Saturday, 04 February 2023 18:20

ከማህጸን ውጪ የሚፈጠር እርግዝና

Written by  ኃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

 ከማህጸን ውጪ ስለሚፈጠር እርግዝና ምንነት፣በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ከሆኑት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ ጋር ያደረግነውን ቆይታ በዚህ ጽሁፍ ለንባብ አቅርበናል።  
እርግዝና የወር አበባ በቀረ በ1 ሳምንት ግዜ ውስጥ ይታወቃል። ስለሆነም አንዲት እናት የወር አበባዋ ሲቀር በቀናት ውስጥ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ እርግዝና የተፈጠረበትን ቦታ ማወቅ ትችላለች። ይህም ከማህጸን ውጪ እርግዝና ከተፈጠረ እንዲታወቅ ያደርጋል። የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ እንደተናገሩት ይህ እርግዝና ያጋጥማቸዋል ተብለው የሚጠረጠሩ እናቶች ከሌሎች እናቶች በበለጠ መልኩ ለምርመራ መሄድ ይኖርባቸዋል። በዚህም ጽንሱ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ አስፈላጊውን ህክምና መስጠት ያስችላል። የከፋ ጉዳት ተብሎ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው እርግዝናው በተረገዘበት ከማህጸን ውጪ በሚገኘው ስፍራ ላይ ፈንድቶ ደም ሲፈስ ነው። ደም መፍሰስ  የእናትን ህይወት ወደ ማሳጣት ከፍ ሊል ይችላል።
95% ያህል ከማህጸን ውጪ እርግዝና የሚፈጠረው በማህጸን ቱቦ ላይ ነው። ከዚህም 70 % አምፑላ [Ampulla] በተባለው የማህጸን ቱቦ ክፍል ውስጥ ነው የሚከሰተው። እርግዝናው የሚፈነዳበት የጊዜ መጠን በቱቦው ውስጥ እንዳለው አቀማመጥ ይለያያል። ከማህጸን ውጪ የተፈጠረው እርግዝና በማህጸን ቱቦ አምፑላ [Ampulla] በሚባለው ላይ ከሆነ የወር አበባ በታየ ከ40 እስከ 50 ቀናት ውስጥ ሊፈነዳ ይችላል። ኢስመስ [Isthmus] ተብሎ በሚጠራው የቱቦው አካል ላይ ከሆነ ደግሞ በ6ኛ ሳምንት እርግዝናው ይፈነዳል። እንዲሁም ወደ ማህጸን ቀረብ ብሎ ባለው ክፍል ከተፈጠረ እስከ 10 ሳምንት ወይም እስከ 3 ወር ቆይቶ ሊፈነዳ የሚችል ሲሆን ይህም ጉዳቱን የከፋ ያደርገዋል። የእርግዝና ጊዜ [በቀን ወይም በወር የጽንሱ እድሜ] ሲጨምር የሚፈሰው የደም ብዛት ይጨምራል። ብዙ ደም ሲፈስ ደግሞ ቀዶ ጥገና ለመስራት አስቸጋሪ ስለሚሆን የእናትን ህይወት የማሳጣት ከፍተኛ እድል ይኖረዋል እንደ ባለሙያው ንግግር። ይህ ማለት ግን ከማህጸን ውጪ እርግዝና ያጋጠማቸው ሁሉም እናቶች ደም ይፈሳቸዋል ማለት አይደለም። ስለሆነም አስፈላጊውን ህክምና ለማግኘት የጽንሱ ጊዜ  ሳይጨምር ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ብቸኛው የመፍትሄ መንገድ ነው።
ከማህጸን ውጪ ለሚፈጠር እርግዝና የሚሰጠው ህክምና ጽንሱ እንዲቋረጥ ማድረግ ሲሆን አገልግሎቱ በተለያየ መንገድ ይሰጣል።
ጽንሱን በአልትራሳውንድ እና በላብራቶሪ ምርመራ ያለበትን ሁኔታ በመከታተል በራሱ ጊዜ እንዲቋረጥ ማድረግ[መጠበቅ]
በመርፌ በሚሰጥ መድሀኒት ህክምናውን መስጠት
በቀዶ ጥገና ጽንሱ ብቻ እንዲወጣ ማድረግ
ከማህጸን ሁለት ቱቦ ውስጥ ጽንስ የተፈጠረበት [የተጎዳውን] ቱቦ እንዲወጣ ማድረግ
እኤአ ከ936 እስከ 1013 [ከ1ሺ አመታት አስቀድሞ] አቡልቃሲስ [Abulcasis] የተባለ የህክምና ባለሙያ ከማህጸን ውጪ የሚፈጠር እርግዝና መኖሩን እንደጻፈ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ነገር ግን ምን አይነት ህክምና ይሰጥ እንደነበር የሚገልጽ ተጨባጭ ነገር የለም። ይህ ጽንስ ላጋጠማቸው እናቶች ህክምና መስጠት የተጀመረው ከ138 አመታት በፊት እኤአ በ1884 በእንግሊዛዊ የህክምና ባለሙያ ሮብርት ላውሰን [Robert Lawson] አማካኝነት ነው። ባለሙያው እርግዝና የተፈጠረበትን የማህጸን ቱቦ በቀዶ ጥገና ሙሉ በሙሉ በማውጣት ነበር ህክምናውን ይሰጥ የነበረው። ይህም የመጀመሪያው ከማህጸን ውጪ በሚፈጠር እርግዝና ላይ የተደረገ ቀዶ ጥገና ነው። ይህ የህክምና ባለሙያ በ4 አመት ውስጥ ከማህን ውጪ ለጸነሱ 42 እናቶች ቀዶ ጥገና ለመስራት ችሏል። እንደ ዶ/ር ሰኢድ ንግግር ሮበርተን ላውሰን የተባለው የህክምና ባለሙያ በቀዶ ጥገናው የ40 እናቶችን ማለትም 96% የሚሆኑትን ህይወት ማትረፍ ችሏል። ከዛን ጊዜ በፊት ይህ እርግዝና ካጋጠማቸው እናቶች መካከል 80% የሚሆኑት ህይወታቸውን ያጡ ነበር።
አንዲት እናት ከማህጸን ውጪ እርግዝና አጋጥሟት ህክምና ከተሰጣት በኋላ ወደ ቀደመ ጤንነቷ ትመለሳለች። በቀጣይም በማህጸን ውስጥ የመጸነስ እድል አላት። ነገር ግን በድጋሚ ከማህጸን ውጪ ለሚፈጠር እርግዝና የመጋለጥ እድሏ ሰፊ መሆኑን ዶ/ር ሰኢድ ተናግረዋል። እናም “በዚች እናት ላይ ዳግም ከማህጸን ውጪ እርግዝና እንዳይፈጠር የሚሰጥ ህክምና ይኖራል?” የሚል ጥያቄ ለዶ/ር ሰኢድ አራጌ አቅርበንላቸዋል። የህክምና ባለሙያው “እንዲስተካከል የምናደርገው የህክምና ዘዴ ባይኖርም በቀጣይ እርግዝናዋ ላይ ተጋላጭ መሆኗን ስለምናውቅ በድንገት ከማህጸን ውጪ እርግዝና ቢያጋጥም የቀደመ አይነት ጉዳት እንዳያጋጥም መከላከል ይቻላል” በማለት ምላሽ ሰተዋል።
ከማህጸን ውጪ የሚፈጠር እርግዝና ጽንስ ማደግ በማይችልበት ቦታ የተፈጠረ እና የእናትን ህይወት የሚቀጥፍ በመሆኑ ጽንሱ እንዲቋረጥ ይደረጋል። ነገር ግን በአለም አቀፍ፣ በአህጉረ አፍሪካ እንዲሁም በኢትዮጵያ ከማህጸን ውጪ የተፈጠሩ እርግዝናዎች ለረዥም ጊዜ ሳይቋረጡ ከሞቆየታቸውም በላይ እንደማንኛውም ልጅ ሲወለዱ ይስተዋላል። ይህ አጋጣሚ ስለሚፈጠርበት ሁኔታ ወይም ምክንያት የህክምና ባለሙያው እንዲያብራሩልን ጠይቀናቸዋል።
የጽንስ እና የማህጸን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ እንደተናገሩት እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ከእርግዝና ክትትል እና ከህክምና ተቋም ውጪ በወለዱ ወይም የእርግዝናው ወር ከገፋ በኋላ ወደ ህክምና ተቋም በሚሄዱ እናቶች ላይ የሚስተዋል ነው። ይህም ከህክምና ባለሙያዎች ውጪ የተፈጠረ ክስተት እንጂ በባለሙያዎች ይሁንታ [ተቀባይነት] ያገኘ አይደለም። በህክምና ባለሙያዎች ዘንድ ጽንሱ እንዲያድግ የሚፈቀድበት ምንም አይነት ምክንያት የለም። እርግዝናው ያለበት ቦታ ጽንስ ለእድገት የሚያስፈልገውን ነገር የሚያገኝበት ስላልሆነ እና ለእናትም ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትል ስለሆነ ነው የማይፈቀደው። ነገር ግን በዚህ ሁሉ ሁኔታዎች አልፎ ጤነኛ ልጅ የተወለድበት አጋጣሚ አለ። “እነዚህ ከብዙ አደጋዎች የተረፉ ጽንሶች እንደ ተአምር የሚቆጠሩ ናቸው ብለዋል ዶ/ር ሰኢድ አራጌ።
ከማህጸን ውጪ እርግዝና በተለያየ የሰውነት ክፍል ይፈጠራል። ከዚህም ውስጥ በሆድ እቃ ውስጥ የሚፈጠር እርግዝና አንዱ ነው። መረጃዎች እንደሚያስዩት ከማህጸን ውጪ ተረግዘው ከተወለዱ ጽንሶች መካከል በሆድ ውስጥ የተቀመጡ[የተፈጠሩ] ጽንሶች ቁጥራቸው ያመዝናል።
ከማህጸን ውጪ የሚፈጠር እርግዝና እንዳይከሰት ለመከላከል አጋላጭ ሁኔታዎችን ማስወገድ ይቻላል። ይህም ማህጸን ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች ማለትም ከማህጸን ውጪ ለሚፈጠር እርግዝና አጋላጭ ናቸው ተብለው የሚጠቀሱትን ነገሮች ማስወገድ ነው። ለአባላዘር በሽታ ላለመጋለጥ እራስን መጠበቅ፣ ሲጋራ አለማጨስ እና የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሀኒቶችን በአግባቡ መጠቀም በዋናነት ይጠቀሳሉ።
የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት ሰዎች ከማህጸን ውጪ ስለሚፈጠር እርግዝና የተሳሳተ ግንዛቤ አላቸው።  “ብዙ ሰዎች ከማህጸን ውጪ ስለሚፈጠር እርግዝና ያላቸውን ግንዛቤ ማስተካከል አለባቸው፣ ጽንስ ወራት ካስቆጠረ በኋላ ከማህጸን ውጪ ሊወጣ ይችላል ብለው የሚሰጉ አሉ” ብለዋል የህክምና ባለሙያው። አንድ እርግዝና ማህጸን ውስጥ የተፈጠረ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ካረጋገጡ በኋላ ከማህጸን ውጪ አይወጣም። በተመሳስይ ከማህጸን ውጪ የተፈጠረ እርግዝና ወደ ማህጸን ተመልሶ ሊገባ አይችልም። ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ሰዎች መጨናነቅ የለባቸውም የሚል ሙያዊ ምክር የህክምና ባለሙያው ለግሰዋል። ዶ/ር ሰኢድ አራጌ አክለው እናቶች ከህክምና ባለሙያዎች የሚሰጣቸውን ምክር በመስማት እንዲተገብሩ የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

Read 825 times