Saturday, 28 January 2023 21:00

ጦርነትን ከመግታት ጋር ከዋጋ ንረትም መገላገል አለብን።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

ሐምሌ 2000 ዓ.ም ላይ የአገሪቱ የገንዘብ ኖት፣ 35 ቢሊዮን ብር ነበር።
ሐምሌ 2014 ዓ.ም ላይ የአገሪቱ የገንዘብ ኖት፣ ከ350 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል።
ጦርነትን የሚገታ መፍትሔ ሲሳካ ማየት አስደናቂ ተዓምር ነው- እጅግ የሚመሰገን።
የዋጋ ንረትን የሚያረግብና የሚያስወግድ መፍትሔም እንደዚያው።


  የዋጋ ንረትን ማብረድና ማስወገድ እንደ ንግግር አይቀልም። በብዙ ችግር የተተበተበ ነው። ግን ጦርነትን  መግታትም ቀላል አልነበረም።
ከሰላም ወሬ ርቀን፣ ለምኞትና ለሕልም አስቸግሮን ነበር። አሁን ከሰላም ጋር ተቀራርበናል። አብሮን ተረጋግቶ እንዲኖር ለሰላም  እንመቸው፤በሰላም ተመችቶን እንድንኖር።
ከሰላም ጎን ለጎን የሚያስፈልገን ሌላው የአገር ምኞት፣ ኑሮን ከሚያጎሳቁል የዋጋ ንረትና ከኢኮኖሚ ቀውስ የምንወጣበት ገላግሌ መንገድ ነው። ገበያው እየተረጋጋ ቅጥ እንዲይዝ፣ ኑሮን የሚያሻሽልና ኢኮኖሚን የሚያሳድግ መንገድ መፍጠር፣ የዓመቱ ትልቅ ምኞት ነው- ሰላምን ከመፍጠር ቀጥሎና ተያይዞ።
የዋጋ ንረትን በፍጥነት ማረጋጋትና መግታት ያስፈልጋል፤ ተገቢ ነው። ደግሞም የመንግስት ሃላፊነት ነው። በእርግጥ፣ ቀላል ስራ አይደለም። በብዙ እንቅፋቶችና በፈተናዎች የተተበተበ ከባድ መከራ ነው- የዋጋ ንረት።
ከባድነቱ ግን፣ በብርታትና በጽናት እንድንጥር ሊገፋፋን እንጂ፤ “መላም የለው!” ሊያስብለን አይገባም። ደግሞ፣ የዋጋ ንረትን ማርገብና መግታት ከባድ ሸክም ቢሆንም፣ በዋጋ ንረት ሳቢያ የሚከሰተው የኑሮ ጉስቁልናና የኢኮኖሚ ምስቅልቅል እጅጉን እጥፍ ድርብ ይከብዳል።
እናም በኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ፣ የዋጋ ንረትን ማብረድና መግታት፣ ቀዳሚ የመንግስት ሃላፊነት ነው።
በፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ፣ ጦርነትንና ግጭትን መግታት፣… ሰላምን መፍጠር፣ ሕግና ሥርዓትንም ማፅናት የመንግስት አውራ ሃላፊነት ነው።
አዎ፣ ቀላል አይደለም። ሰላም ሳይደፈርስ በፊት ግጭት ሳይዛመትና ጦርነት ሳይፈጠር በፊት፣ የሰላምን በረከት አክብረን፣ የጦርነትን መዘዝ ተገንዝበን ቀድሞውኑ ብንተጋ ነበር የሚሻለን። ሰላምን መጠበቅና ማጽናት፣ ጦርነትን ማስቀረትና ማስወገድ ቀላል አይደለም? አይደለም። ግን ይሻላል። ሰላም ከደፈረሰና ጦርነት ከተቀጣጠለ በኋላማ በጣም ይከብዳል።
እንዲያም ሆኖ፣ ጦርነት ከተፈጠረ በኋላ ማስቆም፣…”ከባድ ነው” ስላልን፣ ሌላ የተሻለ ቀላል አማራጭ ይመጣል ማለት አይደለም። ጦርነትን መግታት ከባድ ከሆነ፣ በጦርነት ውስጥ መቅየትማ በስንት እጥፍ ይከብዳል? ጦርነትን መግታትና ሰላምን መፍጠር ከባድ ከሆነ፣ የግጭትና የጥቃት ትርምስ ውስጥ መክረምማ ምንኛ ይከፋል? ስንት እጥፍ ይብሳል?
ሰላም ከከበደን፣ ጦርነትንማ እንዴት እንችለዋለን?
 በእርግጥ፣ የእለት ተእለቱን ብቻ፣ የሩቅ የሩቁንና ላይ ላዩን ብቻ የምናይ ከሆነ፣… እንደትናንቱ በዘፈቀደና  በጭፍን ስሜት ጥላቻንና ጦርነትን ብናራግብ ቀላል መስሎ ሊታየን ይችላል። “አውቶሪፕለይ” ውስጥ ሳይታወቀን ከገባንበት በኋላ፣ ያለ ሃሳብ ያለጥረት መሽከርከር የዘወትር ውሎና አዳራችን ይሆንብናል። ይለምድብናል።
አንዴ ወደ አጥፊ የጦርነት ገደል እየተገፋፉ እየተጓተቱ ከገቡ በኋላ፣ ቁልቁል እየተንሸራተቱ መውረድ ብዙ ትጋት አይጠይቅም። ከጦርነት ቅዠት መባነን፣ ቁልቁል የመንደርደር ውርደትን መግታት፣ ሽቅብ ከገደል ለመውጣት ከአቀበት ጋር መታገል ግን ከባድ ነው።
ቁልቁል በደመነፍስ ወደ እንጦሮጦስ መንሸራተት ቀላል ቢመስልም፣… ከባድ ጥረት ባይጠይቅም፣ መዘዙ ግን በየእለቱ እየበዛ፣ እልቂቱና ውድመቱ እየከፋ፣ ሃዘኑና መከራው እየመረረ የምድር ሲኦል እንደሚሆንብን አስቀድመን ማወቅ ያቅተናል?
ገና ከሩቁ ማወቅ ባንችል ወይም ማወቅ ባንፈልግ እንኳ፣ ሲመጣብን ሲደርስብን፣ ስንሄድበት ስንደርስበት በእውን ስናየው፣ የጦርነትን ጥፋት ብቻ ሳይሆን ውርደቱና ክፋቱንም መገንዘብ አይሳነንም።
እንዲያም ሆኖ ግን፣ ጦርነትን መግታትና ሰላምን መፍጠር ቀላል ስራ አይደለም።

ጦርነትን መግታትና ሰላም መፍጠር፣ እንደ ተዓምር አስደናቂ ነው።
የጦርነት ክፋቱ ከቀን ወደቀን ነገሮችን እያወሳሰበና እየተበተበ፣ መውጫ መንገዶችን ይዘጋል። ባይዘጋ እንኳ፣ የብዙ ሰዎችን አይን ይጋርዳል። ልቦናቸውን ያደነድናል። ተስፋ ያስቆርጣል። መንፈስን ይመርዛል።
በጦርነት መሃል ሆነን፣ ስለ ሰላም መናገር፣ እንደ ከንቱ ምኞት ሆኖ ይሰማናል። “ላም አለችን በሰማይ” እንደማለት ይሆንብናል። ባስ ሲልም፣ ስለ ሰላም መናገር እንደ ክህደት እየተቆጠረ ድምፁ ታንቆ ይጠፋል።
በዚህ መሃል፣ ጦርነትን የሚገቱና የሰላም መንገድን የሚከፍቱ መፍትሔዎች ይመጣሉ ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ በእውን ሲያጋጥሙንም እንደ ተዓምር ነው የሚሆኑብን፡፡ በእርግጥም የተዓምር ያህል ነው አስደናቂነታቸው፡፡
ግን ደግሞ፣ ጦርነትን ከመግታትና ሰላምን ከመፍጠር የተሻለ ሌላ ጤናማ (ኖርማል) ሃሳብና ተግባር አለ? ምን ያህል ዓይንና ልቦናችን ቢደፈን ይሆን፣ ጦርነትን መግታት እንደተዓምር የሆነብን? ተጋርዶብን እንጂ፣ እንዴት ነው የሰላም መንገድ ብርቅ ድንቅ የሚሆንብን?
የተጋረደውን የሚገልጡ፣ የተደፈነውን የሚያናፍሱ መፍትሔዎች እንደ ተዓምር ብቅ ብለው፣ ከሃሳባችንና ከሕልማችን የራቀብንን የሰላም መንገድ በእውን አምጥተው ያሳዩናል፡፡
ሰላም፣ የዘወትር መደበኛ የአገር ውሎና አዳር መሆን እንዳለበት በተግባር ያሳምኑናል፡፡
ጦርነትን የሚያባብስና የሚያራዝም ሰበብ ጠፍቶ አይደለም። በጣጣዎች የተተበተበና የተወሳሰበ መሆኑ አልቀረም።
ቀላል ባይሆንም ግን ጦርነትን መግታት ይቻላል፡፡ የመንግስት ዋና ሃላፊነት መሆንም ይገባዋል፡፡
በተግባርና በትጋት እውን ሲሆን ደግሞ መደገፍና ማመስገን ያስፈልጋል። ከተቻለም በሃሳብ መደገፍ ይኖርብናል።

የዋጋ ንረትን ማስወገድ ሌላው የመንግስት ሃላፊነት ነው።
የዋጋ ንረትን መግታትና የተረጋጋ የገበያ ስርዓትን መፍጠር ከዚህ ጋር ይመሳሰላል፤ ጦርነትን ከማስቆም ጋር ይዛመዳል፡፡ ቀላል ባይሆንም፤ የዋጋ ንረትን እንደ ጦርነት መግታት ይቻላል፡፡ ተገቢም ነው፡፡ የሰላምን መንገድ መፍጠር፣ የተረጋጋ የገበያ ስርዓትን ከማስፈን ጋር ይመሳሰላል፡፡
እንኳን ድሃ አገር እዚያው አገር ውስጥ ጦርነት ሲያካሄድ ይቅርና፣ ሃብታም አገር ከባህር ማዶ ሄዶ ጦርነት ሲገጥም እንኳ፣ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ከሰው ከእልቂት፣ ከስቃይና ሃዘን ጋር፣ የሃብት ብክነትንና ውድመትን፣ የኢኮኖሚ ቀውስንና የኑሮ ጉስቁልናን ያስከትላል፡፡
የጊዜ ጉዳይ እንጂ፣ ጦርነት ሁሌም የዋጋ ንረትን ያመጣል፡፡ ጦርነት፣ በአንድ በኩል ኢኮኖሚን ያዳክማል፡፡ የምርት እድገትን ያሰናክላል፡፡ በሌላ  በኩል ደግሞ፣ የመንግስትን ወጪ ይበረከታል፤ ቀዳዳውን ይበዛል፡፡ መንግስት ወጪውን ለመሸፈን እየተበደረ እዳው ይቆለላል፡፡ የገንዘብ ሕትመቱም ከኢኮኖሚው አቅም በላይ ይሆናል፡፡
በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከገንዘብ ሕትመትጋር የተቆራኘ ነው- የዋጋ ንረት።
በእርግጥ፣ አዎ፣ ከኢኮኖሚ እድገት ጋርም ግንኙነት አለው። ነገር ግን፣ ኢኮኖሚን ማሳደግ የሚቻለው መንግስት በሚያሰፍነው ሕግና ሥርዓት ውስጥ በከፍተኛ የዜጎች ጥረት ነው። ለዚያውም በዓመት ውስጥ፣… ከ10 በመቶ በላይ ኢኮኖሚን ማሳደግ ከባድ ነው።
የገንዘብ ህትመት ግን፣ በመንግስት ውሳኔ ብቻ ይከናወናል። የተለየ ጥረት አያስፈልገውም። ከኢኮኖሚው አቅም በላይ፣ ከልክ ያለፈ የገንዘብ ሕትመት ሲኖርም፣ የዋጋ ንረትን ይፈጥራል።
መንግስት ይህን የዋጋ ንረት መግታት አለበት። ባለፉት ዓመታት የተፈለፈሉ ብዙ ችግሮችንና ተደራራቢ ፈተናዎችን ማቃለል ቀላል ስራ አይደለም። የዋጋ ንረትም በብዙ ጣጣ የተተበተበ ነው።
ቢሆንም ግን፣ “ጣጣው ብዙ ነው” በሚል ምክንያት፣ የዋጋ ንረትን ወይም ጦርነትን ከመግታት ወደኋላ ማለት አይገባም። ጦርነትን ማስቆምና ሰላም መፍጠር የግድ አስፈላጊ ነው።
የዋጋ ንረትን መግታትም፣ ሌላኛው የመንግስት ትልቅ ሃላፊነት ነው።
የአገሪቱ የገንዘብ ኖት ወደ 400 ቢሊዮን ደርሷል።
በ2000 ዓ.ም፣ የአገሪቱ የገንዘብ ኖት 35.5 ቢሊዮን ብር ነበር።
በ2014 ዓ.ም፣ የአገሪቱ ገንዘብ ኖት 362.5 ቢሊዮን ብር ሆኗል።
በአስራ አምስት ዓመታት ውስጥ አስር እጥፍ ሆኗል። ከኢኮኖሚው አቅም በላይ ነው- የገንዘብ ህትመቱ። የዋጋ ንረቱም የዚያኑ ያህል ነው።
ይህን መግታት ትልቅ ስራ ነው- ጦርነትን የመግታት ያህል።
መንግስት ይህን ለማሳካት መትጋት ይኖርበታል። ሃላፊነት አለበት። እንዲሳካለት ብንመኝ፣ ከተቻለም በመፍትሄ ሃሳቦች ብናግዝ መልካም ነው።

Read 423 times