Saturday, 28 January 2023 20:49

የአገር በቀልና የውጭ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቡድን በትግራይ ጉብኝት አደረገ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አስተባባሪነት የተመራ የአገር በቀልና የውጭ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ያካተተ ቡድን ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም በመቀሌ የሥራ ጉብኝት ማድረጉ ተገለጸ።
ጉብኝቱ በትግራይ ያለውን ወቅታዊ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና በቀጣይ ስለሚከናወኑ የመልሶ ማቋቋምና መሰል ተግባራት ላይ በክልሉ ከሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ግንዛቤ  ለመፍጠር ያለመ ነበር ተብሏል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተካሄደው የምክክር መርሃ ግብር ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የምክር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ፤ “እውነተኛ ማህበረሰባዊ ሽግግር እና ዘለቄታዊ ሰላምን ማረጋገጥ የሚቻለው ህዝብን በማዳመጥና ህዝብ ያለውን ሃብትና እሴት ከግንዛቤ ያስገቡ የችግር መፍቻ አካሄዶችን በመቀየስ ነው” ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ “ግጭትና አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት መፍታት የማንችል ከሆነ ችግሮቹ እንዲቀጥሉ እድል ከመስጠት ባለፈ ለመጪውም ትውልድ እዳንና የተደራረቡ ችግሮችን የሚያወርስ መሆኑን ምክር ቤታችን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጽ ቆይቷል”  በማለት ሰላማዊ የግጭት አፈታት አማራጭን መጠቀም አይተኬ ሚና እንዳለው በአጽንኦት ገልጸዋል።
የትግራይ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህብረት ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ በርሄ በበኩላቸው፤ “ባለፉት ሁለት ዓመታት ለብዙ ህይወት መጥፋት፣ ከቤት ንብረት መፈናቀልና  ሰቆቃ የተዳረጉ ወገኖችን የሲቪል ማህበረሰብ ዘርፉ መታደግ ባይችልም፣ ከምንጊዜውም በላይ አሁን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥምረትን በመፍጠር  ጉዳት ላይ ለወደቁ ዜጎች በአፋጣኝ ዕርዳታና ድጋፍ የሚደርስበትን ሁኔታ በመረባረብ ማሳካት ይጠበቅበታል” ብለዋል።
ቡድኑ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያን የጎበኘ ሲሆን፤ በጣቢያው ተጠልለው የሚገኙት ተፈናቃይ ዜጎች አሁንም ከፍተኛ ችግር ላይ ስለሚገኙ አፋጣኝ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። የትግራይ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህብረት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ገ/እግዚአብሄር፤ "ስለደረሰብን ስብራት አብዝተን በማውራት የምንቀይረው ብዙ አይኖርም። በትንሹ ከተግባባን፣ በብዙ ከሰራን  ለህዝባችን ልንደርስለት እንችላለን” ብለዋል። የጉብኝት መርሃ-ግብሩ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና በትግራይ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህብረት የጋራ ትብብር መሆኑ ታውቋል፡፡

Read 1528 times