Saturday, 28 January 2023 20:54

መንግስት፤ በሰሜን ሸዋ ዞን በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን የንፁሃን ግድያ በአስቸኳይ እንዲያስቆም ተጠየቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(11 votes)


  በህዝብ እንደራሲዎች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ኦነግ ሸኔ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም በከፈተው ድንገተኛ ጥቃት በርካታ የአማራ ልዩ ሀይል አባላት፣ የፌዴራል ፖሊሶች ሚሊሻዎች፣ የፀጥታ አስከባሪዎችና ንፁሃን መገደላቸውን በሸዋ የሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ማህበራት አስታውሰው፤ መንግስት ይህንን በአሸባሪ ቡድኑ የሚደርስ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያስቆምና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠየቁ፡፡ ሲቪክ ማህበራቱ ይህንን አስመልክተው ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ልዩ ዞን አጎራባች ወረዳዎችና ቀበሌዎች በተለይም በኤፍራታና ግድም ወረዳ፣ በቀወት ወረዳ፣ በአንፆኪያና ገምዛ ወረዳ፣ በአጣዬ ከተማ አስተዳደር፣ በካራ ቆሬ፣ በቆሪ ሜዳ፣ በማጀቴ፣ በየለን፣ በቆሬ በጀውሃ፣ በኦርሶ እምባዘንና፣ በመንተኬ፣ ሸረፋና በሌሎችም ቀበሌዎች የኦነግ ሸኔ ሀይል፣ ሌሎችንም ፀረ-ሰላም ሀይሎች በማስተባበርና ከአማራ ጠል ሀይሎች ከፍተኛ የስንቅና የትጥቅ ድጋፍ በማግኘት፣ ባለፉት አራት አመታት በማያቋርጥ ሁኔታ በንፁሀን ዜጎቻችን ላይ ከፍተኛ ጥቃትና መከራ ሲያዘንብ ቆይቷል ብለዋል-ሲቪክ ማህበራቱ፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ወንጀል በተደጋጋሚ ሲፈፀም በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፉ አካላትና ከጀርባ ያሉ የሴራ ፖለቲካ አራማጆች በህግ አግባብ ባለመጠየቃቸው ለአሸባሪ ሀይሉም ሆነ ለተባባሪዎቹ የልብ ልብ የሰጠ ጉዳይ ነው ያሉት ሲቪክ ማህበራቱ የጥር 13ቱም ጥቃት፣ የንፁሃንና የፀጥታ ሀይሎች ግድያ፣ የከተሞችና የመንደሮች መውደም እንዲሁም የሀብት ዘረፋ የማናለብኝነት ውጤት ነው ሲሉ እርምጃ ከመውሰድ የተቆጠቡትን የፌዴራል መንግስትንና የአማራ ክልልን መንግስት በእጅጉ ኮንነዋል፡፡   
ምንም እንኳን ወንጀለኞች ከላይ በተጠቀሱት የሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢዎች ባደረሱት ተደጋጋሚ የሰብአዊ መብት ጥሰት በህግ ባይጠየቁም በግፍ ቤሰቦቻቸውን ያጡትን በማፅናናትና እንዲሁም ቤት ንብረታቸው ወድሞባቸው የተፈናቀሉትን መልሶ በማቋቋም ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዲያገግሙ እየተደረገ ባለበት ባሁኑ ወቅት ሆን ተብሎ በተደራጀ የጥፋት ሀይል ጭካኔ በተሞላበት ደባ ንፁሃን በግፍ እንዲገደሉና ከተሞች በድጋሚ እንዲወድሙ እየተደረገ ነው ያሉት ሲቪክ ማህበራቱ፣ በተለይም ደግሞ በፀጥታ ሀይሎቻችን ማለትም በአማራ ልዩ ሀይል፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በአማራ ሚሊሻ ላይ በቡድን መሳሪያና ሎጀስቲክ ጭምር በታገዘና በተቀናጀ መልኩ እርምጃ ሲወስድ ማየት የተለመደ ነው ካሉ በኋላ፣ ይህም ሀገርን የማፍረስና ዜጎችን ሰላም የመንሳት አንዱ የጥፋት መንገድ መሆኑን መላው ኢትዮጵያዊያን ተገንዝበው የጥፋት ሀይሉን እንዲወግዙ ሲቪክ ማህበራቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጥፋት ሀይሉ የኦነግ ሸኔ ቡድን፣ አጋሮቹ በሆኑት በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ልዩ ዞን በአርጡማ ፋርሲወረዳ እና በጅሌጥሙጋ ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች በተለይም  በጋንጋሃና በደዌ -ሃረዋ ስልጠና ሲወለድ እንደነበር እየታወቀ የአማራ ክልል መንግስት በጥፋት ሀይሉ ላይ የማያዳግም እርምጃ አለመውሰዱ፣ እንዲሁም ከዚህ ቀደም በአማራ ህዝብና በፀጥታ ሀይሎች ላይ ግፍ የፈፀሙ ሀይሎችን ለህግ አለማቅረቡ ህዝባችን ለተደጋጋሚ ጥቃት እንዲጋለጥ አድርጎታል ሲሉ አማርረዋል፡፡
ሲቪክ ማህበራቱ ባወጡት የአቋም መግለጫ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በዚህ የጥፋት ሀይል ላይ የሚያዳግም እርምጃ በመውሰድ የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ ህጋዊ ሀላፊነቱን እንዲወጣ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን መስተዳድርና በየደረጃው ያሉ አመራሮች የህዝብን ደህንነት የማስጠበቅ ተቀዳሚ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ፣ የፍትህ አካላትና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እየደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ጉዳት በሚገባው ልክ በመገንዘብ አስፈላጊውን ማስረጃ በማሰባሰብ የጥፋት ሀይሎች በህግ እንዲጠየቁ በማድረግ ፍትህ ይረጋገጥ ዘንድ ለችግሩ ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ፣ የሚዲያ አካላትም ችግሩን በአግባቡ በመዘገብ ለዘላቂ መፍትሄው ግብአት በማመንጨት መስራት እንጂ በሰብአዊነትና በፍትህ ላይ እየደረሰ ያለውን ማስረጃ በማድበስበስ መሸፋፈን ተገቢ እንዳልሆነ አሳስበው  በአጠቃላይ የችግሩን መንስኤ፣ ሂደትና እየደረሰ ያለውን በአግባቡ በመዘገብ ለህዝብና ለሀገር ተገቢውን መረጃ በወቅቱ እንዲያደርሱ እንዲሁም የግብረ ሰናይ ድርጅቶች በጥቃቱ ለተፈናቀለው ከ250 ሺህ በላይ ህዝብ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያገኝና በዘላቂነት መልስ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ተሳትፎ እንዲሳተፉ ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጡት የጋራ የአቋም መግለጫ ጠቁመዋል፡፡

Read 1428 times