Saturday, 28 January 2023 21:08

“ያልተመረጠው የደሴ ከንቲባ”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

በወሎ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚተዳደረው የወሎ ላሊበላ የባህል ቡድን ምን እየሰራ ነው?
በደሴ ለ90 ዓመታት ሳይቋረጥ የዘለቀ የባንዲራ መስቀልና ማውረድ  ሥነስርዓት

  ባለፈው ሳምንት እትማችን ከ “ሰናይ አማተር የጋዜጠኞች ማህበር” መስራች አቶ መላኩ አምባው ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ያደረገችውን ክፍል አንድ ቃለ ምልልስ ማስነበባችን ይታወቃል፡፡ እነሆ ቃለ ምልልሱ በክፍል ሁለት እንደሚከተለው እንድታነቡት ጋብዘናል፡፡

   ለምን ነበር “የጨለማው ጊዜ” የምትሉት?
ምክንያቱም አርአያ የሚሆነን ሞዴል አልነበረንም። ራሳችን በራሳችን ነበር ሁሉን ነገር የምናደርገው። ስቱዲዮ ገብተን የምናየው ነገር አልነበረም። ለመነሻ የሚሆን ነገር ባለመኖሩ፣ እኛው ነን በዚህ በዚያ ብለን ሁሉን የምንሰራው።
በወቅቱ ለአባላቶቻችሁ የጋዜጠኝነት ሥልጠና የሚሰጥላችሁ ማን ነበር?
አንዳንድ በጎ ፈቃኞችን በመጠየቅ ነበር ስልጠና የምናገኘው። ለምሳሌ፡- ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት፣ አቶ ፀሀይ ደባልቀው በነበሩበት ሰዓት ግንኙነት ፈጥረን ነበር። ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቃደ፣ እነ አጋረደች ጀማነህ (ዶ/ር) ፣ እነ ታደሰ በላቸው ወዘተ… እዚህ ሊያሰለጥኑ ይመጡ ነበር። የዚያን ጊዜ “መገናኛ ብዙኃን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት” ነበር የሚባለው። እኛ ነን “የማን ማሰልጠኛ ነው? ለምንድነው ‹የኢትዮጵያ› የሚል ከፊቱ የማይገባው?” የሚል ጥያቄ አንስተን፣ “የኢትዮጵያ” የሚለውን ያስጨመርነው፡፡  እስከዚህ ድረስ ተፅዕኖ ነበረን። እንደነገርኩሽ 22 ቅርንጫፎችና ብዙ አባላት ነበሩን።
እስኪ የት የት ነበሩ ቅርንጫፎቻችሁ?
ከቅርቦቻችን ብንጀምር ኮምቦልቻ፣ ሐይቅ፣ ጃማ ነበረን። ገዛኸኝ ጸጋው (ዶ/ር) ያን ጊዜ ጃማ ነበርና የሰናይ አባል ነበር። በሌሎች ክልሎችም ቅርንጫፎች ነበሩን። ለምሳሌ፡- ጎንደር፡፡ ሁሉንም መዘርዘር ቦታ ማጣበብ ይሆናል እንጂ መዘርዘር ይቻላል። ከየትኛውም ቅርንጫፍ ሆነው የሰናይ አባላት በንቃትና በብቃት  ይሳተፉ ነበር።
ለብዙ ዓመታት በርካታ ሥራዎችን የሰራውና  አያሌዎችን ያፈራው “ሰናይ አማተር የጋዜጠኞች ማህበር” የት ገባ? ምን ሆነ? አሁን የለም አይደል?
እኔ አንድ በኩራት ልነግርሽ የምፈልገው ነገር  ብዙ ተተኪዎችን አፍርቻለሁ፡፡ ቅድም ከሰናይ የወጡትን የተወሰኑትን ብቻ ነው የጠቀስኩልሽ። ለምሳሌ የደቡብ ወሎ ዞን የኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ኢያሱ ዮሃንስ፣ የሰናይ ልጅ ነው። የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ ሰለሞን ይመር፣ የሰናይ ልጅ ነው። የዞን አስተዳዳሪ እስከመሆን የደረሱም አሉ። ለምሳሌ የደሴ ከተማ ጸረ-ሙስናና ስነ-ምግባር ጽ/ቤት ውስጥ ትዕዛዙ እንግዳ የሚባል ልጅ በሃፊነት አለ፣ እሱም ከሰናይ የወጣ ነው። እንደዚህ እያልኩ ብጠቅስልሽ በርካቶች ናቸው። ሰናይ ባሳያቸው ብርሃን ራሳቸውን ለመለወጥ ባሳዩት ትጋት፣ በሃላፊነት ሀገራቸውን እያገለገሉ ያሉ በርካቶች የወጡበት ነው- ሰናይ። በነገራችን ላይ ይህ ማህበር በርካታ ሀብትም የነበረው ነው። ኢንሳይክሎፒዲያ መጽሐፍ፣ ጠረጴዛዎች፣ ወንበሮች፣ ቴሌቪዥን፣ ሞንታርቦ፣ ኪቦርድና ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎች ወዘተ… ነበሩት። እኔ በወቅቱ ሁሉንም አስረክቤአለሁ።
ለማን ነበር ያስረከብከው?
ለተተኪዎች አስረክቤያለሁ፡፡ እነዛ የተካኋቸው ልጆች እኔ ስሄድ በነበረው መንገድ መቀጠል አልቻሉም። አብዛኞቹ ወደ ራሳቸውና ወደ ግል ህይወታቸው አዘነበሉ። በትርፍ ጊዜያቸው በጎ ለመስራት ጊዜ ማጣት ይሁን ፍላጎት ማጣት አላውቅም፡፡ እኔም ተመልሼ መግባት አልቻልኩም። በዚህ አይነት ለበርካታ ጊዜያት ቆሞ ነበር።
አሁን ሰናይ እንዲያንሰራራ እንቅስቃሴ ጀመርክ ልበል? ምክንያቱም በዚሁ ጉዳይ ኮምቦልቻ እንደነበርክ ነግረኸኛል?
አሁን ሰናይን ለማንቀሳቀስ ሥራ ጀምሬያለሁ። በምን ምክንያት ጀመርክ ብትይኝ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዜና አንባቢው ጋዜጠኛ መሰለ ገብረህይወት አማካኝነት ነው። መሰለ “የሚዲያ አመራር” የተሰኘ መጽሐፉን ደሴ ሲያስመርቅ፣ ፕሮግራሙን ያዘጋጀሁለት እኔ ነበርኩኝ። ለዚህ ሥራዬ “ለዋልክልኝ ውለታ” ብሎ የወርቅ ሀብልና ካባ በልዩ ሁኔታ ከሸለመኝና ካመሰገነኝ በኋላ፤ “እባክህ እኛን እንዳፈራህ ሌሎች ተተኪዎችንም አፍራልን” በማለት ጥያቄ አቀረበልኝ። መሰለ ይህንን ጥያቄ በሚያቀርብልኝ ሰዓት የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝም ነበሩ። እነሱ ከጠየቁኝ ይህን ማድረግ አያቅተኝም በሚል አንድ 20 እና 30 ልጆች ለማሰልጠን ነበር ፍላጎቴ። ይሁን እንጂ ከ130 በላይ ሰልጣኞች መጡ። “ተተኪን ፍለጋ” በሚል መርህ ክረምት ላይ ሁሉንም አሰልጥነን አስመርቀናል። በዚህ ስልጠና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል  ማሪዎችም ተካፍለዋል።
የምን ያህል ጊዜ ሥልጠና ሰጣችኋቸው?
የሁለት ወር ስልጠና ነው። ይህንን ስልጠና የወ/ሮ ስህን የፖሊቴክኒክ ኮሌጅ፣ የደሴ ከተማ የተቀናጀ የልማት ማህበር እና የእኔ ድርጅት “መላኩ አምባው የማስታወቂያ ሥራዎችና ኢቨንት ኦርጋናይዘር” በመተባበር ነው የሰጠነው። ሰልጣኞቹን ካስመረቅን በኋላ ልጆቹን ምን እናድርግ የሚል ጥያቄ መጣ። ተማሪው ወደ ት/ቤቱ ሄደ፣ ስራ ያለውም ወደ ስራው ገባ ስራም ትምህርትም የሌላቸውና መሃል ላይ የቀሩትን አየን፡፡ እነዚህ ልጆች አንድም ትምህርት ጨርሰው የተቀመጡ ሁለትም ትምህርት ያቋረጡ ነገር ግን መስራት የሚችሉ ሆነው ስናገኛቸው አንድ ነገር ማድረግ አለብን አልንና ፣በየወሩ የሚካሄድ “የጥበብ ውሎ በስህን” የሚል የኪነ-ጥበብ ዝግጅት ጀመርን። ይህ ዝግጅት ወር በገባ በመጀመሪያው ቅዳሜ በወ/ሮ ስህን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የሚካሄድ ነው። እነዚህ ሰልጣኞች በዚህ ኪነ-ጥበብ መሰናዶ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በነገራችን ላይ እነዚህ ልጆች ከኪነ-ጥበብ ዝግጅቱ በተጨማሪ በራሳቸው ተነሳሽነት አስደናቂ ስራዎችን እየሰሩ ነው። ለምሳሌ የ2014 ዓ.ም የቡሄ በዓል በከተማችን በድምቀት እንዲከበር አድርገዋል። በደሴ ከተማ እስከዛሬ ከተደረገው የደም ልገሳ በእጅጉ የላቀ የደም ልገሳ እንዲካሄድ አስተባብረዋል፤ ቀስቅሰዋል፣ ለግሰዋል። በሌላ በኩል፤ ላለፉት 90 ዓመታት ሳይስተጓጎል የቀጠለ መሃል ፒያሳ ላይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ የሚከናወን የባንዲራ መስቀል ሥነ ሥርዓት አለ፡፡
ይህ ሥነ-ስርዓት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፤ እነዚህ ወጣቶች ይህን ሥነ-ስርዓት የማስቀጠል ስራም ሰርተዋል። ወደ 200 ያህል የጎዳና ልጆችን ሰብስበው ጸጉራቸውን ቆርጠው፣ ገላቸውን አጥበውና ልብስ ቀይረው ምሳ አብልተው በሙዚቃ ካዝናኑ በኋላ እነዚህን የጎዳና ልጆች ምን መሆን ትፈልጋላችሁ?” ብለው ሲጠይቋቸው፤ “ኢንጂነር፣ ፓይለት፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ ሃኪም መሆን እንፈልጋለን” ይላሉ። እንግዲህ ለጎዳና ተወዳዳሪዎች፣ ለአቅመ ደካሞች ተብለው የተቋቋሙ ብዙ ድርጅቶች ይሰራሉ። እነዚህ ድርጅቶች ቢደግፏቸው፣ ተምረው መለወጥና ለሀገር ለወገን ጠቃሚ ዜጎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ስናስብ፣ ሰብሳቢ በማጣታቸው በጣም ነው የምናዝነው።
በአጠቃላይ “ተተኪን ፍለጋ” በሚል በክረምት ያሰለጠንናቸው እነዚህ ወጣቶች፣ በራሳቸው ተነሳሽነት በራሳቸው ሀሳብ እየሰሩ ባሉት ስራ በእጅጉ እየተደነቅኩ ነው። የሚገርምሽ ነገር እዚህ ከተማ ውስጥ ከብሔራዊ ቤተ-መንግስት ቀጥሎ መርሆ ቤተመንግስት (መርሆ ግቢ) የሚባል አለ። በርካታ ቅርስና ንብረት በውስጡ ነበር። በቅርቡ በተካሄደው ጦርነት ተዘርፎ እንዳልሆነ ሆኗል። እነዚህ ሰልጣኞች ምናልባት በከተማው ህዝብ እጅ የገቡ ቅርሶች ካሉ ቤት ለቤት እየዞሩ ለማስመለስ ቃል ገብተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የተራራ ላይ ጉዞ (ሀይኪንግ) እና ሌሎች በአካባቢው ተሰርተው የማይታወቁ አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠርና በማዘጋጀት የከተማው ወጣቶች ከገቡበት ሱስና ብልሹ ተግባር እንዲወጡ በማድረግ ፣አርአያነት ያለው ስራ እየሰሩ ይገኛሉ። በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ። እነዚህ 125 ወጣቶች ናቸው ይህን ተዓምር እየሰሩ ያሉት። በስልጠናው የተሳተፉ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ተማሪዎችም ባሉበት የመልካም ምግባር ምሳሌ ለመሆንም ቃል ገብተው ነው የሄዱት።
እንደሚታወቀው ሰናይ የተመሰረተው በ1986 ነሃሴ ወር ላይ ነው፡፡ በ2016 ዓ.ም ነሀሴ ወር ላይ ድፍን 30 ዓመት ይሞላዋል ማለት ነው። በዓለም ዙሪያ ያሉትም ሆነ በአገር  ቤት  የሚገኙት የሰናይ ፍሬዎችን ሰብስበህ ለምን 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ከጥሩ ትዝታ ጋር አታከብሩም?
ትልቅ ሀሳብ ነው ያነሳሽው። ሀሳቡን ስታነሺ ሁሉ እንደ ውስጥ አዋቂ ነው የሆንሽብኝ። ያለውን ነገር እንደኮረኮርሽ ነው የሚሰማኝ። እንደነገርኩሽ የተመሰረተው በ1986 ዓ.ም ነሃሴ 21 ቀን ነው፡፡  ወደፊት አንድ ዓመት ስንጨምርበት 30 ዓመት ይመጣል። አሁን ላይ ይህን ስራ እንስራ የሚሉ ጥያቄዎች እየመጡ ነው ያሉት። በመንግስት አካላትም ሰናይ እንዲመለስ በተለያዩ ስብሰባዎች ህዝቡ ይጠይቃል። ምክንያቱም ሲሰራ የነበረውን ነገር ስለሚያውቅ እንደዛሬ ሚዲያ በበዛበት ሳይሆን ባልነበረበት ጊዜ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ሲያገለግል ነበር። ባልሳሳት ብላታ ህሩይ ወልደ ስላሴ ይመስሉኛል  “አዕምሮ”” ጋዜጣን በእጃቸው ይፅፉ የነበሩት እኛም “የሰናይ ድምፅ” የተሰኘ ጋዜጣችንን በእጃችን እየጻፍን በነፃ እንሰጥ ነበር።
በዚህ አጋጣሚ አንድ ሰው ላመስግን። የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ወ/ሮ ሙሉወርቅ ያንን አይተው ተደንቀው ነው፣ የመጀመሪያውን ጋዜጣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ በነጻ እንዲያትምልን ያደረጉት፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ጋዜጣውን በየአመቱ ማስቀጠል የቻልነው።
ላቋርጥህና እነዚያ በእጃችሁ ትጽፏቸው የነበሩት ጋዜጦች በዶክሜንትነት ይኖሩ ይሆን?
አሉ! ነገር ግን በአያያዝ ጉድለት የተጎዱም ይኖራሉ። እኛ ያልሽውን 30ኛ ዓመት በዓል ከየቦታው ያሉ የሰናይ ልጆችን አሰባስበን ስናከብር፣ በኤግዚቢሽን መልኩ ለእይታ እናበቃቸዋለን፡፡ በሰላም ያድርሰን እንጂ። በነገራችን ላይ በዛ ወቅት መደበኛ አባል፣ ተባባሪ አባል፣ የሩቅ አባል የሚል የተከፋፈለ የአባልነት ደረጃ ነበረን። እነዚህን አባላት ሁሉ ጋብዘን አንድ ታላቅና አስተማሪ የሆነ ፕሮግራም ለማዘጋጀት ዕቅድ አለን። ይህ እንዲሳካ ግን ብዙ ድጋፍ ያስፈልጋል። ይህን የተቀደሰ ሀሳብ ለመደገፍ ከጎናችን የሚሆኑ አካላት ብናገኝ ደስ ይለናል።
ደሴ ከተማ መሀል ፒያሳ ላይ ላለፉት 90 ዓመታት ሳይቋረጥ የቆየ የባንዲራ ማውረድ ሥነ-ስርዓት  እንዳለና አንዱ የከተማዋ መገለጫ እንደሆነ ይነገራል። እስኪ የባንዲራ አወራረድ ሥነ-ስርዓቱ ምን ይመስላል? ለጥቂት ጊዜ ተቋርጦ ያሰለጠናችኋቸው “ተተኪን ፍለጋ” ወጣቶች ማስቀጠል መቻላቸውንም ነግረኸኝ ነበር፡፡ እስኪ በዚህ ላይ ቆይታ እናድርግ?  
የታሪክ መዛግብት እንደሚያመለክተው፤ ጣልያን ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ ከ1928 ዓ.ም ጀምሮ ሲታሰብ 89 ዓመት ነው የሚሆነው። ነገር ግን ከዚያ በፊት የነበሩት ሲቆጠሩ ከ90 ዓመት በላይ ነው፡፡ ይህ የባንዲራ ማውረድ ሥነስርዓት ከአያቶቻችን፣ ከአባቶቻችን በትውልድ ቅብብሎሽ የመጣ ዕሴት ነው፡፡ ደሴ ወግ ማዕረግ ባለው የባንዲራ ማውረድ ሥነ ሥርዓቷ አይደለም በኢትዮጵያ፣ በውጪው ዓለምም ትታወቃለች፡፡ ከመገለጫዎቿ አንዱ ነው ማለትም ይቻላል፡፡ ልክ ምሽት 12 ሰዓት ሲሆን ፊሽካ ይነፋል፤ ማንም ሰው አይንቀሳቀስም፡፡ አሽከርካሪም ከመኪና ወርዶ ክብር ይሰጣል፡፡ አንዳንድ ለጉዳዩ አዲስ የሆኑ እንግዶች ቢኖሩ እንኳን ህብረተሰቡ አስረድቶ ያስቆማቸዋል፡፡
ሌላው ቀርቶ ትልቅ ሸክም በትከሻው ተሸክሞ የሚሄድ ሰው እንኳን ፊሽካ ሲነፋ ከነሸክሙ ይቆማል እንጂ አይንቀሳቀስም። ይሄ የሰንደቅ አላማ ክብር ከአያቶቻችን ጀምሮ የመጣና የቀጠለ መልካም ባህላችን የደሴ ከተማና የህዝቧ መገለጫ ነው፡፡ ለምን ነበር የተቋረጠው ላልሽኝ፣ በጦርነቱና አንዳንድ እዚህ ልገልፃቸው በማልችላቸው ምክንያቶች ነበር የተቋረጠው፡፡ የሰናይ “ተተኪን ፍለጋ” ወጣቶች እንዲቀጥል እንፈልጋለን ብለን ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ አቀረብን፡፡ ትንሽ የሚያወዛግቡ ነገሮች ነበሩ፡፡ “እናንተ አግዙን፤ እኛ ሀላፊነት እንወስዳለን” አልናቸው፡፡
አንድ ሳምንት ሙሉ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር እየተዘመረ፣ እኛም ድጋፍ እየሰጠን አስቀጠልን፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የባንዲራ ቀን ሲከበርም በድምቀት ተከበረ፡፡ ያንን የ90 ዓመት ታሪክ ማስቀጠል በመቻላችን በእጅጉ ነው የተደሰትኩት፡፡ ብዙ ሚዲያዎችም ሲዘግቡ የሰንደቅ አላማን ክብር በተመለከተ ደሴን በተምሳሌትነት እያነሱ ስለነበር ይበልጥ ተደሰቼ ነበር፡፡ እናም ወደ ደሴ የሚመጣ እንግዳ ይህንን ሥነ ሥርዓት ለማየት ይጓጓል፡፡ ያው አንቺም አንዱን ምሽት ፒያሳ አደባባይ የባንዲራ ማውረድ ሥነ ሥርዓቱን ታድመሽ የሚሰጠውን ስሜት አጢነሽዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ይህን ስነ ሥርዓት በማስፈፀም ሀላፊነት የወሰዱት የደሴ ከተማ አንደኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያና አራዳ ክፍለ ከተማ በመተባበር ሲሆን ፤ጠዋት 12 ሰዓት ይሰቀላል- ማታ 12 ሰዓት በክብር ይወርዳል ማለት ነው፡፡ እኛ ደግሞ እንደ ሰናይ “ተተኪን ፍለጋ” በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የነበረውን ሥነ ሥርዓት በማስቀጠላችን ኩራት፤ ፍቅርና ክብር ይሰማናለ፡፡
ብዙ ጊዜ ሰዎች ወደ ደሴ መምጣት ሲያስቡ እኔንም ጭምር ማለቴ ነው …“ያልተመረጠው ከንቲባ፣ የደሴ ቁልፍ በእጁ ያለው መላኩ አምባው-ነው” እንላለን፡፡ እዚህ እንግዶች ሲመጡ በመቀበል፣ በማስተናገድ፣ ሥራቸው እንዲሳካ ሁኔታዎችን በማሳለጥ፣ የብዙዎችን ሸክም ታቃልላለህና እስኪ በዚህ አስተዋፅኦህ ላይ በጥቂቱ አውጋኝ…?
በነገራችን ላይ በዚህ በእጅጉ ደስ ይለኛል። ይህን በማድረጌም ኩራት ይሰማኛል፡፡ ማንኛውም ሰው ወደ አካባቢያችን ሲመጣ ገና ከመነሳቱ በፊት ለእኔ ይደውላል፡፡ እንነጋገራለን። የሚፈልገውን ነገር፣ የሚሄድበትን ቦታ ይነግረኛል፡፡ በፕሮግራሙ መሰረት እቀበለዋለሁ፡፡ መሄድ ወደ ሚፈልግበት ቦታ እንዲሄድ አግዛለሁ፡፡ መረጃም ከፈለገ መረጃ እሰጣለሁ፡፡ በአጠቃላይ በእንግድነት የሚመጡ ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር በተቻለኝ አቅም አግዛለሁ፡፡
ለምሳሌ መጎብኘት የሚኖርባቸው ቦታዎች ካሉ እንዲጎበኙ አደርጋለሁ፡፡ በእኔ አቅም የሚፈልጉትን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡ ይህንን ለረጅም ጊዜ ሳደርገው ስለኖርኩ እንደ ባህል ወስጄዋለሁ፤ መገለጫዬም ነው፡፡ እነሱ ደሴን ብለው ሲመጡ እኔ ይቺን ትንሿን ነገር ማድረግ ካልቻልኩ፣ ንፉግነት ነው ብዬ ስለማምን የምችለውን አደርጋለሁ፤ እያደረግኩም ነው፡፡ እነዚህ ተስተናግደው የሄዱ ሰዎች ደግሞ እኔን ፕሮሞት ለማድረግና ለማመስገን የሚያደርጉት ጥረት የመንፈስ እርካታ ይሰጠኛል፡፡
እንደገና በተዋቀረውና በወሎ ዩኒቨርሲቲ ሥር በሚተዳደረው የወሎ ላሊበላ የባህል ቡድን ውስጥ የህዝብ ግንኙነትና የገበያ አፈላላጊ ሆነህ እየሰራህ ነው፡፡ አሁን  ቡድኑ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
ወሎ ላሊበላ የባህል ቡድን እንደምታውቂው ለ22 ዓመታት ፈርሶ ነበር የቆየው፡፡ እንደገና እንዲሰባሰብ ያደረገው ደግሞ የደቡብ ውሎ ዞን መስተዳድርና የደቡብ ወሎ ባህል ቱሪዝም ፅ/ቤት ነበሩ፡፡ እነሱ ማስቀጠል ያሰቡት ግን በበጀትና በፕሮግራም አልነበረም፡፡ ስለዚህ በ2009 ዓ.ም ቡደኑ እንደገና ሊፈርስ ሲቃረብ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ተረከበው፡፡ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ኢንተርፕራይዝ የላኮመልዛ የንግድ ስራ ማማከር ተረክቦት በዩኒቨርሲቲው ስር እየተንቀሳቀሰ ነው ያለው፡፡ እንግዲህ በ2005 ዓ.ም ተሰባሰቦና እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ በዞኑና በባህል ቱሪዝሙ ሲተዳደር ቆይቶ እንዳልኩሽ፣ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ስር ነው ያለው። እስካሁን የሰራናቸው ሥራዎች በበዓላት ወቅት ድምቀት በመስጠት፣ በተለያዩ ቦታዎች ማለትም በዞን፣ በክልልና  በፌዴራል ደረጃም ጥሪ በሚደረግበት ሰዓት ጥሪዎችን ተቀብሎ በመሄድ ቱባውን የወሎን ባህል ከምንጩ ከቋቱ. ሳይበረዝ ሳይከለስ  በማስተላለፍ የተሰጠውን ሀላፊነት እየተወጣ ይገኛል፡፡
የወሎን ቱባ ባህል ከምንጩ ለሌሎች ለማስተላለፍ በሙዚቃ፣ በቴያትር ወይም በስነ ፅሁፍ ሊሆን ይችላል። በውዝዋዜም በግጥምም ሊሆን ይችላል፣ ግን ቡድኑ በተለይ በሙዚቃው በኩል እስካሁን ወደ 32 አባላት ሆነን ነበር የምንሰራው፡፡ ነፍሳቸውን ይማርና ብቸኛዋና የመጀመሪያዋ ማሲንቆ ተጫዋች ፋንታዬ ተሰማ፣ ማሲንቆ ተጫዋች ጋሽ አራጌ ይማሞ፣ የማሪቱ ለገሰ ወንድም አሰፋ ለገሰን በሞት አጥተናል፡፡ በተጨማሪም የማሪቱን አስመስላ የምትዘፍነውን ድምፃዊት አለም ውቤን በድምሩ አራት አባላትን  አጥተናቸዋል፡፡ ከትልልቆቹ ሙሃመድ ይመር (ከመከም) በህይወት አለ፡፡ የሙዚቃ ግጥምና ደራሲ እንዲሁም አቀናባሪ ዳምጤ መኮንን (ባቢ) አለ፡፡ ባቢ በሀገራችን ላሉ እውቅ የባህል ሙዚቃ ዘፋኞች ከ800 በላይ ግጥምና ዜማ በመስራት አንቱታን አትርፏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቡድኑን በአስልጣኝነት እየመራ ይገኛል፡፡
በመጨረሻ በጦርነቱ ስለተጎዳችው የደሴ ከተማ በጥቂቱ ብትነግረኝ …
እስካሁን በእውነቱ እንከን የለሽ ጨዋታ ተጨዋውተናል፡፡ ደሴ በወሬ ብቻ ሳይሆን የእውነት የፍቅርና የመከባበር ከተማ ናት፡፡ አንቺ አንድ ጥያቄ ጠይቀሽኝ ነበረ “አንድ ቤት ውስጥ እናት ሙስሊም፣ አንዱ ልጃቸው ኦርቶዶክስ፣ አንደኛው ልጃቸው ደግሞ ፕሮቴስታንት ሆነው ያለ አንዳች ኮሽታ በፍቅር እንደሚኖሩ ሰይድ የሱፍ የሚባል ጓደኛዬ ነግሮኝ ነበር፡፡ እውነት ነው ወይ?” አልሽኝ፡፡ አዎ! እውነት ነው፡፡ ከፈለግሽ እንደዚህ አይነት ቤተሰብ ብዙ አለ፤ ልወስድሽ እችላለሁ፡፡ የሀይማኖት መከባበር የሚለው ወሬ አይደለም፤ ሰዎች በተግባር እየኖሩት ነው፡፡ ፍቅር አለ፡፡ ህዝቡ ገራገርና የስራ ሰው ነው፡፡ ይህቺ ከተማ በጦርነቱ ተዘርፋለች፤ ብዙ ጉዳት ደርሶባታል፡፡ ህዝቡም ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ውስጥ ነበር፡፡
አሁን ላይ ይህንን የህዝቡን ጉዳት የሚረዱ አመራሮች መጥተው፣ ከተማዋንም ህዝቡንም ከስብራት እየጠገኑ ስለሆነ በእጅጉ ደስተኞች ነን፡፡ አሁን ከእኛ የሚጠበቀው በከተማዋ ውስጥና በዙሪያዋ ያሉ መስህቦቿን ማስተዋወቅ ፣ስለቱባ ባህሏ ለአለም መንገር፣ ለዚያ የሚጋብዙ ስራዎችም መሥራት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ እኛም በኪነ ጥበቡ ወጣቱን በማነቃቃት  “የጥበብ ውሎ በስህን” የሚለውን የኪነ ጥበብ መሰናዷችንን ለ8ኛ ጊዜ አካሂደናል።
ከአዲስ አበባም ከዚሁ ከከተማዋም ወጣቱን የሚያነቁ የሚያስተምሩ ልሂቃንን በእንግድነት እየጋበዝን የሚጠበቅብንን እየሰራን እንገኛለን። ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ ደግሞ ሁሉም መልካም ይሆናል፡፡ እኔም አዲስ አድማስ ጋዜጣን፣ አንቺንም ጭምር ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ለምሳሌነት የሚበቃ ተግባር ሰርተሃል፤ ለአንባቢው የምታቀብለው ቁም ነገር አለ ብለሽ እንግዳ ስላደረግሽኝ በእጅጉ ተደስቻለሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡


Read 1634 times