Saturday, 21 January 2023 20:34

ሰዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን ምን ይዞ መጣ?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንጋፋው ሰዓሊና ቀራፂ በቀለ መኮንን፣ ሦስት የሥነጥበብ አውደ ርዕዮችን በአራት ቀን ልዩነት ለተመልካች ሊያቀርብ መሆኑን ለአዲስ አድማስ አስታወቀ፡፡
ሰዓሊው እንደገለጸው፤   “ጤፍና ነጻነት - (GLUTEEN FREE-DOM”) በሚል ርዕስ አዳዲስ የሥነጥበብ ሥራዎቹን አውደ ርዕይ፣ አትላስ ሆቴል ተሻግሮ ወደ አውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በሚወስደው መንገድ መጀመሪያ ላይ  በሚገኘው፣  ዘ ፕሌስ ህንጻ  አንደኛ ፎቅ፣ በኢትዮ  ሜትሮ ጋለሪ አማካይነት  ለተመልካች ያቀርባል፡፡
በተመሣሣይ  ምሽትና ጋለሪ  “መንገዴን በጨረፍታ” (the glimpse of my journey) በሚል ርዕስ በ30 ዓመታት ውስጥ ከሰራቸው ሥራዎቹ የተሰባሰበ ተጨማሪ አውደ ርዕይ ይቀርባል:: ሁለቱም  ከነገ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም ጠዋት  ጀምሮ ለሕዝብ ክፍት ሆነው  ይቆያሉ   ተብሏል፡፡
ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ሦስተኛው የሥነጥበብ አውደ ርዕይ ደግሞ በአራተኛው ቀን ማክሰኞ ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 “የአዘቦት ልሳን” (casual dialog) በሚል ርዕስ በብሔራዊ ሙዚየም ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን  ሰዓሊው ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡ ሦስቱም አውደ ርዕዮች በኢትዮ ሜትሮ ጋለሪ አማካይነት የሚቀርቡ መሆናቸውንም አክሎ ጠቁሟል፡፡
በቀለ መኮንን (ፕሮፌሰር) በቅርቡ የሚከፈቱትን አውደርዕዮች በተመለከተ በሰጠው አስተያየት፤ ”ሦስት አውደ ርዕዮች ባንድ ጊዜ አስቦ ፈጥሮና ሰርቶ ማቅረብ ቀርቶ በቅጡ መኖር መቻል ብቻውን አርት በሆነበት ወቅትና አገር፣ የሚያስከፍለውን የበዛ  መስዋዕትነት  መገመት አያዳግትም፡፡
ሆኖም በምንም ዓይነት ኪሳራ መልካም  ነገር ጮክ ብሎ ደምቆ የሰዎች መነጋገሪያ መሆን ከቻለ እሱ በሕይወት ትልቁ ክፍያ ነው፡፡ “ ብሏል፡፡
በድንቅ ግጥሞቹም ጭምር የሚታወቀው ሰዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣና በሌሎችም በርካታ በሳልና ሸንቋጭ መጣጥፎችን ለዓመታት  ሲያቀርብ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡


Read 3560 times