Saturday, 27 October 2012 10:51

የንባቡ ሰማይ ጨረቃና ክዋክብት

Written by  ደ.በ
Rate this item
(1 Vote)

መጀመሪያ ጣቱን ብዕር ሰድዶ ቃል ያስቀመጠው እግዚአብሄር ራሱ ነው ብለው ከሚያምኑት አንዱ ነኝ፡፡ ..መቼ?..ብትሉ በዘመነ - ሙሴ ብዬ ቁጭ !..ሙሴ ጽላቱን ይዞ ከሄደ በኋላ ስለተፈጠረው ጉዳይ አናወራም፡፡
የመጀመሪያው አንባቢ ሙሴ መሆኑን ካወቅን ብቻ በቂ ነው፡፡ መፃፍ የፈለግሁትም ስለ ንባብ ነውና!
እግዚአብሄር በንባብ ስለሚያምን ባሮክ በካርቶን ላይ እንዲጽፍ አድርጓል፡፡…ነቢዩ ኤርሚያስ እንደ ሶቅራጥስ ይመስለኛል፤ተናጋሪ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ ስለ መጻፉም መረጃ የለኝም፡፡ ቤተመቅደስ ገብቶ ማንበቡን ግን መጽሃፉ ይናገራል፡፡አመንዝራይቱን ሴት ለፍርድ ባቀረቧት ጊዜ ብቻ በጣቱ መሬት ላይ አንዳች ነገር መጻፉ ተነግሯል፡፡ ምን እንደሆነ ግን እስካሁን የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ስዕልም ነው ብሎ መጠርጠር ይቻላል፡፡

ለነገሩ ግሪካዊያን በንባብ ልምድ ከዕብራዊያን እንደሚቀድሙ የታሪክ ጸሃፍት ይናገራሉ፡፡ ግሪኮች ንባብ የጀመሩት ከክርስቶስ ልደት በፊት 2000 ዓመታት ቀድሞ ነበር፡፡ ግሪኮች ህዝባዊ የማንበብ ልማድም ነበራቸው፡፡ 
ሌላው ቀርቶ ታላቁ እስክንድር እንኳ የሆሜርን ኦዴሴና ኦሊሴስ ሳይይዝ የትም አይሄድም ነበር፡፡
በዘመነ ሮማም አንባቢው የራሱ ምርጫ ይኑረው እንጂ ስልጣኔ ያለንባብ የማይታሰብ ነውና ያኔም አንባቢው የሲሲሮን የአደባባይ ንግግር አባዝቶ ለየጓደኛው እስከ ማከፋፈል ሄዶ ነበር፡፡በተለይ ታሪክ፣ግጥሞች፣የሲሲሮ የመጨረሻው ንግግር በጣም ተወዳጅ ነበሩ፡፡የሆራስና የቨርጂል ሥራዎች በህይወት በነበሩበት ጊዜ የትምህርት ቤት ማስተማሪያ ነበሩ፡፡ይሁንና በዘመነ ሮማ የነበረው ስነ- ጽሁፍ በከፍተኛ ደረጃ ለነበሩት ምሁራን፣ማለትም ከሮም ጋር፣ከተቋማት ታሪኳና ከግሪክ ስነ ጽሁፍ ጋር ትውውቅ እንዲኖራቸው፣ ትልቅ ጠቀሜታ የሰጠ ነበር፡፡
ስለ ንባብ ሳስብ አንድ ሌላ ባለ ታሪክ ልቤ ላይ ድቅን አለ፡፡ታዋቂ፣ እጅግ የተከበረና በፍትህ የማያወላዳ፣ አሜሪካዊ ዳኛ ኦሊቨር ዌንዴል ሆልመስ ፣በዘጠና ሶስት ዓመቱ ታምሞ.መኖሪያ ቤቱ ተኝቶ ሳለ አንድ ትልቅ እንግዳ ቤቱ ገቡ-የአሜሪካው ፕሬዚደንት ቴዎዶር ሩዝቬልት፡፡እያቃሰተ ወይም ወደ ግድግዳ ፊቱን መልሶ ሲቃትት አልደረሱበትም፡፡የፕሌቶን ጥራዞች እያነበበ ነበር ያገኙት፡፡
“ምን እያደረግህ ነው?”..ጠየቁት፡፡እውነትም ግራ የሚያጋባ ነገር ነበር፡፡ከዘጠና ሶስት ዓመት ዕድሜ በኋላ የሞት አልጋ ላይ ተኝቶ ፤…እንዴት እንዲህ ይደረጋል?ሆ..
“እያነበብኩ ነው፡፡”
“ምን ሊያደርግልህ ነው አንተ ዳኛ?”
“ዕውቀቴን ለማሻሻል”
ጫን ያለው መጣ ማለት ይሄኔ ነው፡፡…አንድ እግር ጉድጓድ ገብቶ ማንበብ አያስቀናም?…ይህ ሰው ንባብ የጀመረው ገና ልጅ ሳለ ነበር፡፡በወጣትነቱ የራልፍ ዋልዶ ኤመርሰንን ጽሁፎች ብልት እያወጣ ይተነትን ነበር፡፡ ኋላ ሲሞት ደግሞ የነበረውን 50ሺህ ፓውንድና በርካታ መጽሃፍት ለኮንግረሱ ላይብረሪ በነጻ ነበር የሰጠው፡፡ለትውልድ ማውረስ ያለበትን ያውቃል፡፡”መጽሃፍት መውደድም ማክበርም በሃገር ላይ ለውጥ ማምጣቱ አይቀርም፤ የዛሬዋ ትልቋ አሜሪካ የተወለደችው በእነጀፈርሰን በንባብ የበለጸገ ጭንቅላት ነው፡፡አንድ ጸሃፊ በተለይ ስለ ዳኛው ኦሊቨር ዌንዴል ሆልመስ ሲጽፉ፡-“think of it!...ninty-three!...to improve my mind!`…yes,his country has never produced a man of finer character than oliver Wendell holmes,nor one who has had greater influence on the law..እውነት ነው በምድራችን ላይ እንደ ክዋክብት የደመቁ አንባቢዎች አሉ፡፡ የኛ ማሞ ውድነህም'ኮ ታምመው ወደ ሞት ሲሄዱ የነበረቻቸውን ጊዜ ለማንበብ ቀኝ እጄ ላይ ግሉኮስ አትሰኩበት ብለው ነበር፡፡…ለታሪክ ያበቃቸውና አንቱ ያሰኛቸው እርሱ መሆኑን ያውቃሉዋ!! እኛ የቱን እንደምንመርጥ የሚጠቁሙ ብዙ ምልክቶች አሉ፡፡እግዜር ካልተፋን በቀጣዩ አመታት ዲግሪ ያለው ማይም መንጋ ምድራችንን የሚሞላበት ቀን ሩቅ አይመስልም፡፡ከነቃንና ከፈለግን ግን ይህን አስቀያሚ ችግር ልንለውጠው እንችላለን፡፡ ዶክተር ዳኛቸው፤ አንድ ጊዜ በሸገር ሬድዮ ላይ እንዳሉት የተማርኩ ነኝ የሚለውን ማይም ማስተማር ከባድና አደገኛ ነው፡፡አንድ ጊዜ ለቴሌቪዥን ፕሮግራም ስለ ውጤትና ተግባር ያነጋገርኩት ሰቃይ ተማሪ የነበረ እንግዳዬ ሲነግረኝ፤ “ኤ” ያመጣበትን ትምህርት ወደ ስራ መመለስ አቅቶት እንደተቸገረ አውርቶልኛል፡፡ለዚያ ደግሞ መፍትሄው ንባብ ነው-ነበር ያለኝ እርሱም፡፡
መኖሪያውን አሜሪካ ያደረገው የፍልስፍና ዶክተር ምህረቱ ጴጥሮስ ጉታ (በንባብ ፍቅሩ የሚታወቅ የቲዎሎጂ መምህር የነበረ ሰው) የጻፈው የንባብ ባህልን የተመለከተ መጽሃፍ፣ በተለይ ባህላችን በራሱ ለንባብ እንቅፋት እንደሆነብን ሲገልጽ እንዲህ ይላል …የአገራችን ባህል አብዛኛውን ጊዜ ሰውን በማስደሰት ላይ እንድናተኩር የሚያደርገን ከመሆኑ የተነሳ ለንባብ የምንሰጠው ዕድል በጣም የተመናመነ ነው፤ ዶ/ር ሻሮን ሳምሶን በጥናታቸው እንዳስተዋሉት “ሌላው በኢትዮጵያ የንባብ ባህል እንዳይጎለብት ምክንያት የሆነው ባህሉ ራሱ ሰውና ህብረተሰብ -ተኮር በመሆኑ ግለኝነትን ወይም መለየትን አለማበረታታቱ ነው፡፡ ንባብ ደግሞ በግል የሚሰራ ስራ ነው፡፡ በሰው ብዛት የተጨናነቀ ሁኔታና ደካማ የቤት ውስጥ ብርሃን ዘወትር መጻህፍትን ለማንበብ ፍላጎትም ችሎታም እንዳይኖር ያደርጋል፡፡የሚል አንድ ማሳያ ሰጥቷል፡፡ይህ አንዱ ቅንጣት ነው፡፡ዶ/ር ምህረቱ በተጨማሪ የገንዘብ ዕጦት፣አስተዳደግ፣የቴክኖሎጂ ተጽዕኖ፣(ኢንተርኔት፣ሬድዮ፣ቴሌቪዥን፣)ወዘተ..፣የስርጭት ችግር፣የሃገር ውስጥ ጸሃፍት የቋንቋ አጠቃቀም ችግርና ሌሎችንም ምክንያቶች ጠቅሷል፡፡
አሁንም ሃሳቤን ወደ ማጠናከሪያ ገጠመኜ ልውሰዳችሁ ፣ናዝሬት አንድ ሆቴል ያለው ወዳጁ ቤት የሚያዘወትር ሰው የነገረኝ ነገር አንዳንዴ ትዝ ይለኛል፡፡እዚያ ወዳጄ የሚሄድበት ሆቴል ብቅ የሚል አንድ የውጭ ዜጋ ነበረና አንድ ቀን የሚገርም ጥያቄ ጠየቀ፡፡ብዙ ጊዜ ሲያያቸው መጽሃፍ የማይይዙ ወይም የማያነብቡ ግን ሁል ጊዜ የሚያወሩ ሰዎች በማየቱ ተደንቆ “እነዚህ ሰዎች መጽሃፍ ሲያነቡ አይቻቸው አላውቅም፣ግን ሁል ጊዜ ያወራሉ፤ለመሆኑ የሚያወሩትን ከየት ያመጣሉ?”ብሎ ጠየቀ-አሉ፡፡የሚያወሩት ትርኪምርኪ ወይም ሃሜት እንደሆነ አላወቀም፡፡
አትሌትዋ ወዳጄ ደራርቱ ቱሉ በስራ ጉዳይ ተገናኝተን ሂልተን ሆቴል ውስጥ ያወራችልኝ ነገር ሁሌ ይታወሰኛል፡፡(በነገራችን ላይ ደራርቱ በሳል አእምሮ እንዳላት ስንቶቻችን እንደምናውቅ እንጃ!)…ብዙ ሰዎች ያለ መጽሐፍ ወይም ጋዜጣ ብታያቸው”ይሄኔ ውጭ ሃገር ቢሆን ይህ የምታየው ሰው ሁሉ ባዶ እጁን አይቀመጥም ነበር አለችኝ፡፡እውነት ነው፣የስልጣኔ አንዱ መንገድ ማንበብ ነው፡፡
ይህን ነገር ሌሎችም ሰዎች ሲናገሩት ሰምተናል፡፡መቼም ስለ አሜሪካ አንባቢያን ሌላ ጊዜ ብዙ ያልኩ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ጀፈርሰንን፣ሊንከንን፣ፍራንክሊንን፣ኤዲሰንን፣ወዘተ ጠቅሼ፡፡
ዛሬ ደሞ ጭራሽ ያላነሳሁትን ጄነራሉን አሌክሳንደር ሃሚልተንን በጥቂቱ አስታውሳለሁ፡፡ሃሚልተን የፕሬዚደንቱ ጸሃፊ፣ የጦር ጄነራልም ነበረ፡፡ከጀፈርሰን ጋር በፖለቲካ መስመር ይለያያሉ፤ግን ደግሞ ባንድ መንግስት ውስጥ ሰርተው ነበር፡፡
ምናልባት ይህም የማንበብ ውጤት ሊሆን ይችላል በልዩነት ግን ለአንድ ሃገር ያሰራቸው፡፡የሃሚልተንን ነገር ካነሳን የሚገርመን ማንበቡ አይደለም፡፡ የሚያነብበው ገና ከወታደራዊ ስልጠናው መጥቶ እፎይ ሳይል መሆኑ ነው፡፡ጊዜ አይመርጥም ነበር፡፡.
እስቲ ይህንን እንይ፡-“he realized that for years past he had been reading and studying those subjects that would help a man in apposition of public trust. Reading, indeed,was one of the most important things that Hamilton ever did to prepare himself for the greatness which he had always dreamed about.
He never stopped reading ….he had forced himself to read at night after a full day,s work in the army after marches in the heat and cold ,he forced himself to read a few pages at the end of the day.
ፈላስፋውና ጸሃፊው ሄነሪ ዴቪድ ቶሩም የንባብ ፍቅሩ ልዩ ነበር፡፡ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በገባበት ወቅት ዩኒቨርሲቲው የሚፈልግበትን ብቻ ሳይሆን የራሱን ሰዓት ጨምሮ ሌሎች መጻህፍትን ያነብብ ነበር፡፡የህይወት ታሪኩን የጻፉት ጀምስ ፕሌይ ውድ በመጽሃፋቸው እንዲህ ይላሉ፡-“he passed many hours ih the Harvard library,reading specially the writing of all the English poets.`….ዩኒቨርሲቲ ላይብረሪ ውስጥ በርካታ ሰዓታት በንባብ ያሳልፋል፡፡-በተለይ ደግሞ የእንግሊዝ ገጣሚያን ስራዎች እጥብ አድርጎ ያነብባል፡፡ .
ንባብ ስንል ግን የምናነብበው ነገር ምርጫም ወሳኝነት አለው፡፡ንባብ ሂትለርም ያነብባል፡፡የሚያነብብው ግን የጥፋት ተልዕኮውን ለማስፈጸም የሚረዱትን መጻህፍት ነበር ይባላል፤
.አሁን በቅርብ በሞት የተለዩን ጠቅላይ ጠቅላይ ሚንስትር ብቃትም ይህ የማንበብ ችሎታቸው ይመስለኛል፡አቶ መለስ ግን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ገብተው ግቢውን ያመሱበትን ጊዜ ፈጽሞ አንረሳም፡፡ሰዉየው ያንን ያደረጉት በንባብ ባገኙት ዕውቀት ነበር፡፡ያለበለዚያማ እዚያ ግቢ በዲግሪ ብዛት የሚበልጧቸው ሰዎች ቁጥር የትየለሌ ነበር፡፡ዕውቀት ማን እንደሚበልጥ ግን አሳይተውናል፡፡የዩኒቨርሲቲው መምህራን ደብተራቸውን ይዘው ለፊርማ መሰለፋቸውን … እንደ ንባብ ገድል እቆጥረዋለሁ፡፡
ስለ ንባብ ካነሳን አይቀር አራት አይነት ንባቦች አሉ ይሉናል-ምሁራኑ፡፡፡አንድ ጸሃፊ እንዲህ ይላሉ፤-“it seems to me possible to name four kinds of readings,each with a characteristic manner and purpose.” እኛም ሃገር እንደምናየው የየሰው የንባብ ምርጫና ዓላማ ይለያያል፡፡ ከፊሉ ለንግድ፣ ሌላው ለስፖርት፣አንዳንዱም ለስነ-ጽሁፍ ውበት፣ለፍልስፍናና ለሌላም ያነብባል፡፡
ከላይ የጠቀስኳቸው ጸሃፊ እንደሚሉት ፣የመጀመሪያው ንባብ መረጃ ለማግኘት የምናነበው ነው፡፡በዚህም ስለ ንግድ፣ስለ ፖለቲካና ሌሎች ነገሮችን እንዴት አድርገን እንደምናከናውን የምንረዳባቸው ናቸው፡፡ጋዜጦችን ፣የመማሪያ መጻህፍትን፣የምናነበው ለዚሁ ነው፡፡ ብስክሌት እንዴት መገጣጠም እንደምንችል ብናነብ ይህም ከዚህ ጎራ የሚመደብ ነው፡፡
በዚህ ንባብ ወቅት አንባቢው የማይጠቅመውን እየተወ ያልፋል፡፡ በዘይቤ መደመም፣የዐረፍተ ነገር ምት ትዝ አይለውም፡፡እንደ ግጥም ንባብ በየቤት መምቻው ልቡ ጮቤ አይረግጥም፡፡
ፈጣን ንባብ የሚጠቅመው በሰሞኑ የተፈጠሩ ክስተቶችን ለማወቅ ነው፡፡ከዚያ ባለፈ ግጥም ወይም ልቦለድ አያስጎመዠንም፡፡ስናነብ ዝግ ወይም ፍጥን እንድንል የሚያደርገን የምናነበው ነገር ባሕርይና የኛ ፍላጎት ነው፡፡
ኪነ ጥበባዊ ስራዎችን ስናነብ ግን ከዚህ ይለያል፤ የዚህ ዓይነት ጽሁፎችን ስናነብ ዝግ ማለት ቃላቱን ጆሮ ሰጥተን በጥሞና ማዳመጥ ይጠበቅብናል፡፡ ከንፈሮቻችን ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ፡፡ያለበለዚያ ስንፍና ነው፡፡ግጥሞች ስናነብብ ከዜማው ጋር የሚደንስና የሚመታ ተንሳፋፊ ልብ ሊኖረን ይችላል፡፡ በዚህ ንባብ ጉሮሮዋችን፣ጆሮዋችን፣አይናችን ሁሉ ይሳተፋል፡፡ማጣጣም ፣ማጣፈጥም ይኖራል፡፡
ፍልስፍና የሚያነብበው ምስሎችን ወደ አብስትራክት ቀይሮ ያነብባል..ያኝካል፤ያላምጣል፡፡ሁሉም የተለያየ አነባበብ ይፈልጋሉ፡፡
አንድ በምድረ-አሜሪካ ጥናት ያደረገ ጸሃፊ እንደሚለው፤ ብዙ ሰዎች በመማራቸውና በማንበባቸው ምክንያት የህይወት ዝንባሌ ያቸውና ምርጫቸው ሊለወጥ ይችላል፡፡እንደ ጥናቱ አባባል አንድ የቤዝ ቦል ተጫዋችን ብቸኛ ጀግናው አድርጎ ቢያመልከው ወዶ አያደለም፡፡ ከዚያ ያለፈ ለማየት አይኑ አልተከፈተም-ይላል፡፡አንዳንዴ ያነበቡ ሰዎች ባላነበቡ ሰዎች መካከል ሲያወሩ እንደ ትንግርት ሊታዩ ይችላል፡፡ይህ ብቻም አይደለም፤የታሪክ መዋቅር መከተልና መደነቅ የለመዱ አንባቢያን የላቀ ሃሳብና መንገድ ቢመጣ እንደ ዝብርቅርቅ ያዩትና ግርታ ይፈጥርባቸዋል፡፡የሄነሪ ዴቪድ ቶሩ “ዘ ዋልደን” በዘመኑ የዚህ ዓይነት ግራ መጋባት በመፍጠሩ ከራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን በቀር ያደነቀው አልነበረም፡፡ሰዎች በልካቸው የተጻፈውን ግን አንገታቸውን ይነቀንቁለታል፡፡በንባብ ከቀጠሉ ግን ለውጡን ይለዩታል፡፡
እያደር እየበራላቸው ይመጣል፡፡ትናንት ያደነቁትን ነገ ሊንቁት ይችላሉ፡፡አንባቢን በሚመርጠው ንባብ መለየት የሚቻለውም ለዚያ ነው፡፡ያለ አቅሙ ምንም ፍጠር ማለት ግን አይቻልም፡፡
ወደ እኛ ሃገር ስንመጣ የንባብ ባህልን ለማሳደግ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡በሬዲዮ፣በጋዜጣ፣በአዳራሾችና በየትምህርት ቤቱ እየተደረገ ያለው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ለምሳሌ “አዲስ አበባ ታንብብ፣ ናዝሬት ታንብብ፣”አይነቶቹ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡
በተለይ በሬድዮ ፕሮግራሞች ከሚተላለፉት ትረካዎች ውስጥ የአንዱአለም ተስፋዬ፣ጣፋጭና ማራኪ ድምጽ የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ወደ ንባብ የሚያመጣ ይመስለኛል፡፡እኔ ያነበብኩትን መጽሃፍ እንኳ አንዱዓለም ቢያነብበው እንደገና እንዳነብብ ይገፋፋኛል፡፡ከረሜላ ነው-አንዱዓለም፡፡እንዲህ አይነቶቹን ጣፋጮች ፈጣሪ ጨምሮ ይስጠን፡፡ብራና የተሰኘው በንባብ ላይ የሚሰራው የራድዮ ፕሮግራምም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ማንም አይዘነጋውም፡፡
ያለበለዚያ አሁን ባለው አያያዛችን የሚቀጥለው ነገር ምን እንደሚመስል ለማወቅ ጥናት የሚጠይቅ አይመስለኝም፡፡እጅግ ወደ ሚያሳፍር ድንቁርና ቁልቁል እንምዘገዘጋለን፡፡ዩኒቨርሲቲ አንገባም አላልኩም ፤ዕውቀት አይኖረንም፣እንጂ!!ወረቀታችን ታዲያ ያድነናል?እንዴት አድርጎ?ስራህ ያውጣህ ነው -የሚለን!
ለዚህ ርዕሰ-ጉዳይ በጣም የምትመቸውን የዶክተር ፈቃደ አዘዘን ግጥም እንያት፡-
ከበዳ ወደ በዳ ነው-ርዕሷ፤
ይጮኻል ደራሲ
……………..
ይጮኻል ከያኒ፤
ግን ማን አዳምጦ?
ኧረ ማንስ ሰምቶ?
ሁሉም እጆሮው ላይ በሆዱ ተኝቶ፡፡
አንድ ጣሳ አረቄ ፤አንድ በርሜል ጠላ
ጠጃጠጅ አምቡላ
ከአስራአስር ክትፎ ጋር፣አስር ኪሎ ሥጋ
ቢጎምድ ቢሰለቅጥ ቢቸልስ ቢለጋ
ይመርጣል ዘመኑ፤
ጥበብ ለሱ ምኑ?
(ድርሰትና ግጥም ፣ኧረ ምን ለከርሱ
ለበዳ ኀሊናው ለበዳ መንፈሱ) !...ስለዚህ እናንብብ…ንባብ ሙሉ ሰው ያደርጋል፡፡በመጽሃፍት ንባብ ላይ ግጥም የጻፉት ታደለ ገድሌና ዶክተር ፈቃደ ትዝ ይሉኛል፡፡አረቄ መጠጣትን ከዕውቀት ማስቀደም ምን ዓይነት በሽታ እንደሆነ ፈጣሪ ይወቀው፡፡ግን አሳዛኝ ነገር ነው፡፡መቼ ይሆን መጽሃፍ የሚናፈቅበት ቀን የሚመጣው? መቼ ይሆን ምሁራን በንባብ በልጽገው ለሚጠየቁት ነገር በቂ መልስ መስጠት ሲችሉ የምናያቸው? ይናፍቃል፡፡
እዚሁ ሃገር ላይ አንድ ጊዜ ቤታቸውን ለመውረስ ሲል አጎቱን ገድሎ በመጽሃፋቸው ያቃጠለ ወጣት ወሬ ተሰምቷል፡፡ያ ወጣት እነዚያን መጻህፍት አንብቦ ቢሆን ስለ አጎቱ ይቃጠላል እንጂ አጎቱን አያቃጥልም ነበር፡፡
እኔ ከሌላው ሰው ይልቅ የሚገርመኝ የኪነጥበብ ሰዎች ያለማንበብ ነው፡፡ብዙ ሰዎች ጋዜጣ እንኳ አያነብቡም፡፡ ለምን? ቴአትር እየጻፉ አለማንበብ ምን ይባላል? ገጣሚ ነኝ እያሉ አለማንበብስ? ”ጋዜጠኛ ማንበብ አይጠበቅበትም” የሚሉ ዓይን አውጣ ሰው አንዴ ጋዜጣ ላይ ብቅ ብለው አስቀውናል፡፡
“ቆንጆ መሆን ይፈልጋሉ?እንግዲያውስ መጽኃፍት ያንብቡ” የሚል ጥቅስ ያነበብኩት የት ነበር? በድሉ ህንጻ አካባቢ ያሉት መጽሃፍት ቤት!


Read 4364 times