Saturday, 04 February 2023 20:20

ወይ... አንድዬ እመጣለሁ ካለበት ቀድሞ ይምጣልን!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 “--ፈረንጅ “Everything comes with an expiry date.” የሚላት ነገር አለችው፡፡ አዎ ማንኛውም ነገር የማለቂያ ጊዜ አለው፡፡ ይቺ ሀገር እዚህም እዛም የማለቂያ ጊዜያቸው በዘመናት ባለፉባቸው ሀሳቦች ነው መከራዋን እየበላች ያለችው፡፡--”
          
          እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ለምን፣ ለምን ይሄ ሁሉ መከራ! ለምን ይሄ ሁሉ ስቃይ! ለምን ይሄ ሁሉ የማያልቅ ሰቆቃ!  ከወቅቱ ዋነኛ ጥያቄዎች አንዱ ለምን! ለምን! ለምን!  
ስሙኝማ...የማይክል ጃክሰን ትሪለር ቪዲዮን ታስታውሱታላችሁ! እናላችሁ... እዛ ላይ ከመሬት ውስጥ እየፈነቀሉ የሚወጡት አሉ አይደል! ዘንድሮ እኮ ልክ እንደዛ ከመሬት ውስጥ እየፈነቀልን የምንወጣ እየበዛን ነው እኮ የሚመስለው! ግን ደግሞ በየጓዳውና በየጎድጓዳው እየተደረገ ያለውን አንድዬ ይወቀው እንጂ አስቸጋሪ ነው የሆነው፡፡ በጣም አስቸጋሪ!
ሳሙና ተፈልቷል፤ ተወቅጧል እንዶዱ
ልብሳችሁ ሳያድፍ እጠቡ አትሂዱ፣
ትላለች አንድ ቅኔያዊ ስንኝ፡፡ ዋነኛው ወርቋ “ሰውን ለማጋጨት ተንኮለኛ ነገረኛ ከመሆን ተቆጠቡ፣” የምትል ነች፡፡
ይቺን ታሪክ ስሙኝማ...በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2013 የሆነ ነው፡፡ መሀመድ ሙርሲ ስልጣን ላይ የወጡ ጊዜ የሆኑ የሀገሪቱ ባለስልጣናት እነሱ በምስጢር ባሉት ተሰብስበው እያሴሩ ነበር፡፡ ባለስልጣናቱ በዛች ሀገር ኢስላማክ ሌበር ፓርቲ የሚባለውና በአሁኑ ጊዜ የፈረሰው የሞርሲ የፖለቲካ ቡድን አባላት ናቸው፡፡ አጄንዳቸው ደግሞ በወቅቱ ተገናኝተው ተጀምሮ የነበረው የኢትዮጵያው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ነበር። እናማ... ግድቡን ምን ብናድርገው ይሻላል እያሉ ነበር ሲያሴሩ የነበረው፡፡ አብዛኛዎቹ ባለስልጣናት ይሰጡ የነበረው ሀሳብ ለምን ሄደን በጄት አናፈራርሰውም የሚል ነበር፡፡ ሌላ ሀሳብ ሰጪ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አናሳ ህብረተሰብ ክፍሎችን የነጻነት ቡድኖችን በምስጢር መደገፍ አለብን ይላል፡፡
ሌላኛው ሀሳብ ሰጪ ደግሞ አፈትልኮ የወጣ ምስጢራዊ መረጃ ነው በሚል ግብጽ ለጦርነት ከፍተኛ የጦር መሳሪያዎች እየሸመተች ነው የሚል ወሬ እንልቀቅ ይላል፡፡ በመጨረሻ የስብሰባው መሪ የስብሰባውን ምንነት ለሚዲያ እንዳይገልጹ መሀላ መፈጸም አለብን ይላል። አስገራሚው ነገር ምን መሰላችሁ...እነሱ ሆዬ በምስጢር ተሰበሰብን ብለው ለካስ በቀጥታ በቴሌቪዥን እየተላለፈ ነበር፡፡ ለካስ ስብሰባውን ያሰናዳችው ሴትዮ ለተሰብሳቢዎቹ ቀጥታ ስርጭት እንደሚኖር አልነገረቻቸውም ነበር። በቀጥታ የማስተላለፉ ውሳኔ ላይ የተደረሰው በመጨረሻው ሰዓት ስብሰባው ሊጀመር ሲል ነው፡፡
እናማ ምን መሰላችሁ... በዚች ሀገር በሁሉም ነገር ከቦተሊካው እስከ ዕለት በዕለት ኑሯችን አልተሰማን እየመሰለን፣ አልታወቀብን እየመሰለን፣ ከሰው እንደበቅ ብንል እንኳን ገልጦ የሚያይ አምላክ መኖሩን እየረሳን ለዚች ሀገርና ለዚህ ህዝብ ክፉ ከፉውን የምናስብ ምነው በዛን! ይህች ሀገር እኮ ዘመንን አሻግረው፣ ትውልድን አሻግረው፣ ዛሬ የሚያደርጉት ለነገና ከነገ ወዲያ እንዲዘልቅ ወጥነው የሚንቀሳቀሱ ዜጎች የነበሯት ሀገር ነበረች እኮ! ለእከሌና ለእነእከሌ ብለው ሰይሆን፣ ለዚህኛው ቡድን ወይም ለዚያኛው ስብስብ ቡድን ብለው ሳይሆን፣ ለራሳቸው ብቻ ሊፈነጥዙበትና ትከሻ ሊያሳዩበት ብለው ሳይሆን ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ብቻ፣ ለኢትዮጵያውያንና ለኢትዮጵያውያን ብቻ ብለው የአክሱምን ሀውልቶች ያቆሙ፣ እነ ላሊበላን የፈለፈሉ፣ እነ ፋሲል ግንብን የመሳሰሉ ህንጻዎችን የሠሩ፣ እነ ሶፍ ኡመርን የመሳሰሉ የብስል አእምሮ ውጤቶችን  ለትውልድ ያስቀመጡ ዜጎች የነበሩባት ሀገር ነች እኮ! ግብጽን ከአንደኛው ማዶ፣ ደርቡሽን ከሌላኛው ማዶ፣ ጣልያንን ከዚያኛው በኩል፣ ዚያድ ባሬን ከዚህኛው በኩል እየመከቱ ህይወት እየገበሩ፤ ሀገር ያቆዩ ዜጎች ሞተው የተረፈረፉባት  ሀገር ነበረች እኮ!  እና አሁን ምን ተፈጠረ! እናማ... በገዛ ዜጎቿ ብርታት ስንትና ስንት መከራዎች፣ ከአንደኛው የዓለም ጥግ እስከሌላኛው የዓለም ጥግ ሲጎነጎኑ የኖሩ ሴራዎችን አልፋ እዚህ የደረሰች ሀገር፤ በገዛ ልጆቿ ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስባት ወይ “አንድዬ እመጣለሁ ካለበት ጊዜ ቀድሞ መጥቶ ይታደገን!” ማለት አንጂ ምን ማድረግስ ይቻላል!
ወይ አንድዬ እመጣለሁ ካለበት ቀድሞ መጥቶ እንደምንሆን ያድርገን!
እውቀት ነገራችንማ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የዘንድሮ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ውጤት ጉዳችንን አውጥቶ አፍረጠረጠው እኮ፡፡ ከቁሳዊ ድህነታችን ባለፈ የእውቀት ድህነታችን እኮ በፈረንጅ አፍ ‘ክሮኒክ’ ከሚባለው ደረጃም እያለፈ ነው! እንደው በየትኛው ሂሳብ ስሌት ነው ከአጠቃላይ ተፈታኞች ያለፉት አራት በመቶ እንኳን አይሞሉም ሲባል እንደ ሀገር ምናልባትም ፍራሽ አንጥፈን ብንቀመጥ አይበዛብን ይሆናል፡፡
ስሙኝማ... ያለንበት ሁኔታ እንደሌላው ጊዜ ‘ኖርማል’ የምንለው አይነት ቢሆን ኖሮ፣ በዚህ  ዜና ጎልቶ በሚታይ ደረጃ ያለመደንገጣችን በራሱ አስደንጋጭ ይሆን ነበር፡፡ ግን በእጅጉ የባሰ ምናልባት ሃገር እስከ ዛሬ ገጥመዋት ከነበሩት አደጋዎች ሁሉ የከፋ አደጋ መጣብን! እንደ ግለሰብ፣ እንደ ቤተሰብ፣ እንደ ማሀበረሰብ ብሎም እንደ ሀገር ሊመለስ የማይችል ጥፋት የሚያስከትል አደጋ፡፡ ከማንኛውም ጊዜ በላይ ብስለትን፣ አርቆ ማስተዋልን፣ ከራስና ከቡድን ከጎጥና ከመንደር አልፎ በአደገኛና እጅግ ኋላቀር በሆነ ሁኔታ እያጠበብን ያለነውን አእምሯችንን የግዳችንን አስፍቶ እንዲያስብ ማስገደድ ግድ የሚለን አደጋ፡፡ ከምንም ጊዜ በላይ ሁሉም ነገር ለእውነት፣ በእውነትና ስለ እውነት ብቻ መሆን የሚገባው ጊዜ ላይ ደርሰናል። በተለይ ደግሞ ትናንትናና ከትናንት ወዲያ ሌሎች ችግሮች ተፈቱባቸው የሚባሉ፣ ወይም ባይፈቱም ለጊዜው እንዲዳፈኑ የተደረጉባቸው መንገዶች አሁን በገጠመን ችግር ላይ ሊሠሩ አለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን ከተሞከሩ አደገኞች ሊሆኑ እንደሚችሉ አርቆ ማየቱ ሸጋ ነው፡፡
አልታየሁም፣ አልተሰማሁም ብሎ ነገር የትም አያደርሰም፡፡ በቴክኖሎጂ በአንዲት ስማርትፎን ብዙ ጉድ የሚሠራበት ዘመን ስለሆነ ሳይሆን፣ ሁልጊዜም ገልጦ የሚያየው አንድዬ ስላለ፡፡
ከብዙ ነገሮች ጀርባ ጭፍን መናናቅ አለ። ብዙ ነገሮች የሚደረጉትም፣ የሚባሉትም አንደኛችን ሌላኛችንን በመናቅና በተለይ ደግሞ “ምን እንዳያመጣ ነው!” በሚል ስሜት እየሆነ ከመጣ ከራርሟል፡፡ እንደዚህ አይነት ነገሮች ውስጥ ውስጡን የሰው ቆሽት ሲያበግኑና ልብ ሲያቆስሉ ቆይተው የመጨረሻ ውጤቶቻቸው ጥሩ አይሆኑም፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት ሀቅ አለ፡፡ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ወገን ዘወትር እየተናቀና እየተቃለለ ሊሄድ የሚችልበት እርቀት ዘለዓለማዊ አይሆንም፡፡ ተፈጥሮም እንዲህ እንዲሆን አትፈቅድም፡፡ የሆነ ቦታ ላይ ቀይ መስመር የሚባለው ነገር ላይ ይደረሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ ለማንኛውም ወገን ጥሩ አይሆንም፡፡
ወይ አንድዬ እመጣለሁ ካለበት ቀድሞ መጥቶ እንደምንሆን ያድርገን!
በነገራችን ላይ የሌላኛውን ወገን ችሎታና አቅምን መናቅን በተነሳ አንዲት ታሪክ ለመጥቀስ ያህል ብራያን አክተን የተባለው ሰው በ2009 ፌስቡክ ሥራ እንዲቀጥረው ያመለክታል። ፌስቡክ ደግሞ የአንተ ችሎታ አይመጥንም ብሎ በሩን ይዘጋበታል፡፡ ከዓመታት በኋላ ፌስቡክ እኛን አትመጥንም ያለው ብራያን ሆዬ፤ ሁዋትስአፕ አፕሊኬሽንን ይፈጥራል። ከዚያም ምን ቢሆን ጥሩ ነው... ፌስቡክ ሁዋትስአፕን በአሥራ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ገዛው፡፡ ለዕለት ጉርስ እንኳን በር ያልተከፈተለት ሰው አትመጥንም ባለው በዛው በፌስቡክ ረብጣ ቢሊየነር ሆነላችሁ፡፡ ሙያ በልብ ነውና! ዛሬ የናቅነው ወገን ነገና ከነገ ወዲያ የትኛው ቦታ ላይ እንደምናገኘው አናውቅምና፣ ለማንም ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለው መገንዘቡ ሸጋ ነው የሚሆነው፡፡
ልንክደው የማንችለው ነገር በከፍተኛ ደረጃ መናናቅ አለ፡፡ በግለሰብ፣ በስብስብ፣ በቡድን፣ በጎጥ ብቻ ምን አለፋችሁ በብዙ ደረጃ መናናቅ አለ፡፡ በ“አናውቃቸውምና ነው!”፣  በ“ምን እንዳያመጡ ነው!”፣ በ“ተወው ይንጫጫ!”፣ በ“እነሱ እነማን ናቸውና ነው!” አይነት አንድ መቶ አንድ ነገሮች ሀገርን የመናናቅ የሆነ ነገር ሰፍሮባት መከራዋን እያበላት ነው፡፡፡
ፈረንጅ “Everything comes with an expiry date.” የሚላት ነገር አለችው፡፡ አዎ ማንኛውም ነገር የማለቂያ ጊዜ አለው፡፡ ይቺ ሀገር እዚህም እዛም የማለቂያ ጊዜያቸው በዘመናት ባለፉባቸው ሀሳቦች ነው መከራዋን እየበላች ያለችው፡፡
አሳምራቸውና ከብቶቻችን ይብሉ
አሳምራቸውና በጎቻችን ይብሉ
አሳምራቸውና ፍየሎቹ ይብሉ
ያ ሣር አይደለም ወይ የምናየው ሁሉ፤
የምትል ዘለሰኛ አለች፡፡ አዎ፣ ይቺ ሀገር ሁሉ ነገር አሳር እየሆነባት እስከመቼ ልትቀጥል ነው!  ወይ አንድዬ እመጣለሁ ካለበት ቀድሞ መጥቶ እንደምንሆን ያድርገን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1310 times