Saturday, 11 February 2023 21:22

ትምህርት ተራቆተ የልጆች እድሜ ባከነ። ማን ላይ እንፍረድ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

 • የውድቀቱን መንስኤ ያወቀ ይፍረድ።
      • ነገር ግን፣ “ያወቀ” ሰው፣… “ለመፍትሔ” ቅድሚያ ይሰጣል እንጂ “ለውንጀላ” እና “ለፍርጃ” አይቸኩልም። እና እስካሁን መፍትሔ   ሰምታችኋል? ወይስ ውንጀላ ወይም ማስተባበያ ብቻ?
      • ደግሞስ፣ ትምህርት በጣም እንደተራቆተ የሚገለጥልን፣ ገና ዘንድሮ ነው? እስከዛሬ የት ነበርን?
      • በ12ኛ ክፍል ፈተና፣ “የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ” ያገኙ ተማሪዎች፣ 3.3 በመቶ ብቻ መሆናቸው ያስደነግጣል? ያሳዝናል? አዎ ያሳዝናል።  ከአንድ ሺህ ተማሪዎች መካከል፣ 33 ብቻ ናቸው የማለፊያ ነጥብ ለማግኘት የቻሉት። የኪሳራውና የብክነቱ ብዛት ያስቆጫል።
      • ነገር ግን፣ ተማሪዎች በቅጡ ትምህርት ሳያገኙ፣ በወጉ እውቀት ሳይጨብጡ እድሜያቸው በከንቱ እየባከነባቸው እንደሆነ የሚታየን፣ በ12ኛ ክፍል ፈተና ብቻ ነው? ለ12 ዓመታት ዞር ብለን አይተንና ታዝበን አናውቅም? አሳስቦን አያውቅም? “በማትሪክ ውጤት” ብቻ እንጂ፣ በሌላ ዘዴ ሊታይ የማይችል ረቂቅ ምስጢር ነው እንዴ፣ የትምህርት መራቆትና የተማሪዎች የእድሜ ብክነት?
         
        የውድቀቱን መንስኤ ያወቀ ይፍረድ።
ነገር ግን፣ “ያወቀ” ሰው፣… “ለመፍትሔ” ቅድሚያ ይሰጣል እንጂ “ለውንጀላ” እና “ለፍርጃ” አይቸኩልም። እና እስካሁን መፍትሔ ሰምታችኋል? ወይስ ውንጀላ ወይም ማስተባበያ ብቻ?
ደግሞስ፣ ትምህርት በጣም እንደተራቆተ የሚገለጥልን፣ ገና ዘንድሮ ነው? እስከዛሬ የት ነበርን?
በ12ኛ ክፍል ፈተና፣ “የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ” ያገኙ ተማሪዎች፣ 3.3 በመቶ ብቻ መሆናቸው ያስደነግጣል? ያሳዝናል? አዎ ያሳዝናል። ከአንድ ሺህ ተማሪዎች መካከል፣ 33 ብቻ ናቸው የማለፊያ ነጥብ ለማግኘት የቻሉት። የኪሳራውና የብክነቱ ብዛት ያስቆጫል።
ነገር ግን፣ ተማሪዎች በቅጡ ትምህርት ሳያገኙ፣ በወጉ እውቀት ሳይጨብጡ እድሜያቸው በከንቱ እየባከነባቸው እንደሆነ የሚታየን፣ በ12ኛ ክፍል ፈተና ብቻ ነው? ለ12 ዓመታት ዞር ብለን አይተንና ታዝበን አናውቅም? አሳስቦን አያውቅም? “በማትሪክ ውጤት” ብቻ እንጂ፣ በሌላ ዘዴ ሊታይ የማይችል ረቂቅ ምስጢር ነው እንዴ፣ የትምህርት መራቆትና የተማሪዎች የእድሜ ብክነት?
የሦስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ይጋመሱ ተማሪዎች፣ በአብዛኛው አንብበው መረዳት እንደማይችሉ፣ ከዓመት ዓመት ሲገለፅ አልሰማንም? ለዚያውም፣ ረዥም ንባብ አይደለም። ሁለት ወይም ሦስት አጫጭር ዓረፍተ ነገሮችን አንብበው መገንዘብ አይችሉም። “አብዛኞቹ” የአገራችን የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ማለት ነው።
ታዲያ፣ “አብዛኞቹ” ሲባል፣ እንዲሁ የግምት አነጋገር አይደለም። በተደጋጋሚ በመላ አገሪቱ ሰፋፊ ጥናቶች የተካሄዱበትና በቁጥር የተመዘገበ ጉዳይ ነው።
አዎ፣ የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው - በአራተኛ ክፍል የሚሸጋገሩ። ነገር ግን፣ ከመቶ ተማሪዎች መካከል 95 ያህሉ፣ አንብበው መረዳት አይችሉም።
ይህም ብቻ አይደለም። 30 በመቶ ያህሉ ደግሞ፣ ከናካቴው አንዲት ቃል በወጉ ማንበብ አይችሉም። ግን ወደ 4ኛ ክፍል ይሸጋገራሉ።
ስለ አገራችን የትምሀርት ሁኔታ፣ “ተቆርቋሪ ነኝ” የሚል ማንኛውም ምሁርና ባለሙያ፣ ባለስልጣንና ፖለቲከኛ፣… እነዚህ መረጃዎች አዲስ መርዶ ሊሆኑበት አይገባም። አዲስ ወሬ ቢሆኑበት ግን፣ ስንት አመታት ተኝቶ እንዳሳለፈ ቢናገር ይሻላል።
የመጀመሪያው ሰፊ ጥናት የተካሄደው ከ12 ዓመታት በፊት እንደሆነ አስታውሱ። ከዚያ ወዲህስ፣ በየጊዜው ተከታታይ ጥናቶች እየተዘጋጁ፣ ተመሳሳይ የሪፖርት ሰነዶች አልቀረቡም? በ2003፣ ከዚያም በ2007፣ ከዚያም በ2013 የወጡ የጥናት ሪፖርቶችን ማመሳከር አይቻልም? የተሻሻለ ውጤት እንደሌለ ነው ጥናቶቹና ሪፖርቶቹ የሚያረጋግጡልን።
ያኔ ሦስተኛ ክፍል ላይ የነበሩ ተማሪዎች ናቸው፣… አምና፣ ዘንድሮና በሚቀጥሉት ዓመታት 12ኛ ክፍል ደርሰው ለፈተና የሚቀመጡት።
ሦስተኛ ክፍል ላይ ካላሳሰበን፣ አሁን እንዴት ያሳስበናል? 12ኛ ክፍል ላይ ከደረሱ በኋላ ነው የትምህርት ችግር፣ እንደ አዲስ መርዶ የምንሰማው? አሁን ነው አዲስ ግኝት የሚሆንብን?
ለነገሩ የ12ኛ ክፍል ዝቅተኛ የፈተና ውጤትም ቢሆን፣ ካሁን በፊት በስውር ተደብቆ የቆየ ድፍን ምስጢር አይደለም። ዘንድሮ፣ የተፈታኞች አማካይ ውጤት፣ 30 በመቶ ገደማ እንደሆነ ሰምታችኋል።
ከአስር ዓመት በፊትም እንዲሁ፣ በትምህርት ዓይነቶች አንድ ሁለት ተብሎ እየተዘረዘረ፣ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች አማካይ ውጤት እንደ መርዶ በይፋ እንደተነገረን ብናስታውስ ጥሩ ነው። ያው፣ ያኔም የተፈታኞች አማካይ ውጤት 30 በመቶ ገደማ ነበር።
የተራቆተው የአገራችን ትምህርት፣ በድብቅ ተሰውሮ የነበረ ሳይሆን፣ በእርዛት እጅግ ተጋልጦ በይፋ ሲታይ የቆየ አሳዛኝ የዓመታት ታሪክ ነው። በእርግጥ፣ እንደ አዲስ ብንደነግጥ፣ ደጋግመን ብናዝን አይገርምም። ይሁን፣ እንደ አዲስ ያስደንግጠን። ደግሞም በጣም አሳዛኝ ነው።
ጥያቄው ምንድን ነው?
ድንጋጤና ሃዘን ብቻ፣ ወይም ጭፍን ውንጀላና ፍርጃ ብቻ፣… መፍትሔ እንዳልወለዱልን እና እንደማይወልዱልን እስከዛሬ አይተናል።
ከነጭራሹ መንስኤውን ለማወቅና መፍትሔ ለማበጀት ከመትጋት ይልቅ፣ የፖለቲካ ብሽሽቅ ማራገቢያና የተቀናቃኝ ፓርቲዎች መናቆሪያ ወረት፣… ሰሞነኛ ወሬ ሲሆንም ታዝበናል።
ለብሽሽቅና ለነቆራ ብቻ የምንፈልገው ከሆነ ደግሞ፣…
ሁሌም እንደ አዲስ፣ “ኧረ ጉድ! ኧረ ጉድ!” እያልን፣ መንግስትን ለማሳጣትና ለመሳደብ የምንሯሯጥ ሙሾ አውራጅ እንሆናለን። ወይም ደግሞ፣…
የመንግስት አጨብጫቢ ለመሆን የምንሽቀዳደም፣ ሁሌም በማስተባበያና በማመከኛ የአፀፋ ምላሽ የምንሰጥ፣ የከንቱ ውዳሴ ቀሽም አዘማሪዎች እንሆናለን።
የአገራችንን ችግሮች ለብሽሽቅ ብቻ የምናውላቸው፣ … ዋናውን የትምህርት ጉዳይና ችግሮቹን ለይምሰል ካልሆነ በቀር እንደቁምነገር አንቆጥራቸው። እንደ መበሻሸቂያ ሰበብ፣ እንደ መናቆሪያ መሳሪያ እየተጠቀምን እንጥላቸዋለን፤ ከሳምንት በኋላ እንረሳቸዋለን።
ለዚህ ነው ይሄውና ከ12 ዓመታት በኋላም፣… ዘንድሮም እንደ አዲስ መርዶ ከማውራት ውጭ ምንም መጨመር አልቻልንም። ይሄውና ዛሬም፣ ስለችግሩ መንስኤና ስለ መፍትሔው በቅጡ መናገር አቅቶናል።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
በእስከዛሬው ልማድ ከቀጠልን፣ ከ5 ከ10 ዓመት በኋላስ? ከ20 ዓመት በኋላስ? ያው እንደ አምናው ያው እንደዘንድሮው የትምህርት እርዛት ወደፊትም ሰሞነኛ ወሬ ይሆናል?
በእርግጥ በየጊዜው የተለያዩ ምክንያቶችና ሃሳቦች እየተደጋገሙ መነሳታቸው አልቀርም። ነገር ግን፣ ትምህርትን ያራቆቱ ዋና መንስኤዎችን የሚገልፁ አይደሉም። ዋናውን መፍትሄ የሚያሳዩም አልሆኑልንም።
“የመማሪያ ክፍሎች በተማሪዎች ብዛት የተጨናነቁ ናቸው” የሚል ሃሳብ ይነሳ ነበር። ደግነቱ፣ ባለፉት 20 ዓመታት ጭንቅንቁ እየተቃለለ መጥቷል። በአንድ ክፍል ውስጥ ከ65 ተማሪዎች በላይ ይማሩ ነበር። ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችና ክፍሎች እየተገነቡ ወደ 50 ለማቃለል ተችሏል።
ጥሩ ነው። ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ የትምህርት ችግር አልተወገደም። ጨርሶ የመቃለል ምልክት አልታየበትም።
“የአስተማሪዎች ቁጥርና የትምህርት ደረጃ አነስተኛ ነው” እየተባለም ይነገር ነበር።
በእርግጥም በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ የተመደቡ ባለ ዲፕሎማ አስተማሪዎች፣ ቁጥራቸው በጣም ጥቂት ነበሩ። ባለ ዲፕሎማ የኤለመንተሪ መምህር እንደ ብርቅ ነበር። በ20 ዓመታት ግን፣ በአብዛኛው ባለዲፕሎማ ወይም ከዚያም በላይ አንዳንዶቹ ባለ ዲግሪ ሆነዋል - አስተማሪዎች። ቁጥራቸውም በእጅጉ ጨምሯል። መልካም።
ታዲያ፣ በእነዚህ አመታት የትምህርት ችግር እየተቃለለ መጥቷል? የትምህርት ጥራትስ የመሻሻል ምልክት አሳይቷል? በጭራሽ።
“በቂ የመማሪያ ቁሳቁስ የለም፤ የመማሪያ መፃህፍት ለተማሪዎች አልተዳረሰም” የሚል ሃሳብም በተደጋጋሚ ይቀርብ ነበር። እውነት ነው። አንድ መፅሀፍ ከ2 ተማሪ፣ ለአምስት ተማሪ “አብቃቅታችሁ ተጠቀሙ” ብሎ መስጠት የተለመደ ነበር።
ደግነቱ ግን፣ የመማሪያ ቁሳቁስ በተለይ የመጻሕፍት እጥረት ትኩረት አግኝቷል። በዚያ ላይ፣ የመጻህፍቱ ሕትመት በቀለማት የደመቀ ሆኗል። ለእያንዳንዱ ተማሪ በቂ መጻሕፍት ወደ ማዳረስም ተቃርቦ ነበር (የዘንድሮ የአዳዲስ መፃህፍት ህትመት ለተማሪዎች ባይደርስም)።
ታዲያ፣ የመጻሕፍት ብዛትና… በቀለማት ያማረ ህትመት፣ የትምህርት ችግሮችን ለማቃለል ረድቷል? የትምህርት ችግሮች አልተቃለሉም።
ሌላ ምን የተለወጠ ነገር አለ? አዎ፣ በችኮላና በግርግር የሚቀየር የመማሪያ ቋንቋ፣ ዘንድሮ እንዳየነው በጊዜ የማይደርስ የመጻሕፍት ሕትመት፣ እንዲሁም በየጊዜው የሚፈጠሩ በርካታ እክሎች በትምህርት ላይ ብዙ ዓይነት ችግሮችን ያስከትላሉ። ይሄ አይካድም። ግን ጊዜያዊ እክሎች ናቸው።
የአገሪቱ ትምህርት የተራቆተው ግን በአንዳንድ ቦታዎች ሳይሆን፣ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢ ነው። ለዚያውም ከዓመት ዓመት የማይሻሻል።
እና ታዲያ ምንድነው መንስኤው ? ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
ባለፉት 10 ዓመታት በርካታ ጥናቶችንና ሰነዶችን በማመሳከር በአዲስ አድማስ የቀረቡ ዘገባዎች ላይ በተደጋጋሚ የተጠቀሰ አንድ ሌላ ጉዳይ አለ።
የአገሪቱ የትምህርት ይዘትና የማስተማሪያ ዘዴ ከዓመት ዓመት ወደ አንድ የፍልስፍና ቅኝት እየገባ መምጣቱ ተገልጿል - በዘገባዎቹ። ከላይ እስከ ታች የአገሪቱን ትምህርት የሚያራቁት፣ የተማሪዎች እድሜን ያለ እውቀት በከንቱ የሚያባክን የችግር መዓት የሚፈጠረውም በሌላ ምክንያት አይደለም። መንስኤው፣ እጅግ የተሳሳተ ጠማማ የፍልስፍና ቅኝት እንደሆነ በዘገባዎቹ ተጠቅሷል።
በእርግጥ፣ “የፍልስፍና ቅኝት” መኖሩ አይደለም ችግሩ። ፍልስፍናው የተሳሳተ ቅኝቱም ጠማማ መሆኑ ነው ችግሩ። ምን የሚሉት የፍልስፍና ቅኝት?
“መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ” ይባል የለ!
የትምህርት ይዘትን የሚያራቁትና የትምህርት ዘዴን የዘፈቀደ ጨዋታ እንዲሆን የሚያደርግ ነው - ጠማማው ፍልስፍና።
አዎ፣ እውቀትን በግላጭ ያጥላላል።
አዎ ስርዓት የያዘ የትምህርት ዘዴን ያንቋሽሻል። እንደ አምባገነንነት ይቆጥረዋል - authoritarian በሚል ውግዘት።
እንዲህ እውቀትንና የትምህርት ስርዓትን የሚያናንቅ ጠማማ ፍልስፍና አማካኝነት የመጣው የትምህርት ቅኝት ምን ተብሎ ተሰየመ?
“ተማሪ ተኮር” የሚል ስያሜ ተስጥቶታል። student-centered ወይም student-led የሚሉት መሆኑ ነው። የትምህርት ውሎና ሂደት፣ በአስተማሪ ወይም በመማሪያ መፅሐፍ ሳይሆን፣ በተማሪዎች አምሮት መመራት አለበት ይላሉ፣ የዚህ ፍልስፍና አቀንቃኞች።
የአገሪቱ የትምህርት ይዘትና ዘዴ ወደዚህ ቅኝት እየገባ መምጣቱ ማንም አይክደውም። ክርክር ወይም ውዝግብ የለውም። ጎጂ ነው ወይስ ጠቃሚ? አልሚ ወይስ አጥፊ በሚለው ጉዳይ ላይ የሚከራከር ሰው ይኖራል። በአብዛኛው ግን እየተጨበጨበለት፣ በመላ አገሪቱ በእጅጉ ተስፋፍቷል።
አጥፊና ጎጂ የሆነ ጠማማ ቅኝት፣ እንደ በጎ ከተጨበጨበለት ምን መላ አለው?
እንዲያውም፣ ይህን ቅኝት ይበልጥ በፍጥነት ማስፋትና የዓለም ቀዳሚ አርአያ መሆን አለብን ብለው የሚረባረቡ ሰዎች ሞልተዋል። ከዚህ ጎን ለጎን፣ “ፍጥነቱ በቂ ነው”፤ “አይ ፍጥነት ይጨመርበት” ብለው የሚከራከሩ ይኖራሉ።
ያለ ማቋረጥ ባለፉት 20 ዓመታት እየተስፋፋና ቅኝቱ ስር እየሰደደ መምጣቱ ግን አያከራክርም። ባለሙያዎቹ ከሞላ ጎደል ይሰማሙበታል።
ብዙ ገንዘብ የፈሰሰበት፣ ብዙ ጊዜ የፈጀና እጅግ የተደከመበት ከፍተኛ ለውጥ ነው ማለት ይቻላል። ደግሞም ተሳክቷል። የብልሽት ለውጥ መሆኑና መሳካቱም ነው አሳዛኙ ነገር።
እንደምታዩት የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች አጭር ዓረፍተ ነገር አንብበው መረዳት አይችሉም። የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይም ያያችሁት ነው።



Read 1945 times