Saturday, 11 February 2023 21:10

የነባሩ አለኝታ ወራሽ? ወይስ አዲስ የለውጥ አርበኛ? በጠማማ መንገድ ሁለቱን ለማስታረቅ የሚደረግ አንድ ሙከራ አንመልከት።

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ንጉሡ የሃምሌት አባት፣ ከቤተመንግስቱ መናፈሻ ውስጥ ያለስጋት ዘና ብሎ  በተጋደመበት ነው የሞተው። የንጉሡ ወንድም ነው ገዳዩ። ማለትም የሃምሌት አጎት ነው ወንጀለኛው። ቤተኛም ወንበዴም ሆነ  ማለት ነው።
ገዳይም ተቆርቋሪም፣ ከሃዲም አልጋ ወራሽም፣ ሀዘንተኛም ደስተኛም ለመሆን ይጣጣራል።
ስለመርዶና ስለ ቀብር ያወራል- የቅርብ ዘመድ ነውና።
ለንግስ በዓልና ለሰርግ ድግስም ይዘጋጃል- አልጋ ወራሽ ለመሆን፣… የዙፋን ወራሽ ብቻ ሳይሆን የመኝታ ቤትም ወራሽ ሆኗል። ንግስቲቷን ያገባልና።
ትያትሩ የሚጀምረው ይህን ባለሁለት ፊት ቅዠት በማሳየት ነው።
ጥበበኛው ባለቅኔ ፀጋዬ ገብረመድህን ወደ አማርኛ እንዴት እንደተረጎመው ተመልከቱ።
የወንድሙን ዙፋን ወርሷል። የወንድማችን ዘውድ ዘውዳችን ነው በሚል ስሜት እንደማለት ነው። የወንድሙን ሚስት ንግሥቲቱንም ይወርሳል- የወንድማችን ፍቅረኛ ፍቅረኛችን ናት የሚል ሃሳብ ያቀርባል።
አዲሱ ንጉሥ፣ በሃዘን እንጉርጉሮ ንግግሩን ከጀመረ በኋላ፣ ሃዘኑን በእንጥልጥል ትቶ፣ ስለወራሽነቱ ያወራል።
ብዙም ሳይቆይ የደስታና የፌሽታ ስሜቱን እንዳይጋነን፣ ገዳይነቱም እንዳይጋለጥ፣ በንግግሩ ላይ ሀዘንተኛ ስሜት ይጨምርበታል።
እንደገና ሁለቱንም ስሜቶች  ለማስታረቅ ይጣጣራል።
አንድ ዓይን ቢስቅ ሌላው እንደሚያነባ ይናገራል። የዘውድ ውርስና ንግስቲቱን ማግባት አገራዊ ግዴታችን፣ መንግስትንም የሚያበረታልን፤ ነውና አባሪ ተባባሪ ሁኑ ብሎ ያግባባል። አለበለዚያ እኔን ካልደገፋችሁ  ከሃዲነት ይሆናል ባይ ነው።
ደግሞ የውጭ ጥቃትና ወረራ እየመጣብን ነው፤ አገራችን እየተደፈረች ነው በማለት ያስጠነቅቃል።
ወራሽነቱን ለማሳመን ይሰብካል። ድል አድራጊ አዲስ የለውጥ አርበኛ መሆኑንም ይናገራል። አዲስ ፀሐይ ወጥታለች ተብሎ እንዲታወጅ ትዕዛዝ ይሰጣል።
አዲሱ ንጉሥ፡…
በግርማዊ ወንድማችን ድንገተኛ ሞት መቀጠፍ፣
ቅስማችን በሀዘን  ሲገረፍ፣
ቁስሉ እስከ ወዲያኛውም በልቦናችን ሲነደፍ፣
ዳር- እስከ-ዳር ግዛታችን በዋይታ ዓዋጅ ስትመታ፣…
…ግና የተግባር ግዴታ
በእንባ ስለማትገታ፤…
ልቅሶአችንን በመጽናናት እግበናችን ስር ቋጥረን፣
ፍቅሩም ፍቅራችን መሆኑን፣ ተገንዝበን አስገንዝበን፣
የተፈጥሮና የጊዜን ፍቃድ እንቀበላለን።
እና… እስከዛሬ ድረስ፣ የሟቹ ወንድማችን ሚስት
የነበረችይቱን ንግሥት፣
ሕገኛ ባለመብቲቱን፣ ለዚህ ጦር ላሳሳው መንግስት፣…
የፍስሐችን ፈገግታ፣… ለሐዘን ግንባር ገብሮ፣
አንድ ዓይን የሳቀ ቢመስል፣… ሌላው በእንባ ወዝ ተቋጥሮ፣
ባክፋይ ምሳ እንዳመቁት ምርቅ፣
መከራና ደስታችን ባንዲት ጀንበር ላይ ብትወድቅ፣
ሁለቱንም አነጻጽረን፣ ተከታትለው እንዲውሉ
ብንወስናቸውም ቅሉ፤
ልባችን ከቀብሩ ስርዓት፣… ተግባራችን ከተክሊሉ
መሆኑንም አስተውሉ፤…
ታዲያ፣ እናንተም በዚህ ጉዳይ በሃሳብ እንደምታብሩ፣
ለሀገር ነውና ዕድሩ፣
የግብረ አበርነታችሁ መታመን ነው ምስክሩ።
ከዚህ ጉዳይ ጋር አስታክከን፣ በየልቦናችሁ ማኅደር፣
የኖርዌይን መስፍን ድፍረት እንፈቅዳለን ለማሳደር፤
በፎርጠንብሮስ፣ በልጅ አፍ፣ ዴን አትዘልቅም ተሰድባ፣
በዚያ በአፍላ ኮበሌ፣ ምራቁን ባልዋጠ ጉርባ፣
የጦር ኃይላችንን ንቆት፣ አቅማችንን ገምቶት፣
በወንድማችን ሞት ሳብያ፣ የተነጣጠልን መስሎት፣
የኔ ነው የሚለው ግዛት የሱ አለመሆኑን አጥቶት፣
ሟቹ ጀግናው ወንድማችን፣ አባቱን ፉክክር ገጥሞት፣
በጎበዝ ወግ አሸንፎት፣
በጉግሥ ሥርዓት ገድሎት፣
በሕግ መርታቱን ረስቶት፣…
የልብ ልብ ደንድኖ፤ የድፍረት ድፍረት ደፈረን፣
ነጋ ጠባ በደብዳቤው በነገሩ አሰለቸን።…
አዲሱ ንጉሥ፣ ደጋፊዎችን ለማበራከት፣ ከማስፈራሪያና ከማስጠንቀቂያ ጎን ለጎን የማባበያ ዘዴዎችንም ይጠቀማል። እንዲህ እንፈልጋለን ብለው ሲጠይቁት፣ “ይሁን፤ ፈቅደናል” እያለ ውለታ ያስመዘግባል። የሟቹን ልጅ፣… ኀምሌትንም ለመሸንገል ይሞክራል።… እንዲህ ይላል፣ አዲሱ ንጉሥ።…
አዲሱ ንጉሥ፡
አንተስ የወንድምዬ ልጅ፤ ኀምሌትስ ምን ያሰኝሃል?
የወንድም ልጅ እኮ፣… ልጅ ነው። “ባይወልዱትም ልጅ” ይባላል።
ኀምሌት፡
ይባላል አዎን እርግጥ ነው፤
የፍቅሩንማ ሆድ ይፍጀው።
አዲሱ ንጉሥ፡
ታድያ፣ አሁንም ምነው ልብህ፤ ይመስላል የቀዘቀዘ?
ኀምሌት፡
ኧረ ምን ቆርጦት ጌታዬ። ወብቆት ነው የነበዘ።
ንግሥት፡
ተወው ልጄ፣ ተወው ኀምሌት፤ ካልተዉት አይተውም ሐዘን፤
ለሀገሪቱ ስትል፣ ይፍካ ልብህ፤ በሷስ አይጨፈን።
አባትክን ታስመልስ መስሎህ፣ በሐዘን ጥልቀት ምርምር፣
በምድር ዴን ትቢያ ላይ፣ ግንባርክን ከቶ አታኮስትር።
ኗሪ ሁሉ ሟች መሆኑን፣ ታውቃለህ ሁሉም በተራ፣
በዕድሜ ድልድይ ተሻግሮ፣ ወደዘለዓለሙ ሥፍራ፣
የማታ ማታ እንዲያመራ።
አዲሱ ንጉሥ፡
እኛም አላጣነው ኀምሌት፣ ልብህ የሬት ማቅ ማጥለቁን፣
መክፈል ግብርህ እንደሆነ፣ ለአባትህ የሐዘን ምሱን፤…
አባትክም አባት ነበረው፤ የዚያም አባት፣ አለው አባት፣
ግን በየተራው ሲለየው፣ የሞትን ጽዋ እየጠጣት፣
የዚያም ልጅ እንዳንተው አዝኗል፣ እንደየሐዘኑ ጽናት፤
ግን ሐዘንን እንደ ድግምት፣ ከዕለት ወደ ዕለት ማኘክ፣
ፍሬ ቢስ መሰላቸት ነው፣ እንዲሁ በከንቱ መቸክ።
የወንድ ልጅ ወግ አይደለም፣ ይኸ እንደዚህ ብጤው ግድፈት፤…
ለመንግሥተ ሰማይ ድፍረት፣
ለመለኮት ኀይል ንፍገት፣
የአእምሮም ሰላም ማጣት፣ ከመንፈስ ጸጋ መራቆት፣
አለመገመት ይባላል፣ ያንዳች አስተያየት እጦት።
ሞት የተለመደ ጽዋ፣ መፈጸሙ የማይወገድ፣…
እኛ ምን እንደሆንን ሳናውቅ፣ ዛሬ ሰው ነገ ትቢያ ዐመድ።
እምን ላይ ነው መበለጡ?
የከንቱ መንፈራገጡ?
በተፈጥሮ ግፍ መዋል ነው፤ ይኸ ህገ-ወጥ ሀዘን፣
ከእግዚአብሔር አብ መቀናቀን፣
ከሙታንም መቀናቀን፤…
ፍሬ ከንቱ ነው ጥበቡ፤ በአእምሮም ሚዛን ቢሆን፣
“ሰው ሆይ አንተ አፈር ነህ” ብሏል፤ ከዘፍጥረት እስከ ጽዮን፤…
በል እንግዲህ ተለመነን፣
ይኸን የወይታ ሰቀቀን፣
ከልብህ አውልቀህ ጥለህ፣ እንደ አባት ተቀበለን፤
አገር በይፋ ይወቀው፤ አባት እንሁንህ ልጅ ሁነን።
ለኛም ሆነ ለአልጋችንም፣ አንተ ብቻ ነህ የምትቀርበን፤
እኛ እንደ ልጅ ፈቅደንሃል፤ አንተም እንደ አባት ፍቀደን።…
ቪተንበርግ ዩኒቨርሲቲ፣ ልትሄድ ላሳሰበህ ጉዳይ፣
ልባችን ቅር ተሰኘ፤… ርቀኸን ፊትክን  እንዳናይ፣
ይሆናልና አትሂድብን፣ አንተው ነህ ያለኸን ሲሳይ፣
ልጃችን ባለሟላችን፤ ፍቅራችን የዓይናችን አዋይ።
ንግሥት፡
ሰሞኑን ጸሎቴ ይኸው ነው፤ ኀምሌት ልጄ አታሳፍረኝ፣
አትሂድ ወደ ቪተንበርግ፤ እኔን እናትክን ጥለኸኝ።
ኀምሌት፡
እናት ዓለም ከምታፍር፣… ልቅር እሺ፤ ምን ቆረጠኝ።
አዲሱ ንጉሥ፡
እሰየው ልጄ፤ ተባረክ፤ ቀና አንደበት እንደዚህ ናት፤
ምድረ ዴን የኛም ያንተም ነች፤ እና አብረን እናገልግላት።…
ይኸው በጥሞና ስሜት፣ ግንባርህ ድንገት ቢፈካ፣
የኛም ልቦና ተነካ።…
አዲሱ ንጉሥ ያሰበውና የተመኘው ሁሉ እየተሳካለት ይመስላል። ገዳይና ሐዘንተኛ፣ ቀብርና ንግሥ፣ ገርሳሽና ወራሽ መሆን እንደሚቻል አምኗል። ደግሞስ ምን ቀረ? ፌሽታና ርችት የደስ ደስ?
እንዲህ ይላል አዲሱ ንጉሥ።
…የምስራች መድፍ ይተኮስ።
ሁሉ ሰምቶ ይቀበለን፤ ምድሩ፣ ሕዝቡ፣ አገሩ፣
አዲስ ፀሐይ መፈንጠቋን፤ ለመላው ዓለም ያብሥሩ።
አድባራቱ በየአድማሱ፤ አስተጋብተው ይመስክሩ።Read 593 times