Saturday, 04 February 2023 18:26

የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ ጉዳይን የሚመለከት የድንበር ኮሚሽን ሊቋቋም ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

 ኢትዮጵያና  ሱዳን  የሚወዛገቡበትን “የድንበር ይገባኛል”  ጉዳይ የሚመለከት  የድንበር ኮሚሽን ለማቋቋም የሚያስችል ሥራ እየተሰራ  እንደሆነ ተገለፀ።
የድንበር ኮሚሽን የማቋቋሙ ተግባር በሱዳን ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፤ አገሪቱ  ከጅቡቲ ጋር ላላት የድንበር ይገባኛል ጥያቄም ተመሳሳዩን አካሄድ ለመከተል ዝግጅት እያደረገች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር   በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ   ኮሚቴ   አባላት የመሥሪያ ቤቱን  የስድስት ወር የስራ አፈጻጸም  ሪፖርት ትናንት   አቅርቧል ። ሪፖርቱን ለቋሚ ኮሚቴው አባላት  ያቀረቡት፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ  የዕቅድ ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተሩ አቶ አለማየሁ ሰዋገኝ ናቸው።
አቶ አለማየሁ  ለቋሚ ኮሚቴው አባላት  የመስሪያ ቤታቸውን የስድስት ወር የስራ  አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ከድንበር ይገባኛል ጋር በተያያዘ  ሱዳን  በኢትዮጵያ  ላይ ተደጋጋሚ ግጭቶችን ፣ ትንኮሳዎችንና  የጦርነት ጉሰማዎችን ስታደርግ ቆይታለች።   የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያለፉትን ስድስት ወራት ዕቅድ በሚያዘጋጅበት ወቅት ትኩረት ያደረገው በጎረቤት ሀገራት ላይ እንደሆነ ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፤  ባለፉት ስድስት ወራት  የድንበሩን ውዝግብ በውይይት ለመፍታት በርካታ ስራዎች መሠራታቸውንና  ከስምምነት ላይ መደረሱን  ገልጸዋል።
ቀደም  ሲል ከድንበር ውዝግቡ ጋር በተያያዘ በሱዳን በኩል የተለያዩ ትንኮሳዎች ከመፈጸማቸውም ሌላ  “ድንበሩ የእኛ ነው፤ መሬቱ የእኛ የሱዳናውያን  ነው፤ ይኼ  ያለቀ ጉዳይ ነው” የሚሉ ድምጾች ጎላ ብለው ይደመጡ ነበር ያሉት አቶ አለማየሁ፤ አሁን ግን ከዚያ በተቃራኒ  በሆነ ሁኔታና በሰከነ መንገድ መግባባት ላይ የሚደረስበት  ዕድል እንዳለ ጠቁመዋል። ይህንን ሁኔታም ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል  የድንበር ኮሚሽን ለማቋቋም  አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ    ኮሚቴ   አባላቱ  በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዕቅድ ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተሩ የቀረበውን  የመስሪያ ቤቱን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ካዳመጡ በኋላ  የተለያዩ ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል።
  “ከሱዳን ጋር ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?” በሚል ከቋሚ ኮሚቴው አባላት  ለቀረበው ጥያቄ  ምላሽ የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን፤ “ከሱዳን ጋር ወደ ከፋ ነገር ውስጥ ሳንገባ፣ የተደረሰው ስምምነት  የወጣንበት መንገድ፣ የደረስንበት ደረጃ፤ ቀሪውንም ችግር ለመፍታት የሚያስችል መሰረትን የጣለ  ነው”  ብለዋል ።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለበርካታ ዓመታት የይገባኛል ጥያቄ ሲነሳበት በቆየው የአል-ፋሽጋ አካባቢ ሳቢያ፤ እንደ አዲስ ውዝግብ ውስጥ ከገቡ ሁለት ዓመታትን አስቆጥረዋል። የውዝግቡ መንስኤ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ወታደሮች በቁጥጥራቸው ስር ይገኝ የነበረውን ስፍራ ለቅቀው ከወጡ በኋላ የሱዳን ወታደሮች በአካባቢው መስፈራቸው ነው።
ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት በአል-ፋሽጋ አካባቢ በተለያዩ ወቅቶች ውጊያዎች ሲካሄዱ እንደነበር ከስፍራው የሚወጡ ዘገባዎች ሲያመልክቱ ቆይተዋል። የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌፍተናንት ጄነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን፣ ከአንድም ሁለት ጊዜ አካባቢውን በመጎብኘት በስፍራው የሚገኘውን ጦራቸውን ማበረታታቸውም ይታወሳል። ኢትዮጵያ በበኩሏ፤ “በአካባቢው ያለው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ሊፈታ የሚገባው በንግግር ነው” የሚለውን አቋሟን በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።

Read 1505 times