Saturday, 11 February 2023 20:47

“መንግስት ከገለልተኝነት ባሻገር ወደ ህጋዊው አካል ማዘንበል አለበት”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 “ትልልቅ የመንግስት ሚዲያዎች አለመዘገብ ምንም ችግር እንዳልተፈጠረ ማስመሰል ነው”
                           ጋዜጠኛና ደራሲ በኩረ ትጉሃን ጥበቡ በለጠ)


        ከአንድ ሳምንት በፊት በቀድሞው አቡነ ሳዊሮስ የሚመራው አካል የኦሮሞያና የብሄር ብሄረሰቦች ሲኖዶስ መሰርቻለሁ ማለቱን ተከትሎ ቅዱስ ሲኖዶስ እነዚህን አካላት ማውገዙ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ አካላት በተለያዩ አካባቢዎች ቤተክርስቲያናትን እያስገደዱ በመግባታቸውና ይህን ድርጊት  በመቃዎማቸው ምዕመናን በመንግስት ታጣቂዎች እየተገደሉ መሆናቸውን ተከትሎ  በሀገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም መንግስትንና የተወገዙትን አካላት በሰላማዊ ሰልፍ እየተቃወሙ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ተከትሎ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና በመንግስት መካከል ውጥረት ነግሶ ይገኛል፡፡ ይሄ ጉዳይ መንስኤው በትክክል ምንድን ነው?መፍትሄውስ ምን መሆን አለበት? ከመንግስትስ ምን ይጠበቃል ከቤተክርስቲያን በኩልስ? በሚሉና በተያያዥ ጉዳዮች የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ በኩረ ትጉሃን ጥበቡ በሰጠና የቤተክርስቲያንን በደል ለፍርድ ቤት ከወሰዱት የህግ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ከሆነው አንዱ አለም በውቀቱ ገዳ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች እንድታነቡት እንጋብዛለን፡  

    የቤተክርስቲያኗን ጉዳይና ወቅታዊ ሁኔታውን እንዴት ታየዋለህ በትክክል ችግሩ የቋንቋ ነው ወይ ላልሽው እውነት ለመናገር በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የቋንቋ ጉዳይ ከዚህ ቀደም ይነሳ ነበር፡፡ ጥያቄው ረጅም አመታት አስቆጥሯል፡፡
በኦሮምኛ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የብሄር ብሄረሰቦች ቋንቋ እናስተምር በየገጠሩ ገብተን ዜጎች በሚገለገሉበት ቋንቋ ካህናትን እናፍራ የሚል ትልቅ ፕሮጀክት እንደነበር በጋዜጠኝነት ህይወቴ ውስጥ አውቀዋለሁ፡፡ ፕሮጀክት ተቀርፆ ሲሰራበትም አውቃለሁ፡፡ ይህ እንግዲህ ከአስር ዓመታት በፊት ነው፡፡ ምክንያቱም የቋንቋው ፖለቲካም በሀይማኖቱ ላይ ጫና እያሳደረ ስለነበረ እንዲሁም የአንድ ወይም የሁለት ብሄር ሀይማኖት ነው የሚል ትርክትም መጥቶ ስለነበር የዛን ጊዜ በስፋት ተሰርቶበት በጣም ብዙ ከተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ለክህነት የበቁ ካህናት እንዳሉ አውቃለሁ፡፡  
ከዚያ በኋላ እንዲያውም ትንሽ ወጣ ባለ መልኩ ጳጳሳትም ከተለያዩ ብሄሮች እንደተሾሙም አውቃለሁ፡፡ አሁን ተገንጥለው ያሉትም እኮ በቋንቋና በብሄራቸው ተሹመው የነበሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ የቋንቋ ጉዳይን ካነሳን የቀድሞው አቡነ ሳዊሮስ የተሾሙት በቋንቋቸውና በብሄራቸውም ጭምር ነው፡፡
ይህንን ካልን በኋላ ከእሳቸውና እሳቸውን መሰል ሹሞች የሚጠበቀው ደግሞ በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ የበለጠ መምህራንንና ዲያቆናትን በቋንቋቸው ማፍራት ነው፡፡ እነሱ ሀላፊዎች ስለሆኑ ወንጌለ ስብከትን፣ አገልጋዮችን በራሳቸው ቋንቋ ማስፋፋትና ማሳደግ ያለባቸው ራሳቸው ናቸው የቋንቋ ጥያቄም ካለ ተጠያቂዎቹ እነሱ ናቸው፡፡
ሌላው ግን በቋንቋዬ አልተማርኩም ብሎ ያመፀ ምዕመን አለ ወይ? ምዕመኑ መቼ ጠየቀ? መቼስ ቅሬታ አቀረበ? የሚለው ነው የኔ ጥያቄ፡፡ ምዕመኑ መቼ ነው የጠየቀው በየትኛው ጉባኤ? በየትኛው ደብዳቤ? ማንስ ነው የከለከለው? ተከልክሎ ያውቃል ወይ? የሚሉ ነገሮች አላየናቸውም፡፡ ነገሩን በአጠቃላይ ስናየው ሐይማኖት የቋንቋ ጉዳይ ብቻም አይደለም፡፡ ለምሳሌ እስልምና በአረብኛ ቋንቋ ነው በብዙ መልኩ የሚሰበከው ፖፕ ፍራንሲስ የሁሉንም አገር ቋንቋ አይችሉም፡፡ ምናልባት ሁለት ሶስት ቋንቋ ቢችሉ ነው፡፡
እዚህ አሁን እኛ ጋር የመጣው ነገር የሚመስለኝ ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት 30 ምናምን ዓመታት የሄደችበት ብሄርን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዳለ ወደ ሀይማኖት ውስጥ በመግባቱ ነው፡፡ ሀይማኖቱ ደግሞ ይህን በብሄር በጎሳ መደራጀቱን አያውቀውም፡፡ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ልትሆኚ ትችያለሽ፣ የሀይማኖቱን ቀኖና እና ዶግማ ተከትለሽ መሄድ ብቻ ነው የሚጠበቀው። እናም ሀይማኖት የትኛውንም የፖለቲካ አደረጃጀት አያውቅም፡፡ እስልምናውም ያንን የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ እናም ያ አስተሳሰብ ሀይማኖቱ ውስጥ ገብቶ ነው ቤተክርስቲያኒቱን እንዲህ እየበጠበጣት ያለው፡፡ ስለዚህ ህጋዊ የሆነው ሲኖዶስ አለ፡፡ ከእሱ ውጪ ያሉ ሲኖዶሶች፣ ህጋዊ ናቸው ማለት አይደለም በፍፁም ትክክልም አይደለም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰናቸውን ውሳኔዎች ህጋዊ በሆነ መንገድ የማስፈፀም ሀላፊነት ደግሞ የመንግስት ነው፡፡
መንግስት ደግሞ ይህንን ማድረግና የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ማስፈፀም ብሎም እንዲህ አይነት ስህተቶች እንዳይደገሙ ማድረግም አለበት፡፡ የተገነጠሉ አባቶችም ደግሞ ለክህነትና ለመሰል ማዕረግ የደረሱ ሰዎች ናቸውና በእነሱ ምክንያት የኔ ናት የሚሏት ቤተክርስቲያን በልዩ ልዩ መልክ ስትፈርስ ማየት፣ ምዕመኖቿ ሲገደሉና ሲሰቃዩ ሲመለከቱ ምንድን ነው የሚሰማቸው? ምንስ አይነት ክህነት ነው የሚልም ነገር ያሳስበኛል፡፡
ከሁሉም በላይ ሀገር ትቀድማለት፣ ሐይማኖት ትቀድማለች እና ለሀገርና ለሀይማኖታቸው ሲሉ ለምን ይህን ነገር አልተውም? ይህን ያህል ፅንፍ  የተወጣውስ ለምንድን ነው? ይሄ ሁሉ መከራ፣ ይሄ ሁሉ በደል፣ ይሄ ሁሉ ሀዘንና ማቅመልበት ድረስ አምንበታለሁ፣ ተክኜበታለሁ፣ ቦታ ይዤበታለሁ፣ ደሞዝ አገኝበታለሁ፣ ከምንም በላይ ደግሞ መንፈሳዊ ፀጋ አለኝ አስተምርበታለሁ የሚሉ ሰዎች ይሄ ሁሉ ሞት ይሄ ሁሉ ደም መፋሰስ ይሄ ሁሉ ከፊት የተደቀነ አስፈሪ ነገር ሁሉ አልታይ ያላቸው ለምንድን ነው የሚለው ጉዳይ ሁሉ መታየት አለበት፡፡ ይህም ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ እንደ ሀገር ሁሉም ሊያሳስበው ይገባል ምክንያቱም መጪው ጊዜ አሳሳቢ ስለሆነ፡፡
ዛሬ አንዱ አካል አሸናፊ ሆኖ ነገ አንዱ ተሸናፊ ሆኖ ዝም ሊል ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ያ ነገር ደግሞ ሌላ ነገር ቆስቁሶት ሊነሳ ይችላል ስለሆነም ይሄ ነገር ዘላቂ እልባት ሊበጅለት ይገባል፡፡
ከሁሉም በላይ ግን ህግና ሥርዓት መከበር አለበት፡፡ ህጋዊ የሆነውን አካል ህጋዊነቱን ማፅናት ብቻ ነው የመጀመሪያውና ትክክለኛው አማራጭ፡፡ እዚህ ላይ ቢሰራ ትክክል ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡
እንዳልሽው ቤተ ክርስቲያን ለነገ (እሁድ) ምዕመኑ ታቦታቱን ከየደብሩ እያወጣ ወደየ ባህረ ጥምቀቱና መስቀል አደባባዩ እንዲወሰድ በዚያውም ያለውን ችግር ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲያሰማ ትዕዛዝ ሰጥታለች፣ በተወገዘው አካል በኩል ያለውም ሰልፍ እንወጣለን የሚል መግለጫ አውጥቷል የጋራ ግብረሀይሉም ሁለት ሰልፍ አይሆንም ከልክያለሁ ብሏል፡፡ በዚህ ላይ ምን ይታይሃል ላልሽኝ እኔ የሚያየኝ ችግሩ እየከረረ ሁኔታው እየተወጠረ በቀላሉ ለሌላ ግጭትና ደም መፋሰስ አገራዊ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ነው፡፡ ስለዚህ ለሚያልፍ ነገር ብዙ ዜጎቻችን ባያልፉብን እመርጣለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ እነዚህ ተቋማት ትልልቅ ናቸው መንግስትም ቤተክርስቲያኒቱም ማለቴ ነው፡፡ መንግስት የፀጥታና የሀገር ደህንነት የመጠበቅ ሀላፊነት ያለበት ተቋም ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም ደግሞ መንፈሳዊ የሆነውን ነገር በማስተማር ዜጎችን በሀይማኖታዊ ዕሴቶች የመጠበቅ ሀላፊነት አለባት ፣ ስለሆነም በሁለቱ መካከል መቀራረብ በእጅጉ ያስፈልጋል። መንፈሳዊና ሥጋዊ መቀራረብ ማለቴ ነው። አሁን ችግሩ በሁለቱም መካከል መራራቅ መፈጠሩ ነው፡፡ መሃል ላይ ደግሞ ትልልቅ የሀገር ሽማግሌ ካለን ይህን ውጥረት ለማርገብ መግባት አለባቸው ብየ አምናለሁ፡፡ እንደገና ደግሞ ሰልፎች በተመሳሳይ ጊዜ ባይጠሩ ጥሩ ነው፡፡ ሁልጊዜ እከሌ እኔ እወጣለሁ ሲል ሌላው ያንን ተከትሎ እኔም በዚያውቀን እወጣለሁ ሲባል ለሌላም ጊዜ ይሄ ጥሩ ልምድ አይደለምና መታረም አለበት፡፡
እንዲህ አይነት ነገር ሲፈጠር በሌላ ጊዜ መርጦ የሚወጣበትን መንገድ መፈለግ ነው የሚበጀው፡፡ ምክንያቱም አደባባይ መውጣት፣ መቃዎም ህገ መንግስታዊ መብት ነውና። ነገር ግን ወደ ግጭት ሊያመሩ የሚችሉ ሌላ ደም አፋሳሽ ነገሮችን የሚያሳዩ ነገሮች ካሉ መንግስት እንደመንግስት አቋም መውሰዱ የሚኮነን አይደለም፡፡ ምክንያቱም መጪው ነገር ለሀገርም ለህዝብም ጎጂ ነው ብሎ እስካመነ ድረስ የመንግስትንም ነገር መጠበቅ አለብን፡፡ መንግስት ይህንን ሲያደርግ እከሌ በዚህ ቀን አድርግ እከሌ ደግሞ ይሄኛውን ቀን ጠብቀህ አድርግ የሚል ጠበቅ ያለ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት እንጂ ሙሉ ለሙሉ ከልክያለሁ ማለትም የመብት መንፈግ ጥያቄ ስለሚያመጣ ሊያስብበት ይገባል፡፡ እኔ በአጠቃላይ የማየው እልህ መያያዝና የነገሮችን ውጥረት ነው፡፡ ይሄ መርገብ አለበት ባይ ነኝ፡፡
ከቤተክርስቲያን ዶግማና ቀኖና ውጪ የተገነጠሉትን አካላት መንግስት ለምን አደብ ማስገዛት አልቻለም ብለሽ ላነሳሽው ጥያቄ መልስ መስጠት የሚችለው እራሱ መንግስት ብቻ ነው። ይህንን መገመት አልችልም፡፡ የተገነጠሉትን መንግስት እየደገፋቸው ነው ይባላል ያልሽውን ነገር በተመለከተ በሲኖዶስ የተወገዙት አካላት በመንግስት ድጋፍና ጥበቃ ነው ወደ የቤተ ክርስቲያናቱ እየገቡ ያሉትና ይሄ ፈፅሞ ትክክል አይደለም፡፡
መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ኒውትራል ነው መሆን ያለበት፡፡ ከገለልተኝነትም ባሻገር ህጋዊ ወደ ሆነው ተቋም ማዘንበል አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ህጋዊነት ያለውን ተቋም እስካላከበርነው ድረስ ሁከቶች እየተባባሱ ለሌላ ደም መፍሰስና ግጭት ብሎም አላስፈላጊ ለሆነ ተግባር ይዳርጋሉና የመጀመሪያው ነገር ህጋዊ ለሆነው ተቋም ህጋዊነቱን ማፅናት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ ወገን ጥያቄዎች አሉ ከተባለም ጥያቄ አቅራቢዎቹ ህጋዊ በሆነው በቤተ ከርስቲያኒቱ ዶግማና ቀኖና መሰረት እንዲሄዱ ማድረግ ወይም አሁን በተጀመረው በፍርድ ቤት ሂደት ጉዳዩ ስለተያዘ ፍርድ ቤት ውሳኔና ብይን እስኪሰጥ ድረስ ሁሉም ባለበት እንዲቆም መደረግ አለበት፡፡ ይህ ማለት ቤተ ክርስቲያኒቱም በያዘችው እነዛኞቹም ባሉበት እንዲፀኑ አድርጎ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ መጠባበቁ የተሸለ ይመስለኛል፡፡ እኔ ይሄ ነው የሚታየኝ፡፡
ታዋቂ አትሌቶችና ባለሀብቶች ያሉበት የሽምግልና ቡድን ተቋቁሟል ከእነሱስ ምን ይጠበቃል?
ለተባለው ጉዳይ እንዲህ አይነት ነገሮች ሲከሰቱ የሽማግሌዎች ሚናም ትልቅ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ የእነሱ እንቅስቃሴ መጀመሩም ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም የሽማግሌዎቹ እንቅስቃሴ ምንን መሰረት ያደረገ ነው ለሚለው ቅዱስ ሲኖዶሱ በሰጠው መግለጫ የቤተ ክርስቲያኒቱን ህግና ቀኖና ጠብቀው እነ አትሌት ኮ/ል ደራርቱ ቱሉ እየሰሩ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይሄ ጥሩና ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ በዚህ ነገር መሃል ያሉት እነሱ ናቸውና ይሄንን ውጥረት አርግበው ሀገር ወደ ሰላም የምትመጣበትን መንገድ ቢሰሩና ለሀገራቸውም ለህዝባቸውም ታሪካዊ አሻራ ቢያስቀምጡ ደስ ይለኛል፡፡ የማንም ሰው ደም መፍሰስ የለበትም፡፡ በዚህች አገር ላይ ግጭት ደም መፋሰስ፣ መፈናቀል ጦርነት ሁሉም ይበቃል፡፡ ምክንያቱም በሰሜኑ ጦርነት ብዙ ወገን አጥተን ፣ ብዙ ንብረት ወድሞ ህዝቡ ከቀየው ተፈናቅሎ ለረሀብና ለችጋር ተጋልጦ ያ ችግር ተቋጨ እፎይ አልን ስንል ነው ይሄ ውጥረት የመጣው፡፡ አሁን ላይ አዛውንት ህፃናት ጎልማሳው ሁሉም ጭንቀት ላይ ነው፣ ሀገር ከሀዘኗ ብዛት ማቅ የለበሰችበት ጊዜ ነውና ይህ እንዳይከሰት፣ ዳግም ደም እንዳይፈስ፣ አገር እንዳትፈርስ የሚጨነቁና የሚቆረቆሩ አካላት ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በርትተው ሌሎችንም ሰዎች ከጎናቸው ይዘው አልቅሰውም ሆነ ተንበርክከው ህንን ጉዳይ ቢያስቆሙ ምኞቴ ነው፡፡
ከሜይኒስትሪም ሚዲያውም ሆነ ከማህበራዊ ሚዲያው ምን ይጠበቃል ለተባለው ትልቁ ጉዳይ እዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ የሚዲያው ሚና ትልቅ ነው ለበጎ ነገሩም ሆነ ለግጭት መባባስ፡፡ እናም እዚያ ላይ ትልቅ ሀላፊነት ያላቸው የሚዲያ አካላት ያስፈልጋሉ። ሀላፊነት ሲባል ሁሉ ነገር ተዘርግፎ አይነገርም አደጋ ሊያመጣ ይችላልና፡፡ በህዝቦች መካከል መቃቃርና ግጭት፣ ለሀገርና ለህዝብ የማይበጁ ነገሮች ላይ ጥንቃቄ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ሀላፊነት ማለት ይሄ ነው፡፡  
የአንድ ሚዲያና የባለሙያ ብቃት የሚለካው ለሀገርና ለህዝብ ደህንነትና ሰላም በሚወስደው ጥንቃቄ ነው፡፡ ነገር ግን  አለመዘገብና ዝም ማለት ደግሞ በራሱ ሌላ ችግር ነው፡፡ በዚህ ወቅት ዝም ያሉ ትልልቅ ሚዲያዎች አሉ፡፡ ይሄ ማለት በሀገሪቱ ውስጥ ምንም አይነት ችግር እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል እየሞከሩ መሆኑ ነው፡፡ ይሄ ጉዳይ በታሪክም የሚወቀሱበት እንዳይሆን የጋዜጠኝነት ሙያቸው በሚፈቅደው የሙያ ስነምግባር ላይ ተመስርተው ዘገባ የመስራት ግዴታ አለባቸው፡፡ ዝምታው ግን የሚያዋጣ አይደለም፡፡
በሌላ በኩል የማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ እያንዳንዱ ሰው በምግባሩም በምኑም የተማረ ነው ማለት አይደለም፡፡ ከወዲያኛው ከወዲህኛው ሆኖ ሀይማኖት የሚዘልፍ፣ በቃላት በምን የሚወራወረው ብዙ ነው፡፡ ህዝቡ ደግሞ ይህን እየተመለከተ እንዳይታበይ መደረግ አለበት፡፡ አንዳንዴ እኛ ኢትዮጵያዊያን ብዙ ሳናነብ ብዙ ሳናውቅ ገና ብዙ ሳንመራመር ቴክኖሎጂው እየቀደመን ነው ማህበራዊ ሚዲያ ውስጥ የገባነው፡፡ አንድ መፅሀፍ ያላነበበ ሁሉ ነው ሶሻል ሚዲያ ላይ እንደልቡ የሚፅፈውና የሚናገረው፡፡ ስለዚህ ትራንስፎርሜሽኑ (ሽግግሩ) በእውቀት ላይ የተመረኮዘ ባለመሆኑ እዛ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምናየው መበጣበጥ ሀገሪቱ የፈጠረችው የብሄርተኝነት ፖለቲካና ሳናውቅ ሳንመራመር የገባንበት ስለሆነ ይሄም በራሱ ችግር ፈጣሪ ነውና አንዳንድ ጊዜ ይሄንንም የመቆጣጠር ሂደት ሀላፊነት በሚሰጣቸው አካላት ቢደረግ መልካም ነው፡፡
ስለሆነም የጥላቻ ንግግሮች፣ ህዝብን ከህዝብ ፣ሀይማኖትን ከሀይማኖት የሚያጋጩ ንግግሮችና ቪዲዮዎች የሚተላለፉባቸውን የማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞች ወዲያውኑ እያጠፉ መቆጣጠር ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ችግሩ ያለ ደም መፋሰስ የሚቋጭበትን መንገድ በጋራ መፈለግ አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡



Read 876 times