Sunday, 22 January 2023 00:00

ከ”ሰናይ አማተር የጋዜጠኞች ማህበር” መሥራች ጋር የተደረገ ቃለምልልስ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 · የጆናታን ዲምቢልቢን የ2 ሰዓት ቃለምልልስ በታሪካዊ ሰነድነት አስቀምጠናል
       · በቢል ክሊንተን ዘመን ለዋይት ሐውስ ደብዳቤ ጽፈን ምላሽ ሰጥተውናል


        ወደተለያዩ ከተሞች ሰዎች ለስራም ሆነ ለጉብኝት ሲጓዙ እንግዳ በመቀበል፣ አካባቢን በማስጎብኘት ሁኔታዎችን ለስራ ምቹ በማድረግና በመንከባከብ ስማቸው ከፍ ብሎ የሚጠሩ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ምናልባትም በየከተማቸው ያለው የባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ከሚሰራው በላይ በመስራት አካባቢያቸውን፣ ከተማቸውን፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብትን ለሚመጡ እንግዶች በማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ምንም እንኳ ተገቢውን እውቅናና ምስጋና ባያገኙም። ከነዚህ ሰዎች መካከል የጎንደሩን ዋሴ ነጋሽን፣ የድሬደዋውን ሲሳይ ዘለገሀሬን፣ የባህርዳሩን ደምስ አያሌው ቢሻውን፣ የአዳማዎቹን ወንድምና እህቶች ቆንጂት ሁሴንና አደም ሁሴንን እንዲሁም የደሴውን መላኩ አምባውን በዋናነት መጥቀስ ይቻላል።
ለዛሬ የደሴውን መላኩ አምባውን የመረጥን ሲሆን በቅርቡ ለስራ ወደ ደሴ ተጉዛ የነበረችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከታሪከ ብዙው መላኩ አምባ ጋር ባደረገችው ቆይታ ስለመሰረተው “ሰናይ አማተር የጋዜጠኞች ማህበር” እና ስላፈራቸው አንጋፋ ጋዜጠኞች፣ በከተማዋ ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ፣ በወሎ ላሊበላ የባህል ቡድን ውስጥ ስላለው የስራ ድርሻና  ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚከተለው አነጋግረዋለች፡፡ እንድታነቡት ተጋብዛችኋል፡፡               በመጀመሪያ መላኩ አምባው የሚለው ስም በተለይ ደሴ ላይ በጣም ታዋቂ  ነው። እንዴት ታዋቂ ሆነ? ለመሆኑ መላኩ አምባው ማነው? እስቲ  ራስህን  ለማያውቁህ አስተዋውቅ?
መላኩ አምባው ተፈሪ ሲጠራ እንዳልሽው ብዙ አብረው የሚጠሩ ነገሮች አሉ። አንዱ የሚጠራው የደሴ ከተማ ነው። ሌላው “ሰናይ አማተር የጋዜጠኞች ማህበር” ነው። ሌሎችም የሚጠሩና የሚነሱ በርካታ ነገሮች አሉ። ተወልጄ ያደግኩት በዚሁ አካባቢ ነው። በአሁኑ ወቅት ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነኝ። ስራን በተመለከተ በወሎ ዩኒቨርስቲ የወሎ ላሊበላ የባህል ቡድን የህዝብ ግንኙነትና ገበያ አፈላላጊ ሆኜ እየሰራሁ ሲሆን ባለኝ ትርፍ ሰዓት ደግሞ  “መላኩ አምባው የማስታወቂያ ሥራዎችና ኢቨንት ኦርጋናይዘር” የሚል ድርጅት አቋቁሜ የተለያዩ የኪነጥበብና ፕሮሞሽን ሥራዎች ላይ እንቀሳቀሳለሁ። በሌላ በኩል፤ በይበልጥ የምታወቅበት የበጎ አድራጎት ስራ ላይ ነው። አካባቢው ላይ የተለያዩ ችግሮች በሚከሰቱበት ሰዓት በማስተባበር፣ በማገዝና በመርዳት ብዙ ጊዜዬን አጠፋለሁ። ለምሳሌ ከሁለት ዓመት በፊት የበረሃ አንበጣ በአካባቢው በተከሰተ ጊዜ፣ አንቺም በርካታ ሚዲያዎችን አስተባብረሽ መጥተሽ ተገናኝተን ነበር፡፡ ያን  ጊዜም አብረን ስንሰራ እንደነበር ታስታውሻለሽ።  በኮቪድ - 19 ወረርሽኝ ወቅትም እንደዚሁ በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ስሰራ ነበር። ይህም ብቻ አይደለም። በሀገራችን በማዕከላዊ መንግስትና በህወሓት መካከል  በተከሰተው  ጦርነት ወገኖቻችን ከሰሜን ወሎ ተፈናቅለው ደሴ ከተማን ባጥለቀለቁበት ወቅት እርዳታ እንዲያገኙ በማስተባበር፣  በቦታው እየተገኘሁ በማበረታታት ተሳትፌአለሁ። በተጨማሪም፣ በበዓል ወቅት ከሞቀ ቤታቸው ሀብት ንብረታቸውን ጥለው መጠለያ በመግባታቸው ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው ልዩ የመዝናኛ ዝግጅት በማዘጋጀት እንዲሁም በቤታቸው ቢሆኑ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር እንዳይጎድልባቸው ህዝቡን አስተባብረን በሬ እንዲታረድላቸው በማድረግ፣ ለቡሄ በዓል ዳቦ እንዲቀርብላቸው በማስተባበርና በመዝናኛው በኩል  ሙዚቃ፣ ግጥምና መሰል መዝናኛዎችን በማዘጋጀት ደስ ብሎአቸው እንዲያሳልፉ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ በመጠለያዎቹ  አካባቢዎች በመገኘት ለተፈናቃዮቹ የጎደለ ነገር ካለ እንዲሟላ የመረጃ ምንጭ በመሆንና ለተለያዩ የሚዲያ አካላት መረጃ በማድረስ ህብረተሰቡም ሆነ መንግስት ያለውን ክፍተት እንዲያውቁና አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያቀርቡ  ስንሰራም ቆይተናል።
ቀደም ሲል አንተም እንደተናገርከው መላኩ አምባው ሲነሳ ወደ ሰዎች አዕምሮ በቅድሚያ የሚመጡት ደሴ ከተማና “ሰናይ አማተር የጋዜጠኞች ማህበር” ናቸው፡፡ ከዚህ ማህበር በርካታ አንቱ የተባሉ ጋዜጠኞች ወጥተዋል። መሥራቹ ደግሞ አንተው ራስህ ነህ። እስኪ እንዴት እንደመሰረትከው  በደንብ አውጋን---?
“ሰናይ አማተር የጋዜጠኞች ማህበር” ዋና ጽ/ቤቱን ደሴ ከተማ ላይ በማድረግ በ22 ቅርንጫፎች የተዋቀረ ነበር፡፡ የተመሰረተውም በ1986 ዓ.ም ነሐሴ ወር ላይ ነው። እንዳልሽው የመሰረትኩትም እኔ ነኝ። ሲመሰረት ዋና ዓላማ ያደረግነው ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታዎች እንዳያሳልፉ፣ እራሳቸውን እንዲፈትሹና እንዲሞርዱ፣ ለታሪክና ለትውልድ የሚበቃ ልምድና ተሞክሮ የሚያገኙበትን መድረክ መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ ማህበር ወጥተው በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጪም እየሰሩ ያሉ ልጆችን አፍርቻለሁ።
በስም ልትጠቅሳቸው ትችላለህ?
እንደምታውቂው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ታዋቂው ዜና አንባቢና ደራሲ መሰለ ገብረህይወት ከሰናይ የወጣ ልጃችን ነው። የኢቲቪ መዝናኛ አዘጋጅ የነበረችው ኤደን ገብረህይወትም አንዷ የሰናይ ፍሬ ናት። ጋዜጠኛ ሔለን አይችሉህምን መጥቀስ እንችላለን፡፡ የኢቢኤሱ ያረጋል የኋሌም የእኛው ፍሬ ነው። የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ፋና ቴሌቪዥንና ሬዲዮ) አንጋፋው ጋዜጠኛ ሀበኒዮም ሲሳይም ከዚሁ ከሰናይ የወጣ እንቁ ልጃችን ነው። በዋልታም ሆነ በሌሎች ጣቢያዎች ላይ  ብዙ ልጆች አሉን። በጂማ ዩኒቨርስቲ ዋሲሁን ሲሳይ የሚባል ከፍተኛ የእርሻ ተመራማሪ የሆነ ከሰናይ የወጣ ልጅም አለን። ባጠቃላይ እነዚህ ልጆች፣  በሰናይ መድረኮች ባገኙት ልምድና ተሞክሮ ራሳቸውን በስነ-ምግባር አንጸው፣ መንገድ እየከፈቱ፣ እስከ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ትምህርት በመዝለቅ፣ በማዕረግ ሁሉ የተመረቁ የምንኮራባቸው ልጆች አፍርተናል።
በሰናይ አማተር የጋዜጠኞች ማህበር ለምሳሌ ጋዜጣ እስከ ማሳተም የደረሰ ትልልቅ ስራዎች  ስትሰሩ እንደነበር ሰምቻለሁ። እስኪ ጋዜጣውን ጨምሮ ሌሎች የማህበራችሁን እንቅስቃሴዎች አብራራልኝ?
እንዳልሽው በርካታ እንቅስቃሴዎችን እናደርግ ነበር። ለምሳሌ “የሰናይ ድምጽ” የሚል ጋዜጣ እናዘጋጅ ነበር። ይህ ጋዜጣ በእጅ ከመጻፍ ተነስቶ ወደ ማተሚያ ቤት እስከማስገባት የዘለቅንበት ሂደት ነበረው። ልዩ ልዩ መዝናኛ ዝግጅቶች አዘጋጅተን ወጣቶች ልምድና ተሞክሯቸውን እንዲያዳብሩ እናደርግ ነበር። ለምሳሌ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች ግጥም፣ ጭውውት፣ ሥነጽሁፍና ሌሎች ፈጠራዎችን ይዘው ወደ መድረክ በመምጣት ራሳቸውን ይፈትሻሉ። መድረኩ ቅርብ ስለነበር እነዚህ ልጆች ከዚህ ተነስተው አሁን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰው ራሳቸውን ለውጠዋል። ይህ የምነግርሽ የ30 ዓመት ታሪክ ነው፡፡ ደግሞ  በሀገር ውስጥ ብቻ አልነበረም የምንሰራው። የአሜሪካ ሬዲዮ ቅርባችን ነበር፣ ቢቢሲ ላይ እንሰራ ነበር። ለማመን ሊከብድ ይችላል፤ ግን አድርገነዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ አስገራሚ ነገር ልንገርሽ።  ቢል ክሊንተን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ዋይት ሀውስ ጽፈን የላክነው ደብዳቤ ደርሶ ምላሹን አግኝተናል፡፡
እስኪ ስለ ደብዳቤው ይዘት በደንብ ንገረን?
ምን መሰለሽ?  የቢል ክሊንተን “ሶክስ” የተባለ ድመታቸው ከግቢ ወጥቶ በርካታ ጋዜጠኞች መሬት ላይ እየተንከባለሉ ፎቶ ሲያነሱት የሚያሳይ የውጭ አገር ጋዜጣን ቆርጠን ልከንላቸው ነበር። ደብዳቤው ከላይ በእንግሊዝኛ፣ ከውስጥ በአማርኛ ነበር የተጻፈው። ይህ ደብዳቤ ከደረሳቸው በኋላ የሶክስን የህይወት ታሪክ ጽፈው ልከውልናል። ድመቱ መቼ እንደተወለደ፣ የራሱ ሞግዚትና ጠባቂ እንዳለው፣ በስሙ ሀብት እንደተቀመጠለት ሁሉ የሚያስረዳ ታሪክ ከዋይት ሀውስ ተልኮልን ነበር። እኛ ደግሞ ያ ታሪክ እንደተላከልን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ “ዕድለኛው ድመት” በሚል ርዕስ ጽፈን  ለንባብ በቅቷል።
ቆይ እናንተ ዋይት ሀውስ የላካችሁት ደብዳቤ ይዘት ምን ነበር  የሚለው?
ምን መሰለሽ? ድመቱ ከግቢ ወጥቶ የዛ አገር ጋዜጠኞች እየተንከባለሉ ፎቶ ሲያነሱት የሚያሳይ ጋዜጣ አገኘንና ያን ክፍል ቆርጠን ፖስታ ውስጥ አደረግነው። ከጋዜጣው ቁራጭ ጋር “እባክዎትን ስለ ድመትዎ አጠቃላይ ሁኔታ የሚያትት ማብራሪያ ላኩልን፤ ይህን ጋዜጣ አይተን ተገርመናል” የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ በአማርኛ ጽፈን ፖስታውን ካሸግን በኋላ፣ ከላይ “አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ዋይት ሀውስ” የሚል አድራሻ በእንግሊዝኛ ጻፍንበት። በዚህ መሰረት ደብዳቤው ዋይት ሀውስ ደረሰ ማለት ነው።
ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ወይም ጸሀፊዎቻቸው ነጮች ናቸው፤ እንዴት ይረዱታል ብላችሁ ነው በአማርኛ ደብዳቤ የጻፋችሁት?
ጥያቄው  ተገቢ ነው፤ ልክ ነሽ። እኛ ይሄ ጠፍቶን አይደለም። ነገር ግን ደብዳቤው በአማርኛ ተፅፎ ሲያገኙት ይወረውሩታል ወይስ እስከማስተርጎም የሚዘልቅ ቁርጠኝነት አላቸው የሚለውን ለማወቅ ነው የፈለግነው። ዋይት ሀውስ ውስጥ አማርኛ ቋንቋ እንዴት ነው? የሚለውንም ለማየት ጓጉተን ነበር። ብቻ በምንም መልኩ ደብዳቤው ደርሶ፣ ጥያቄያችን ገብቷቸውና ተቀባይነት አግኝቶ፣ የሶክስ አጠቃላይ ታሪክ ተልኮልናል ነው የምልሽ። ሌላው ቀርቶ ለዚህ ድመት ከመላው አለም የፍቅር ደብዳቤ እንደሚላክና ለደብዳቤዎቹ መልስ እንደሚሰጥለት ሁሉ ነው የጻፉልን።
ይሄ መቼም አጃኢብ የሚያሰኝ ነው ---  
እጅግ በጣም ይርማል። አዲስ ዘመን ላይ ታትሞ ለንባብ ሲበቃም ብዙ ሰው ተገርሞ እንዳንቺ አጃኢብ ሲል ነበር። እኛ ስለወለድናቸው ልጆች የተሟላ ዶክመንትና ማስረጃ የለንም፤ እነሱ ግን ለሚያስተዳድሩት እንስሳ ይህን ያህል እንክብካቤና ጥበቃ ያደርጋሉ፡፡ በሰናይ ቆይታዬ ካስገረሙኝና ካስደነቁኝ ነገሮች አንዱ ይሄ ነው። ሌላው በሰናይ ውስጥ ከማይረሱኝ፣ የ1966ቱን ድርቅ ለዓለም ያጋለጠው ጋዜጠኛ ጆናታን ዲምቢልቢ ደሴ ድረስ መጥቶ ሁለት ሰዓት ርዝማኔ ያለው ቃለመጠይቅ ማድረጋችን ነው፡፡  ዲምቢልቢ ኢትዮጵያ ሲመጣ ከሰናይ በስተቀር ለሌላ ለማንኛውም ሚዲያ ቃለ-ምልልስ አልሰጠም።  ያ የቪዲዮና የድምጽ ሪከርድ አለን። ይህ የሆነው ከ20 ዓመት በፊት ነው። እኛን በጣም ያስገረመን፣ የህይወት ታሪኩን ሲገልጽልን፣ መሆን የሚፈልገውና የሆነው መለያየቱ ነው።
እንዴት ማለት?
ጆናታ ዲምቢልቢ መሆን የሚፈልገው ገበሬ እንጂ ጋዜጠኛ አልነበረም። “ገበሬ ስላችሁ እንደ እናንተ አገር የበሬ ግንባር የምታህል እርሻ ላይ መወሰን ሳይሆን እጅግ ግዙፍ በኮምባይነርና በተለያዩ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች የታገዘ የግብርና ሥራ ነበር መስራት የምፈልገው--” ነበር ያለን። ሳይሳካ ቀርቶ ጋዜጠኛ እንደሆነና በአንድ ወቅት ቢቢሲ እና ሲ.ኤን. ኤን. ላይ ከወንድሙ  ጋር በተመሳሳይ ሰዓት ቀርበው፣ እናታቸው የትኛውን መርጣ ለማየት ተቸግራ እንደነበር ሳይቀር የህይወት ታሪኩን አካፍሎን፣ በታሪካዊ ዶክመንትነት እኛው ጋር ተቀምጦ ይገኛል። የትኛውም ሚዲያ ላይ አላወጣነውም። በነገራችን ላይ በወቅቱ ድምቢልቢ “የሰናይ ድምጽ” የሚለው ጋዜጣችንን በእጃችን እንደምንጽፍ ተረድቶ፣ ለምን አታሳትሙም በማለት የአንድ ዙር ማሳተሚያ ገንዘብ ሰጥቶ ሁሉ አበረታትቶናል።
ምን ያህል ገንዘብ ሰጣችሁ?
አይ በወቅቱ ጋዜጣ ለማሳተም ከ5 ሺህ ብር በላይ አታወጪም ነበር’ኮ! ያን ጊዜም እኛ ጋዜጣውን ለቢዝነስ ስለማንሰራው የማሳተሚያውን ብቻ ነው የሰጠን። ጋዜጣው ወጥቶም በነጻ ይከፋፈላል እንጂ አይሸጥም ነበር። የዛን ጊዜ እኛ እርካታችን ለህዝብ መስራታችን እንጂ ቢዝነስ ገንዘብ የሚባለው አያሳስበንም ነበር። ለምሳሌ መዝናኛ ፕሮግራም ስናዘጋጅ ግጥሞች፣ ጭውውቶች ሙዚቃው ሁሉ ነገር ይቀርባል። ይህንን ለመታደም ለሚመጣው ሰው ኩኪስ መስሪያ ልጆቹ (አቅራቢዎቹ) ከየቤታቸው ዘይት፣ ዱቄት ስኳር አምጥተው ሰርተን አሽገን ለታዳሚ እናቀርባለን። ግጥም ጭውውት ሙዚቃ በነጻ ይታደማል፤ ጋዜጣ በነጻ ይወስዳል - ህዝቡ። ነፍሳቸውን ይማርና ደራሲና ተርጓሚ ማሞ ውድነህ፣ ኩኪስ አሽገን ስናድል የሚያሳይ ቪዲዮ አዩና፤ “ይሄ ምንድነው?” አሉን። “ኩኪስ ነው” አልናቸው፡፡ “ሸጣችሁ ነው?” “አይ በነጻ ነው” አልናቸው፡፡ “ጋዜጣውስ ይሸጣል?” “አይ አይሸጥም” ስንላቸው፤ “ምን መሆናችሁ ነው? ቢያንስ በአንዱ እንኳን የኢኮኖሚ ድጋፍ እንዴት አታገኙም? የሰውን ሆድ ሞልታችሁ አዝናንታችሁ፣ ዕውቀት ሰጥታችሁ፣ ሁሉም በነጻ እንዴት ይሆናል?!” ብለው መከሩን ተቆጡን። እስከዚህ ድረስ መስዋዕትነት እንከፍል ነበር። የሚገርመሽ ዝግጅታችንን ጨርሰናል ብለን ተሰናብተን ሁሉ ሰው ቁጭ ብሎ ይጠብቀን ነበር፡፡ በእውነቱ ኪነጥበብ ምን ያህል ተፈላጊ እንደነበር ያወቅንበትና ራሳችንን የፈተሽንበት ጊዜ ነበር፡፡ እንዲያም ሆኖ ጊዜውን “የጨለማው ጊዜ” እያል ነበር የምንጠራው፡፡
(ይቀጥላል)


Read 1107 times