፡፡
“ከማል ከማል ከማል….”
“እኔ የምልህ የሀገሩን ሰው ስልክ ቁጥር ሁሉ ተሸክመህ በሰሃራ በርሃ አልደከመህም?” ብዬ ጮክ ብዬ ተናገርኩ፡፡ ምናልባት ከጭንቀቱ መለስ ብሎ ፈገግ ይላል በሚል፡፡
“አይ አንቺ ወረዳዋ እኮ ትንሽ ናት፡፡ ወለጋ ስልሽ በመላው ቦታ የኖርኩ መሰለሽ፤ በዛ ላይ የምንሳደደው አማሮቹ ጥቂቶች ነን፡፡” ባዘነ ድምፁ እሱም ጮክ ብሎ መለሰልኝ፡፡
ሽንኩርቱ አቃጥሎኝ ዕንባዬ መፍሰስ ጀምሯል። በእጅጌዬ ጠረግኩና፤ “ጥቂት ከሆናችሁ እዛ ለምን ትኖራላችሁ?” አልኩት፡፡
“በድርቁና በጦርነቱ ምክንያት ነው አያቶቻችንን ደርግ አምጥቶ እዚህ ያሰፈራቸው። ደኑን መንጥረው መንደር መስርተው እዚያ መኖር የጀመሩት እንዲያ ነው ይባላል፡፡ ኋላ ያው ሲወልዱ ሲዋለዱ ኖሩ። እትብት የተቀበረበት፣ ዘርቶ የቃመበት፣ ወልዶ የሳመበት ቦታ ያው ሀገሬ ነው ብሎ ወገኔ ኖረ፡፡” ብሎኝ ዝም አለ፡፡
ቀይ ሽንኩርቱ እያቃጠለኝ ከዚህ በላይ እየጮሁ ማውራት አልፈለግሁም፡፡ እኔም ዝም አልኩ፡፡
ከትንሽ አፍታ በኋላ “ጠራ የከማል ስልክ ጠራ…” ቢያዝን በኃይል ጮኸ፡፡ ደንግጬ ቢላዋውን አስቀመጥኩና በፍጥነት እሱ ወዳለበት ክፍል ሮጥኩ።
ከተቀመጠበት ተነስቶ “ጠራ ጠራ…” ይላል፡፡
በመጨረሻ ስልኩ ተነሳና፤ “ሄሎ” አለ ከኢትዮጵያ “ከማል ከማል ቢያዝን ነኝ፡፡” ሲርበተበት ሲያሳዝን የስልኩ ድምፅ ከፍተኛ ስለነበር ቢያዝን ጆሮው ላይ ቢለጥፈውም ለእኔም በአግባቡ ይሰማኛል፡፡
“ቢያዝን” ብሎ ከወዲያኛው መስመር ለአፍታ ዝም አለና፤ “ቁጥሩ እኮ የውጭ ሀገር ነው” አለ፡፡ በዝምታው አፍታ የተደወለበትን ቁጥር ሲያስተውል እንደነበር ገባኝ፡፡
“አዎ ወንድማለም ጀርመን ገባሁ እኮ፤ ከትናንት ጀምሮ የእነ እመይን ስልክ የሁላችሁንም የጎረቤቱን ስልክ ብቀጠቅጥ ብቀጠቅጥ አልሰራ ብሎኝ ተጨነቅኩ፡፡”
ከማል ትንፋሹን ብቻ ልኮ ዝም አለ፡፡
ቢያዝን ስልኩ የተቋረጠ መስሎት “ከማል ከማል…” ጩኸት፡፡
“ወንድሜ አንተ ቀንቶሃል፡፡” አለና አሁንም ዝም።
“ከማል የት ነህ? እባክህ ቤት ሂድና አንዳቸውን አገናኘኝ”
ከማል አሁንም ዝም፡፡
“ከማል”
“አቤት ወንድሜ” ድምፁ ተቀይሯል፡፡
ቢያዝን ረገብ አለ፤ “የተፈጠረ ነገር አለ፡፡ አያቴ ደህና ነው?”
ግራ እንደተጋባሁ ተጠግቼው ቆምኩ፡፡ አሁን የእኔ ሁለመናም በስልኩ ውስጥ ካለው ከማል ጋር ሆኗል፡፡
“አይ አንተ ምን እልፈት አለን ብለህ ነው” ያዘነ ተስፋ የቆረጠ ሰው ድምጽ፡፡
“ንገረኝ ምን ተፈጥሮ ነው?” ቢያዝን እንደገና መጮህ ጀመረ፡፡
“በቀደም ለት መጡብን እኮ…” ሳግ ያዘው፡፡
ቢያዝን ለአፍታ ቃል አልወጣውም፡፡ ቆይቶ ቆይቶ “መጡ?!” አለ፡፡
ትናንት ማታ ስልክ ሊሞክር ቤቴ መጥቶ ሲያወራኝ ነበር፡፡ በዚህ ሶስት አራት ዓመት ውስጥ  ታጣቂዎች በተለያዩ የወለጋ ወረዳዎች የሚሰሩትን ግፍ፣ በመንግስት ኃይሎች ገበሬው አብሮት የኖረ ምንሽሩን ተነጥቆ ራሱን መከላከል እንደማይችል፣ የመንግስት ታጣቂዎች ከተጎጂ ወገኖች ጋር እንደማይቆሙ፣ በአንድ መንደር ጨካኝ ታጣቂዎች ሲመጡ የስልክ ኔትወርክ ቀድሞ እንደሚቋረጥ በፊት  ነግሮኝ ነበር፡፡
እንኳን ለእሱ ለእኔም “እነማን ናቸው የመጡት?” የሚል ጥያቄ አስፈላጊ አልነበረም፡፡
“አሁን የት ናችሁ?” አለ በሰለለ ድምፅ
“ያው ድንገት በሌሊት በከባድ መሳሪያ ሳይቀር ተኩስ ከፈቱብን፤ የበረታነው ወደ ጫካ ሮጥን”
“እነ እመይን አይተሃቸዋል?” እመይ እናቱ ናት፡፡
“ትናንት ጫካ ውስጥ አብረን ነበርን። አሁን እኔ ሌሊቱን ስገሰግስ አድሬ ወደ ቡሬ እየተቃረብኩ ነው። ስልክ የሰራልህ ለዚያ ነው።”
“ከማል ወንድሞቼስ?”
“ጉብሉ በቻለው መጠን ወደ ጫካ ገብቷል። ሴቶችና ህፃናትም ነፍሰጡር አልቀረ ጫካ ናቸው። እንጃላቸው በረሃቡ ሕፃናቱ ዋይ ዋይ እያሉ ነው:: የጫካዉ አውሬም ሲዞራቸው ያድራል::”
“አበይን አይተኸዋል?” የቢያዝን ድምፅ በኃይል ይንቀጠቀጣል፡፡ የእኔ ሰውነትም መራድ ጀምሯል፡፡
ከማል ደግሞ እንደገና ተነሳበት፤ ዝም አለ፡፡
“ከማል አበይ አበይ….”
“ሀጂ ሐሰንን እንደምንም ደጋግፌ ይዤ ወጥቼ ነበር፡፡ ጫካ ልንገባ ትንሽ ሲቀረን ከብቶች መዋያ ሜዳ ላይ ከጀርባው መቱብኝ፡፡” አለና አለቀሰ፡፡
ቢያዝን በደመነፍስ ወንበሩ ላይ ቁጭ አለ። ልብ ያላልኩት ዕንባው ከምኔው አንገቱ ላይ እንደደረሰ እንጃ፡፡
በስልኩ የከማል መንሰቅሰቅ ልቤን ሰቅዞት ዕንባዬ ይወርዳል፡፡ ረጅም የሚመስል የዋይታ ጊዜ ካለፈ በኋላ ቢያዝን እንደምንም ሳጉን ተቆጣጥሮ “ከማል አበይስ?” አለ፡፡ አበይ በልጅነቱ የሞተው የአባቱ አባት መሆናቸውንና በጣም የሚወዳቸው አያቱ እንደሆኑ ማታ ሲያወራኝ ነበር፡፡
“የአበይ ፀሎት ባይከተለኝ የሰሃራን ነገር ተይው አይወራ…..” ትናንት ደጋግሞ እንዲህ ብሎኛል፡፡
ከማል እስካሁን መልስ ስላልሰጠ “ወንድሜ አበይም ሞቷል አይደል?” አለ ቢያዝን፡፡
“አላወቅኩም” አለ ከማል ፡፡
“ንገረኝ እንዴት አታውቅም” እንደገና ጩኸት፡፡
“ከወንድሞችህ የሰማሁት…..”
“እ ምን አሉህ…?”
“አበይ እናታችሁን ይዛችሁ አምልጡ፤ እናንተ ለዘር ትረፉ ብሎ እምቢ አለ….”
በታላቅ ድንጋጤ “ትተውት ሄዱ?” ከወንበሩ ተነሳ፡፡
“ጊዜም ምርጫም አልነበራቸውም፡፡ አበይን ታውቀው የለ፤ እሱ ካለ አለ ነው፡፡ ሰይፍ ይዞ ውጡ እናታችሁን አድኑ፤ ለዘር ትረፉ እያለ ጮኸባቸው፡፡ ምን ያድርጉ..”
ቢያዝን ጥያቄው አለቀ መሰለኝ፡፡ በዝምታ ደርቆ ቀረ፡፡
“አበይ ታውቀው የለ፡፡ በተቀመጠበት ሰይፉን ይዞ አንድ አውሬ እገድላለሁ ሲል ነበር አሉኝ”
ተረኛው ዝምታ ከወዲህ ነው፡፡
“ምን ታደርገዋለህ እኔስ የምወደው የአያቴን አስከሬን አፈር መች አለበስኩ፤ እያጣጣረ ትቼው እንድሄድ ለመነኝ፡፡ የተኩሱ ድምፅ እየቀረበ ነበር፡፡ ዓይኑን እስኪከድን ብቻ አጠገቡ ነበርኩ፡፡” ከማል እንደገና ማልቀስ ጀመረ፡፡
ሙሾው ተቀባይ አልነበረውም፡፡ ቢያዝን በድኗል፡፡
ትናንት ስለ ስሙ ጠይቄው አያቱ እሱን ቢያዝን፣ አባቱን ያደርሳል ብለው እንዳወጡለት፣ የራሳቸው ስም ይሁኔ እንደሆነ አጫውቶኝ ነበር፡፡
“ቢያዝን ያደርሳል ይሁኔ” አልኩ ሳላስበው ድምፅ አውጥቼ፡፡
ስልኩን ተቀብዬ ከማልን ለማፅናናት ሞክሬ ከዘጋሁ በኋላም፣ ለረጅም ጊዜ ከተቀመጠበት ሳይነሳ በዕንባ የታረሱ ጉንጮቹ ደረቅ ሸንተረር እንደሰሩ ተጎልቶ ብዙ ቆየ፡፡ ልረብሸው አልፈለግኩም፡፡ ድንጋጤዬ ቀለል ሲልልኝ የጀመርኩትን ቁርስ ሰርቼ ወፍራም ቡና አፈላሁ፡፡
ከተዋወቅን ሳምንት ያልሞላን ቢሆንም፣ የሀገሬ ልጅ እንዲህ ሆኖ እያየሁት እንግድነት አልተሰማኝም። በተቀመጠበት አቀፍኩትና፤ “እንግዲህ ምን ማድረግ ይቻላል፡፡ በሰው ሀገር ነው ያለኸው ጠንከር በል” አልኩ፡፡
ቀና ብሎ አየኝ፡፡ ቆይቶ ቆይቶ፤ “አበይ በሀገሩ ነበረ” አለ፡፡
ዝም አልኩ፡፡
“አበይ እኮ ማይጨው ዘምቶ ነበር” ፈገግ ሲል እቅፌን አነሳሁ፡፡
“ጎራዴው ጎራዴው…. እድሜ ልኩን ከእሱ ጋር የኖረ ነበር፡፡”
ዝም፡፡
“ጠላት አራውጬበታለሁ ብሎኛል፡፡”
ትንሽ ቆይቶ ፈገግታው ጠፋ፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን እንዳፈጠጠብኝ ስለሆነ የምይዘው የምጨብጠው ጠፍቶኛል፡፡
“አያትህ ጀግና ናቸው፡፡ አሁን ሲል አልሰማህም ጎራዴያቸውን ይዘው ጠበቋቸው” አልኩ፡፡
“ጀግናን ፈሪ ከመሸ አገኘው፡፡” አለና ብድግ አለ፡፡
“ቆይ እንጂ ወዴት ልትሄድ ነው፡፡” የምለው ጠፋኝ፡፡
“አመሰግናለሁ፡፡ ወጥቼ ትንሽ ተዟዙሬ ልመለስ” በፍጥነት ወደ በሩ አመራ፡፡
“ቡናው…”
“አመሰግናለሁ፡፡” ብሎኝ ወጣ፡፡
በዚህ ኃዘን ውስጥ ሆኖ መብላት ለእኔም እርም ሆነብኝ፡፡  ምግብ ለመስራት ጓዳ ስገባ ሶፋው ላይ የወረወርኩትን ጋቢዬን ተከናንቤ ሶፋ ላይ ተጠቀለልኩ፡፡
ምን ያህል እንደቆየሁ እንጃ ሰመመን ውስጥ ሆኜ ሙሾ ይሰማኛል፡፡
“ይኼን የለጋስ ዘር እጁን አትቅበሩት ጣሉት ከመንገዱ የሚያልፉትም ሁሉ እያዩት ይሂዱ…”

“ገፋኸኝ ገፋኸኝ ጥንት የነበረ ነው
ኸረ ወለጋዎች ሞትማ ቁርጥ ነው፡፡”
ቀስ እያልኩ በደንብ ነቃሁ፡፡ በር ከፍቼ ከእነ ጋቢዬ ወጣሁ፡፡ ቢያዝን በቀዝቃዛው አየር እጆቹን ወደ ኋላ አጣምሮ አጎንብሶ፣ ወዲያ ወዲህ እያለ የለቅሶ ግጥም እያወጣ በወግ እያለቀሰ ነው፡፡
ወደ ሰማይ አንጋጦ ደግሞ እንዲህ አለ፡-
“አንተ ፈራጅ ዳኛ አታመላልሰነ
ውድማውን ጠርገህ አንደግዜ ፍጀነ”
“አንተ ፈጣሪያችን ወይ ፍረድልነ
ሁልጊዜ ዝም እያልክ አታስጨረሰነ...”
በመኪና የሚያልፉ ነጮች ለአፍታ አየት አድርገው ያልፉታል፡፡ እንኳን በመኪና የሚያልፉትን አጠገቡ የቆምኩ እኔን ማስተዋል እስኪሳነው ሀዘን ሰብሮት ነበር፡፡
እንደምንም አቅፌ ወደ ቀልቡ ለመመለስ እየሞከርኩ፤ “ቢያዝን ቢያዝን እባክህ ስማኝ፡፡ ብርዱ ሁለታችንንም እያደረቀን ነው፡፡ እባክህ ወደ ቤት እንግባ” በጩኸት ጭምር እናገራለሁ፡፡
***
ከዚያ  ቀን ጀምሮ ቢያዝን ከቀልቡ አልሆነም።  በተቻለኝ ሁሉ አፅናናዋለሁ። አንዳንዴ ሲመቸኝና አየሩ ጥሩ ሲሆን  አጠገባችን በሚገኘው ጫካ ውስጥ አብረን እንንሸራሸራለን። በብርዱ ምክንያት ሁሉም አሞሮች ሄደው ሁለት ብቻ ቀርተው ነበር። በዚህ መንገድ ሁልጊዜ እናያቸዋለን፡፡ አርጅተውና አቅም አጥተው እንደቀሩ ስላወራሁት በተለይ ቢያዝን እነሱን ሳያይ ወደ ቤቱ መግባት አይፈልግም::
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ እየተንደረደረ ቤት መጣ። እንደለመደው ደውሉን አንጫጫው። እሱ መሆኑን አውቄያለሁ፡፡ ከእንቅልፌ ተነስቼ  ተንደርድሬ በሩን ከፈትኩለት። ከውጭ የገባው ብርድ በአንዴ ንቁ አደረገኝ።
እየተጣደፈ፤ “ቶሎ በይ የሆነ ነገር ልበሽና ነይ"
“ ምን ሆንክ? “ ብዬ በድንጋጤ ጠየቅሁት።
“አገኘኋቸው እኮ ሀጂ ሐሰን ሞተው ነበር።" አለኝ:: እስካሁን ልብ ያላልኳቸው ሁለት ነጫጭ ያረጁ አሞሮች እግሩ ስር አንቀላፍተዋል፡፡
“አበይን ሳገኘው አልሞተም ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል ማለፉ ላይቀር ንፋሱ ጎዳው፡፡ እንደተቆጣ ዓይኖቹን ከደነ፡፡” አለኝ፡፡
“ቢያዝን ምንድነው የምታወራው?”
 እግራችን ወደ ምናፍታታበት ቀጭን መንገድ እያሳየኝ፤ “ሁለቱንም እዚያ አገኘኋቸው፤ሀጂን ሳገኘው አስከሬኑ ቀዝቅዞ ነበር” ቀስ ብሎ አንዱን የሞተ ነጭ አሞራ አነሳና በክብርና በፍቅር ስሞ አቀፈው፡፡
ዕንባ ባቀረሩ ዓይኖቼ በታላቅ ዝምታ ውስጥ ሆኜ አየዋለሁ፡፡
እንደገና ወደ መሬት ዝቅ አለና አንዱን ነጭ አሞራ እያነሳ፤ “አበይን አየሽው ከዛፉ አልወረደም ነበር፤ ግን ነፋሱ እያየለ መጣ፤ ምን ታደርጊዋለሽ ተሸነፈ፡፡” አለኝና አበይ ያለውን አሞራ አቅፎ ሳመ፡፡
በማየውና በምሰማው ነገር ከመመሰጤ የተነሳ አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማውን ብርድ እንኳን ረሳሁት፡፡ ቢያዝን ነጭ ጋቢ የለበሱ ሽማግሌዎች የሚመስሉትን ነጭ አሞሮች በክብር አስቀምጦ፣  የመንደራችን መግቢያና የመኪና ጎዳናውን የሚለየው ሳር የበቀለበት ቦታ ላይ ሁለት ጉድጓድ ጫረ፡፡
ሀጂ ሐሰን በአንደኛው ጉድጓድ ገቡና አፈሩን መለሰላቸው፡፡ በቅጠል የጨረቃ ምስል ሰርቶ መቃብራቸው ላይ አኖረ፡፡ ቀጥሎ አበይ ተቀበሩ፡፡ በእንጨት ስንጥር መስቀል ሰርቶ ምልክትን ሠራና በመካከላቸው ተንበርክኮ ጥቂት ቆየ፡፡ ፀሎት ላይ ይመስላል፡፡
ተነሳና ተመለከተኝ፡፡ ከእሱ ያልተናነሰ ሀዘን እኔ ሆድ ውስጥ ገብቷል፡፡
“ባለፈው ስለ እነዚህ አሞራዎች ስታወሪኝ በደህና ጊዜ ሀገር አማን ብለው ወደዚህ ሀገር መጡ፡፡  ብርዱን ስለማይችሉ ብዙዎቹ ወደ ደቡብ ግር ብለው ይሄዳሉ አልሽኝ፡፡ ደካሞቹ ትንሽ በረው መንገድ ላይ ይወድቃሉ፡፡ አንዳንዶች የሚመጣባቸውን መከራ በቆራጥነት ለመቀበል ይቀራሉ፡፡ ጊዜው ከባድ ስለሆነ መሞታቸው አይቀርም አልሽኝ፡፡ አየሽ የሆነው ሁሉ እንዲህ ነው፡፡” አለኝና ዓይኖቹ ዕንባ አቀረሩ፡፡
ከብዙ ዝምታ በኋላ አንድ ነገር ተናገርኩ፡፡
“ያልከው ሁሉ ትክክል ነው፡፡ ግን አቅም ኖሯቸው መከራውን ሸሽተው የሄዱት ወጣቶቹ አሞራዎች አንገት ደፍተው እንደሄዱ በዚያው አይቀሩም። ደግሞ ፀደይ ይሆናል፡፡ ጨለማው በብርሃን የሚሸነፍበት ጊዜ ብዙ ሩቅ እንዳይመስልህ፤ እመነኝ የተበተኑት እንደገና ብዙ ሆነው በግርማ ሲመጡ አብረን እናያለን፡፡” አልኩ፡፡
ይኼ እውነት ያቀረረ ዕንባውን መጠጠና ሀሞት አደረገው፡፡        

Read 762 times