Saturday, 21 January 2023 20:37

ለፍቅር ያሉት ለጠብ!

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(3 votes)

ቤቱን ቢጫ ፎቅ ይሉታል። ስሙን ያገኘው በለበሰው ቀለም ነው። ብዙ ታዋቂ ሰዎች ወደዚህ ህንፃ ይመጣሉ። ለመግባት የሚሻኮተው  የጉንዳን ሰልፈኛ ይመስላል። ከተጋቡ የሰነበቱት ፣ያልተጋቡትም ደምቀው ይቀመጣሉ። እኔም በነጠላ አጭር ወንበር ስቤ፣ ከሰዎች ጋር የሚያፋጥጥ አቀማመጥ እቀመጣለሁ። የሚስቴ እራት ወሬ ነው። እኔ እሱን ስሸቅል እውላለሁ።
ባለ ልጆች።
ዓይናቸው፣ ሳቃቸው፣ ወሬአቸው ኹሉ ሳይቀር የሚጫወተው ልጃቸውን ታኮ ያልፋል። የሕይወት ትርጉማቸውን፣ ለመኖር የሚገፋፋቸውን የሚያስገድዳቸውንም ያገኙ ይመስላሉ። ኮሽ ባለ ቁጥር ኹለት ጥንድ እጅ ወደ አንድ ፍሬ ልጅ ሲወረወር ማየት ይደንቃል። ከአባቱ ወገብ የዘር ፍሬ፣ከእናቱም ሰፊ ማኀፀን ተዋጥቶ የተወለደ መግባቢያቸው /መቀራረቢያቸው ሆኖ ይታያል።
የተጋቡት።
ነገን የሚናፍቁ፣ ለእኔ ከሚለው ለእኛ ወደሚለው ለመሸጋገር የሚጥሩ፣ በመሐላቸው ያለችን የጋብቻ ክር በፍቅር ያጠነክራሉ። ከኹለት አካልነት ወደ አንድ አካልነት የመምጣትን ሂደት ያለዝባሉ፤ ይሞርዳሉ...
ያልተጋቡት።
ይሳሳማሉ፣ ይቃበጣሉ። ለሴቷ ዓለም ወንዱ፣ለወንዱም ዓለም ሴቷ ሆነው ይታያሉ። ለከበባቸው ሰው ደንታ-ቢስ ናቸው። ማንንም አይሰሙም፤ ማንንም አያዩም። ፍቅር እውር ነው የሚባል ይኼኔ ነው።
በየቀኑ ቢጫ ፎቅ እገባለሁ።
በየቀኑ አዲስ ነገር አላጣም_ለሚስቴ።
[አጭር ቀሚስ፣ እስከ ጉልበቷ የሚደርስ ጫማ፣ ፀጉሯን በአጭር የተስተካከለች፣ በግራ እጇ ለሳንበዋ አይበጀውን፣ በቀኝ እጇ ለአእምሮዋ አይሆነውን የያዘች፣ የባልኮኒውን አንድ ጠርዝ የተቆጣጠረችሕሉ።]
[ደረቱ ሞላ ያለ ጠይም ወንድ፣ ፀጉሩ በስሱ የተመለጠ፣ ሲያወራ እጁ የሚወናጨፍ፣ ከጥሩ ጥርሶቹ ጎልታ ሸራፋው የምትታይበት ሄኖክ]
ሕሉ እና ሄኖክ ፊት ለፊት ተቀምጠዋል። እኔ የሕሉን የቀኝ ጉንጭ፣ የሄኖክን የግራ ጉንጭ በሚያሳይ ቦታ ጋር ነኝ።
«ድገመኝ» [ወደ አስተናጋጁ ዞራ]
ዓይኔ እያየ ብዙ የቢራ ጠርሙሶችን እና የጅን መለኪያዎችን ደረደረች። ዓይኗ ቀልቷል። የደም ሥሯ ስልቹነትን ያሳብቃል። ማንንም ልትሰማ ማንንም ልታወራ ፈቃዷ አይደለም። ታስቀዳለች... ትጠጣለች..
ከፊቷ ተማጻኝ ፊት።
ሲቀዳ አይኑ የሚንቀዋለል፣ ስትጎነጭ ሳይታወቀው የእሷን እንቅስቃሴ የሚደግም _ሄኖክ። ምንም ነገር እያወራት አይደለም። በስስት ያያታል።
ቢጫ ፎቅ ውስጥ ያልገባ ይሞታል የተባለ ይመስል ልጅ አዋቂው ገብቶ ታጭቋል። የሰዎች ድምፅ ሲቀላቀል _ልሳን ቢጤ ሆኖ ይሰማኛል። የብርጭቆዎች ኳኳታ፣ የወንበሮች ሲጢጥታ ይረብሸኛል። እዚህ ቤት አይደለም መደማመጥ መሰማማት ይቻላል? አልኩት ለራሴ።
ሕሉ በቀጭን ሰንሰለት የታነቀች ቦርሳዋን ይዛ ከሂል ጫማዋ ላይ ተንጠለጠለች። እንብርቷ ለተመልካች እስኪታይ ተንጠራራች። ከኋላ ኪሷ እጇ የሳበውን አውጥታ ለአስተናጋጅ አስረከበች።
ወጣች።
በስስት የሚከተላት ሄኖክ አለ። እሷ ቢራ ስትጠጣ እሱ ስፕራይት (ውኃ በስኳር) ሲጎነጭ ቆየ። ስትወጣ የገፈተረቻቸውን ሰዎች እየቀረበ ይቅርታ ጠየቀ። ከውጭ ያሉትንም ሰዎች እንዳትተናኮል ቀርቧታል።
«ፈረስ ...ፈረስ...» [ተጣራች]
ዳር ይዞ ቆመላት። ገባች ።ሄኖክ ተከታትሎ ሊገባ ሲል በር ዘጋችበት፤ ከዛም ሄደች። ነሆለለ።
ሁለተኛ ቀን።
ለማልጠጣው ነገር ቢጫ ፎቅ እገኛለሁ። ሰዎች የተኮነኑ ስለሚመስለኝ እራሴን እንደ ጻድቅ ለመቁጠር አደርገዋለሁ። ሥራቸውን ስወቅስ አምሽቼ ለሚስቴ የነገር እራት ይዤ እሄዳለሁ እሷም ይኼ ጸባዬ ተስማምቷታል ወይም ላለማስቀየም እየታገለች ይሆናል።
በተለመደው አቀማመጥ ተቀምጠዋል።
በመሐላቸው ወሬ የለም። የዓይኑ ቀለም እስኪለቅ ያያታል። ሊያናግራት ከንፈሩን ያሻሻል። እርሷ ግን ለአንዴም እንኳ ልታወራው አልያም ልታናግረው ፈቃደኛ አይደለችም።
ታስቀዳለች ... ትጠጣለች።
ታስቀዳለች ... ትጠጣለች።
ተይ የማለት ሥልጣን አጣ ሄኖክ። አኳኋኑ የመርበትበት ነው። እንደ ሸጋ አባትም ለመሆን ይቃጠዋል። ከጎኔ ያሉት ግን ሕሉን ሲወቅሷት ሰማሁ። አማረልኝ ብላ ነው? እርሱስ ቢሆን አጎዛ! ዠልጦ አያስወጣትም እንዴ? ምን ውጥንቅጥ ገጥሟት ይሆን? ኧረ ተወው የወንድ አልጫ ነው ባክህ! የበላይነት ስሜት ተሰምቷት ይሆን? ሴት ሌጅ ስብስብ እፍር ስትል ነው እንጅ... ጆሮዬን ደፈንኩ!
ከአፍታ በኋላ።
አጠገቤ ከተቀመጡት አንዱ ድንገት ፓንቷን አይቶ ኖሮ ተቁነጠነጠ። ለምን እንዲህ ትሆናለች፣ ስሜታችንን ለመስረቅ ነው የምትጋጋጠው፣ እናሲዝ ይቺን ሴት እተኛታለሁ...ብዙ ነገር ተባባሉ።
ሄኖክ አለቀሰ።
እንባው እንደ ሴት ልጅ ተለል አለ። ከልቡ ስቅስቅ ብሎ ተነፋረቀ። ቀረብኩት። ሦስተኛ ወንበሬን ወደ እነሱ አስጠጋሁ_ ላጽናናም የወሬ ጥሜንም ልቆርጥ።
«ምን ሆንክ ወንድሜ? ወንድ ልጅ ያለቅሳል?» የአፌን አልጨረስኩትም ፊቴ በቢራ ሲጠመቅ። ፊቴን ጠራርጌ ስቃና አራስ ነብር የሆነች እርሷን አየሁ...
«ለቅሶን ለሴት ልጅ ማን ሰጣት? ይኼ ለእኛ ውርስ ነው?..» ብዙ ቁጣዎችን አከታትላ ጣለችብኝ።
ጸጥ አልኩ።
ከለቅሶው አገግሞ ይማጸናት ገባ። “ሕሉዬ ስለሁሉም ነገር ይቅርታ። ወደ ቤትሽ ተመለሽ። ይኼ ነጋ ጠባ ባልኮኒ መደገፍ አያዛልቅም። እራስሽን አትጉጂ...”
«አቁም!..» ድንገት ደረቅ ቃል ወጣት።
 ልጆቿን የነኩባት ውሻ፣ቁጡዋን አራስ ነብር መሰለች። የጀመረችውን ጨልጣ ትገላምጠው ጀመር።
«እረጋ ብለሽ ስሚኝ..» [ተማጸናት]
“አቦ የሚሰማ ይስማህ። እኔ ሕሉ እያንዳንዷን እርምጃዬን ቆጥሬ አውቃለኹ። በዚህ ውጪ በዚህ ግቢ አትበለኝ። ነፃ..ነፃፃፃፃ መሆን ነው የምፈልገው። ከአንተ ሌላ ወንድ አይቼ አላውቅም ዛሬ ግን...”
«እንዳትጨርሽው!»
“ከአጠገቤ ብትርቅ መልካም ነው። ሥራዬ ኹሉ የሲዖል አሽከር እንደሚያደርገኝ እያሰብክ አጠገቤ አትወዘፍ። ኃጢያተኛ አይደለሁም።ለምን አትተወኝም? የተሰጠኝን ነፃ ፍቃድ በጋብቻ ሰንሰለት ማሰር በቅቶኛል። ገንዘቤ እስካለ እጠጣለሁ። እዝናናለሁ። የፈለግኩትን አደርጋለሁ። ክንፎችህን ዘርግተህ ልታቅፈኝ አትሞክር። ለዓመታት የተደበቅኩበት ጉያህ ሰልችቶኛል። አንዲቷን የሕይወት ሪትም መደጋገም ይበቃኛል። ሰማህ?”
ስለት ቢለዋ ነች፤ የሚናገራትን ቃል በሙሉ ትከትፋለች።
አንገቱን ወደ መሬት መለሰ። ከፀጥታ ብዛት ጠብ ጠብ የሚሉ እንባዎቹን አየሁ። የሚናገረው አላጣም ግን ላትሰማው፣ የሚመክራት አልቸገረውም ግን ላታደምጠው ሆነበት።
«አትነፋረቅ!»
ርኅራኄ የሌለው ቃል ከአፏ ወጣ። እንባዎቹን እንደ ህጻን በልብሱ ኮሌታ ጠራረገ። “ቤት አፅድቼ፣ምሳ ሰርቼ፣አስቤዛ ሸምቼ፣እህል አስፈጭቼ የምመጣ ባልሽ ነኝ። ምናልባትም ነገሬን አቅልለሽው ከሆነ አላውቅም። ስለምወድሽ ለሌላ አልመኝሽም። ከነ... ነው የምወድሽ። ለዛም ነው እንደ ፓቭሎ ውሻ ለሃጬን እያዝረበረብኩ የምከተልሽ። እንደ ወንዝ የሆነ ፍሰት ላይ ነሽ። ተመልሶ የማይመጣ የማይታሰብም። እኔ አንቺን በመከተል እግሬ ቀጠነ። የማዝነው በራሴ ነው። ስለምሳሳልሽ ከአጠገብሽ እርቄ አላውቅም። ስትሰክሪ ደግፌ፣ ስትናገሪኝ ችዬ ነው ኑሮዬ። ወደ ቤትሽ ተመለሺ!...”
«ቤትሽ? አምስት ሣንቲም ያላወጣሁበትን ቤት ቤትሽ አትበለኝ። ለእራሴ እራሴ አላንስም»
«የኔ ማለት የአንቺ ከሆነ ቆይቷል...»
«ተዋ!»
እንደ ዋሻ ሲሆንላት አየሁ። እሳት ስትሆን ውኃ ሆኖ ለማቀዝቀዝ ይሞክራል። እንደ ካንጋሮም በሆዱ ሊደብቃት ይመኛል። የምትጥልበት መጥፎ ቃል ደንታው አይመስልም። ከአለፍ አለፍ የሚገልጣት ሸራፋው የደስ ደስ አላት። እርሷን ብሎ ከሕይወት መስመር መውጣቱ ገብቶታል። እሷን ብሎ ይኼን ሕይወት በማየቱ ደግሞ ሲያማርር አይታይም።
የቢራ ቀጂውን ሚና ወደድኩት። እየቀዳ ቁጣዋን ያብሳል። ሌላዎች ጋርም እንባቸውን ፣ፍቅራቸውን ኃይል ይሰጣል_ወንዋና!
ጯ! የሚል ድምፅ ... ጥፊ ነው። የሕሉ እጅ የሄኖክን ፊት ለሰነ።
ዝም ብላ ስታየው ደሟ ፈላ። ልሙት ልቀበርልሽ ቢላት ባሰባት። አፈንጋጭነቷን ሊከረክመው ሲታገል በሸቀች፤ ደረገመችው።
«ጨክነሽ መታሽኝ?»
«እደግምሃለሁ ከፈለግክ!»
እናትና ልጅ እንጅ ባልና ሚስት አልመስልህ አሉኝ። ዳግም አቀረቀረ። ጸጥታው እንባ ሰጠው። አከታትሎ ወደ መሬት አፈሰሳቸው። የተደፋ ውኃ እስኪመስል ድረስ በእርሱ በኩል እንባ ታቁሯል። ቀና ብሎ ሊያያት አልፈለገም። ጠብደል ክንዱን ተንተርሶ በደንብ አቀረቀረ፡፡ የእሷም ፊት ተቀያየረ። እጇ ለጥፊ ሲቅለበለብ አየሁት። ወደ እኔ ለመዞር ሲቃጣት ተመለከትኩ። እስካሁን የያዝኩትን ለሚስቴ አወራለሁ ብዬ ሾልኬ ወጣሁ።Read 609 times