Saturday, 21 January 2023 20:42

“ቀይ ፍርፍር”

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(0 votes)

ማዕበሉ  ሲበረታ፣ የተስፋዬ ግት ሲነጥፍ ... ዓለም ነውሯ ስታደርገኝ ፣ የሰዎች አይን በመጠየፍ ሲቃኘኝ  ፣ የጭንቅ ውሽንፍር ሲበዛ የተጠጋሁት የልቧን እድሞ  ነበር።   ኦና  በኣት ውስጥ በሃ ተንተርሼ ብቻዬን  ስትከዝ ያየሁት ብርሃናዊ ነፍስ እሷን  ብቻ  ነበር።
ዝንጋኤ ያጠላበት ዓይኗ እኔን አይቶ ሳስቷል። ባይተዋር አካሏ የጎኔን ሙቀት ሲናፍቅ ርሔ ጠረኔ አጓጉቶ አልነበረም።
አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ናቸው። ዓለም ላንተ  ድንቁራ በታወረችበት ምድረ በዳ ህይወት ውስጥ የህመምህን ዜማ መስማት የሚችል ተዓምረኛ ልብ አላቸው።
ጠዋይ ነፍሴን  ያቀናች፣ ከበረሃ ልቤ የፍቅር ምንጭ ያፈለቀች ማን ነች?  እሷ አይደለችምን!
ነፍሷ የፍቅር ደሴት ነበር።
ትላንትን ማስታወስ ያልቻለ ዛሬ፣ ለነገ ተስፋ እውር ነው።
ከዛሬው ወዝ ከሞላው ግንባሬ ፣ ከዛሬው  ምቾት ካጎላው አካሌ፣ ከዛሬ የደስታዬ ቀለም በላይ  የትላንቱ ጉስቁልና፣ የትላንቱ መቆሸሽ፣ የትላንቱ ስቃይ ውድ ነው ለእኔ!
የውድ ነገሮች  መቀመጫ  እርካሽ ሙዳይ እንደሆነ የገባኝ ዘግይቶ ነበር።
የጥጋብ ቅኝት ዜማ  ከረሃብ ፀሊም ሙሾ አይበልጥም።  አንዳንዴ የሃብት ማማ ከድህነት ንጣት በታች ዝቅ ይላል።  ሃቀኛ ወዳጅ ብቸኝነት በሚሰማን ሰዓት ወደ ልባችን የፍቅር ጥይት የሚተኩስ ወታደር ነው።
 እና ለትላንት  ነጋ!
 የብርሃን ዘሃዎች  በላስቲክ ቀዳዳ   በኩል የጨረር እግራቸውን ዘርግተዋል። ውብ ህልማቸውን፣ ልባም ተስፋቸውን አይቸሩም... የሰመመን  ክርታዝ የጋረደውን ዝምታ እያባበሉ ይጓዛሉ። ንፉግ ናቸው። ብርሃን የጨለማን ያህል ለህይወት ቸር አይደለም!
 ነጋ። ለሌላ ድካም፣ ለሌላ መባተል...ለሌላ ህመም፣ ለሌላ ፅልመት ነጋ!
ወጣሁ። የተንጨበረረ ፀጉሬ፣ እድፍ ያጠቆረው መልኬ... ጭርንቁስ ልብሴ የጋረደው የነፍሴን  ጮራ ብቻ አልነበረም... ያደፈ ስጋዬ የጋረደው ህልሜን  ጭምር ነበር።
ትላንት ቀን ሙሉ ስላልበላሁ እርቦኝ ምግብ ፈለጋ ወደ ቆሻሻ መጣያው ማተርኩ። ተጠጋሁት ... በፌስታል ውስጥ ያለ  እንጀራ ያየሁ መሰለኝ... ስከፍተው የተበላሸ ምግብ ነው። ቤት እስክደርስ አላስቻለኝም። እዛው ሆኜ  ወደ አፌ ልከተው ስል ለስላሳ እጅ፣ ቀይ...ቀጭን እረጅም ጣት ያዘኝ።
ዞርኩ!
“አንተ ጣለው ቆሻሻ  እኮ ነው”
ግራ ገባኝ!
እጄን አስለቅቄያት በዝምታ እንጀራውን ይዤ ሄድኩ!
“ቁርስ ልግዛልህ?”
ዞርኩ በድጋሚ!  ተጠጋዃት። ፊት ለፊታችን ያለ ሆቴል ገባን።
“አትፍራኝ ፤  ሰው እኮ ነኝ”
ዝም አልኩ።
ምግቡ ሲቀርብ በምን ፍጥነት ወደ አፌ እንደከተትኩት፣ በምን ፍጥነት እንደጨረስኩት አላውቅም። በፊት ቀይ ፍርፍር እወድ ነበር። በርበሬ የበዛበት  ቀይ ፍርፍር!  እናቴ ቀይ ፍርፍር መስራት ትወድ ነበር። እና ቀይ ፍርፍር ትዝታ ነው። ቀይ ፍርፍር እናቴን  ካጣሁ በዃላ በልቼ አላውቅም። ቀይ ፍርፍር ሲበሉ እንኳን ካየሁ አለቅስ ነበር። አሁን ግን ርሃቤ ትዝታዬን ፣ የእናቴን ትዕምርት ... የእምዬን  ጉርሻ... የጣሯን ዳና ሳይቀር አስረሳኝ።
“ይጨመር” አለችኝ
“አዎ” መልሴ ነበር....
ስንወጣ የተወሰኑ ብሮች አስጨበጠችኝ።
“ከቆሻሻ ላይ ምግብ አትብላ”
“እና ከየት ልብላ?”
“እኔ አለሁ እኮ... የት ነው የምትኖረው? እዚህ ሰፈር ነኝ አታውቀኝም እንዴ? አሁን ስራ ረፈደብኝ እሺ ማታ ስመጣ ... እ”
የላስቲክ ቤቴን ጠቆምኳትና ሄድኩ።
ስለያት ታምቆ የቆየው እንባዬ  ጉንጬ ላይ ተዘረገፈ። ቀይ ፍርፍር ትዝታ ነው ለእኔ ። የእናቴ ፍቅር፣ የእናቴ ጉርሻ ከቀይ ፍርፍር ጋር የተቁላላ የህይወቴ ቁሌት  ነበር።  ስታቅፈኝ የፍርፍር ቁሌት ትሸተኝ ነበር።
ምግብ ከቆሻሻ መጣያ እየለቀምኩ ስበላ፣ የዚህን ያህል ዝቅ ብዬ ፣ የዚህን ያህል አድፌ ስታይ በእናቴ እጅ ቀብጬ ያደኩ ፣ በእናቴ ከንፈሮች ተስሜ ያለፍኩ አልመስልም። የዚህን ያህል ከሰውነት  ጎድዬ፣ የዚህን ያህል ዘመንና ሰው ጠልቶኝ፣ የዚህን ያህል ብቸኛ ሆኜ  ስታይ በእናቴ ልብ ውስጥ ከክርስቶስ በላይ የተወደድኩ፣ በእናቴ እቅፍ ውስጥ ለሰዓታት በፍቅር ያንቀላፋሁ አልመስልም።
ሳያት ከሃሳቤ ተናጠብኩ። ፀሃይ ልትጠልቅ እንደ አይናፋር ልጃገረድ ስትግደረደር ለምንድነው የምትቀላው?  ... ብቻ አየዃት። እንደ ጀንበር የሚጠልቁ ወዳጆች ፣ እንደ ጀንበር የሚርቁ እውነቶች... ብቻ አየዃት! ቀይ ፍርፍር... ጉንጬ ላይ ያለው የእናቴ የከንፈር ወዝ በችግር እድፍ ደብዝዞ ይሆን? ትዝታዬ በስቃይ ጥይት እንዳይሞት... ብቻ ዓለም ንፁህ አትሆንም ያለ ትዝታ...
በሳህን የተቋጠረ ምግብ አቀበለችኝና ጎኔ ድንጋይ ላይ ተቀመጠች።
በለስላሳ ጠርሙስ ውስጥ የምጠጣውን አረቄ አየችው።
“ይጎዳሃል እኮ... “ ብላኝ ዝም አለች።
“እኛን  አረቄ ብቻ፣ ሰው ብቻ፣  ህይወት ብቻ አይመስልሽ የሚጎዳን መለኮትም እኛ ጋር ሲደርስ  ብርቱ ክንድ አለው”
“በእግዜር ታምናለህ?”
“ሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃ.... “
ደጋግማ ወደ  እኔ ስትመጣ ተረበሽኩ።
 ልብስ ይዛልኝ መጣች። ገላዬን መታጠብ ወደምችልበት ቦታ ይዛኝ ሄደች። በደጄ ስታልፍ የተቋጠረ ምግብ ይዛ  መምጣት ሰርክ ስራዋ ሆነ። ዓይኖቿ ሲሳሱልኝ እይዛቸዋለሁ። ሳይታወቃት አቅፋኝ፣ በነሲብ ስማኝ... ታፍራለች። ስታፍር የሚያምር ውበት ያጠላባታል። መሳቅ ፈልጋ ሳቋን ስትሸሽግ ዓይኗ ያሳብቅባታል።  የጎዳና ቤቴ ውስጥ ለደቂቃ ተቀምጣ ብትሄድ ጠረኗ ሌሊቱን ሙሉ አይጠፋም።
እና ተረበሽኩ።
ከንፈሬን ስትስመኝ ምን ተሰማኝ? እንጃ!
አፈቀርኩህ ስትለኝ ምን አልኳት? እንጃ!
ምትሃት ብቻ...ቀለማም ውበት...ዳር አልባ ብርሃን...
እንዴት ቆሻሻ መሃል የተገኘች  ጨለማ ነፍስ ትፈቀራለች?
እንጃ! ብቻ ሆነ!
ታምራለች አልኩ ለእራሴ። ዓይኗ ምትሃት አይነት ነው። ክርስቶስ አላዛርን ከሞት ያነቃው የዓይኗን ብርሃን ተጠቅሞ መሰለኝ። እና ሳልጠራጠር፣ ሳይገባኝ... ልቧን ተጠለልኩ። እና አንድ ቀን ፈንድቃ... ሳቋ ደምቆ መጣች...
“ስራ አገኘሁልህ” አለችኝ...
እና ባልጠበኩት ሁኔታ ውስጥ ነጋዴ ሆንኩ። እሷ ሁሉ ነገር ሸፍና... እና ገረመኝ! ከዚህ ህይወት ልታወጣኝ ስትጎትተኝ እኔ እዚሁ  ፅልመት ውስጥ እዳክር ነበር።
እሷ ግን  ምትሃት ናት።
በትንሽ ጊዜ ውስጥ ንግዱ ይደራ ጀመር። በቀን ወደ ኪሴ የሚገቡ ገንዘቦች እየበዙ መጡ። መዝናናት ጀመርኩ። ጓደኞች አፈራሁ።
አመታት የስኬት ድል ነበሩ። ጎበዝ ሰራተኛ ሆንኩ። ከብዙ ዓመታት በዃላ ቤት ተከራይቼ አልጋ ላይ ስተኛ የተሰማኝ ደስታ አይደለም። የተሰማኝ እረፍት አይደለም። የተሰማኝ ድንግርግር ቁጭት፣ ግትልትል ጨለማ ነው።
 የተፀየፉኝ ሰዎች እኔን ፈልገው መጡ... ቆሻሻ ለቅሜ ስበላ ተፍተው ያልፉ የነበሩ ሰዎች ወደ ደጄ ጎረፉ። ከሞተ ሰው በታች ያዩኝ ሰዎች ከሰው በላይ መሆኔን መሰከሩ።
ዘመናት ተጓዙ!
ደግሞ ሌላ ፅልመት .
ደግሞ ሌላ ህመም...
የመለያየታችንን ጉድባ፣ በመሃላችን የገባውን ጥላ፣ የተጓዝንበትን መንታ መንገድ ልብ አላልኩም። መቼ ታዝንብኝ፣ መቼ ትታዘበኝ እንደጀመረች አላውቅም። ብቻ ጊዜዬን እንኳን ስነፍጋት እራሴን ያዝኩት። ብቻ የሚናፍቀኝ አይኗን ስሸሽ እራሴን ታዘብኩት። ብቻ... ምን ተፈጠረ...?!
እንደ  አይን ጥቅሻ ሁሉም ነገር ፈጣን ነበሩ።
አንድ ቀን ጠቋቁራ ሱቄ መጣች።
“ብዙ አትጨነቅ እሺ።” አለችኝ...
“ማለት ?”
“ማለት ካስጠላሁህ፣ ከደበርኩህ.. ማለቴ ገባህ? ካልፈለከኝ ብዙ አትፀፀት .... እየተነጣጠልን ይመስለኛል። እየራቅከኝ ነው። ፍቅርህ  ሳያልቅ አይቀርም። ከሳምከኝ መንፈቅ ማለፉን ቆጥሬያለሁ እኮ። በሙሉ አይንህ ካየኸኝ ስንት ጊዜ ሆነ? ...ማለት ደስተኛ መሆንህ ይበቃኛል። አትጨነቅ እሺ።”
ዝም አልኩ!
ግን ትንሽ አስመሰልኩ። አቀፍኳት... ድንገት ከእቅፌ ወጥታ፤
“አልገባህም! እንደምትወደኝ ማስመሰል የለብህም ። እንደምትጨነቅልኝ ምናምን.... በቃ እኮ አልቋል”
ጉንጬን ሳመችኝ....
እጇን ደረቴ ላይ አሳረፈች።
ቆሻሻ መሃል  የተበላሸ  ምግብ  ልጎርስ ስል እጄን ይዞ ንፁህ ፍርፍር ያጎረሰኝ ይሄ እጇ ነው - ዛሬ ግን ጦር እንደ ጨበጠ የጠላት እጅ በጥርጣሬ ነው የማየው። እድፌን ሳይፀየፍ እቅፌ ውስጥ የገባው ይሄ የቆመ አካሏ ነበር - ዛሬ  ግን ጊዜና ድሌን  ተከልዬ እራቅሁት።
ከሱቄ ስትወጣ አየዃት። አዝናለች። ተሸንፋለች። ክንፎቿን ያጣች ምስኪን ወፍ መስላለች።
ወደ መጠጥ ቤት ነጎድኩ። ሰከርኩ።
ጊዜዬን ከከበቡኝ ሰዎች ጋር ጨረስኩ። እሷ  ግን ከዚያ ቀን በዃላ ጠፋች።
ከወራት በዃላ ቤቷ ሄድኩ። በስም ብቻ የሚያውቁኝ እናቷ፣ እንደ ልጃቸው አቅፈው  እንዲህ አሉኝ...
“ጣልያን ገባች... ትታኝ። ደስታ ርቋት ነበር። ታክታ ነበር። ድካሟን እታዘባለሁ። ግን ልሂድ አለች።  በተወለዱበት አገር ባይተዋር ከመሆን ከባዕድ መዛመድ ይሻላል አለች። ተፈላሰፈች አዪዪዪ-- ልጄዋ”
አድራሻዋን ተቀብዬ ወጣሁ። ግን ዝምታን ደርቤ ከመክረም ውጪ ምንም ላደርግ፣ ደብዳቤ እንኳን ልፅፍ አልከጀልኩም።
በመልካም ስራዋ አልተገበዘችም። በመጥ ፎ ቃላት ትላንቴን ማስታወስ አላስፈለጋትም። ለዚህ ያበቃችኝ እሷ ስለመሆኗ እየዞረች ለዓለም አላወራችም። እረከቦት መሃል፣ ቡና ላይ “ጠላኝ” ብላ አላማችኝም። ሲደላደል እራቀ እያለች ለሰው አፍ አልሰጠችኝም። እኔን  ለህሊናዬ ብቻ ትታ እራቀች። ፍርዱን ለእራሴ.... ትታ ሄደች።
እራቀች....
ሄደች....


Read 224 times