Saturday, 04 February 2023 18:37

“ኦርቶዶክስን ማፍረስ ሀገርን ማፍረስ በመሆኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል” በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረው ድርጊት እንዳስጨነቃቸውና በቤተ ክርስቲያኒቱ የተፈጠረው ችግር  በቤተ ክርስቲያኗ የውስጥ ሕግና ስርዓት ብቻ ሊፈታ እንደሚገባ  በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን ገለጹ::
አምባሳደሩ  ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት   ቆይታ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ባህልና አንድነት  መሠረት የሆነችና የሀገሪቱን ታሪክ ሰንዳ ያቆየች ባለውለታ ናት ብለዋል።  
ሩሲያ እና ኢትዮጵያ የረጅም ዓመታት  የቆየ ግንኙነትና ትስስር እንዳላቸው ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ ለዚህም ጥንካሬ መንፈሳዊ ትስስሩ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በአሁኑ ሰዓት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይቀር እውቅና ያገኙበት እንቅስቃሴ ቢኖርም፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ግን በቤተ ክርስቲያኗ ለዘመናት የተሠራው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ቤተ ክርስቲያኗን “የአረንጓዴ አሻራ እምብርት” ያደርጋታል ብለዋል።
 በአሁኑ ሰዓት  ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለችበት ሁኔታ እጅግ  እንዳሳዘናቸውና እንደ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይነታቸውም  ጉዳዩ በጣም እንዳስጨንቃቸው የተናገሩት   አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን፤ ይህቺን ቤተ ክርስቲያን ማፍረስ ማለት ሀገር ማፍረስ ማለት  በመሆኑ  ከፍተኛ ጥንቃቄ  ማድረግ ያስፈልጋል  ብለዋል።
በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ በርካታ የፈተና ጊዜያት አልፈዋል ያሉት አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ከባድ ጊዜ እንደምታልፈው እምነታቸው  የፀና መሆኑን ተናግረዋል።
አምባሳደሩ በቆይታቸውም ጥያቄ ያነሳው አካልም “አጥቂ” እርምጃ ከመውሰድና ከመገንጠል ይልቅ ቅሬታውን በቀጥታ ለአባቶችና ለምእመናን ማሳወቅና በቤተ ክርስቲያኗ ሕግና ስርአት  መሄድ ይገባው ነበር ብለዋል። በቀጣይም ጉዳዩ  በራሷ በቤተ ክርስቲያኗ ሕግ መሰረት በውይይት እንዲፈታ ፍላጎታቸው መሆኑን  ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስቸጋሪ ጊዜ ላይ በሆነችበት ሰዓት የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ፓትርያርኳ በኩል ሀዘኗን በመግለጽ አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን ያስታወሱት አምባሣደሩ፤ ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናትም እንደቀደመው ጊዜ በመተባበር እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናንን ከቀድሞው በበለጠ ሁኔታ  አንድነታቸውን  ማስጠበቅና  በጽናት መቆም ይኖርባቸዋል ያሉት አምባሳደር ኢቭጌኒ፤ ይህ ሳይሆን  ከቀረ ግን በቀጣይ ትውልድ ሁሉ የሚያስጠይቅ ይሆናል፤ ብለዋል። “በዚሁ ሂደትም ከጎናችሁ እንደምንቆም ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።Read 2566 times