Thursday, 09 February 2023 17:29

በወቅታዊ ጉዳዮች ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን የተሰጠ መግለጫ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በወቅታዊ ጉዳዮች ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን የተሰጠ መግለጫ
 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በውስጥ አሠራር እንዲፈታ መንግሥት አቋም መያዙ ይታወቃል። ለዚህምም የሀገር ሽማግሌዎችና የሚመለከታቸዉ ሁሉ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በሕገ መንግሥታችን መንግሥታዊ ሃይማኖትም ሆነ ሃይማኖታዊ መንግሥት ሊኖር እንደማይችል ተደንግጓል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረው ልዩነትም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዉስጣዊ አሠራርና ከዚያም ካለፈ በፍትሐ ብሔር ዳኝነት የሚታይ ነው። አስፈጻሚው አካልም በፍርድ ቤት ሲወሰን ብቻ የማስፈጸም ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ይታወቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አጋጣሚዉን ለእኩይ የፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም የሚንቀሳቀሱ አካላት እየተገለጡ መሆኑን መንግሥት በልዩ ልዩ መንገዶች አረጋግጧል።
"የመሥዋዕትነት ሰልፍ አዘጋጅ " በሚል ከባለ ሀብቶች፣ ከፖለቲከኞች እና ከ"መንፈሳውያን የወጣት አደረጃጀቶች" የተውጣጣ ቡድን ከማዕከል እስከ ታች መዋቀሩን መንግሥት ደርሶበታል። አጋጣሚዉን በትጥቅ በተደገፈ ሁከት መንግሥትን የመነቅነቅ ፍላጎት ያለው ይህ ቡድን ወጣቶችን እየመለመለ ማሠማራት መጀመሩን፣ ለዓላማዉ በልዩ ልዩ መንገዶች ገንዘብ በመሰብሰብ እያሠራጨ መሆኑንና በሕገ ወጥ መንገድ ከታጠቁ ኃይሎች ጋርም ግንኙነት እየፈጠረ መሆኑን መንግሥት አረጋግጧል። ለዚሁ እኩይ ዓላማ አስቀድሞ አስቦበት ያደራጁት የሚዲያ ቡድን ሥራዉን መጀመሩም ተረጋግጧል፡፡
በዚህ የክትትል ሂደት ድምጽ ያላቸውና የሌላቸው መሣሪያዎች ይዘው ሁከት የሚፈጥሩ አካላት በሥምሪት ላይ እያሉ ተይዘዋል። የቤተ ክርስቲያንን ደወል ላልተገባ ዓላማ በመጠቀምሕዝብን ለብጥብጥ የሚዳርጉ ቡድኖችም ታይተዋል። በየአካባቢው ወጣቶችን ለግጭት የሚመለምሉና የሚያሠማሩ አካላት ተደርሶባቸዋል። የፖለቲካ ዓላማቸውን በሃይማኖት ሽፋን ለማስፈጸም የሚሞክሩ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመጠቀም የሰዎችንና የእምነት ተቋማትን መብቶች በመጣስ የመንግሥትን መልካም ስም ለማጥፋት የሚፈልጉ ሥውር እጆች እንዳሉም ታዉቋል።
በአጠቃላይ የተፈጠረውን ችግር ከመፍታት ይልቅ ችግሩን ለግልፅ የፖለቲካ ዓላማ ማሳኪያ አድርገዉ ወደ መጠቀም ተሸጋግሯል። ይህ ደግሞ የሀገርን ሰላም፣ ደኅንነት እና ልማት የሚጎዳ ነው። በመሆኑም በዚህ ተግባር ሆን ብለው የተሠማሩትን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለሕግ የማቅረብ ተግባር ተጀምሯል። ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ከዚህ በኋላ መንግሥት ቀደም ሲል ሲገልፅ እንደ ነበረዉ ጉዳዩ ቀይ መሥመር ያለፈ ሆኖ በማግኘቱ፣ “የመሥዋዕትነት ሰልፍ” ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ የሌለ በመሆኑ ሀገራዊ መረጋጋትን ለመፍጠርና የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ሲባል መንግሥት ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ ዉስጥ የሚገባ መሆኑን ከወዲሁ ያሳዉቃል። በዚህ አጋጣሚ ባለማወቅና በቅንነት የጥፋት ኃይሎችን የምትከተሉ ሁሉ መንገዱ ወደ ከፋ ጥፋት እንደሚወስዳችሁ ተረድታችሁ ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ መንግሥት ያሳስባል።
 መላዉ ህዝባችንም እንደቀደመዉ ሁሉ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር አካባቢዉንና ሰላሙን እንዲጠብቅ መንግስት ጥሪ ያቀርባል፡፡ ሕጋዊና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመናድ፣ በአቋራጭ በማንኛውም ዓይነት ጉልበትና ሁከት እኩይ የፖለቲካ ፍላጎትን መሳካት አይቻልም።
የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ/ም
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ

Read 2624 times