Saturday, 04 February 2023 18:18

“አገባሽ ያለሽ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ!”

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ መንገደኛ በፈረስ እየገሠገሠ ሳለ፣ አንድ ምስኪን አንድ እግሩ ጉዳተኛ ሰው ዳገቱን በእንፉቅቅ ሊወጣ አበሳ ፍዳውን ሲያይ ያገኛል። ያ ጉዳተኛ ሰው፤ “ወዳጄ እባክህ አፈናጥጠኝና እቺን አቀበት እንኳ ልገላገል” ይለዋል።
ፈረሰኛውም ከፈረሱ ወርዶ ያን እግረ- ጉዳተኛ ሰው ተሸክሞ ፈረሱ ላይ ያፈናጥጠውና መንገድ ይቀጥላሉ። ብዙም ሳይሄዱ ተፈናጣጩ፤
“ወዳጄ ካዘንክልኝ አይቀር እባክህ በተራ በተራ እንንዳ፤ ጉዳተኛው እግሬ ተቆልምሞ ስቃዬ ጭራሽ በረታብኝ” አለው።
ፈረሰኛውም አዝኖ፤
“ግዴለም! አንተ በፈረስ ዳገቱን ውጣ። እኔ በፍጥነት እርምጃ እየሮጥኩም ቢሆን እደርስብሃለሁ” ብሎ ወርዶ ፈረሱን ሙሉ በሙሉ ለቀቀለት።
በተባባሉት መሰረት ጥቂት ርቀታቸውን ጠብቀው ከተጓዙ በኋላ፣ ፈረስ የተዋሰው ሰው ፈረሱን ኮልኩሎ እንደ ሽምጥ ጋለበ።
ባለፈረሱ በማዘን በሩጫ እየተከተለው፤
“ወዳጄ ግዴለም ፈረሱን ውሰደው። ግን አንድ ነገር ብቻ ስማኝ?” ይለዋል።
ያኛው ተንኮለኛ ነውና እየጋለበ ባለፈረሱ ሮጦ የማይደርስበት ርቀት ጋ ሲደርስ፤
“እሺ፣ አሁን ልትለኝ የፈለግኸውን ነገር ንገረኝ” አለው።
ባለፈረሱም፤
“ወዳጄ ሆይ! ሌላ ምንም ነገር ልልህ አይደለም። አንድ ነገር ግን እለምንሃለሁ። ይኸውም፡-
“ይሄንን ዛሬ እኔን ያደረግኸኝን ነገር፣ አደራ ለማንም አትንገር። አለዛ ደግ የሚሰራ ይጠፋል” አለው ይባላል!!
*        *            *
ዱሮ በየሰው ቤት ግድግዳ ላይ በስክርቢቶም በፓርከርም በከረርም ተፅፋ የምትለጠፍ ጥቅስ ነበረች፡
“ጽድቅና ኩነኔ፣ ቢኖርም ባይኖርም
ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም!”
ዛሬም ውሃ  የምታነሳ ጥቅስ ናት!
በሌላ አቅጣጫና ገጽታውን ስናየው ደግሞ የፖለቲካ ክፋትና ደህንነት፤ የኢኮኖሚ ክፋትና ደህንነት፤ እንዲሁም የማህበራዊ ክፋትና ደህንነት የሚል ትርጓሜን እናገኝበታለን ማለት ይሆናል። በፖለቲካው ረገድ የጭካኔያችንን፣ የጦርነታችንን፣ የደም መፋሰሳችንን መጠን እንለካበታለን። በተቃራኒው ደግሞ የልግስናችንን፣ የሰብዕናችንን ስፋት እናመዛዝንበታለን፡፡ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ህዝብ እንዳይደርስ “አገቱ” የሚባለውን አይነቱን ዜና መመርመር ነው። ለማን ነው የሚታገሉት?  ለምን  አገቱት? ምን ይጠቀማሉ? ወዘተ እያሉ መጠየቅ ነው። የተቃውሞ እንቅስቃሴ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ መስኩ ላይ የሚያደርሰውን  ጉዳት ለማስተዋል መቼም ጭንቅላትን ይዞ ማሰብን አይጠይቅም። በባህሉም ረገድ እንደዚያው ነው። አብያተ ክርስቲያናቱ እንደምሽግ እንዳገለገሉ አይተናል።
አያሌ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የባሕል ፍጭቶችንና ደም-መፋሰሶችን በምስክርነት አይተን ስናበቃ፣ የተለመደው የሰላምና የድርድር ወቅት ሲከሰትም ማየታችን የማይታበል ሀቅ ነው! ድግግሞሹ አቋም እስከምናጣ ድረስ ለቋሳ አደረገን እንጂ ክስተቱንስ እንደ ፀሀይ መውጣትና መግባት ተዋህደነዋል። “ጣሊያን ሊማሊሞን በመድፍ ሲደበድበው አደረ” ቢለው፤ “ተወው ይበለው፣ እሱም መገተሩን አብዝቶት ነበር” አለው እያልን የምንሸሙር ሰዎች ያለንባት አገር ናት! መንግሥቱ ፀጥታውንና ሰላሙን ማስከበሩ ግዴታውና የሚያስጠይቀውም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በሌላ በኩል ግን ሌላው የህብረተሰብ ወገን ተገቢውን እገዛና ተሳትፎ ሊያደርግለት ይገባል የሚለውን እሳቤ በአግባቡ ማጤን የማንኛውም ወገንና ዜጋ ኃላፊነት መሆኑንም ማስተዋል ያባት ነው።
በሌላ መልኩ የሀገራችንን ሁኔታ ስናስተውል አሳሳቢውና አላባራ ያለው ሙስና ነው። በየመንግሥት መዋቅሩ ታማኝ ሰው መጥፋቱን የተሻለ ተብሎ የሚመደበው ሹም፤ “የምበላው ሳጣ፣ ልጄ ጥርስ አወጣ” እያሰኘን መምጣት ነጋ ጠባ እየመሰከርን ነው። የቀድሞው ቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ “እኛን ያስቸገረን የአማራ ተረትና የሶማሌ ባጀት ነው” ብለው ነበር ይባላል። አይ ዛሬ ባዩ!... የኢትዮጵያ ጠቅላላ ባጀት ራስ የሚያዞር መሆኑን በይፋ ይነግሩን ነበር። በጀቱ በራሱ ወንጀል የለበትም። ወንጀለኛው በጀት ያዡና ተቆጣጣሪው ነው። ገንዘብ  ሚኒስቴር፣ ፋይናንስ ቢሮ፣ አገር ውስጥ ገቢ፣ የፖሊስ ጣቢያዎችና ፍትሕ አካላት… ማን ከማን ይመረጣል። በጠቅላላ ሽንፍላ ማጠብ ነው! አሁንም ሰው መቀያየሩ፣ ሹም- ሽሩ፣ እርምጃና እሥሩ፣ ተግባራዊ መፈክር ነው። እስኪጠራ ድረስ  ሂደቱ መቋረጥ አይችልም። ዛሬም፡-
“… አገርህ ናት በቃ
 አብረህ እንቀላፋ፣ ወይ አብረሃት ንቃ!” እንላለን።
የውጪ አገር መንግስታት በእኛ ጉዳይ ውስጥ እጃቸውን ከማስገባት መቼም ቦዝነው አያውቁም- በቀጥታም በተዘዋዋሪም። “ብርድ ወዴት ትሄዳለህ?” ቢሉት “ወደለበሱት።” “የተራቆቱትስ?” ቢሉት፣ “እነሱማ የኔው ናቸው!” አለ አሉ። የምዕራብ አገሮች ብድር ራሳችንን እስክንችል ድረስ አይፋታንም። ስለዚህ ከገዛ ሕዝባችን ጋር በጽንዓት መቆም፣ በራስ መተማመንና መታገል ቁጥር አንድ ተግባራችን ነው - “አገባሽ ያለ ላያገባሽ፣ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ!” የምንለው ለዚህ  ነው።

Read 2690 times