Saturday, 28 January 2023 21:16

ኢትዮጵያ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር ከ3 ዓመት በፊት AAHRUS 2019 Facts & Figures በሚል ርዕስ ልዩ የታሪክ መዝገብ አሳትሞ ነበር፡፡ ከ1973 እኤአ ጀምሮ  የተካሄዱትን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች በ147 ገፆች ይዳስሳል፡፡
ባለፉት 50 ዓመታት ሻምፒዮናውን ያዘጋጁ ከተሞች በአመዛኙ  ከአውሮፓ  አህጉር ናቸው። 25 የአውሮፓ ከተሞች ሻምፒዮናውን የማስተናገድ እድል አግኝተዋል፡፡
በ2026 እኤአ ላይ 45ኛውን የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና እንድታስተናግድ የተመረጠችው አሜሪካ በፊት በ1984ና በ1992 ላይ አዘጋጅ ነበረች፡፡  ከአፍሪካ ሞሮኮ በ1975 እና በ1998 አኤአ በራባትና በማራካሽ ከተሞቿ ሻምፒዮናን ሁለቴ በማዘጋጀት ግንባር ቀደም ናት፡፡ በ1996 ደቡብ አፍሪካ፤ በ2007 የኬንያዋ ሞምባሳ እንዲሁም በ2017 የኡጋንዳ ካምፓላ ከተሞች ሻምፒዮናውን አስተናግደዋል። ከኤሽያ ቻይና በ2015ና ጃፓን በ2006፤ ከመካከለኛው ምስራቅ በ2009 ዮርዳኖስ አዘጋጆች ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ በታሪክ መዝገቡ ላይ በከፍተኛ ውጤት  ዋናዋ ተጠቃሽ ናት፡፡ ከ175 በላይ አገራትን የሚወከሉ ከ12ሺ ሯጮች በላይ ባሳተፉት ያለፉት 43 ሻምፒዮናዎች 35 ጊዜ ተሳትፋለች፡፡ በአጠቃላይ 275 ሜዳልያዎች (105 የወርቅ፤ 108 የብርና 62 የነሐስ) በማግኘት በከፍተኛ ውጤት ኢትዮጵያን ከዓለም በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠችበት ነው፡፡ 424 ሜዳልያዎችን በሻምፒዮናው የሰበሰበችው  ኬንያ በተለይ በቡድን ውጤት ስኬታማ በመሆን  በመሰብሰብ ከዓለም አንደኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቶች በግል ያስመዘገቧቸው የላቁ ውጤቶችና የሜዳልያዎች ብዛት  ከዓለም ግንባር ቀደም ያደርጋቸዋል፡፡
በሻምፒዮናው ታሪክ በሁለቱም ፆታዎች ከፍተኛውን የሜዳልያ ስብስብ ክብረወሰኑን ይዘዋል፡፡
በግልና በቡድን ከሚቀርቡት የሜዳልያ ሽልማቶች ቀነኒሣ በቀለ 27 ሜዳልያዎችን (16 ወርቅ፣ 9 ብር ና 2 ነሐስ) በመሰብሰብ፤ እንዲሁም ወርቅነሽ ኪዳኔ 21 ሜዳልያዎችን (13 የወርቅ፣ 6 የብር እና 4 የነሐስ) በማግኘት  ከዓለም አንደኞች ናቸው፡፡
በከፍተኛ ውጤት እስከ አምስት ያሉትን ደረጃዎችም ኢትዮጵያውያኑ ተቆጣጥረዋል። በወንዶች ከቀነኒሳ ከፍተኛ ውጤት በኋላ    ገብረእግዚአብሔር ገ/ማርያም (6 የወርቅ፣ 7 የብርና 3 የነሐስ) 16 ሜዳልያዎች፤ ሐይሉ መኮንን (2 የወርቅ፣ 6 የብርና 5 የነሐስ) 11 ሜዳልያዎች፤ አሰፋ መዝገቡ (1 የወርቅ፣ 8 የብርና 2 የነሐስ)  11 ሜዳልያዎች እንዲሁም በቀለ ደበሌ(5 የወርቅ፣ 2 የብርና 2 የነሐስ) 9 ሜዳልያዎችን ተቀዳጅተው በታሪክ መዝገቡ ላይ ሰፍረዋል፡፡
በሴቶች    ደግሞ   ከወርቅነሽ በመቀጠል ጥሩነሽ ዲባባ (14 የወርቅና 6 የብርና) 20 ሜዳልያዎች፤  ጌጤ ዋሚ (9 የወርቅ፣ 8 የብርና 2 የነሐስ)  19 ሜዳልያዎች፤ መሰለች መልካሙ (9 የወርቅ፣ 4 የብርና 5 የነሐስ) 18 ሜዳልያዎች እንዲሁም መሪማ ደንቦባ (6 የወርቅ፣ 7 የብርና 2 የነሐስ)  15 ሜዳልያዎች በመጎናፀፍ ከዓለም ከፍተኛውን ስኬት አስመዝግበዋል፡፡
ቀነኒሳ በቀለ በሻምፒዮናው ያስመዘገባቸው አንፀባራቂ ታሪኮች ያስደንቃሉ፡፡  በግልና በቡድን 16 የወርቅ ሜዳልያዎች ወስዷል፡፡ በግሉም ከፍተኛውን ውጤት አስመዝገቦ ከዓለም አንደኛ ነው፡፡ በአጠቃላይ 13 ሜዳልያዎች 12 የወርቅና 1 የብር ሜዳልያ ተጎናፅፏል፡፡ ከ2002 እስከ 2006 እኤአ በተደረጉት 5 ሻምፒዮናዎች በአጭርና ረጅም ርቀት ደራርቦ በማሸነፍም ብቸኛው ነው፡፡
ደራርቱ ቱሉ  12 ሜዳልያዎች (6 የወርቅ፤ 5 የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያዎችን) አግኝታለች፡፡
መሪማ ደንቦባ 12 ሻምፒዮናዎችን እንዲሁም ጌጤ ዋሚና ጌጤ ኡርጌ  11 ሻምፒዮናዎችን በመሳተፍ ይጠቀሳሉ፡፡
በአንድ ሻምፒዮና ላይ በግልና በቡድን አራት የወርቅ ሜዳልያዎችን በማግኘት የተሳካላቸው ሰባት አትሌቶች ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ሐይሉ መኮንን 1999፤ ጌጤ ዋሚ 2001፤ ቀነኒሳ በቀለ ከ2002 እስከ 2006፤ ወርቅነሽ ኪዳኔ 2003ና 2005፤ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም 2004፤ ጥሩነሽ ዲባባ 2005 እንዲሁም መሰለች መልካሙ 2006 እኤአ ላይ ነው፡፡

Read 761 times