Saturday, 21 January 2023 20:42

የተስፋ ቅኝት፤ ‹‹አፍላ ገጾች››

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ዘውግ፡- ሥነ-ግጥም
                         ገጣሚ፡- ዮናስ መስፍን
                         የኅትመት ዘ መን፡- 2 015 ዓ .ም.
                         የመጽሐፍ ዓይነት፡- E-book, Afro Read
                         ሒሳዊ ዳሰሳ፡- ዮናስ ታምሩ ገብሬ         1. መነሻ
ሥነ-ግጥም ውኃ ቢሆን በሊትር ወይም በሚሊ ሊትር ተለክቶ/ተሰፍሮ ይኼ ነው የሚባል ብያኔ ያገኝ ነበር። ሥነ-ግጥምን ማንበብም ሆነ መግጠም ከተመንና ከሕግጋት ያልፋል፤ ቋንቋ፣ ጭብጥ፣ ሥነ-ውበት፣ ፍካሬ፣ ሙዚቃዊነት፣ ስዕላዊነት፣ ምት፣ ምጣኔ… ጂኒ-ቋልቋል ሥነ-ግጥምን ለመግለጽም ሆነ ለመስፈር በቂ አይመስሉኝም፤ ወይም ሁነኛ መለኪያ የወጣለት አይመስለኝም፡፡ ሥነ-ግጥም፤ ከእነዚህ መሥፈርቶች እንዲዘል እሙን ነው…
…በአገራችን ‹ጥሩ›፣ ‹ዓይነተኛ› ወይም ‹ሸጋ› የሚባል ሥነ-ግጥም ድንበሩ አልለየለትም። የአገራችን ታላላቅ ገጣሚያን ‹ውበት-ዘመም› እና ‹ሀሳብ-ዘመም› ተብለው በሁለት ጎራ ቢመደቡ መልካም ነው፤ የመጀመሪያዎቹ፣ ‹ውበት-ዘመሞቹ› በሥነ-ግጥሞቻቸው የውበት ልክፍተኞች እንደሆኑ ያስተጋባሉ፤ በሥነ-ግጥሞቻቸው ብርሃንና ጽጌያትን፣ ጨረቃና ጸሐይን፣ አንጡባርና አልባብን…ወዘተ. ከእውኑ ዓለም ጋር በመፈከር ይሰናኛሉ፤ የዚህ ምድብ ቀንደኛ ተጠቃሽ ደበበ ሠይፉ ይመስለኛል፤ ገብረክርስቶስ ደስታ ጭምር፤ ግና በግጥሞቻቸው ሌጣ ውበት ላይ ብቻ ሳይሆን ሀሳብ/ጭብጥ ላይም ያተኩራሉ። ‹ሀሳብ-ዘመሞቹ› በበኩላቸው በጭብጥ መራሽ ሥነ-ግጥም የተለከፉ ናቸው፤ ለዚህ ደግሞ ዮሐንስ አድማሱ እና ዮፍታሔ ንጉሴን ማንሳት ይቻላል። የግጥም ሀሳባቸው ለበቅ ነው፤ ዳግማይ ልብ መባል ያለበት ነገር በሁለቱም ጎራ የውበትና የሀሳብ ልክፍት በጉልህ መኖሩ ነው።
ሥነ-ግጥምን አውራና ብሉይ የሚያሰኙት አላባዊያኑ ብቻ አይደሉም፤ ነፍሲያን የማናወጽ አንድምታውም ነው፤ እንደ ተዐምር ዓይነት፣ ሽባ የመተርተር ከኀሊነት ቢባል መልካም ነው። ገጣሚ የዓለምን ስብጥርጥር ሃቂቃ ከእራስ ተሞክሮ ጋር አዋዶ ይትነፍሳል፤ በሥነ-ውበት እየታገዘ የተለያዩ ጉዳዮችን ይፈክራል፤ መፈከር በፈሊጣዊው ቋንቋ እየታገዙ እውነታንና ልምድን በምሳሌ ማቅረብ ነው፤ ሥነ-ግጥም ከዚህም እንዲልቅ እሙን ነው…         
…አሁኔ ‹‹አፍላ ገጾች›› የተሰኘ የሥነ-ግጥም መድበል ነው። የመጽሐፉ ዓይነት E-book ሲሆን፣ ዘጠና የሚደርሱ ሥነ-ግጥሞችን በውስጡ አቅፏል። ገጣሚ ዮናስ መስፍን በዚህ መድበል ብርሃን አሳባቂ ሀሳቦችን በውብ ቋንቋ እያሸገነ ተሰናኝቷል፤ በአብዛኛው የመድበሉ ሀሳብ የተስፋ ቅኝት ነው፤ ሌሎች ገጸ-በረከቶችንም አጭቋል መድበሉ፡፡
ድኅረ-ዘመናዊ የሥነ-ጽሑፍ ኅልዮትን/ትወራን ተንተርሼ የ‹‹አፍላ ገጾች››ን ሙክርታዊ አበክሮዎች ስመረምር እንዲህ ሆነ…
2. ሥም/ርዕስ
ገጣሚ ርዕስና ሥምን ያማከለ ሀሳቡን በግጥም ገላ ውስጥ ሊያሰርጽ ይችላል፤ ርዕስና ሥም ቀዳማይ ስንኝ ደግሞ ተከታይ የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፤ ሃቲት ከርዕስ ከተቃረነ የትርጉም መዛባት ይከተላል፤ ርዕስ ደግሞ ሃቲቱን መወከል መቻል አለበት። ዮናስ መስፍን ርዕሳቸውን ማዕከል ያደረጉ ግጥሞችን ለንባብ አብቅቷል ብዬ አስባለሁ።
3. ውበት (Beautiful Lines)
ገጣሚ በቃላት አጠቃቀሙ፣ በገላጭ ቃላትና ሐረጋት መረጣውና በዘይቤአዊነቱ ውበታም ስንኞችን ሊሰናኝ ይችላል። ገጣሚ ዮናስ መስፍን ውበታም ስንኞችንና ገላጭ ሐረጋትን በአብዛኛዎቹ ግጥሞች በመሰግሰግ የግጥም ሀሳቡን ውብ አድርጎ አቅርቧል ብዬ አምናለሁ። ለመተማመን እንዲበጀን ማሳያ እያጣቀስኩ ላውጋ፡- ‹‹ንጋት›› በተሰኘ ግጥም ‹‹የጸሐይ ማሾ ፍካሬ››፤ ‹‹አቅም›› በሚል ግጥም ‹‹እጄ ያለመጠኑ ከሰማይ ዳስ ደርሶ ጉም ሲዘግን አሳየኝ፤››፤ በ‹‹ፍቅርን በአበባአየሁ›› ግጥም ‹‹የልቤ ቄጠማ ላንቺ ተጎዝጉዞ ከቶ አለመድረቁ››፤ ከ‹‹ባለጠግነት›› ውስጥ ‹‹የዛሬው ሰው ለጋ የእድሜ ባለጠጋ››፤ ከ‹‹እንቆቅልሽ›› ግጥም ‹‹ከበድኖች መሀል በወጣ አንድ ቅሪት አንዲት ነፍስ ማዳኑ››፤ ‹‹ናፍቆት›› ከተሰኘ ግጥም ‹‹ናፍቆትሽን ወስዶ ጊዜን ከኔ የሚያስቀር››፤ ‹‹አዋቂ›› በሚል ርዕስ ‹‹የሀሳብ ፀሐይ መውጫ››፤ በ‹‹አጥንቴን መልሺ››  ስር ‹‹እስከ ዳግም ሔዋን አጥንቴን መልሺ››፤ ከ‹‹አንድ ብር›› ግጥም ገላ ‹‹በያኔው ዘመንህ በአዲሱ ገንዘብህ እስቲ አሁንን ግዛ›› ‹‹ጤዛ›› ከሚል ግጥም ደግሞ ‹‹ጠዋቱስ ፍካት ነው ለነፍሴ ያደረ››… እና ሌሎች በውበታቸው የሚማርኩ ሐረጋትንና ስኝኞችን መጥቀስ ይቻላል።  
4. ፍካሬ
ለድኅረ-ዘመናዊነት/post-modernism ገለታ ይግባውና አንድ እውነታ ብቻ ስለሌለ፣ ገጣሚ በቋንቋ ተራዳኢነት ሀሳብ ይመረምራል፤ ሀሳብ አይዘግብም/አይናገርም። ፍካሬ፣ ወይም መፈከር ማለት ሕይወትን መተርጎም ማለት ነው፤ ገጣሚ ሀሳቡን አይዘግብም፤ የዓለምን እውነታ አዟዙሮ ይፈክራል/ይተረጉማል እንጂ፤ ይኼንን ሀሳብ ለማጦንቸት እንዲህ ልበል፡- ፈሊጣዊ-ንግግርን፣ ሥነ-ቃልን፣ አፈ-ታሪክን፣ ተረት-ተረትን፣ ድርሳነ-ደብተራን እንደ ግብዐት ተጠቅሞ ወደ ተነሱበት ሀሳብ መሰግሰግ ነው መፈከር ማለት፤ የዚህ ፋይዳ ሕይወትን በሥነ-ውበት መፈከር ነው፤ ሥነ-ግጥምና ሥነ-ውበት የተቆራኙ እንደመሆናቸው መጠን ፍካሬያዊ አንደበት ጭብጥ ያጎላል፤ እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ነገር አንድ ገጣሚ ሕይወትን ለመፈከር ሲተልም (ተልሞም ግብዐት ሲወሰውስ) ከተነሳበት ሀሳብ ጋር የሚጋጭ አለመሆኑን ልብ ማለት አለበት፤ ይኼ ጣጣ ምናልባት ‹ግጥም እየገጠምኩ ነው› ብሎ የሚነሳ ሰው ሊያጋጥመው ይችላል ብዬ እሰጋለሁ፤ እውነታው ‹ግጥም እገጥማለሁ› ብሎ ብዕር የሚጨብጥ ግለሰብ ከተነሳበት ዐውድ፣ ሀሳብ/ ጭብጥ የማይጣጣም ትርጉም ያለው ፍካሬያዊ ቃል፣ ሐረግና ስንኝ ሊያካትት ስለሚችል ነው።
ዮናስ መስፍን በ‹‹የአፍላ ገጾች›› ሥነ-ውበትንና ሥነ-ግጥምን በመጠኑም ቢሆን ፈክሯል ብዬ አምናለሁ። ለዚህ ማሳያ ‹‹አዋቂ›› ከሚል ግጥም ውስጥ ‹‹የሀሳብ ፀሐይ መውጫ›› የሚለውን ሐረግ መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፤ ገጣሚው የሀሳብ/የመፍትሔ አቅጣጫ ስለ ጠፋበት ገጸ-ባሕሪይ/ባለድምጽ ያትታል፡፡ በዚህ ግጥሙ፤ አስከትሎ የብርሃንና የተስፋ ምልክት ተደርጋ የምትወሰደዋን ፀሐይንና የፀሐይ መውጫን/አቅጣጫን በተምሳሌትነት በመጠቀም ሀሳቡን ያትታል። ብሎም ባለድምጹ ሁነኛውን ዘዴ ባለመምረጡ የተነሳ ጣጣ ውስጥ ሲገባ እናስተውላለን፤ ይኼ ሙከራ ተሳክቷል ብዬ አምናለሁ። ከዚህ በተጨማሪ በ‹‹አጥንቴን መልሺ›› የግጥም ገላ ውስጥ ‹‹እስከ ዳግም ሔዋን አጥንቴን መልሺ›› የሚለውን ስንኝ መመልከት እንችላለን፤ ዳግም ምጽዐት እንጂ ዳግም ሔዋን አይታወቅም፤ ገጣሚው ‹‹ዳግም ምጽዐት›› የሚለውን ሐረግ ወደ ራሱ ጠምዝዞ ተገልግሏል። ገጣሚው የሚነግረን በአፍቃሪው ስለተከዳ ባተሌ ታሪክ ነው፤ ጉዳቱ ስለሰፋ ምንም ነገር እንዲቀር ስላልፈለገ የተፈጠረችበትን የጎኑን አጥንት እንድትመልስለት ቀጠሮ ይዞ ይሞግታል ታዲያ። ሁነኛ ሙከራ ነው።
ከላይ የተጠቀሱ ነጥቦች እንደ አንድ ሙከራ የሚደነቁ ቢሆንም ገጣሚው በቀጣይ ሥራዎቹ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ እሻለሁ!          
5. የተስፋ ቅኝት
‹‹ግጥም እምባ ይፈልጋል›› ይላል ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ)። እውነት አለው፤ አዛኝ፣ ተቆጭ፣ ሒስ ወሳጅ መሆን አለበት ገጣሚ ብዬ አምናለሁ። ከዚህ ሻገር ሲል የተስፋ ፋና ወጊ መሆን አለበት፤ አዛኝ ሰው ስለ ተስፋ አይሰብክም ማለቴ እንዳይደለ መዝግቡት! ሥነ-ግጥም ብርሃንን፣ ተስፋን አዲስ ንጋትንም መስበክ አለበት ባይ ነኝ፤ ገጣሚ የብርሃንን፣ የትጋትን፣ አሉታዊ መልክ ማንጸባረቅ አለበት፤ ገጣሚ ማስረጽ/Canonization የቤት ሥራው ነው።
‹‹አፍላ ገጾች›› በአብዛኛው ተስፋ የሚዘሩ የሥነ-ግጥም ሀሳቦችን ሰባስባለች ብዬ አምናለሁ። ለዚህም ማሳያ ‹‹ፍጻሜ አልባ ጅምር›› እና ‹‹ጤዛ›› የሚሉ ግጥሞችን ማንሳት እንችላለን።  
6. ለበቅነት
ሥነ-ግጥም በሀሳብም በቋንቋ/በቃላት አጣጣልም የጎመራ መሆን አለበት፤ ጥበቅትና ፍላት በጥብቅ ይገደዋል። ተራ ጉዳይ ላይ መዘባዘብ የለትም ገጣሚ፤ ከዚህ በተቃራኒ ገጣሚ ሀሳቡን ለማግዘፍ በመተለም ችኮ መሆንም አይጠበቅበትም፤ ከራራ አሰነኛኘት ሥነ-ውበትን ገደል ሊከተው ይችላል፤ በሥነ-ግጥም ውስጥ የሥነ-ውበትና የዓለም እውነት የማይነጣጠሉ ስለሆኑ። የዮናስ መድበል እንደተንደረከከ ፍም የሚፋጁ ሀሳቦችን አቅፏል፤ ሁነኛ ምሳሌ ‹‹ቀጣይ ክፍል›› እና ‹‹የአፈር ምስል›› የተባሉ ግጥሞች ናቸው። ዳሩ በአብዛኞቹ ግጥሞች ሀሳብን ለማጉላት ሲል ከሥነ-ውበት ሸርተት ብሏል የሚል ሥጋት አለኝ፤ ‹‹ቢያስተምሩት ኖሮ›› እና ‹‹ጀግና ማነው?›› የሚሉ ግጥሞች እማኝ ናቸው። በሌላ ጊዜ እንደሚያሻሽል ተስፋ ይዤአለሁ።  
7. ድንቃይ አጨራረስ
ድንቃይ አጨራረስ/Surprise ending ራሱን የቻለ የአሰነኛኘት ይትባሃል ነው። ይኼ ነጥብ በአብዛኛው የግጥም ሀሳብ አዘጋግን ይመለከታል፤ ገጣሚ ከርዕሱ ተነስቶ ሀሳቡን የሚያትትበትን መንገድ በቤት መዝጊያው ላይ ባልተጠበቀ መልኩ ሊቀለብሰው ይችላል፤ ወይም ከተጠበቀው በተቃራኒ መልኩ ሊደመድም ይችላል። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ሙከራ ለመራቀቅ ፍጆታ ሳይሆን የሕይወትን ምሰላ ለማመላከት ቢውል መልካም ነው ባይ ነኝ። በዚህ ሀሳብ በመታገዝ የ‹‹አፍላ ገጾች›› ገጣሚ የዓለምን እውነታና የግሉን ምሰላ በበጎ መልኩ አመላክቷል፤ ለአብነት ያህል ‹‹መከራ ይምከረው›› እና ‹‹ጠመኔ›› በሚል ርዕስ የተነሱ ሀሳቦችን መጥቀስ ይቻላል። ‹‹ናፍቆት››፤ በሚል ግጥም ስር ‹‹ናፍቆትሽን ወስዶ ጊዜን ከኔ የሚያስቀር›› በማለት ጊዜን ይሞግታል። አሁንም ይኼ ሙከራ ለወደፊት እንዲሻሻል መጠቆም እፈልጋለሁ!
8. ድግምግሞሻዊና ገለጻዎች
ከ‹‹የሚናገርለት›› ግጥም ስር፡- ‹‹አብጠርጥሮ የሚያውቅ››፤ በ‹‹ፍቱልኝ አልልም›› ግጥም ‹‹ከርታታው ልብ››፣ በ‹‹እድሜ ማራዘሚያ›› ግጥም ‹‹አንተዬ›› … እና ሌሎችም አሰልቺ መስለውኛል። ዮናስ የገጣሚ መብቱን/Poetic-license ተጠቅሞ ውበታም ቃላትንና ሐረጋትን ተጠቅሞ መሰናኘት ነበረበት።   
9. በተሃ ግጥሞች
በተሃ ማለት ያልተብላላ፣ የደነበሸ፣ ያልጎመራ…ወዘተ. ማለት ነው። ሥነ-ግጥም በተራ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የሚባክንና የደነበሸ መሆን የለበትም። በግጥም የሚነሳ ሀሳብ ለሚዛን የቀለለ መሆን የለበትም፤ በተሃ ግጥም ከገጣሚው የመፈከር አቅም ማነስ የተነሳ ሊወለድ ይችላል።   
የሚከተሉ ግጥሞች በተሃ ናቸው ብዬ አምናለሁ፤ ‹‹የሚናገርለት››፣ ‹‹ጀግና ማነው››፣ ‹‹ምን ኖረው ለጠቢብ›› እና ሌሎችም።
10. ተቀራራቢ ቃላት/የቃላት ድረታ
ይኼ መደብ በአንድ ግጥም ገላ ውስጥ ተደጋግመው የተነሱ ተቀራራቢ ቃላትን ይመለከታል። በአንድ ግጥም ውስጥ ተመሳሳይ ቃላትን መደጋገም በንባብ ወቅት መታከትን ሊያስከትል ይችላል። መሰልቸትንና መታከትን ሊያስከትሉ ይችላሉ፤ በዚህ መድበል በአንድ ግጥም ውስጥ ተደጋግመው የተነሱ ተቀራራቢ ቃላትን እንመልከት…
‹‹ውዳሴ ለፍቅርሽ›› ከተሰኘ ግጥም ‹‹የሀሳብሽ›› - ‹‹ሀሳቡ››፤ በ‹‹ልዩነት›› ግጥም ውስጥ፡- ‹‹መንጋ›› - ‹‹መንጋውን›› - ‹‹ከመንጋው››፣ ‹‹ሀሳብ›› - ‹‹ሀሳቡን›› እና ሌሎችም።   
11. ስልተ-ምት
ይኼ ነጥብ የሚያተኩረው አንድ ገጣሚ በሥነ-ግጥም ውስጥ የሚፈጥረውን የዜማ ቀለምና ድምጸትን ነው። ዮናስ ለእራሱ ባመቸና በተመጠነ መልኩ በበርካታ ቀለምና ድምጾች የተንቆጠቆጡ ስልተ-ምቶችን ፈጥሯል። ይኼ ሙከራ በግጥሞቹ ገላ ላይ ሙዚቃዊነት የሚዳዳው ዜማ እንዲፈጠር ረድቶቷል የሚል እምነት አለኝ። ለምሳሌ፡-
‹‹ጠወለገ አትበል
ያ ያሸተ ቅጠል›› - ከ‹‹የታነጸበቱ›› ግጥም ገላ ውስጥ፤
አልፎ-አልፎ የተከሰቱ የቸኩ ስልተ-ምቶችንም መጥቀስ ይቻላል….
‹‹የዘመን ሽሚያ›› ከሚል ግጥም፡-
‹‹ካንቺ የልጅ ነፍስያ ከንጹህ ቅን ልብሽ
ጋራ ውሎ ገጥሞ
እርሱ አንቺን ሊመስል ወደ ዘመንሽ ጫፍ
ሲጎተት በአርምሞ›› እና ከ‹‹ልቤ›› ግጥም መካከል፡-
‹‹ያለ አቅሙ ተችሮት አድናቆት ሙገሳን
ባይጠግብ እንኳን ሰምቶ
መሸሸግ መረጠ ጫንቃው መቻል ከብዶት
ውዳሴውን ፈርቶ››
የሚሉትን ማንሳት ይቻላል።
12. መደምደሚያ
ዮናስ መስፍን ‹‹አፍላ ገጾች›› በተባለ መጽሐፉ ፈርጀ-ብዙ ሙከራዎችን ሊያሳየን ሞክሯል፤ በአብዛኛዎቹ ግጥሞች የዚህችን ዓለም ስብጥርጥር ሃቂቃ ከሥነ-ውበት ጋር በማናበብ ለመሰናኘት መጣሩ የሚበረታታ ነው። በተለያዩ መዘርዝሮችና ነጥቦች ስር የተነሱ ሀሳቦች ለቀጣይ ሥራዎቹ ግብዐት ይሆኑታል የሚል እምነት አለኝ።


Read 1014 times