Saturday, 28 January 2023 21:04

ጥሬ ስጋ እንደጉድ በሚበላበት አገር ይህን ዜና ሰምቶ ዝም ማለት ወንጀል ነው!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአንጀት ካንሰር ተይዞ በሽታው ወደ ጉበቱ ተሰራጭቶ የነበረው የ42 ዓመቱ ጎልማሣ፣ የሕመም ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች በፍጥነት ሃኪም እንዲያዩ ይመክራል
በብሪታንያ ከ1980ዎቹ ወዲህ፣ በአንጀት ካንሰር የሚጠቁ ከ50 አመት በታች የሆኑ ዜጎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው

  በ40ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ብሪታኒያዊ ጎልማሳ ባጋጠመው ተደጋጋሚ ሸርተቴ ምክንያት ሃኪም ዘንድ ሲቀርብ ነበር፣ የአንጀት ካንሰር ታማሚ መሆኑ የተነገረው፡፡
ቶም ማክኬና ለእንግሊዙ “ኢንሳይደር”  ጋዜጣ በኢሜይል እንደገለፀው፤ እ.ኤ.አ. በ2020 ዓ.ም ለመፀዳጃ ከተጠቀመበት ወረቀት ላይ በተመለከተው ያልተለመደ  ነገር ነበር ወደ ሃኪም ዘንድ ለመሄድ የተገደደው፡፡
ማክኬና የድካም ስሜት አዘውትሮ ቢሰማውም፤ ጉዳዩን ተደራራቢ ከሆነው ሥራውና በቂ እንቅልፍ ካለማግኘቱ  ጋር ነበር በቀጥታ ያገናኘው፡፡  
“ፍፁም ደህና ነበርኩ” ይላል  ማክኬና፡፡
ተደጋጋሚው ሸርተቴ አሳስቦት ወደ ሆስፒታል በሄደ ጊዜ ሃኪሞቹ፤  የcolonoscopy (በካሜራ የአንጀትን የውስጥ ክፍል ማሣየት የሚችል የህክምና መሣሪያ) ምርመራ አደረጉለት፡፡ በምርመራ ውጤቱም፣ የአንጀት ካንሰር እንዳለበት አረጋገጡ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተደረገለት ቀጣይ ምርመራ፣ ካንሰሩ  ወደ ጉበቱ የተሰራጨ መኾኑ ተነገረው፡፡ ይህም ማለት በሽታው “ደረጃ 4” ላይ ደርሷል ማለት ነው፡፡  
ከ1980ዎቹ አጋማሽ ወዲህ፤ በአሜሪካና በሌሎች  ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገራት የአንጀት ካንሰር ስርጭት እንደ ብሪታኒያ ሁሉ በእጅጉ ቀንሷል፡፡ ይኽም የኾነው በአሜሪካ ከ45 ዓመት በላይ፣ በብሪታኒያ ደግሞ ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ጎልማሶች፣ ቅድመ ምርመራ ስለሚያደርጉና  በሽታው ሥር ሳይሰድ በፊት ስለሚደርሱበት ነው ተብሏል፡፡
ነገር ግን  በፊንጢጣና በአንጀት ካንሰር የሚጠቁ ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች ቁጥር  ከ1980 ወዲህ እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡
የሆድ እቃ መቆጣትን የሚፈጥረው ከፍተኛ የኾነ የቀይ ሥጋ ፍጆታ ለበሽታው መንስኤነት በዋናነት ይጠቀሳል፡፡   
የሚሰጠው ሕክምና ሕመሙ እንዳለበት ደረጃ ይወሰናል፡፡ በዚሁ መሠረት ኬሞቴራፒ፣ ሬዲዮቴራፒ እና ቀዶ ጥገና  በጥምረት ወይንም በተናጠል ሊከናወኑ  ይችላሉ፡፡ ማክኬና የጉበቱ 60 በመቶ ያህሉ በመስከረምና የካቲት 2020 ዓ.ም በተደረጉለት ተከታታይ ቀዶ ሕክምናዎች ተወግዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ግማሽ ያህሉ የትልቁ አንጀቱ ክፍልና  የሃሞት ከረጢቱ፣ በግንቦት 2021 ዓ.ም በተደረገለት ቀዶ ጥገና ተወግዷል፡፡
የቀዶ ጥገና ህክምናው የፈጠረው ጠባሳ  አካባቢ፣ ሕመም እንደሚሰማው የሚናገረው ጎልማሳው፤ ቅባት ያላቸው ምግቦችና አልኮል  መጠጥ እርግፍ አድርጎ መተዉን፤ እንዲሁም ፋይበር ያላቸው ምግቦችን እንደሚያዘወትር  ገልጿል፡፡
በታህሳስ  2021 ዓ.ም በተደረገለት ምርመራ፣ ምንም ዓይነት ካንሰር በሰውነቱ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል እንዳልተገኘ የተረጋገጠ ሲኾን፤ በመጪው ግንቦት ወር ድጋሚ ምርመራ ይደረግለታል፡፡ ካንሰሩ ዳግም ላለማገርሸቱ እርግጠኛ ለመሆን በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት፣ በየስድስት ወሩ ተመሳሳይ ምርመራ እንደሚያደርግም ለኢንሳይደር  ጋዜጣ  ጠቁሟል፡፡
የአሜሪካ የካንሰር ማህበር፤ በ2023 ዓ.ም  106,970 ገደማ ሰዎች በአንጀት ካንሰር ሊጠቁ እንደሚችሉ  ግምቱን አስቀምጧል፡፡
በአንጀት ካንሰር የተጠቃ ሰው ሕመሙ ከታወቀ በኋላ ከ5 ዓመት በላይ በሕይወት የመቆየት እድሉ የሚወሰነው እንደ በሽታው  የስርጭት መጠን ነው፡፡  
“የአንጀትና የፊንጢጣ ካንሰር ሳይታወቅ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል” የሚለው ማክኬና፤ ጥርጣሬ ያላቸው ሰዎች ሳይዘገዩ  ምርመራ እንዲያደርጉ  ይመክራል፡፡
ማክኬና ከተሰማው የሕመም ስሜት በተጨማሪ፤ በሽታው ከሚያሳያቸው የተለመዱ ምልክቶች መካከል፡ ከተፀዳዱ በኋላ የሆድ መክበድ፣ የክብደት መቀነስ፣ በሆድ አካባቢ የሕመም ስሜት ይገኙበታል፡፡ እኒህ ስሜቶች  የሚሰማው ሰው፣ በፍጥነት ሃኪም ማንገር አለበት፡፡  
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1716 times