Sunday, 22 January 2023 00:00

የስብሐት ሌላኛው መልኮች (በሁለት ስብስቦች)

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(0 votes)

 “…አቤት እቺ ዘኔ ሰው ስትወድ! የፍቅር አድባር ትመስላለች እኛ ስናያት፡፡ ከሷ ጋር ግማሽ ቀን ማሳለፍ ግማሽ አመት የመኖር ያህል ደስ ይላል፡፡ የከበቡዋት ሁሉ ደግሞ እንደሚወዷት በአይናቸው በገፅታቸው ይነበባል፡፡ ሁሉ ነገሯ ደስ ይላል፡፡ ግልፅ፣ ቀና፣ ተጫዋችና ግጥም አዋቂ ናት፡፡…”
        
        መቼም እሱን የማያውቅ የለም፡፡ ያለን ምስልና የምናውቅበት መንገድ የተለያየ ነው እንጂ!  የልቦለድ  ስራዎቹን አንብበን ይሆናል!...ለተረት የቀረበ ግላዊ ህይወቱን፣….ደግሞም ሥራዎቹ ላይ ተንተርሰው በተለያዩ ደራሲያን የተሰነዱለትንም እንዲሁ አልቀረንም፡፡ የእግረ መንገድ አምድ ወጎቹ ስብስብ (ሁለት ቅፆች) ጥራዝ፣ ዛዚ... ትርጉሙንም ጨምሮ አጣጥመንለታል፡፡ በዚህ መነሻነት ሰውዬውን አውቀዋለሁ ካልን ግን ተሳስተናል፡፡ ከሞላ ጎደል ተገንዝበነዋል  ልንልም አንችልም፡፡ ከፊል ስዕሉ ይኖረናል ማለትም አይደለም፡፡ ስብሀት አይጠረጠርም፡፡ እልፍ መልኮች አሉት፡፡ በስንዝር ሲመረምሩት በማይል እሚዘረጋ…በርዳን እየወጣለት በኪሎ እሚሰፈር፡፡ ከአራቱም አቅጣጫ በተባዘተ ቁጥር እንደ አዲስ እሚፈተልና-እሚፍተለተል ደራሲ ነው፡፡ (ህይወቱም ስራዎቹም!)
እንኳን ፊደል ለይተንና ለአቅመ ንባብ ደርሰን ይቅርና ለመወለድ ባልታሰብንበት ዘመን ላይ የፃፋቸው ስራዎቹ ሲገጥሙን እንኳን… ስብሀት ግን ስንት ነው? ብለናል፡፡ ሌላውን ትተን አብሮት እየዋለ የግል ህይወቱንና ትዝታዎቹን የከተበው ዘነበ ወላ “ማስታወሻ” ድርሳኑን ደራሲው ለህልፈት መብቃቱን ተከትሎ ዳግመኛ የህትመት ብርሃን ባየበት ሰሞን የማናውቃቸውን አዳዲስ ታሪኮችን አካቶ ኖሮ አንብበን ጉድ ብለናል፡፡ እሱ እንዲህ ነው….አይነት-ብዙ የሆነ ዛሬም ወደ ኋላ ብናማትር ደርሰን የማንቋጨውና እማንደመድመው አለላ፣ የህይወትና የሥነ-ጽሁፍ ክህሎት የተቸረው ደራሲ ነበር፡፡ እንኳን ሊረሳ ላፍታ እሚዘነጋ አይደለም፡፡ ሆነ ብለን በወሲባዊ ጉዳዮች ላይ በነበረው ያፈነገጠ ግላዊ አቋሙ ሳቢያ አሳስተን ለማስታወስና ትውስታችንን ለማጥፋት የምናደርገው ከንቱ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር! ይህ የብዙ ደራሲያን ስጋት ነው፡፡ መቀረፍ ያለበት አጉል አባዜ!….ለዚህም ነው አዳም ረታ “የስብሀት ተረቶች ትዝታ” በሚል ርዕስ በመልክዐ ስብሀት መጽሐፍ ውስጥ ባሰፈረው ማስታወሻ፣ ይህንን ሀሳብ እንዲህ በማለት አጉልቶ የሚያጠናክረው… “ብዙ ጊዜ የምናስታውሰው ላለማስታወስ ወይም አሳስተን ለማስታወስ በምናደርገው ልፋት ይመስላል፡፡ ትውስታን አሳስቶ ማቅረብ፣ ትውስታን በርዞ ማቅረብ፣ ትውስታን ሆን ብሎ ማጥፋት በአገራችን የኪነ-ጥበብ መልክዓምድር ላይ ይታያሉ፡፡ ምክንያታቸው ግላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ስሜታዊ ሊሆን ይችላል፡፡ በአያያዛችን አሪፍ አንመስልም፡፡”
አዳም ጥሩ አድርጎ አስቀምጦታል። የሚጨመር የለውም፡፡ ትውስታን ሆነ ብሎ ማጥፋት ቂልነት እንጂ አሪፍ መሆን አይደለም፡፡ ምናበ ሰፊውን፣  አሰላሳዩንና አጫዋቹን ደራሲ በዘመኑ ለደረሱበት እንዳይዘነጉት፣ ላልደረስንበት ደግሞ ጨርሶ ለማናውቃቸው ስራዎቹ ዳግመኛ ንባብ እነሆ በሁለት መንፈቅ ውስጥ ተጋልጠናል፡፡ አዎ በእነዚህ የሁለት ስራዎቹ ስብስብ ውስጥ ለስብሀት የሳይንስ፣ የሃይማኖት፣ የፍልስፍና፣ አፈታሪክ፣ ማህበራዊ ትዝብት…እሳቤዎች ንባብ እንጋለጣለን፡፡ በንባብ ጉዞዋችን እንደወትሮ ሁሉ በደራሲው የምናብ ስፋት ብቻ ሳይሆን፣ ዘርፈ ብዙ ጥልቅ አንባቢነትና አስታዋሽነት መደነቅና መገረማችን አይቀርም፡፡ እኚህ ሁለት ስራዎች ተሰብስበው በሁለት ጥራዝ የቀረቡልን በሁለት አመት ልዩነትና የጊዜ እርዝማኔ ነው፡፡ በዚህ የጊዜ ወሰን ውስጥ ቀዳሚ ሆኖ ብቅ ያለው “የትረካ ጥበብ” ነው፡፡..ትረካ ታላቅ ጥበብ ነው። የስብሀት ትልቁ ፀጋና መክሊቱ ትረካው ነው። ሲፈልግ በአንድምታ፣ ሲያስፈልግ በሰምና ወርቅ…ከተራ ርዕሰ ጉዳይ እስከ አለም አቀፍ አበይት ትርክትና ክንውን አጣፍጦ በመተረክ የተዋጣለት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ባማረ የትረካ ፍሰት ቀለል ብሎ የሚወርድ እንጂ በደረቁ የሚሰፍር ታሪክና ወግ የለውም፡፡ ትረካዎቹ ሁሉ በዘገባ መልክ ሳይሆን በትረካ ጥበብ የተለወሱ ናቸው፡፡ ትረካና ጥበብ ለእርሱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ለዚያም ይመስለኛል ጊዜ ሳይገዳደራቸው፣ በየትኛውም ዘመን ላይ በተጻፉበት አቅም ደረጃቸው ዝቅ ሳይል ተወደው ለመነበብ የበቁት፣ ለመነበብ ያለማዳገታቸው፡፡ የምንኖረው የምናውቀውን ሀቅ ነው… የሚለን ስብሀት፤ በትረካዎቹ ከኖረው ባሻገር አስገራሚ የህይወትን መሰረታዊ ሀቅ እየነገረን በአዚማም ቋንቋው ልቀትና በቃላት ምትሀት…የራቀውን አቅርቦ፣ አሮጌውን አዲስ አድርጎ ያሳየናል፡፡ በኑሮ ውጣ ውረድ ውጥረትና በልማድ መደነዝ ብዛት እንደ መርሳት ያልነው፣ ተዳፍኖ የነበረው….ቁልጭና ፍንትው አድርጎ ያጎላልናል፡፡ “የትረካ ጥበብ” ስድሳ ያህል መጣጥፎችን መርጦና ሰድሮ አቅፏል፡፡ ከስድሳ ስድስት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና ዘመን የተፃፉ ናቸው፣ በተለያዩ ልሳናት!….አዲስ ዘመን፣ አዲስ አድማስ፣ ኔሽን፣ እፎይታ፣ ነጋድራስ፣ መነን….፡፡ በርግጥ አንዳንዱ መጣጥፍ የትኞቹ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ እንደወጣ ባይጠቀስም ዞሮ ዞሮ ጽሁፉን ከዘመኑ ጋር አቆራኝተን በምናባችን እንድናሰላስለውና እንድንገረምበት እድል ይሰጠናል፡፡ ጓደኝነት በየአይነቱ፣ እብደት በየአይነቱ፡፡ ባህል እንደ ቀንበር፣ ባህል እንደ ኩርኩም፡፡ ኑሮ በተረት መልክ፣ ቅድስት አገር በታሪክ መድረክ…ሌሎችም!፡፡
“ስብሀት ስለዘመነኞቹ ደራሲያን”
ደራሲና ተርጓሚ ሳህለስላሴ ብርሃነማርያም…“ሹክታ” በምትሰኝ የወግ ስብስብ መድበላቸው ውስጥ ስለ ዳኛቸው ወርቁ የመጨረሻዎቹ ቀናት ትውስታቸውን ያወሱበትን ምዕራፍ ከመጽሐፋቸው አስፍረው ከአመታት በፊት ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህ ሌላ ስለ እውቁ ደራሲ ዳኛቸው (አደፍርስ ላይ ካልሆነ በስተቀር) በሚያውቁት ዘመነኞቹ ደራሲያን  የተጻፈ እስከማውቀውና በንባቤ እስከፈተሽኩት ፈፅሞ አላጋጠመኝም፡፡ “የትረካ ጥበብ” ካካተታቸው ስብስቦች አንዱ ስብሀት ስለ ዘመነኞቹ-አቻዎቹ ደራስያን ያተተበት “ከዳኛቸው ወርቁ ጋር” የሚል ርዕስ አለው። በጋሽ ስብሀት ህይወት ውስጥ ገብተው ከወጡና ውስጡ በበጎ ከሚመላለሱ እኩያ ፀሃፊያን…ከበአሉ ግርማ፣ ከአውግቸው ተረፈ፣ ሀይለመለኮት መዋዕል…ቀጥሎ ከዘረዘራቸው ሁለተኛው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ነው… ዳኛቸው ወርቁ። ሞገደኛው ደራሲ ዳኛቸው በሳህለስላሴም ሆነ በስብሀት ብዕር ሲገለፅ ሰብዕናው ትሁትና አዛኝ… ስሱ ነፍስ ያለው ሰው ነው፡፡ ስብሀት እንደሚከተለው ይገልፀዋል፤ “አንድ ከሰአት ቢሮው ሄጄ “ሰሞኑን የፃፍከው እንዳለ ለማንበብ ነው የመጣሁት” አልኩት፡፡ እነዚያ እንደ ኮከብ የሚያበሩት አይኖቹ እንባ አቀረሩ፡፡ “እኔኮ ልቡናዬ ሰላም ከሌለው ልፅፍ አልችልም” አለኝ፡፡ “አስራ ስምንት ሬሳ በአንድ ጉድጓድ ውስጥ!” የደርጉ ቀይ ሽብር እየተፋፋመ ነበር፡፡ የፃፈውን ማንበብ ብቻ ሳይሆን የምፅፈውንም ሁሉ ለዳኛቸው አሳየዋለሁ፡፡ ጥንቁቅ አርታኢዬ ነበር፡፡ ያችን ደቂቃ ሳስታውስ  John Donne የገጠማት ትመጣብኛለች፣ No man is an island-At most he is promontory. Every men’s death reduces me… send not to ask for whom the bell tolls; it tolls for thee… ማንም ሰው ደሴት አይደለም፣ ራቀ ቢባል ሰርጥ ይሆናል፣ የማንም ሰው ሞት ያጎድለኛል፣ ለማነው የቀብር ደውሉ የተደወለው ብለህ ጠያቂ አትላክ፣ የሚደወለው ላንተው ነው፡፡ (ገፅ113)
ስብሀት ከደራሲያን ወዳጆቹ ባሻገር ወጣ ብሎ ደግሞ በትወናው አለም በቲያትር ዘርፍ ውስጥ እውቅናን ካተረፉ አንቱ የተባሉ ብርቅዬ የመድረክ ፈርጥ ጓደኞቹን ገጠመኝና የአብሮነት ትዝታውን ያስቃኘናል፡፡..የፍቃዱ ተክለማርያም፣ ስዩም ተፈራ፣ ዘነበች ታደሰ (ጭራ ቀረሽ)    ሌሎቹንም…ጋሽ ስብሀት ከሁሉም በተለይ ለጭራ ቀረሽ ያለው ቦታና ፍቅር ልዩ ነበር፡፡ እንዴት? ከመልካም የዋህነትና፣ ከልብ የመነጨ ቅንነት ጋር …በወይን ጠጅ የታጀበ….ቡናም ጎን ለጎን እያፈላች፣ መሳቅ መጫወቱን ማስተናገዱን ሁሉንም እኩል እየሾፈረች፣ የምሳና የዱአ መስተንግዶ (ከብፌ ጋር) ታደርግለታለች። ልትጋብዘው ተቀጣጥረው ቤቷ በመጣ ቁጥር እንዲመቸው አድርጋ ትንከባከበዋለች፤ ትመቸዋለች፡፡ “አቤት እቺ ዘኔ ሰው ስትወድ! የፍቅር አድባር ትመስላለች እኛ ስናያት፡፡ ከሷ ጋር ግማሽ ቀን ማሳለፍ ግማሽ አመት የመኖር ያህል ደስ ይላል፡፡ የከበቡዋት ሁሉ ደግሞ እንደሚወዷት በአይናቸው በገፅታቸው ይነበባል፡፡ ሁሉ ነገሯ ደስ ይላል፡፡ ግልፅ፣ ቀና፣ ተጫዋችና ግጥም አዋቂ ናት፡፡…
ሰአትህን አትየው ከደረሰው ይድረስ
ላንተም እኛ አለኽን ለኛም እግዜር ይድረስ
ሳላነሳህ ውዬ ሳላነሳህ ባድር
እንዴት ትታዘበኝ የቆምንባት ምድር
ጣሊያን የኛ ሰፈር አትርዘም እጠር
ያቦይዬ ጫማ አይችልም ጠጠር….፡፡
እያለች ስብሀትን እሷም ስለምትወደው፣ በውብ  ግጥሟ ታዝናናው…. ነፍሱን ታፍነከንከው ነበር፡፡ አቦይ ለዘመናት በሚያውቁትና እናውቀዋለን በሚሉ (በገባቸውም ባልገባቸውም) ሲነገርለትና ሲፃፍለት እንጂ እንዲህ ስለሚያውቃቸው በራሱ ብዕር ሲተርክ ገጥሞኝ ሳነብ ይሄ የመጀመሪያዬ ነውና አጃኢብ ረቢ አስብሎኛል፡፡

Read 1103 times