Saturday, 04 February 2023 20:39

ግንደ-ቆርቁር - (ወግ)

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(5 votes)

 ማለዳ የአእዋፋትን ውብ ዝማሬ ልሰማ እነቃለኹ። ዝማሬ፣ ንጋቴን ስሙር ከሚያደርጉት ባለውለታዎቼ አንዱ ነው። ከሩቅ የሚመጣው የቤተክርስቲያን ደውል፣ ሊነጋጋ ሲል ያለው አዛን፣ ቅዳሴው፣ደውሉ፣ ኹሉም...ኹሉም ስልተ-ምታቸውን ጠብቀው ሲደርሱኝ እረካለኹ። ነፍሴን የጨመደዳት ብርድ፣ የተዋረረኝ ዘመነኛ ሸቀን ለጊዜውም ቢሆን አያሳክከኝም። አንድ ድምጽ ግን በተለየ ጤና ይነሳኛል። ስለሌሎቹ ነፍሴ ሆይ ሐሴትን አድርጊ እላለሁ!
[ለሰኞ አጥቢያ፣ ሌሊቱ የአህያ ሆድ እንደመሰለ፣ ሼህ አብዱ አዛን ሲያደርሱ ልማደኛ መንቃቴን ነቃሁ። ቃተት...!]
ኹሌም ምሥጋና፣ ኹሌም ውዳሴ። ኦ! ትጋት። ሙስሊሞች ወደ አምላካቸው ለመጸለይ ግርማ ሌሊቱን ይዳፈሩታል። ካህናት ለምሥጋና ጸበ-አጋንቱን አልፈው ይቀድሳሉ። ሕይወት ፈተናዋ የበዛ ነው። ቁስሏ እከኩኝ..እከኩኝ ይላል። ምርቅዟ በቶሎ አይለቅም። ቢሆንም እንዲህ የሚኖሩለት ምክንያት ሲገኝ ሕይወት ትርጉም እና ቅርጽ ይኖራት ይሆናል።
[ከመኝታዬ ተነሳኹ። ፊቴን ከበረዶ በቀዘቀዘ ውኃ ታጠብኩ። ኾዴን ዶናት በሻይ ሰጥቼ ደለልኩት። ጉልበቴ ዳገት ላይ እንደማይለግም አውቃለሁ በጎመን አይደለማ የደለልኩት!]
ከባለቤቴ ጋር ተፋተናል። ልጆቻችን እሷን ተከትለው ኼደዋል። ልጆቼ፣ እኔን ጠልተውኛል አልያም እሷን ወደዋታል። መፋታቴ ውስጥ የሚሰማኝ “Any fool knows men and women think differently at times, but the biggest difference is this. Men forget, but never forgive; women forgive, but never forget.” የሚለው የRobert Jordan, |The Dragon Reborn| ምስልስሎሽ ነው።
(ምሽት ቁዘማ። ኹለት ተቃራኒ ጾታ (ጥንዶች)። ወደ ቤተ-ክርስቲያን ደርሰው በመመለስ ላይ። ተጠጋኋቸው።)
«ለመሆኑ፣ ሴቶች ይቅርታ ያደርጋሉ ግን አይረሱም፤ ወንዶች፣ ይቅርታ አያደርጉም ግን ይረሳሉ ...የሚባለው እውነት ነው?»
ወንዱ ፈገግ አለልኝ። ፍቅረኛውን ቁልቁል አያት። እሷም ብርኀን የተሞላበት እይታ አየችው። ለመመለስ የፈሩ ይመስላሉ። ስስ ፈገግታቸውን እያሳዩ አስጠበቁኝ። “አንድ ነገር ቢሉ አንድ ነገር እንደሚሆኑ” እያሰቡ ቆዩ። መፈራራት ያጀበው ፍቅር። ምላስ ተስቶት ከቀላመደ የሚበጠስ ቅርበት። አዝኜ ራቅኳቸው።
100 ሜትር ራቅ እንዳልኩ ጠና ያሉ ባል እና ሚስቶችን አገኘሁ። ጥያቄውን ለእነሱም ሰነዘርኩ።
«እኔ ይቅርታ አደርጋለሁ፤ ግን ይቅርታ ያደረግኩላቸውን ሰዎች መፈጠር እረሳለኹ»
ከልቤ ሳቅኩ። ከሰጠኋት አማራጭ ውጭ ነበር የመለሰችው። ምናልባት ተጨማሪ ጾታ ...
ወደ ወንዱ ዘንበል አልኩ።
«ይቅርታ አላደርግም፤ አልረሳምም ይልቅ አስታውሳለሁ» አለኝ።
ምርጫዎቻችን እንደየመልካችን መለያየቱ ገባኝ። ሰው ማማከር አልወድም ነበር። የማማክረው ኹሉ ፍራቻውንና ስጋቱን እንጅ ጥሩ መላ ሰንዝሮልኝ አያውቅምና።
ንግድ ልጀምር? ብለው...ብትከስርስ?
ኮንትሮባንድ ልጀምር? ብለው...ብትያዝስ?
እሺ ዝቅ ብዬ ጫማ ልጥረግ?...ቢንቁህስ?
...ብዙ ስጋት...ብዙ የኪሳራ ዶፎችን ይዘረዝራል- ያወያየሁት ኹሉ።
[ምድር እየበረዳት ነው ነገ ልትሞቅ። ፀሐይዋ እየተሸኘች ነው ልትመጣ። ዓይን ጉልበቱ እየፈዘዘ፣ አካባቢው እየቀዘቀዘ ሲሄድ ወደ ቤቴ አመራኹ]
ያለ አንዳች ጉዳይ ኮቴ መለጥኩ የሚል ጸጸት አርግዤ ተጋደምኩ። መኝታዬ ከገብስ ገለባ የተበጀች ፍራሽ ነች። ገልበጥ ስል ጀርባዬን የገብስ እግር እንደማይወጋኝ እርግጠኛ አይደለሁም።
ከቤቴ ጀርባ ትልቅ የዋርካ አድባር አለ። አምልኮቴ በእሱ ነው። ጠይቄው ያልደረሰልኝ ፣ለምኘው ያልሆነልኝ የለም። እርሱን የምትታከክ «ግንደ-ቆርቁር» ነች ምድር ላይ ቀንደኛ ጠላቴ። እፎይ ብዬ ከተኛሁበት የምትወቅሰኝ፣ ሌሊት ከብዙ ቅላጼዎች መሐል ሾልካ የምታነጫንጨኝ እሷ ነች።
ነቃሁ። በግምት 11:30 ነው። የግጥም ደብተሬን ጎተት አድርጌ ለተለየኋት ሚስቴ ልጦምር ሻትኩ። እንቅልፌ ባለማለቁ በተከታታይ አፌን አላቅቃለሁ። የያዝኩት ብዕር እንደኔው ያስባል። «አስቦ መጻፍ፤ እየጻፉ ማሰብ»
ድንገት እቀየመው ድምፅ ...
ቆፍ ቆፍ የሚል። አስማተኛ አልኩ በልቤ። ደብተሬ ከብዕሬ መነካካት ሲጀምር እኩል ጀመረች። ወፏ፣ ግንደ-ቆርቁሯ። የሚልካት የበላይ አካል አለ። የሚያመልኩበት ዛፍ ያልወፈረላቸው መካሪዎቿ እንደሆኑ እሰማለሁ። በእኔ ዋርካ ቅናት ይዟቸዋል።
ከሐሳብ ስሜት ይቀድማል። ማሰብ ስሜትን ይከተላል በእኔ ቤት። ያሰብኩት ለባለቤቴ የነበረውን ጽሑፍ፣ ጥሩ እንዳይሰማኝ ላደረገችዋ ግንደ-ቆርቁር ሆነ ...
«ግንደ ቆርቁር ...ግንደ ቆርቁር
አትወጂም መሰል..ካለ ጭር።
ቆፍ..ቆፍ...ድርጁውን ዛፍ፥
ባልታጠበ ...ባልፀዳ አፍ።»
ይኼን ጽፌ የልቤ አልደረሰም። ላቤ በፊቴ ያሻርታል። ምናልባትም ጠልቶ የማያውቅ አይረዳኝም። ኗሪውን ዛፍ መቆፍቆፏ ሐሳቤን ሰርቋል። ጥላቻዬ ጥርስ ሲያወጣ ይታወቀኛል። ተነስቼ ብሄድባት ትበራለች፤ ዝም ብላት ሂጂ አድባሩን ነቋቁሪበት ብለው ይልኳታል። አማራጬ «ፀሐፊ አያለቅስም» ማለት ሆነ። ካለቀስኩም በብዕሬ በኩል ወደ ወረቀቴ ይኹን አልኩ።
«ግንደ ቆርቁር...
የወጋሽው ዛፍ ፥ ካልጮኸልሽ
ምነው የበላሽ አይመስልሽ?»
አትችልማ። ድምጿን ካልሰሙላት፣ እወቁልኝ ካላለች ጭራሽ ነው የማትረካው። በእሷ ጩኸት የተበሳው የኔ፣ የባለአድባሩ፣ የባለዋርካው ጆሮ ነው። አመልክበት ዋርካ ስንቱን አስጠለለ? ስንቱን ምግብ መገበ? ስንቱን ማገዶ ቻለ? ስንቱን አጥር ሸፈነ? ለስንቱስ ገመና ከታች አድባር ሆነ?.. ውለታ ቢስ ኹሉ። ወፎች ፍሬውን በልተው ኩሳቸውን ጥለውበት ይነሳሉ፣ ሰዎች ማፍራቱን ሲያዩ ድንጋይ ይወረወሩበታል፣ ከፀሐይ ሙቀት የተጠለለው ቅርንጫፉን ቆርጦ ይወስዳል፣ ኹሉም..ኹሉም ለአድባሬ የጡረተኛ ክፉዎች ናቸው። ግንደ-ቆርቁር ሥራዋን አልፈታችም...
«ቆፍ ቆፍ...
ቆፍ ቆፍ ...
የኑሮ አዚም ፥ጽኑ  ሰንኮፍ!
ከቤት በላይ ተንጠልጥለሽ
ጤና የለሽ!»
ዋርካው፣ ምስኪን ነው። ስትበላው ይበላታል። ፍርዱ ቅርብ አይመስልም። ለቆረጡት ሲቆረጥ፣ ለቀጠፉት ሲቀጠፍ ፣ለበሉትም ሲበላ ነው የማየው። እኔ ጸሐፊ ነኝ። የጸሐፊ ነፍስ ደግሞ ንክ ናት። ህመሙን እጋራዋለሁ። ዝም ቢልም ዝም አልላትም። ከታች ሆኜ ከበላዬ የምትቆፈቁፈዋን ግንደ ቆርቁር ወንጥዬ ባወርዳት እመኛለሁ። በእግር -ብረት አስሬ ስልሳ ብገርፋት ፣ሽንቷን ባስጠጣት አልያም በርበሬ ባጥናት አልጠላም። በአዋዋል ከእኔ ርቃለች ወደ ላይ፤ በግብር ከእኔ አንሳለች። እየቆየ ይብስባታል። ንዴቴን የምታውቅ ይመስለኛል...
«ግንደ ቆርቁር...
አንቺ የአዕዋፍ አስተኔ
አትፈሪ ፍዳ ኩነኔ
በኗሪ ...በአድባሩ ዋርካ
መንቁርሽ እየተሰካ
ቱርቱራ ...ሆነ ቱርቱራ
እንዴት ይኖራል?፥ ከአንቺ ጋራ።»
አታስመኝም አብረዋት ሊኖሩ። መንቁሯ ወፍራሙን ግንድ ቦረቦረው። ለዓይንም ቱርቱራ ሆነ። ታመልክበትን ቢነኩባት ምን ይሰማት? አድባሬን መጠናዎት ምነው አያም መሠላት? ዘለለች..ከዋርካዬ፣ ከአድባሬ፣ ዘለለች... ከዋርካዬ፣ ከአድባሬ...
የሰላም እንቅልፍ ካጣሁ ቆየሁ። ባለቤቴን ከፈታሁ ጀምሮ ጤና የለኝም። ልጆቼ ከጉያዬ ከራቁ ጀምሮ ቆሌዬ ተገፏል። ይኼን ኹሉ ድባቴ የተሸከመ ጫንቃዬ ስለምን በእሷ ቆፍ ቆፍ ይሰቃይ? ኑሮ ከእሳት በላይ የሚያነደኝ መች አነሰኝ? ድሮ የአጠፋ ልጅ በርበሬ ይታጠን ነበር። ዘንድሮ ግን በርበሬ ውድ ነው። እንኳን ያጥኑት ይበሉትም የለም። ወጣችን ነገራችንም አልጫ ሆኗል። ኑሮ ረመጥ ነው ይፋጃል። ይኼን ረመጥ የቻለ ሆድ ግንደ ቆርቁር ከበላዩ እየቆፈቆፈች አላስተኛ ማለት ነበረባት? በፍጹም!
«ግንደ ቆርቁር ...ግንደ ቆርቁር
አፍሽ ግንዱን ሲወጋ ፥የሚሰማን ልብ ሥር።
ግንደ ቆርቁር..
አንቺ ወጋሴ እንቅልፍ
ካንቺ ‘ሚከልለን የቱ ጽንፍ?
ቆፍ... ቆፍ...
ቆፍ... ቆፍ...
ትግልሽ ከግንድ ጋራ
ፍሬማ ለአንቺ  መራራ!»
ጽሑፌን ማገባደድ ተሳነኝ። ሌሊቱም ለብርኅን ተዳረ። ቀን ባለ ጊዜው የራሱን ፀሐይ በምሥራቅ ይዞ መጣ። ሙቁሉኝ ይላትን። ለ12 ሰዓት ብቻ ሰጥቶ ማታ ወደ ምዕራቡ ይነጉዳል። ቀን ብርኀንን ሌሊት ጨለማን ተካፍለዋል-ድንበራቸው አይታወቅም። ስስ..ከስስም የሳሳ ነው። ወፌ...ግንደ ቆርቁሯ እና እኔ ወፍራም ድንበር እያለን ተናናቅን። አድባሬን ቱርቱራ ስታደርገው ዓይኔ እያየ ነው። ከጀርባዋ አይዞሽ የሚላት፣ መንቁሯን የሚያደረጅላት አካል አለ። ድንበራችንስ?...
ሊባዝን የተፈረደበት አእምሮዬ ያሳዝነኛል። ወረቀቴ የደም እንባ ነካክቶት ባይ ፈራሁ። የዓለም ውጥንቅጥ ገርሞኝም አያውቅም ነበር። ሬሳ ክምር አያስለቅሰኝም ነበር። አድባሬ... ዋርካዬ..እጠለልበት ዛፍ ...ኗሪው...ድርጁው  ቱርቱራ ሲሆን ግን ፈራሁ!..ጨነቀኝ። ደጋግሜ በግጥም ገረፍኳት፤ የልቤ አልደረሰም። ቃል ኃያል ነው ይሉ የለ፤ ለምን እሷን ዠልጦ አላወረደልኝ ? ድንጋይ ወርውሬ እንኳን ቅሽሽ የማይላት ግንደ-ቆርቁር ከሆነ ዘመን አንዴ ተደገመች። ኃፍረቷን የረሳች፣ ነውሯን ከታች ሆኜ እያየሁባት የማትሸማቀቅ፣ በቆፈቆፈችው የምታድር ፣ጤና በነሳችው ጤና የምታገኝ እርጉም ወፍ አልኩ።...የተፋታማ ተገላገለ ሲል ውስጤ ተባበረ።
«ግንደ ቆርቁር...
የወጋሽው ዛፍ ፥ ካልጮኸልሽ
ምነው የበላሽ አይመስልሽ?»

Read 946 times