Saturday, 28 January 2023 21:06

በስዊድን ለዳንስ ፈቃድ ማውጣት ሊቀር ነው

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 የዳንስ ፈቃድ ለማግኘት 4ሺህ ብር ይጠየቃል!  


እንግዲህ የትኛውም መንግስት በተፈጥሮው የመከልከልና የመቆጣጠር አባዜ እንዳለበት ይታወቃል፡፡ በተለይ ደግሞ አምባገነን መንግስት ሲሆን ይብሳል፡፡ በዓለም ላይ የኮቪድ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ፣በርካታ መንግሥታት “የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት” በሚል ሰበብ ዜጎች ከቤታቸው እንዳይወጡ፣ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ፣ ወደ መዝናኛ ተቋማት ድርሽ እንዳይሉ ጥብቅ ህግና መመሪያ አውጥተው ነበር - በገንዘብና በእስር የሚያስቀጣ፡፡ ቤተ አምልኮ ለመሄድ ሁሉ መንግስት  ካልፈቀደ አይሞከርም ነበር፡፡   
ከሰሞኑ ከወደ ስዊድን የተሰማው ዜና ያልተለመደ ነው፤ ግራ የሚያጋባ። “በስዊድን ለዳንስ ፈቃድ መጠየቅ ሊቀር ነው” ይላል። ለመሆኑ ለምንድን ነው ለዳንስ ፈቃድ የሚጠየቀው? ያውም በሰለጠነችውና በበለፀገችው አገረ ስዊድን!
አሶሼትድ ፕሬስ እንደ ዘገበው፤ በስዊድን ሬስቶራንቶች፣ የምሽት ክለቦችና ሌሎች የመዝናኛ ተቋማት ከመንግስት ፈቃድ ሳያገኙ የዳንስ ፕሮግራም ማዘጋጀት አይችሉም- ከባድ ቅጣት ይጣልባቸዋል፡፡ የመዝናኛ ተቋማት ደንበኞቻቸው እንዲደንሱ ከመፍቀዳቸው በፊት ራሳቸው ከመንግስት  ፈቃድ ማግኘት አለባቸው - የዳንስ ፈቃድ! (አይገርምም!?)
አሁን ታዲያ የስዊድን ወግ አጥባቂ ጥምር መንግስት፣ ለዳንስ ፈቃድ ማውጣት የሚጠይቀውን ለአስርት ዓመታት የዘለቀ አሰራር ሊያስቀር መሆኑ ተዘግቧል፡፡ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የተቀረጸው ፕሮፖዛል እንደሚለው፤ ለዳንስ ከመንግስት ፈቃድ መጠየቅ አያስፈልግም፡፡ ለፖሊስ ማስመዝገብ በቂ ነው - ያውም በቃል! ለምዝገባው የሚከፈል ገንዘብም አይኖርም - በፕሮፖዛሉ መሰረት፡፡
እስካሁን ባለው አሰራር በስዊድን ማንኛውም ሬስቶራንት፣ የምሽት ክበብ፣ የመዝናኛ ተቋምና ሌሎችም የዳንስ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ለማመልከት ቢያንስ 67 ዶላር (4ሺህ ብር ገደማ) መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡  
የዳንስ ፈቃድ ሳያወጡ ደንበኞቻቸውን ሲያስደንሱና ሲያስጨፍሩ የተያዙ የመዝናኛ ተቋማት ባለቤቶች  የንግድ ፈቃዳቸውን ሊነጠቁ ሁሉ ይችላሉ፡፡
የስዊድን ፍትህ ሚኒስትር ጉናር ስትሮመር  በሰጡት መግለጫ፤ “መንግስት የሰዎችን ዳንስ መቆጣጠሩ ተገቢ አይደለም፡፡” ብለዋል፡፡
አክለውም፤ “የዳንስ ፈቃድ ማውጣት የሚጠይቀውን አሰራር በማስቀረት፣ ቢሮክራሲውን እንዲሁም የንግድ ተቋም ባለቤቶችን ወጪ እንቀንሳለን፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡  
የስዊድን ሚዲያዎች ይህን “ጊዜ ያለፈበትና ሞራላዊ” ሲባል የቆየ የዳንስ ፈቃድ  የመጠየቅ አሰራር ለማስቀረት የተወሰደውን እርምጃ በአዎንታዊነት እንደተቀበሉት ተጠቁሟል፡፡  
መንግስት፤ አዲሱ አሰራር ከመጪው ጁላይ 1 ቀን 2023 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ እንደሚውል ጠቁሟል፡፡ በእርግጥ ከዚያ በፊት ረቂቅ ፕሮፖዛሉ በፓርላማው መጽደቅ ይኖርበታል። ያኔ በስዊድን ምድር ፈቃድ ሳይጠይቁ  እንደ ልብ መደነስ ይቻላል፡፡  ዳንስም ከመንግስት ቁጥጥር ነጻ ትወጣለች ማለት ነው፡፡






Read 1715 times