Saturday, 11 February 2023 21:02

ጉዳዩ የቋንቋም የብሄርም ሳይሆን ፖለቲካዊ ይዘትና ተፈጥሮ ያለው ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

`ችግሩን እንዲባባስ ያደረገው የመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው
                           (የህግ ባለሙያ አንዷለም በውቀቱ ገዳ )


        የዚህ ችግር መንስኤ በእርግጥ የቋንቋ ጉዳይ ነው ወይ በሚል ላነሳችሁልኝ ጥያቄ የቋንቋ ጉዳይ አይደለም የሚል ምላሽ ነው ያለኝ፡፡ ታዲያ የችግሩ ምንጭ ምንድነው የሚል ጥያቄ ካስከተላችሁ ደግሞ ፣ የቤተ ክርስቲያኗ ችግር ስር መሰረቱ በቀጥታ ከሀይማኖት ጋር የተያያዘ ሳይሆን የመደበኛው ዓለም ላይ ያለው የፖለቲከ ነፀብራቅ እንጂ ከቤተ ከርስቲያን በኩል አዲስ ዶግማና አስተምህሮ መጥቶ አይደለም፡፡ የተወሰኑ አካላት ሲሞክሩት የቆዩ ባህል አለ። እሱን በዚህኛውም ለመድገምና ያንን ንዶ አዲስ ነገር ለመፍጠር የፌዴራል ሥርዓቱን የተከተለ አደረጃጀት በሚል እነ አባ ሳዊሮስ ከማንሳታቸው በፊት አምናም በነቀሲስ በላይ የተሞከረ ነገር ነበር እንደምታስታውሽው፡፡ ታዲያ ያን ጊዜም ወደ ፊት ለፊት አይውጡ እንጂ እነ አባ ሳዊሮስም እንቅስቃሴውን ይደግፋት ነበር፡፡ አሁን ተሾሙ ከተባሉት ውስጥም የዚህ ጉዳይ አንቀሳቃሽ የነበሩ ነበሩ፡፡ ያኔ ይህ ቡድን ሲደገፍ የነበረው በፖለቲካ ሀይሎች ነበር፡፡
እነ ጃዋር መሀመድ፣ ኦፌኮዎች፣ በአጠቃላይ የኦሮሞ ብሄርተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ቡድንና እንቅስቃሴ ይደግፉት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ለጊዜው በእርቅም በይው በመነጋገር ተዳክሞ ቆየ፡፡ ቀጥሎም ሀገሪቱ ላይ የነበረው ሁኔታ እንደዚህ አይነት ጉዳይ ለማንሳት የሚያስችል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ማዕከላዊ መንግስቱ ከህውሃት ጋር በገጠመው ጦርነት የሁሉንም ድጋፍ ይሻ ስለነበረ ህውሃትን እስኪያሸንፍ ድረስ ይሄ ነገር የለም ነበር። አሁን መረጋጋቱንና የሰሜኑን ጉዳይ አንድ አቅጣጫ መያዝ ተከትሎ ይመስለኛል ይሄ ነገር አገርሽቶበት፣ ከማገርሸትም አልፎ አግሬሲቭሊ እየተኬደበት ነው ያለው፡፡ የሆነ ሆኖ የዚህ ችግር ስር መሰረት የውጪው ፖለቲካ እንጂ ቤተክርስቲያን ውስጥ ምንም አዲስ ነገር የለም። ቀደም ሲል እንዳልነው ችግሩ የቋንቋም የምንም አይደለም፡፡ አባቶችን የሚሰማቸው ጠፍቶ ነው እንጂ ቤተክርስቲያን በቀኖና ደረጃ የያዘችው “ሰው መስበክ ያለበት በቋንቋው ነው” የሚል ነው፡፡ ሲጀመር ቀላል ሎጂክ እናንሳ። ቤተ ክርስቲያን ቋንቋውን የማይሰሙ ዜጎች ጋር ሄዳ ምን ታገኛለች? ሌሎች ተፎካካሪ ትልልቅ እምነቶችም እኮ አሉ፡፡ እስልምና አለ ፕሮቴስታንቶች አሉ፡፡ ሁሉም ሰው አስተምህሮውን ለምዕመኑ ማስረዳት ይፈልጋል እኮ፡፡ የዛን አካባቢ ሰው ቋንቋ ካልተናገርሽ ከአካባቢው ሰው ጋር ካልተግባባሽ ትርጉም የለውም ወንጌልም እየተሰበከ አይደለም ማለት ነው፡፡ ይሄ በቋንቋ መስበክ ከበፊቱም ጀምሮ የሚሰራበት ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ ይህን ሁሉ ምዕመን ያፈራችውና እዚህ የደረሰችው ሰብካ ነው እንጂ በጠብመንጃ አስገድዳ አይደለም፡፡ ይሄ በጭራሽ ከቋንቋ ጋር የተገናኘ አይደለም፡፡ የቋንቋ ችግር ነው የሚል ካለ የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ እንኳን ኦሮሚኛን የሚያህል ብዙ ተከታይ ያለው ቋንቋ አይደለም በጣም በማትጠረጥሪያቸውና ጥቂት ቁጥር ባላቸው ማህበረሰብ ቋንቋዎች ሁሉ ትምህርቶችም ዝማሬዎችም ተተርጉመው ተዘጋጅተዋል፡፡ ይህ የተሰራው በቤተክርስቲያን በጀትና በቤተክርስቲያን ልጆች ነው፡፡
ለምሳሌ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተከሰተና በቴሌቪዥን በሚተላለፍ ጊዜ በየቤታችን ሆነን ነበር የምንከታተለው፡፡ ያው በወረርሽኙ ባህሪ መሰብሰብና አካላዊ ቅርርብ ስለማይፈቀድ ማለቴ ነው፡፡ ያን ጊዜ ታዲያ በማትጠረጥሪያቸው ቋንቋዎች ትምህርቶች ይሰጡ ነበር በሁዳዴ ጦም ጊዜ በቤታችሁ ሆናችሁ ተከታተሉ ሲባል በጣም ትንንሽ ቁጥር ያላቸው ብሄረሰቦች ዲያቆናት ወጥተው አስተምረዋል፡፡ ቤተክርስቲያን ያን ጊዜ “ስንዱዋ ወይዘሮ” ትባል ነበር፡፡ ምክንያቱም ሁሉ ነገር እንዳይጓደል ይሰናዳ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ያንን ያደረገችው በይድረስ ይድረስ ተሯሩጣ ሳይሆን ሁል ጊዜም የተሰናዳ ነገር ስላላት ነው፡፡ በአጠቃላይ ጉዳዩ የቋንቋም የብሄርም ሳይሆን ሌላ የፖለቲካና ከዚያም ከፍ ያለ አጀንዳ የመያዝ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ትልልቅ የሆኑ የኦሮሞም የደቡብም ጳጳሶች አሉ፡፡
ጉዳዩ የብሄርና የቋንቋ ቢሆን ኖሮ እነዚህ የኦሮሞና የደቡብ ጳጳሶች እነዚህን ህገ-ወጥ አካላት አያወግዟቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ግልፅ የሆነ ፖለቲካዊ ይዘትና ተፈጥሮ ነው ያለው፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዙት አካላት የመንግስት ድጋፍ አላቸው ብለህ ታምናለህ ወይ ላልሺኝ አዎ የመንግስት ድጋፍ አላቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ድጋፍ አላቸው ያልኩበትም ምክንያት አለኝ፡፡ አንደኛ ራሳቸው የመንግስት የመጀመሪያ ቁንጮ ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጥር 23 ቀን ለካቢኔያቸው በሰጡት ማብራሪያ አነጋገራቸው ቤተክርስያን ተበድያለሁ እያለች የሰጡት ትዕዛዝ “ኒውትራል መሆን አለበት” አሉ፡፡ እንዴ! ኒውትራል የሚኮነውኮ ሁለት እኩል በሆኑ አካላት ነው፡፡
አንደኛው አካል አንደኛውን አካል እያስገደደ እየዘረፈ ነው፣ አንደኛውን አካል “እኔ ህገወጥ ነው ብየዋለሁ” እየተባለ “ተነጋገሩ ተግባቡ” ማለት ኒውትራልነት አይደለም ገና ከመነሻው። ሁለተኛ ሰዎች ሞተዋል፡፡ ሰዎች ሲሞቱ አንድም ቦታ ላይ ምዕመን ከምዕመን ተጋጨ የሚል የለም፡፡ ሰዎቹን እየገደሏቸው ያሉት የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ናቸው፡፡ አሁን እኔና አንቺ በምናወራበት ጊዜ እንኳን ወለቴ ሰው እየተገደለ ነው፡፡ እኛም በጭንቀት ላይ ሆነን ዳታ እየሰበሰብን ነው፡፡ በጣም ጭንቀት ውስጥ ነው ያለነው ምክንያቱም እኛ ይህንን ነገር ለማስቆም እያደረግን ባለነው እንቅስቃሴ ቢያንስ ፍርድ ቤቱ የፀጥታ ሀይሎቹ ላይ እግድ ያወጡልናል ብለን ካመለከትን ሳምንት አለፈን፡፡ እና እያንዳንዱ ሰው ሲገደል የጥፋተኝነት ስሜት እየተፈጠረብን ነው፡፡ ምዕመናኑን የገደሉት የፀጥታ ሀይሎች እንጂ ምዕመን አይደለም፡፡ በክሳችንም ያቀረብነው ይሄንኑ ነው፡፡ አንድም ቦታ ምዕመን ከምዕመን አልተጋጨም፡፡ የትኛውም ቦታ ማለቴ ነው፡፡
የፀጥታ ሀይሎች ይህን ህገ-ወጥ አካል እያጣደፉና እያዘዋወሩ እዚህ ቦታ ግባ ባሉ ቁጥር ሰው እየሞተ ነው፣ እየተረበሸ ነው፡፡ በሞራልም እየደቀቀ ነው፡፡ የመንፈስ ስብራትም በህዝቡ ላይ እየደረሰ ነው፡፡ በአንድ በኩል ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ ፈለጉ እያልሽ ከዚያ እጥፍ ብለሽ በአጃቢና በኦራል ካልገቡ እያልሽ የምታደርጊው ግብግብ ነው የሰው ህይወት እየቀጠፈ ያለው፡፡ ይሄ ደግሞ የተለመደ ችግር ነው ከመንግስት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ መንግስት እንኳን ኒውትራል ሊሆን ቀርቶ ጭራሽ ቅዱስ ሲኖዶስ ባወገዘው ቡድን በኩል እየሆነ ለነገሩ መቀጣጠልና ፈር መልቀቅ ምክንያት እየሆነ ነው ባይ ነኝ፡፡
የቤተክርስቲያኗን በደል በተመለከተ ወደ ፍርድ ቤት የወደሳችሁት ጉዳይ ከምን ደረሰ ላልሽኝ እኛ የተደራጀ አቤቱታ ነው ለፍርድ ቤት ያቀረብነው፡፡ አቤቱታውን ያቀረብነው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ችሎት ነው፡፡ ይህ ችሎት እንደሌሎች ችሎቶች አይደለም፡፡ ሶስት ዳኞች ያሉት ሆኖ የሚያየው ደግሞ በህገ- መንግስቱ አንቀፅ 3 ላይ ያሉ መብቶች በሚጣሱ ጊዜ አቤቱታ ለሚቀርቡለት ስፔሻላይዝድ ችሎት ነው፡፡
ይህ ችሎት አቤቱታ በቀረበለት ጊዜ የመሰለውን ትዕዛዝና ውሳኔ ይሰጣል የሚል አንቀፅ አለ፡፡ ይሄ በአዋጅ ቁጥር 1234/13 ንዑስ አንቀፅ 11 ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ የተቀመጠ ምክንያት ነው፡፡
በዚህ መሰረት እኛ ለዚህ ችሎት የጠየቅነው የአካል ደህንነት መብት፣ የህይወት መብት፣ ከግጭትና ከጦርነት ቀስቃሽ ንግግሮች መታቀብ፣ የመልካም ስም መብት፣ የክብር ጉዳይን በተመለከተ የንብረት ጉዳይ ፣ ሌላው ቀርቶ መንግስት ቤተክርስቲያንን መጠበቅ እንዳለበት የሚደነግግ አንቀፅ 41 ንዑስ አንቀፅ 9 ላይ ያለ መንግስት የባህልና የቅርስ መንከባከብ ሀላፊነት እንዳለበት የሚገልፅ ነውና ባህልና ቅርስ አብዛኛው ያለው ቤተክርስቲያን ውስጥ ስለሆነ ማንም ቡድን ተነስቶ ይህን ባህልና ቅርስ ያለበትን ተቋም እንዲወር ማድረግ በእኛ አረዳድ ይህን አንቀፅ የሚጥስ ነውና በዚህም አቤቱታ አቅርበናል፡፡ ምንም እንኳ ባህልና ቅርስ ሌላም ቦታ ያለ ቢሆንም አብዛኛው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳለ ነው የምናምነውና በዚህም ላይ በአቤቱታችን ትኩረት ሰጥተነዋል፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው ኢትዮጵያ የምትኮራባቸው ቅርሶች ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዳሉ እየታወቀ ሆን ተብሎ አንድ ቡድን እንዲወር ማድረግ ቅርስና ባህልን ማጥፋት ነውና ይህን ባለማስጠበቁ መንግስት ተጠያቂ ነው ስንል አቤቱታው ላይ አካትተናል፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ባለፉት ሁለት ሺህ አመታት ቅርሶችን ባህሎችን ሀላፊነት ወስዳ ስትጠብቅ ኖራለች። አሁን የፈለገው አካል ይውሰድ ተብሎ ሲተው መንግስት በባህልና በቅርስ መንከባከብ ግዴታው ላይ ግድየለሽ እየሆነ ነው ማለት ነው፡፡
በቃል ደግሞ ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ንግግሮች እየተላለፉ ነው፡፡ ለምሳሌ በቀድሞ አቡነ ዴስታጢዎስ የተባሉት ግለሰብ አንድ ደብር ላይ ያደረጉት ንግግር ምን ይላል መሰለሽ “እናንተ የወለጋ ህዝቦች ቤተክርስቲያን ያወገዘችው እኛን ሳይሆን እናንተን ነው ቤተክርስቲያን እናንተን እረገመች ይህንን መፍቀድ የለባችሁም” የሚል ለአመፅና ለግጭት የሚያነሳሳ ንግግር አድርገው በሚዲያ ተላልፏል፡፡ ይሄ በጣም ነውር ነው፡፡ ይሄ ንግግር ማለት አንደኛ እዚህ አካባቢ ካህናት አሉ፡፡ ሁለተኛ እነዚህ ሰዎች ሊያስተዳድሩ ሲሄዱ ግደሏቸው ማለት ነው ተመልከቺ እንግዲህ፡፡ እነዚህ ሰዎች ጉዳዩ እኛ ጋር ነው ብለው አውርደው እንደ መያዝ አንተን ነው የሰደቡህ አንተን ነው ያወገዙህ ብሎ ማለት ግጭት ቀስቃሽና በሚዲያ የተላለፈ ነው ብለናል፡፡
ሁለተኛ ሲኖዶሱ የተከበረና ከ60 ሚሊዮን በላይ አባል ያለው ነው፡፡ ስሙም የተከበረ ነው። ይህን ሲኖዶስ የሰሜን ሰዎች መሰባሰቢያ፣ ለጥቅም የተሰባሰበ እየተባለ የተከበረን ስም አዋራጅ የሆነ ንግግር ሲደረግ መንግስት ዝም ማለቱ በራሱ ተገቢ አይደለም፣ ቤተ ክርስቲያኗ ራሱን የቻለ ክብር አላት ብለን አመልክተናል። ከዚያ ደግሞ በህገ- መንግስቱ አንቀፅ 27 ላይ የተቀመጠ የእምነት፣ የአመለካከት፣ የሀይማኖት መብት አለ፡፡ እና አንድ ሰው አመለካከቱን፣ እምነቱን ሲቀርፅ በፈለገውና በሚያምንበት መልክ መቅረፅ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ብሄር ብሄረሰብ ብሎ ማሰብ ኑፋቄ ነው ብሎ ማሰብ መብቱ ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው የሰውን ልጅ አበበ ከበደ ብሎ በብሄሩ አማራ ኦሮሞ ትግሬ ብሎ መተንተን በቤተክርስቲያን የተገባ አይደለም ስለዚህ ይህንን ቤተክርስቲያን እንድትቀበል ማስገደድ ተገቢ አይደለም፡፡ ያንን ፖለቲከኞችና ሌሎች ማመን ይችላሉ። ነገር ግን ቤተክርስቲያን ይህን ተቀበይ እየተባለች እየተገደደች ነው፡፡ ቤተክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ የሰው ልጆችን አቡነ እከሌ ብላ ትሰይማለች፡፡ የዓለም ስሙን ትቶ የክርስትና ሥም ይሰጠዋል በዚያ መልክ ነው የሚካሄደው፡፡ ይህንን ጥለሽ አይ በዓለም ስሜ እጠራለሁ ብለሽ የመወሰን መብት የለሽም።
ሰው በስሙ አይጠራ ማለት ሳይሆን በሲኖዶስ ስትሾሚ የዓለም ስምሽን ትተሸ ነው ቤተክርስቲያኗ በምትሰጥሽ ስያሜ የምትጠሪው ይሄ የቤተክርስቲያኗ ህግ ነው፡፡ ይሄ ጉዳይ መሻሻል ቢኖርበትና ይሻሻል ቢባል እንኳን የሚያሻሽለው ቅዱስ ሲኖዶስ እንጂ ሌላ አካል አይደለም፡፡ እኛን ምሰሉ ማለት አይቻልም። በፌዴራል አደረጃጀት ተደራጁ ማለት አይቻልም፡፡ ሀገረ ስብከት በራሷ አቅጣጫ የምትቀርፀው ነው፡፡ ይህንን አድርጎ እነ እንትናን ምሰሉ ማለት እራሱ የቤተክርስቲያኗን የእምነትና የዓመለካከት ነፃነት የሚጋፋ ነው፡፡ ማነው የቤተክርስቲያንን አይዶሎጂ የሚቀርፀው? ስለዚህ ያንንም እየተጋፋ ነው፡፡
ክርስቲያኖች ወይም ማንኛውም የእምነት አባላት ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት የአስተዳደርና የትምህርት ተቋም ያቋቁማሉ የሚል ህገ-መንግስታዊ አንቀፅ አለ፡፡ አሁን መንግስት እያደረገ ያለው ይሄ የኦሮሚያና የብሄር ብሄረሰቦች የተባለው ሲኖዶስ ሲቋቋም ያኛውን ሲኖዶስ እየተጋፉ ነው ማለት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ማድረግ ያለባት እኔ ማጆሪቲዬ ተሰብስቤ ይሄን ይሄን ሁን ብያለሁ፡፡ ያኛውን አካል መንግስትን አግድልኝ ነው የምትለው። ሄንን ነገር ዝም ማለት በራሱ ቤተክርስቲያን ያላትን ለማንኛውም ሰው የተሰጠ መብት እንደመጋፋት ነው፡፡
በሌላ በኩል ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ሰትቷል እነዚህ የሚከተሉት አባቶች ከአሁን ጀምሮ ከድቁና እስከ ጵጵስና ያለው ማዕረጋቸው ተገፍፏል የተወገዙ ናቸው፣ ያቀረቡትም ሀሳብ በቤተክርስቲያን የተከለከለ ነው ብሎ አውጇል ቅዱስ ሲኖዶስ። ይህንን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና አዋጅ አንድም የመንግስት መገናኛ ብዙሃን አልዘገበም፡፡ ይሄ በመንግስት ኮሙኒኬሽን በኩል በትዕዛዝ ነው የተደረገው፡፡ ይሄንን ደግሞ እኛ የምንለው በህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ በተለይ በመንግስት ፈንድ የሚተዳደሩ የሚዲያ ተቋማት የሁሉንም አይነት ወገን ሀሳብ ማስተላለፍ አለባቸው ይላል፡፡ ይሄ የቅዱስ ሲኖዶስ ሀሳብ የብዙ ሚሊዮኖች ሀሳብ ነው፡፡ ትክክል ነው አይደለም የሚለው አይደለም፣ ማስተላለፍ ግን ግዴታ ነው፡፡ ይሄም ህገ መንግስታዊ መብትን የጣሰ ነው ብለን ለመሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ችሎት አቅርበን ነበረ፡፡ ባለፈው አርብ ለሰኞ ተቀጠርን ሰኞ ለረቡዕ ተቀጠርን ረቡዕ ከቀኑ 8፡00 ስንሄድ ትዕዛዝ እንደሚሰጡንና ትዕዛዙን ይዘን እግዱ ወደ ሚመለከታቸው ለመሮጥ ነበር ሀሳባችን፡፡ ረቡዕ 5፡30 ላይ አቤቱታ ቀርቦባችኋል ተባልን፡፡
አቤቱታው በተወገዙት አካላት በኩል ባለ ቃል አቀባይ ነው የቀረበው፡፡ “እግዱን ከማውጣታችሁ በፊት እኔን ስሙኝ በሚል አቤቱታ አቅርቦ ነበር እኛ ደግሞ እሱን በግሉ ከሰነው ነበር፡፡ እኛ  የከሰስነው ከተወገዙት ከሶስቱ ተሿሚዎችና እነዚህ ከሾሟቸው 25ቱ ጋር አብረን ነበር፡፡ ለምን ከሰስነው መሰለሽ ራሱን በሚዲያ የኦሮሚያና የደቡብ ሲኖዶስ ቃል አቀባይ ብሎ ስለገለፀ ክስ ውስጥ አስገብተነው ነበር፡፡ “አቤቱታውን በቴሌቪዢን ሰምቻለሁና አስተያየት ልስጥበት ብሎ ለችሎቱ አቀረበ። እኛ ስላልሰማን ጊዜ ለመቆጠብ አቤቱታውን እዚያው ተቀበልንና ከችሎት ወጠን፡፡ እኛ እዚያው ተነጋግረን ለችሎት ምላሽ ለመስጠት ነበር የወጣነው፡፡ ይሄ ሰው ብቻውን ነው የመጣው ነገር ግን “እኛ” እያለ ነው የፃፈው፡፡ ነገር ግን እርግጠኛ ነን ውክልና የለውም ስለዚህ ይህን ልጅ ከክሱ ብናስወጣው  ችሎቱ በዕለቱ ወደያዘው መደበኛ ቀጠሮ እናልፋለን የሚል ዘዴ ፈጠርን፡፡ ከዚያ ልጁን በክሱ አንፈልገውም ብለን አመለከትን፡፡ በግድ ልካተት አለ፡፡ በግድ ክሰሱኝ ማለት አይቻልም፡፡ ከሳሽ ካልፈለገሽ አልፈለገሽም አበቃ፡፡ ከዚያ ይሄ ልጅ ምናለ የነ አቡነ ሳዊሮስ ጠበቃ መሆኔ  አይቀርም እኔ ነኝ የምሆነው አለ፡፡
ገና ለገና ጠበቃ ሳይሆን እሆናለሁ ብሎ መከራከር አይችልም ይሰናበትልን ፍርድ ቤቱም ዛሬ ወደያዘው ጉዳይ ይሻገርልን አልንና አመለከትን፡፡ አንተ እጅህ ላይ ምናለ ተባለ አባቶች በፀጥታ ችግር ስላልቻሉ ነው እንጂ የጥብቅ ናውን ስራ ይሰጡኛል አለ፡፡ ፍርድ ቤቱ ይዘህ ና የሚል እድል ሰጠው፡፡ እኛ ትዕዛዝ እንወስዳለን ያልን ሰዎች እሱ ገና ውክልናና ከነ አቡነ ሳዊሮስ አቤቱታ ይዞ ይመጣል በሚል ለትላንት ለአርብ ተቀጠርን፡፡ አርብም ትዕዛዝ ይሰጣል ማለት አይደለም፡፡ ልጁ የነሱን ውክልና ይዞ መጥቶ ልንከራከር ነው ማለት ነው  በዚህ መሃል ችግሩ እየተባባሰ ነው፡፡ ረቡዕ ዕለት ትዕዛዝ ከፍርድ ቤቱ ወጥቶ ቢሆንና ለኦሮሚያ ፖሊስ እግድ ቢሰጥ ኖሮ (ሀሙስ) ወለቴ ላይ ሰው አይሞትም ነበር፡፡ ይሄ እያሳዘነን ነው በእርግጥ ፍርድ ቤቱም የአንድ የአንድ ቀን አጭር ቀጠሮ ነው እየሰጠን ያለው፡፡ ነገር ግን በዚህ መሃል ሰው እየሞተ መሆኑ እያስጨነቀን ነው ያለውና በዚህ ቅሬታ አለን፡፡
መፍትሄው ምንድነው? የመንግስትስ ዝምታ አንድምታው ምንድነው? የተጀመረውስ ሽምግልና እስከ ምን ይዘልቃል ለተባለው ዛሬ (ሀሙስ) ቅዱስ ሲኖዶሱ ከረር ያለ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
እንደዚህ መካረሩ የትም አያደረስም። መንግስት ይደግፋቸዋል ብየ የማሰባቸው አካላት ላይ እጁን ማንሳት አለበት፡፡ መንግስት ባይደግፋቸው እኮ እነሱም ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ይደራደራሉ፡፡ መንግስት የማይመለከተው ውስጥ ገብቶ ነው እየደገፈ ያለው፡፡ እነዚህ ሰዎች ቅዱሳን አባቶች የነበሩ ናቸው ቁጭ ብለው ከወንድሞቻቸው ጋር ይነጋገሩ፡፡ እንዳይነጋገሩ እያደረገ ያለው የመንግስት አቋም ነው፡፡ መንግስት እያቻቻለ አይደለም፡፡ አሁን የተወገዙት አካላት ይቅርታ ጠይቀው መመለስ ይችላሉ መነጋገር ይችላሉ። ነገር ግን መንግስት በኦራልና በወታደር እያጀበ እየገፋቸው ከሄደ ወደ ቀልባቸው አይመለሱም። እንደኔ እንደኔ መንግስት አሁንም ኒወትራል መሆን አለበት ጉዳዩ ከቁጥጥር ውጪ እየወጣ የሚሄድ ይመስለኛል፡፡
ከዚህ አንፃር መንግስት እጁን መሰብሰብ አለበት አደራዳሪም ቢሆን ንፁህ አደራዳሪ ይሻላል ባይ ነኝ፡፡ አደራዳሪ ስልሽ ዞሮ ዞሮ ቤተክርስቲያን በራሷ ቀኖና ነው ጉዳዩን የምታየው የሚመጣ ምንም የለም፡፡ የሆነ ሆኖ እነዚህ የተወገዙ አካላት ቤተክርስቲያን የሚያከብሯት ቤታቸው ስለሆነች ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ ከኋላ ሆኖ ጎሽ ጎሽ እያለ የልብ ልብ የሚሰጣቸው መንግስ እጁን ይሰብሰብ የሚል መልዕክት አለኝ አመሰግናለሁ።  

Read 1025 times