Saturday, 21 January 2023 20:31

ሕይወት፣… በዚህ ሲሉት በዚያ ያመልጣል፤ ወይ ይደምቃል

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

  እምነትና እውቀት፣… መስማትና ስሌት።
“እንደ እምነትህ ይሁንልህ”፣… “በእምነትሽ ድነሻል”፣… “በእምነትህ ተፈውሰሃል”፣… በማለት ደጋግሞ ይነግረናል። ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው እንደማለት ይመስላል። “ጭፍን እምነት” ማለት ነው? ሊሆንም ላይሆንም ይችላል።
በእርግጥ፣ ዛሬ የማይታይ ነገር፣… በስራና በጥረት ነገ እውን እንደሚሆን በማመን ላይ የተመሰረተ ነው - ኑሯችን ሁሉ። ዛሬ የማይታይ ምርት ነገ ማፈስና መጨበጥ እንደምንችል “በማመን” ዛሬ እንዘራለን፤ እንገነባለን።  ይሄ “ጭፍን እምነት” አይደለም። ግን እምነት ነው።
ደግሞም፣ ሳናይ ሳንመረምር እንዳንቀበል ይነግረናል። በሐሰተኛ ስብከቶች እንዳትታለሉ ተጠንቀቁ ይላል። ትንቢት የሚናገሩና ድንቅ ተዓምር የሚሰሩ ቢሆኑም እንኳ፣ ሐሰተኛ ነቢያትን አትመኑ በማለት ያስጠነቅቃል።
ከጭፍን እምነት እንድንርቅ፣ ልብ ብለን እንድናይ፣ እንድናስተውልና እንድንመረምር ይመክረናል። እንድንሰማ ብቻ ሳይሆን እንድናደምጥ፣ እንድናገናዝብ ያሳስበናል።
ፍሬያቸውን በማየት፣ ጥሩዎቹንና መጥፎዎችን ለይተን እንድናውቅ ለእያንዳንዳችን ከባድ ሃላፊነት ይጥልብናል።
እሺ። ይሁን። ጥሩ ነው። ነገር ግን ተጨማሪ ሃላፊነትን ያመጣብናል።
እምነትና ኑሮ፣ ንግግርና ተግባር።
ሰምቶና አስተውሎ፣ መርምሮና አረጋግጦ ማመኑ አንድ ቁም ነገር ነው።
በሌላ በኩል ግን፣ የሰማውንና ያመንበትን ነገር በተግባር የማይኖርበት ከሆነ፣ ጥቅሙ እድሜ እንደማይኖረው ያስተምራል።
…ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ፣ ቤቱን በዓለት ላይ የሰራ ልባም ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ፤ ጎርፍም መጣ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንም ቤት ገፋው፤ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።
…ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ፣ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ፤ ጎርፍም መጣ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንም ቤት መታው፤ ወደቀም። አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።
ሃሳብንና ተግባርን፣ ሰማይንና ምድርን የማዋሃድ ተዓምር?
የሰናፍጭ ፍሬ ያህል ቅንጣት እምነት ቢኖራችሁ፣ ተራራውን ከወዲህ ወዲያ ዙር ብትሉት ይታዘዛችኋል ይላል።
ግን ደግሞ፣ ማመንና ማነብነብ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ ማለት ብቻ እንደማይበቃ፣… ትንቢት መናገርና የተአምር ዓይነቶችን መስራትም ጭምር በቂ እንዳልሆነ ይገልጻል።
“…ብዙዎች፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፣ ከቶ አላወቅኋችሁም እናንት ዓመፀኞች፣ ከኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።” በማለት ረዥሙን የተራራ ትምህርት ወደማሳረጊያው ያሸጋግረዋል።
ማመንና ተዓምር መስራት፣… በቂ ካልሆነ ምን ይሻላል?
የሙሴ አባባልን በመጥቀስ፣ ቀዳሚዋ ሕግ፣ እግዚሄርን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ ሃሳብህ ውደድ የምትል ናት ይላል።
ይህች ህግም በተግባር በምድር የምትገለጸው፣ “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” በምትል ሁለተኛዋ ህግ እንደሆነ ይናገራል።
ባልንጀራ ማለትም፣ የዝምድና ወይም የትውውቅ ጉዳይ እንዳልሆነ፣ “የሳምራዊውን” ምሳሌያዊ ታሪክ በመጥቀስ ያስተምራል። “በጎ ነገር ሊሰራ የሚችል ሰው” ሁሉ ባልንጀራህ እንደሆነ ትምህርቱ ይጠቁማል። ምን ይጠየቃል? ሰውን እንደ የተግባሩ እንደ የባሕርይው ልክ፣ አይቶና መዝኖ በጎ በጎውን መውደድ ተገቢ ነው።
በሌላ በኩል፣ “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” የሚለውን መርህ በአናቱ “የሚገለብጥ” ትምህርት ያመጣል። “የሚገለብጥ” ባንለው ይሻላል መሰለኝ። ባልንጀራህን ጥላ አይልማ። ነገር ግን፣ “ጠላትንህን ውደድ” ይላል። ከዚያም ያልፋል እንጂ።
ጠላታችሁን ወደዱ፤
የሚረግማችሁን መርቁ፤
በቀኝ ቢመታችሁ የግራ ፊታችሁንም አዙሩለት፤ ግማሽ ንብረት ለመውሰድ ለሚሟገታችሁ ሌላኛውን ግማሽ ጨምሩለት ይላል።
እነዚህን አባባሎች ቃል በቃል ለማመን የሚሞክሩ ሰዎች ቢኖሩ አይገርምም።
“አይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ጣላት። አንድ እጅህ ብታሳስትህ ቆርጠህ ወርውራት” የሚለውን ትምህርት ቃል በቃል ለመከተል የሚሞክርም አይጠፋም። የትምህርቱ ምሳሌያዊ ቁምነገር ግን ጠፍቶበታል። ወይም በጭፍን እምነት ሳቢያ ሕይወቱ ይጠፋበታል።
በቀኝ በኩል ቢመታችሁ የግራ ፊት አዙሩለት የሚለውስ? የይቅርታ መርህ ይሆን?
በግራ ሲመታህ ቀኝህን አመቻችለት ሲባል፣… በመልዕክቱ ቃል በቃል ሊሆን ይችላል? ሊሆን ይችላል። ነው የሚሉ ይኖራሉ።
በሌላ በኩል ግን፣ ቢመታችሁ ወይም  እቃ ቢነጥቃችሁ፣ የይቅርታ እድል አትንፈጉ ለማለት ሊሆን ይችላል - ትምህርቱ። ለምን በሉ።
ሞባይል ከነጠቀ በኋላ፣ የይቅርታ እድል ከተሰጠው፣ የኪስ ቦርሳችሁን ለስርቆት አጋልጣችሁ እንዳቀረባችሁለት ቁጠሩት። በይቅርታ ባታቀርቡት ኪሳችሁ አጠገብ ለመድረስ አይደፍርም።
ድንገት ጥቃት የሰነዘራችሁ መስሎት፣ በድንጋጤና በቁጣ፣… በግልፍተኛ ስሜት የተማታ ሰው፣… በፀፀትና በሐዘን ይቅርታ ቢጠይቅ ምን ይሉታል? መቼስ ምን ይደረግ? ይቅር ትላላችሁ።
ነገር ግን፣ ይቅርታ መስጠት ቀላል ጉዳይ አይደለም። በይቅርታ ካስጠጋችሁት፣ ሌላ ፊታችሁን እንደገና ለጥቃት አሳልፋችሁ እንደሰጣችሁ ቁጠሩት። ሌላ ፊታችሁን አዙሩለት ተብሏል - በትምህርቱ።
ግን ደግሞ፣ እንኳንና የሰውን ንብረት መዝረፍ ይቅርና፣… ያልደረሰባቸውን ሰው ግራና ቀኝ እያገላበጡ መማታትና መደብደብ ይቅርና፣ አላግባብ መቆጣት፣ በክፉ መናገርና መሳደብም መጥፎ ተግባር መሆኑን በአፅንኦት ይገልጻል።
ሰውን የሚያጥላላና የሚያዋርድ፣… ደደብ ደንቆሮ ብሎ ወይም ችጋራም ኮተታም ብሎ የሚሳደብ፣ “ፍርድ ይገባዋል” በማለት ከክፉ ስሜትና ከመጥፎ ንግግር መቆጠብን ይመክራል።
በእርግጥ፣ “አትፍረዱ፣ እንዳይፈረድባችሁ!” ደግሞ ይላል።
“አትፍረዱ” ሲባል፣ እንደ ቀልድ እንደ ዋዛ አትፍረዱ ለማለት ሊሆን ይችላል። ሰው እስከሆናችሁ ድረስ፣ ወደዳችሁም ጠላችሁም፣ ዳኝነትና ፍርድ መስጠታችሁ አይቀርምና።
ተበዳይን ማጽናናትና ማካካሻ እንዲያገኝ መጣር፣ በዳይ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ እንዲጠይቅና እንዲክስ፣ ወቀሳና ተግሳጽ መስጠት ያስፈልጋል።
ግን፣ ዳኝነታችሁና ፍርዳችሁ፣ ያልተዛባና ያልተጓደለ፣ የተቃናና ተሟላ እንዲሆን መጣር የግድ ነው። ደግሞም በትውውቅ፣ በዝምድና፣ በትውልድ ቦታ፣ በመደለያ መሆን የለበትም።
የሆነ ሰው በሌላ ጉዳይ ልታደንቁት ልትንቁት ትላላችሁ። በሌላ ጉዳይ ትጠሉት ትወዱት ይሆናል።
ለዳኝነት የቀረበላችሁ ጉዳይ ላይ ግን፣ በጥላቻ ወይም በፍቅር ስሜት ፍርዳችሁ መዛባት የለበትም። ለጠላችሁትና ለወደዳችሁት ሰው፣ የዳኝነት መጽሐፋችሁ አንድ መሆን አለበት። ለምትንቁትና ለምታደንቁት ሰው፣ በእውነት የተቃና ዳኝነትንና የፍትህ ፍርድን ትሰጣላችሁ። “ጠላትን መውደድ” ይመስላል ይሄ።
ያው፣ የተቃና ዳኝነትንና የፍትህ ፍርድን የምትሰጡ ከሆነ፣ እናንተም በዚያው መፅሐፍ በዚያው ሚዛን ነው ዳኝነትና ፍርድ የምታገኙት።
በሰፈራችሁበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ ይሰፈርባችኋል። በመዘናችሁበት ሚዛን ይመዘንላችኋል። ይመዘንባችኋል።
ሚዛንና ስሌት፣… መርህና እምነት።
ማብሰልሰልና ማገናዘብ፣ ወጪና ገቢም፣ ማመዛዘን፣ ስሌትና ቀመር መስራት እንደሚያስፈልግ በብዙ ምሳሌዎች ይገልጽልናል። ጎን ለጎ ደግሞ፣ የመርህና የእምነት ዋናነትን ይነግረናል። ስሌትና ቀመር ፋይዳ የሚኖራቸው፣ ዋና የመርህ መሠረትና ንጣፍ መደብ ከተበጀላቸው ብቻ ነው።
እውነትን በአወንታ ከመቀበልና ከማመን ጎን ለጎን፣ የሰው ሕይወትን ወይም ነፍስን ማክበር ነው ትልቁ የመርሆች መሰረት። የሰው እኔነትን ወይም የግል ማንነትንና መንፈስን ካከበርን ነው፣ የስነ-ምግባር መርሆች ትርጉም የሚኖራቸው።
በእነዚህ መሠረቶችና ንጣፎች ላይ፣ በእነዚህ መስመሮችና መርሆች ላይ ከቆምን ነው፣… የማንኛውንም ነገር ጥቅምና ጉዳት ማስላት ወይም ማመዛዘን የምንችለው።
አለበለዚያ፣ ጥቅምና ጉዳት የሚሉ ቃላት ትርጉም ያጣሉ። ስሌትና ሚዛን ከንቱ ድካም ይሆናሉ።
የሰው የግል ማንነትን፣ የሰው ተፈጥሯዊ የማስተዋልና የማወቅ አቅም፣ አላማውን የመምረጥና ተግባሩን የመወሰን፣ የራሱን ሕይወት የመምራትና የራሱን ሰብዕና የመቅረፅ… እነዚህ ልዩ የሰው አቅሞችንና ብቃቶችን ካከበርን ነው፣… ጥሩንና መጥፎን የሚለይ የሥነምግባር መርህ (መስመር) ሊኖረን የሚችለው።
መምከርና መገሰፅ፣ መዳኘትና መፍረድ፣ ማድነቅና መንቀፍ፣… ትርጉም የሚኖራቸው፣ ሰዎች ከሌሎች ሕያዋን፣ ከዕፅዋትና ከሌሎች እንስሳት የተለየ ተፈጥሯዊ አቅም እንዳላቸው እስከተገነዘብን ድረስ ነው።
በሌላ አነጋገር እንግለጸው ከተባለ፣ ሚዛኖች ፋይዳ የሚኖራቸው፣ ጠጠሮችንና ጥራጥሬዎችን መለየት ከቻልን ብቻ ነው።
ስሌትና ቀመር፣ ሚዛንና ሜትር ያስፈልጋል። ጥቅምና ጉዳትን ማነፃፀር ተገቢ ነው። ነገር ግን በቂ አይደለም።
ምን ያህል ሰዓት ልስራ? ምን አይነት እህል ልዝራ? ምን ዓይነት ቤት ልገንባ? በስንት ብር ልከራይ? ስንት ኪሎ ልግዛ? ከማን ልበደር? ማንን ላግዝ? ከማንስ ድጋፍ ልጠይቅ?
እነዚህ ስሌቶችና ቀመሮች፣… አየር ላይ የተንሳፈፉ ጉሞች አይደሉም። የመስራትና ንብረት የማፍራት መርህና ላይ የተመሰረቱ ስሌቶች ናቸው። የመከባበርና የመተጋገዝ መርህም፣ ለግብይት ድርድሮችና ሚዛኖች መሰረት ነው።
በተቃራኒው፣ የሸፍጥና የዝርፊያ፣ የጥቃትና የውድመት ተግባራት ሁሉ ሚዛን ላይ አይቀመጡም። ስርቆትና ድብደባ ከመርህ ከመስመር ውጭ መሆናቸውን በመገንዘብ፣ ስሌትና ቀመር ውስጥ መግባት እንደማይኖርባቸው ማመን ያስፈልጋል። የሥነምግባር መርህን የተከተለ አኗኗር፣ እንዲህ ነውና።
በሌሎች ሰዎች ኪሳራ የማትረፍ፣ በጉልበትና በግዴታ ሌሎች ሰዎችን እየማገዱ የመሞቅ ተግባር፣ እንደ “አማራጭ” የኑሮ ተግባር አይቆጠርም። ስሌትና ቀመር ውስጥ አይገባም። ከስነ-ምግባር መርህ (ከመስመር) ውጭ የሆነ ተግባር ነውና።
በአጭሩ የስነ ምግባር መርህ፣… በጣም ትልቅ የከፍታ እመርታ ነው። ለስሌትና ለሚዛን ዋና መሰረት የሚሆንልንም የስነ-ምግባር መርህ ነው።
እንዲህም ሆኖ ከስሌትና ከቀመር፣ ከሚዛንና ከሜትር ጋር እየተጎዳኘ ነው የሚበለፅገው። የእሳቱን ሙቀትና ብርሃን፣ ኑሯችንን ለማየትና ለማብሰል ሲያገለግል እለት በእለት በተግባር እንመለከት የለ!
አላግባብ ከተጠጋነው ወይም ከቁጥጥር ውጭ ከተግለበለበ ደግሞ፣ አካልንና ኑሮን እንደሚለበልብ እንደሚያነድ ማየት አያቅተንም።
ይሄን እውነታ፣ በየእለቱ እንደ አዲስ ነገር ማየት አለብን? በየእለቱ እንደ ድንገተኛ ጉዳይ ጥቅምና ጉዳቱን ማስላት ይኖርብናል? እስከዛሬ ያስተዋልነው እውነታ እና የሰራነው ስሌት በቂ ነው - ግንዛቤ ለመጨበጥ።
በዚህ መንገድ የጨበጥነው ግንዛቤ ወይም መርህ ጊዜና ቦታ አይገድበውም። በሄድንበት አካባቢና በማንኛውም አጋጣሚ የምንጠቀምበት እውቀት ይሆንልናል። እንደ አዲስ የእሳትን ጥቅምና ጉዳት ማስላትና ማመዛን አይኖርብንም ማለት ነው።
ይልቅስ፣ ከቀድሞ ስሌቶችና ቀመሮች በመነሳት አዲስ እውቀት ስንጨብጥ፣ ለአዳዲስ ስሌቶችና ቀመሮች በር የሚከፍት ፅኑ መነሻ መሠረት ይሆንልናል። መርህም እንደዚያው ነው።
ነገር ግን፣ መርህ ወይም እምነት፣ ወይም እውቀት፣… ምንም እንኳ ድንቅ እመርታ ቢሆንም፣…በቂ አይደለም።
ይህን ለመግለጽ ይመስላል የኖህን ትረካ በምሳሌነት የሚጠቅስልን።
ስሌትና ተግባር በቂ አይደለም።
መርህና እምነት በቂ አይደለም።
እንደ ኖህ “ሆኖ” መገኘት ያስፈልጋል።
ሆኖ መገኘት! ፅድቅን ፈልጉ። ሌላው ሁሉ ይጨመርላችኋል ይላል።
ለአደጋ ጊዜ ተዘጋጅቶ መጠበቅ የሚቻለው፣… በስሌት በቀመር ብቻ አይደለም። በሥነምግባር መርህ ብቻ አይደለም። በተግባርና በእምነት ብቻ አይደለም።
ከጎርፍ ከመጥለቅለቅና ሰምጦ ከመጥፋት ለመዳን፣ መርከብ የመስራት አላማና ውሳኔ፣ ሃሳብና መርህ ብቻ የትም አያደርስም። በትክክለኛ ርዝመትና ስፋት፣ ቁመትና ውፍረት፣ በተገቢ ቁሳቁስና መጠን፣… በቅጡ ዲዛይኑን አውጥቶ፣ ስሌትና ቀመር ሁሉ አስተካክሎ፣ በተግባር መርከቡ ካልተገነባ ምን ዋጋ አለው? ግን፣ በመርከብ ግንባታ ዙሪያ፣ ኖህ በወቅቱ ብቁ ባለሙያ ሆኖ ተገኝቷል? ጥሩ ጥያቄ ነው።
ትክክለኛ ስሌትና መርህ፣ ትክክለኛ ተግባርና እምነት መልካም ናቸው። ያለነሱ የሚገኝ ሌላ ውጤት የለም። ግን በቂ አይደሉም። ከነሱ ውስጥ የሚዋለድ ሌላ ተጓዳኝ የሕይወት ገፅታ ያስፈልጋል።
ብቁ ሆኖ መገኘት!
መርህና ስሌትን፣ ሚዛን እምነትን፣ ተግባርንና ሃሳብን ሁሉ በትክክል እያሟሉ መኖር ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህን ሁሉ ከሁለመናው ጋር ያዋሃደ ማንነትን ማነፅ ያስፈልጋል።
በሌላ አነጋገር፣ “ሆኖ” መገኘት ማለት ነው።
አደጋ ሲመጣ ሮጦ ማምለጥ ወይም ፈጥኖ መጋፈጥ፣…
አዲስ እድል የተፈጠረ ጊዜም ሮጦ መቀበል ወይም ቶሎ ለፍሬ ማድረስ ይቻላል።
የምንችለውግን፣… ቀድሞውኑ ሯጭ ሆነን ከተገኘን ነው። ተምረንና ሙያ ለምደን ከተገኘን ነው፣ አዲስ የስራ እድል ሲያጋጥም ብድግ ብለን መሄድና መወዳደር የምንችለው።
እውቀትንና ሙያን ከራሳችን ጋር አዋህደን የማንነታችን ገፅታ ካደረግነው፣… ማለትም፣ የእንጨት ወይም የፀጉር ስራ፣ የልብስ ስፌት ወይም የልብስ ሱቅ ባለሙያ፣ የኤሌክትሪክ ወይም የግንባታ፣ የጤና ወይም የትራንስፖርት ባለሙያ ሆነን ከተገኘን፣… በዚሁ ሙያ ውጤታማ የመሆን እድል ሲፈጠር፣ ወዲያውኑ እንጠቀምበታለን።
ክፍት የስራ እድል ካየን በኋላ፣ በአንድ ጀንበር በፍጥነት ቱር ቱር ብለን ባለሙያ መሆን አንችልምና። አስቀድሞ መዘጋጀት ማለትም፣…ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል።
አዎ፣ በትክክለኛ ስሌትና መርህ፣ በትክክለኛ ተግባርና እምነት የእለት ተእለት ኑሮን መምራት ተገቢ ነው። ነገር ግን፣ እነዚህ በቂ አይደሉም።
እነዚህን ሁሉ ከሁለመና ጋር ያዋሃደ ማንነትን ማነፅ፣… (ሆኖ መገኘት) ያስፈልጋል።
በእርግጥ፣ “ሆኖ መገኘት”፣… ብቻውን በቂ አይደለም።
“ሆኖ በመገኘት” ብቻ የሚገኝ ቅንጣት ፍሬ የለም። ሐኪም በመሆን ብቻ ጤና አይገኝም። የምግብም ሆነ የመዝናኛ ባለሙያ፣ ሐኪም ወይም መሀንዲስ ሆኖ መገኘት ትልቅ እመርታ ቢሆንም፣… በሃሳብና በተግባር፣ እለት ተእለት ቁምነገር እንዲሰሩበት እንጂ፣ ማጌጫ ሜዳሊያ አይደለም።
“እከሊት ምርጥ ባለሙያ ናት። እገሌ ድንቅ ጥበበኛ ነው” ብሎ ደሞዝ የሚከፍል ይኖራል?
“ይሄውና የእርሻ ባለሙያው መጣ። ይህችውና የመስኖ ሊቅዋ መጣች” ብሎ በአድናቆት የሚለመልም ማሳ የለም።
“ሙያተኛ ሆነው ተገኝተዋል” ብሎ የሚመጣ ሕንጻና ግድብ አይኖርም።
“ሆኖ መገኘት” በቂ አይደለም።
በየእለቱ እያሰብንና እያሰላሰልን፣ እያገናዘብንና እያመዛዘንን፣…
ትክክለኛና የተቃና መርህን እየተከተልን፣
…በሙያዊ ጥበብና በፍሬያማ ትጋት በመስራት ኑሯችንን እንመራለን። ምርትና ትርፍ፣ ደሞዝና መተዳደሪያ የምናገኘው፣ እለት ተእለት በምናስበውና በምንፈፅመው ተግባር ነው።
በእርግጥ፣
ተግባራችንና ውጤታችን፣ የሙያችንና የጥበባችን ያህል ነው።
ሆነን በተገኘነው መጠን ነው፣ የተግባራችን ልክ።

Read 1184 times