Saturday, 04 February 2023 19:44

መንግሥትና የህብረተሰብ አስተዳደር

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“--እንሆ ነፍስና ውሃ እንኳ ሳይቀሩ እንዲያገለግሏቸው አድርገው ድካማቸውን ከቀድሞው ያቃልላሉ፡፡ በነፍስየሚዘወር ወፍጮና በውሃ የሚዘወር የዕንጨት መቁረጫ መጋዝ ያበጃሉ፡፡--”

         የሚበልጥ ብዙ ነገር ይገኛል፡፡ ነገር ግን እንደዚህ የሆነበት ምክንያት ምን እንደ ሆነ በዘመናት ብዛት ተረስቶ ኑሮ ሊቃውንት እየመረመሩ፣ የመሬቱ መልክ ልዩ ልዩ የሆነበትን የያንዳንዱ አገር አየር ለብቻው የሆነበቱ ሁሉ በምን ምክንያት እንደ ሆነ ራሳቸው መርምረው ተረድተው ደግሞ ለዓለም ሕዝቦች ለማስረዳት ይጣጣራሉ፡፡
እውነትም የኤውሮፓ ሊቃውንት ስለዚሁም ነገር ብዙ ደክመዋል፡፡ ድካማቸው ግን ከንቱ አልሆነም፡፡ ታሪክ ሳይፃፍ የነበሩ ሰዎችና ሕዝቦች ምንስ ስማቸውና ሞያቸው በርግጥ ባይታወቅ ኑሯቸውም እንዴት እንደነበረ በዘመናቸውም የሆነው የአየርና የመሬት መለዋወጥ በምርምር ተለይቶ ታውቋል፡፡
የኤሮፓም ሊቃውንት በሚነግሩን መንገድ ከሄድን ዘንድ ሰው የዛሬውን ዕውቀትና የኑሮ ምቹነት ያገኘ ካንዱ ደረጃ ወዳንዱ ደረጃ እየወጣ ነው እንጂ ባንድ ጊዜ አይደለም፡፡
የሰውም አስተዳደር ከጥንት ከመሰረት እንዴት እንደ ነበረና እንዴትስ እየተለዋወጠ እንደ ሄደ በፍፁም እንድንረዳው ትልቁ ያሜሪካ ሊቅ ካሬ እንደ ፃፈው፤ ለምሳሌ አንድ ሰው ከነሚስቱ ለብቻው ተለይቶ ሌላ አጋዥ ሳይኖረው መሣሪያም አልባ ሆኖ ወዳንድ የባህር ደሴት መሰደዱን እናስብ፡፡
በመካከልም መሰናክል ነገር ካላገኘው የሱና የልጆቹ፤ የልጅ ልጆቹም ኑሮ በዘመናት ብዛት እንዴት  እየተለዋወጡና እየሰፋም እንዲሄድ በተራ አስተውለን እናስብ፡፡
ይህ የምናስበው ሰው ከነሚስቱ ባንድ ሰፊ አገር ውስጥ ብቻውን ሲሆን መሣሪያም ሳይኖረው ትዳሩ በመጀመሪያ እንዴት ያለ ኑሮ ኑሮት ይሆን። መቼም ደሴቱ ሰፊ ነውና እሱ ግን ሁለት ራሱን ብቻ ነውና የሄደ የሚመቸውን አይቶ ለትዳሩ የሚሆነውን ቦታና መሬት ሳይመርጥ አይቀርም፡፡ ፍሬያማውን መሬት እንዳያቀና ግን ትልልቅ ዛፎችና ቁጥቋጦ መልተውበታል፡፡ ወይም ደግሞ ትልልቅ ረግረግ ይሆንበታል፡፡ ዛፎቹንም ለመቁረጥ ቡቃዮቹንም ለመንቀል ረግረጎቹንም ለማድረቅ ጉልበትና መሣሪያ ያጣል፡፡
ደግሞም የደኑና የረግረጉ አየር ከነከታቴውም ለጤናው የማይመቸው ይሆናል፡፡ በእጁም የሚነቅለው ቁጥቋጦ ወዲያው እንደ ነቀለው ተመልሶ እንዳይበቅልበት ያስፈራዋል፡፡ ስለዚህም በተራራው አግድመት ያለው ገላጣ መሬት ዛፍና ብዙ ቁጥቋጦ የለበትም፡፡ ውሃም አይቆምበትም፤ ረግረግም አይሆንምና፤ ከዚያው ላይ የሚበቃውን መሬት አይቶ መሬቱንም ባንድ በትር ምሶ ፍሬ ይተክልበታል፡፡ ይህም የተከለው ፍሬ በመከር ጊዜ ዕጥፍ ሆኖ ይገባለታል፡፡
ይህንንም ፍሬ በሁለት ደንጊያ መካከል አድርጎ ይፈጨዋል፡፡ ባንድ ደንጊያም ላይ እንደ ቂጣ ዓይነት አድርጎ ጋግሮ ይበላዋል፡፡ የተከለው ፍሬ እስኪበቅልለት ድረስ ግን ሥራ ፈቶ ዝም ብሎ አይቀመጥም ይሆናል፡፡ ዐውቆ የበቀለውን የደን ፍሬ ለመሰብሰብ አውሬውንም ለመያዝ ወይም ለመግደል ወዲያና ወዲህ ሲመላለስ ይቆያል፡፡ እንዲህና እንዲህም ሲል ለራሱና ለሚስቱ የሚሆን የዕለት ምግብ ያገኛል። ይህም ሲሆንለት ኑሮው እየተሳለ ይሄዳል፡፡ የሚመቸውንም  አንድ ደንጊያ አይቶ መጥረቢያ እንዲሆንለት በሌላ ደንጊያ ይስለዋል፡፡ በብዙ ድካምም ዛፎቹን ይጥልበታል፡፡ ነገር ግን በጊዜ ብዛት የመዳብን ዐፈር ያገኛል፤ አቀላለጡንም እሱው ራሱ አስቦ ይማራል፡፡ በዚሁም ባዲስ ዕውቀቱ በጥቂት ድካም የተሳለ መጥረጊያ ለማበጀት ይችላል፤ ከመዳብም አንደኛ መናኛ ዶማ ያበጃል፡፡
በዶማውም መሬቱን አጥብቆ ወደ ውስጥ ዘለቃ ይቆፍረዋል፤ መሬቱም ደህና ሁኖ ስለ ተቆፈረ የሚዘራውንም ፍሬ ፀሐይ ያደርቀዋል፤ ጎርፍም ይወስደዋል ተብሎ እንደ ዱሮው አያስፈራም፡፡
መከሩም የተዘራውን ሦስት እጅ አኽሎ ሳይገባ አይቀርም፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ዚን ያለበትን ዐፈር ያገኛል፡፡ ዚኑንና መዳቡንም ባንድነት አጋጥሞ ቢያቀልጠው ብሮንስ ይሆንለታል። ከብሮንስም ከዱሮ የበለጠ መሣሪያ ያበጃል። ሥራውም በዚሁ ምክንያት ከዱሮው ይልቅ በጣም ይቀልለታል፡፡
ያንን በፊት በማይገባ መሣሪያ ሲቆፍረው የነበረውንም መሬት ከእንግዲህ ወዲህ አጥብቆ ሊቆፍረው ይችላል፡፡ ከፍሬያማውም መሬት ቡቃያ ከነበረበቱ ጥቂቱን በዚሁ ባዲሱ መሣሪያ ያቀናዋል፤ መሬቱንም በደህና ይቆፍረዋል። ቡቃያው እንደ ገና በቅሎ የዘራውን ፍሬ እንዳይውጥበት አያስፈራውም፤ በዚሁ መካከል መቼም ልጆች ይወልዳል፤ ልጆቹም ለሥራ ይደርሳሉ፡፡ የሱ ጉልበትና የልጆቹ ጉልበት ይተባበራል፡፡ ከመተባበራቸውም የተነሣ የበለጠ ሀይል ያገኛሉ፡፡ የሚያስፈልጋቸውንም ነገር ሁሉ፡፡ መሬት በሆዷ እንደ ያዘች ተረድተውታል፡፡ ለመሣሪያም የሚሆናቸውን ነገር ከመዳብና ከዚን የበለጠ ሌላ ነገር እንዲያገኙ ይመረምራሉ፡፡ እንሆም የብረት ዐፈር ያገኛሉ፤ ያቀልጡታልም፡፡ እንዲሁም ሆኖ ከሚወጣው ብረት ምንም እንኳ ጨርሶ ለጊዜው ባያምር እውነተኛ ብረት ያገኛሉ፡፡ ወዲያው ዶማና መጥረጊያ ያበጁና ሥራቸውን ከዱሮ ይልቅ በበለጠ ይሰሩበታል፡፡
እንግዲህም ይህ መጀመሪያ ስደተኛው ሰውዬ ከልጆቹ ጋር በተራራው አግድመት የነበረውን ትልቁን ጥድ ጥሎ እርሻውን ያሰፋል። በብረቱም ዶማ መሬቱን በጣም እስከ ውስጡ ድረስ ዘልቆ ይቆፍረዋል፡፡ የላይኛውንም ዐፈር ከታችኛው ዐፈር ጋር ያደባልቀዋል፡፡
ልጆቹም ልጆች ይወልዳሉ፤ የልጅ ልጆቹም ያድጉለታል፤ ከዚያም በኋላ ከልጆቹና ከልጅ ልጆቹ ጋር ሁኖ ብቻውን ሳለ ለመሥራት ያልቻለውን አሁን ግን ቤተ ሰቦቹን ይዞ ብዙ ሥራ ለመሥራት ይችላል፡፡
ቤተ ሰቡም እየበዛ ሲሄድ እያንዳንዱ ሰው የሚያገኘው ምግብ እየበዛ የያንዳንዱም ድካም እያነሰ ይሄዳል፡፡ ቤተ ሰቦቹም ከበዙ ዘንድ ሥራውን ይከፋፍሉታል፡፡ እኩሌቶቹ የእርሻን ሥራ ይሠራሉ፤ እኩሌቶቹም ደግሞ ብረትና መዳብ ዚንም የሚገኝበትን ዐፈር እያቀለጡ ልዩ ልዩ የሆነ ደህና ደህና መሣሪያ ይሰራሉ፡፡ እኩሌቶቹ ግን ደግሞ የተበላሹትን መሣሪያዎች እያሻሻሉ ያድሳሉ፡፡
ለእንክርዳድ መንቀያ የሚሆናቸውንም ራሳቸው መርምረው አንድ አዲስ ዐይነት ዶማ ይሰራሉ፡፡ ይህንንም አዲስ መሣሪያ ይዘው ትንንሾቹም ልጆች ቢሆኑ እንክርዳዱን በመንቀላቸው ማለፊያ አድርገው ሥራውን ይረዳሉ፡፡ ሰዎቹ እንደዚህም በመተባበራቸው ትዳራቸው እየሰፋ፤ እነሱም እየበረቱና እየተጠቀሙ ይሄዳሉ፡፡
እንግዲህም በሥራና ባሳብ እየተረዳዱ የጠነከረ መሣሪያ አብጅተዋልና ከተራራው አግድመት በታች ወዳለው ቁጥቋጦ ወደ በዛበት መሬት እርሻቸውን ለማስፋት ይወርዳሉ፡፡ ወርደውም ቁጥቋጦውን በእሳት ያቃጥሉታል። ከዚያም በኋላ ትልልቆቹን ዛፎች በመጥረቢያ ይጥላሉ፡፡ በጊዜም ብዛት ራሳቸው መርምረው በሬውን ለማሰራት ያስባሉ። በሬውም በጉልበቱ እንዲረዳቸው የሚረዳበትን መሣሪያ አስበው ያወጣሉ፤ ይህነንም መሣሪያ በጠረፍ አጋጥመው ከበሬው አንገት በእንጨትና በጠፍር ያስሩታል፤ ከዚያም በኋላ ያርሱበታል፡፡ እንሆ እንደዚህ ያለው መሣሪያ  ባልሰለጠኑት ሕዝቦች እስከ ዛሬ ድረስ ይኖራል፡፡
እንሆም ዱሮ በዶማ ዐስር ሰዎች ሲቆፍሩ ይውሉበት የነበረውን የእርሻ መሬት ኋላ ግን አንድ ሰው በሁለት በሬ አርሶት ይውል ጀመር። እንደዚህም ሲሆን እርሻቸው ከድሮው በጣም የተሻለ እኽል የሰፋም ይሆናል። የሰዎቹም ቁጥር እየበዛ ይሄዳል፡፡ በመሣሪያና በእኽል በልብስም ሀብታቸው ይበዛል፡፡ የሚኖሩበትም ቤት በጊዜ ብዛት የተሻለ ይሆናል፡፡
ያ በደሴት የገባው የመጀመሪያው ሰው ከነሚስቱ እንደ አውሬ በጉድጓድ ወይም በዋሻ ውስጥ ይኖር ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ዐውቆ የወደቀውን ዕንጨት ሰባስቦ አንዲት ጎጆ ሰራ። የመጀመሪያው ቤት መቼም መስኮትና የጢስ መውጫ አልነበረውምና ሰውዬው በብርድ እንዳልሞት ሲል በጢስ ውስጥ ታፍኖ ይኖር ነበር፡፡
ነፍሱም ሲበረታበት መዝጊያውንም ለመዝጋት የግድ እየሆነበት በጢሱ ውስጥ በጨለማ ሥራ እየፈታ ሲቀመጥ ነበር፡፡ ይህ ኑሮ ግን ለጤናው እጅግ የሚስማማው አልነበረም። ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ካደጉና ለሥራ ከደረሱ በኋላ ከእነሱ ጋር በህብረት ተጋግዞ ደህና መሳሪያ አውጥቶ ሃይሉ ሲሰፋለት አይቶ፣ ጥዱንና ዝግባውን ቆርጦ ፈልጦ የተሻለ ቤት ሰራ፡፡ የሚኖርበትም ቤት እየተሻለ ስለ ሄደ ቤተ ሰቦቹ እየተመቻቸው ይበዛሉ፡፡
ከመብዛታቸውም የተነሳ ባህሪያቸውና ሞያቸውም ይለያያል። እኩሌቶቹ በእርሻ የሰለጠኑ ይሆናሉ። ያውሬንና የከብትን ቆዳ እየፋቁ ልብስ ያበጃሉ። እኩሌቶቹም መሳሪያውን በማበጀት ይሰለጥናሉ። ከዚህም ስራ መከፋፈል የተነሳ የያንዳንዱ ሰው ድካም እየተቃለለ ይሄዳል፡፡ በዚህ ሥራ ብዛት ገንዘብ እየተረፋቸው ስለ ሄደ ለክፉ ቀን እንዲሆነን እያሉ ትርፉን ያከማቻሉ፡፡
እርሻቸውም ብዙ ፍሬ ከማይሰጠው አግድመት ወደ ፍሬያማው ሜዳና የወንዝ ዳር እየሰፋ ሲሄድ ሰዎቹም ደኑን መንጥረው ረግረጉንም አድርቀው እየዘሩ ከድሮው በጣም የተሻለ መከር ያገኛሉ፡፡ ለከብትም መሰማሪያ የሚሆን አይተው ደህና ግጦሽ ይለያሉ፡፡
እንሆም በጥቂት ድካም ከድሮው የበለጠ ስጋና ወተት፤ ቅቤም ቆዳም ለማግኘት ይሆንላቸዋል፡፡
በበታቹ ያለው ሜዳ የተሻለ የእርሻ መሬት ስለ ተገኘበት ያ ድሮ ሲታረስ የነበረው የተራራው አግድመት የእርሻ መሬት ለፍየልና ለበግ መሰማሪያ እንዲሆን ይለቀቅና ወደ አዲሱ የእርሻ መሬት ይወረዳል፡፡
ይህም ሁሉ ነገር እስኪሆን ድረስ ብዙ ትውልዶች አልፈዋል፡፡
አዲሶቹ ትውልዶች አባቶቻቸውና አያቶቻቸው ባከማቹት ሀብትና ዕውቀት ተጠቅመው ነበርና ለወደፊት የበለጠ ጥቅም እንዲያገኙ ራሳቸው መርምረው ለማግኘት በመጣጣር  ይሆንላቸዋል፡፡
እንሆ ነፍስና ውሃ እንኳ ሳይቀሩ እንዲያገለግሏቸው አድርገው ድካማቸውን ከቀድሞው ያቃልላሉ፡፡ በነፍስ የሚዘወር ወፍጮና በውሃ የሚዘወር የዕንጨት መቁረጫ መጋዝ ያበጃሉ፡፡ የዕንጨት ከሰልም የሚነድበትን የብረት ማቅለጫ ሸክላ ያበጃሉ፡፡
እንሆም ድሮ ብዙ ቀን የሚደከምበትን ጥቅም ባንድ ቀን ለማግኘት ይቻላቸዋል፡፡ ሕዝቡም በዝቶ የደሴቱን ተራራና ሜዳ ሁሉ እያቀና ይመላዋል፡፡
የሰዎቹም ቁጥር ሲበዛ ሥራቸውና ሞያቸው ዐይነቱ በጣም የተለያየ ይሆናል፤ አራሾች ሰፊዎች፤ ቤት ሰሪዎች፤ ብረት ሰሪዎች፤ የተባሉ ሞያ ሞያቸውን ይይዛሉ። ረግረጎች በሰው ብልኃት ይደርቃሉ፡፡



Read 994 times