Saturday, 21 January 2023 20:19

ጠ/ሚኒስትሩ በአንድ ሳምንት ብቻ 10 አዳዲስ ከፍተኛ ሹመቶች ሰጥተዋል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለከፍተኛ የሀላፊነት ቦታዎች የተመረጡትን አዳዲስ ተሿሚዎች ይፋ አደረጉ ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሹመት ይፋ ያደረጉት በትላንትናው ዕለት ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ተሿሚዎች የህዝብ እንደራሲዎች ምክር ቤት እንዲያፀድቅላቸው በጠየቁት መሰረት አፅድቋል፡፡ በዚህም መሰረት አለሙ ስሜ (ዶ/ር) የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ ሲሆን ፣ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) ደግሞ የማዕድን ሚኒስትር እንዲሁም ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የግብርና ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌሎች ሹመቶችንም የሰጡ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት ከጥር 10 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ አቶ ማሞ ምህረቱ የብሄራዊ ባንክ ገዢ፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር፣ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጪ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር ፣ ወ/ሮ አለምፀሀይ ጳውሎስ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ሀላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር እንዲሁም አቶ መለሰ አለሙ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ የዘርፍ አስተባባሪ ሆነው ተሾመዋል፡፡
በሌላ በኩል፣የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥር 6 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው 16ኛ መደበኛ ሥብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጎ ውሳኔዎችን ካስተላለፈ በኋላ የማዕድን ሚኒስትሩን ታከለ ኡማን (ኢ/ር) የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትራን ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስን ፣ የግብርና ሚኒስትሩን አቶ ኡመር ሁሴንና ተፈሪ ፍቅሬን በክብር ከሸኘ በኋላ  ቀጣይ ጉዟቸው የተሳካ እንዲሆን ተመኝቶላቸዋል፡፡
 ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊና ምክትላቸው አቶ ሰለሞን ረዳ በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ 6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባውን ካካሄደ በኋላ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንትንና ምክትል ፕሬዚደንትን ሹመት አፅድቋል፡፡ በዚሁ መሰረት ም/ቤቱ አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ከበደን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አድርጎ በ3 ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምፅ ሲያፀድቅ፣ ወይዘሮ አበባ እምቢአለን ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ በሙሉ ድምፅ ሹመታቸውን ማፅደቁ አይዘነጋም፡፡

Read 4242 times