Saturday, 11 February 2023 21:20

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ጥንትም አንድ ናት፤ ዛሬም አንድ ናት።
                           ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እድሪስ

       “ቤተክርስትያን በአሏህ የተመሰለች ናት” አሏህ አንድ ነው፣ አሏህ አይከፈልም። ኦርቶዶክስ ኃይማኖትም ጥንትም አንድ ናት፤ ዛሬም አንድ ናት። አትከፈልም!
ከጥንት ጀምሮ በታሪክ የምንሰማው፣ እኛም በእድሜያችን የተመለከትነው ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሰላማዊ እንግዶችን በክብር ስትቀበል፣ ከሌላው ኃይማኖት ጋር ተከባብራ አብራ ስትኖር፣ ህመም ወረርሽኝ ሲመጣ፣ በሃገር ላይ ጦርነትና ሃዘን ሲመጣ ዱኣ አድርጋ ስትታደግ፣ አንድ ሆና ሃገርን አንድ ስታደርግ ነው።
የቤተክርስትያኗ አባቶችም፣ አንድም ቀን እንኳን ሊለያዩ ቀርቶ፣ አንድ አካል አንድ አምሳል ሆነው፣ አባት ልጁን ልጅም አባቱን አክብረው ከመኖር ያለፈ፣ በመሃላቸው ልዩነት ተፈጥሮባቸው አይተን አናውቅም። ዛሬ ልጆች ከአባቶቻቸው ለመለየት የሚያበቃ ምን ተገኘና ነው ፣አባቶቻቸውን አስቀይመው አሳዝነውና አስለቅሰው ለመለየት የፈለጉት?
አባቱን የናቀ ሁሉ አላህን የናቀ ነው። አባቱን ያከበረ ሁሉ አላህን ያከበረ ነው። አባቶችን ንቆ እነርሱ  ያቆሟትን ጥንታዊና አንድ የነበረችዋን የኦርቶዶክስን ሃይማኖት በመክፈል ከአባቶች መለየት ማለት ከአላህ መለየት ማለት ነው።
ኧረ ተው! ይሄኮ አላህን ለማስቆጣት መቻኮል ነው!  እኔ እስከገባኝ ድረስ፣ ቤተክርስትያን በአሏህ የተመሰለች ናት፣ አሏህ አንድ ነው፣ አሏህ አይከፈልም። አሏህ፣ አንድ ሁኑ ተደጋገፉ በአንድነት ድመቁ ይላል። ኦርቶዶክስ ኃይማኖትም፣ ጥንትም አንድ ናት፤ ዛሬም አንድ ናት አትከፈልም።>>
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እድሪስ

______________________________________

                 የዶ/ር ወዳጄነህ መልዕክት (ስለ እውነት ምን እለዋለሁ?! በበዛ ክብሩ ያቆየው።)


           እኔማ የኢትዬጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንን የማውቃት ይመስለኝ ነበር። ባለፉት ሶስት ቀናት እንደተረዳሁት ግን ስላንቺ የነገሩኝ ሰዎችና መጻህፍት ሁሉ ካለሽ ክብር፣ ሞገስና ዝና ከፊሉን እንኳን እንዳልነገሩኝ ነው።
ተዋህዶ ሆይ! ንፁህ እምባ፣ ጥልቅ ትህትና፣ ብርቱ ትዕግስት፣ ታላቅ ጥበብ፣ ብዙ እውቀት፣ ሰፊ ማስተዋል፣ የሚያስፈራ ግርማ አየሁብሽና ተገረምኩኝ፡፡
 ልቤ ተደነቀ፡፡
 እጄን በአፌ ላይ ጫንኩኝ!
 የጸሎትና የምልጃሽ እጣን የልዑል እግዚአብሔርን ቤተመቅደስ ሲያጥነው፣ ዙፋኑን ሲያውደው ማየት እንኳን እኔን ደካማውን ሰው ይቅርና ቅዱሳን መላዕክቱን ያስደንቃል።
 በነብዩ በዳንኤል መፅሃፍ እንደሚነበብ እጅ ያልነካው ድንጋይ ከሰማይ ወርዶ ሳይፈርስ ፣ ሳይከፈል፣ ሳይቆረስ ታላቅ ተራራ ሆኖ ጸንቶ እንደኖረ አንቺም በኢትዮጵያ ምድር ላይ ታላቅ ተራራ ሆነሽ ለአፍሪካ ትምክህት፣ ለመላው አለምም ክብር ሆነሽ ትኖሪያለሽ።
ከእግዚአብሔር የተማሩት፣ ትሁታንና ብሩካን የሆኑት፣ ማቅ የለበሱልሽ የተወደዱ ልጆችሽ እንዴት የታደሉ ናቸው!
ከሩቅ እያየሽ የሚወድሽና የሚያከብርሽ
ዶ/ር ወዳጄነህ መሐረነ

_____________________________________________________

                  ሃይማኖቱን እንኳ ተዉለት!


      በዓለም ከድካም በቀር ምንም ላልተረፈው፤…
የዕለት ተዕለት ሕይወቱን ለማሸነፍ ብርቱ ትግል ለሚያደርገው፤…
መሠረታዊ የሚባሉ ነገሮችን ለሟሟላት ብቻ ሲለፋ ዘመኑን ለሚፈጀው፤
ቢከፋው፣ ቢያዝን፣ ቢመረው በምድር ምንም መጽናኛ ለሌለው፣…
ለዚህ ምስኪን ሕዝብ... ልቡ ሲበርደው፤ አንጀቱ አልችል ሲለው የሚጽናናበትን ሃይማኖት እንኳ ተዉለት እንጂ።
በብዙ መከራ ውስጥ ለሚያልፍ፤ ከፀሐይ በታች ሁሉም ዓይነት የመከራ ዶፍ ለዘነበበት፤  አለኝ ብሎ የሚማጸንበትን፣ ይኽን ዓለም የሚንቅበትን፤ የተጓደለበትን ምድራዊ ፍትሕ በትዕግሥት እንዲያሳልፍ ምክንያት የሆነውን እምነቱን እንዴት አይተዉለትም?
እንደ ሕዝብ ከቀዬው ተፈናቅሏል። በቋንቋው ተሰዷል። በሰውነቱ ተጎሳቁሏል።
በቅድመ አያቶቹ ታሪክ ምንም የማያውቀው ሰው፤ ላልነበረበት ጊዜ በመካካሻነት በጠላትነት እየተፈራረጀ እንዲኖር ተፈርዶበታል።
ይኽ በሕዝቦች መካከል የተዘራ እንክርዳድ ነው። በፓለቲካው ዓለም በጸብ ለሚነግዱ አካላት ይኽ እንክርዳድ እንደ ትልቅ የኃይል መሣርያ በማገልገል ዘልቋል።
ሃይማኖት ግን መነካት የሌለበት እሳት ነው።
ሃይማኖት የምትጫወትበት መሳሪያ አይደለም። ምድራዊ እሳት ለሚያምኑት የመለኮት እሳት ነው። 
ከቅጽሩ ወዳልተቀደሰ የፖለቲካ ሜዳ ልታወጣው ብትሞክር ቅድሚያ የሚፈጅህ አንተኑ ነው። ሃይማኖት፣ ሀገር እንደ ሀገር እንድትቀጥል ሕዝብን ከሕዝብ አንድ አድርጎ አያይዞ በኅብረት አቆይቷል።
ፈርሀ እግዜርም ከትውልዱ ላይ እንዳይጠፋ ግብረገብን በማሥረጽ “moral compass” ሆኖ ያገለገለውም ሃይማኖት ነው።
ኅሊናውን በጥላቻ የታወረ ሰው ሊገድልህ ቢመጣ፣ ቢያንስ “በእግዜር፥ በጌታ፣ በማርያም፥ በአሏህ፥ በዋቃ... ብቻ በፈጠረህ!” ትለዋለህ።
እንደ ሕዝብ ተከባብረን የኖርነው የሠለጠነ ሕግና ሥርዓት ስላለን አልነበረም። ይልቁንም በፈጠረን አምላክ በኩል አንድ እንደሆንን ስለሚሰማን ነበር። እንደ ሕዝብ የሥልጣኔ ታሪክ ቢኖረንም በቅርብ ጊዜ ያስተናገድናቸው ቀውሶችና የሰማናቸው ዜናዎች፣ ባለአእምሮዎች ለመሆን ብዙ እንደሚቀረን፤ ሥልጡን ነን ብለን የምንመጻደቀውን ያህል ሥልጡን እንዳልሆንን ይናገራሉ። የትምህርት፣ የጤና፣ የፍትሕ... ሥርዓቶቻችን በስብራት የተሞሉ ናቸው።
ምንን ተማምነን ምንን እንደምናፈርስ አናውቅም።
በርሀብ ብዛት ከአንጀቱ የተጣበቀ ሆዱ እስኪቀደድ ድረስ እያከከ የፒያሳን ወርቅ ቤቶች ያለስርቆት ውልብታ ደክሞት የሚደገፍ የ’ኔ ቢጤና ምንዱባን ያላጣነው በእንተ ስማ ለማርያም ብሎ የሚላስ የሚቀመስ በማምሻ እንደማያጣ ተስፋ ስለሚያደርግ ነው። እንጂማ የሚበላው ያጣ ሕዝብ መሪውንም እስከ መብላት ይደርሳል።
የሃይማኖትን አንድነት የነጠቅከውን ሕዝብ  በምን አንድ ታደርገዋለህ? ነገ ከነገ ወዲያ የእንትን ክልል እግዜር ከእንትን ክልል እግዜር ጋር ኅብረት እንደሌለው በግልጽ የሚሰበክበት ጊዜ ይመጣል። የሃይማኖት አንድነትን ማዳከም (ሲዳከምም በዝምታ ማየት) እያደር  ቅጥ ላጣ ዓለማዊነት፣ ግብረሰዶማዊነት...  አውሮፓ እየተሰቃየ ላለበት የስመ ሥልጣኔ በሽታና ውጥንቅጥ ሁሉ  በር እንደመክፈት ነው። በቀሪው ዓለም ሲቀደስባቸው የነበሩ ትላልቅ ካቴድራሎች መጠጥ ቤትና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ሆነዋል።
በክርስትና ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።
አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችንም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ነን። (ገላ. 3፥27-28) ክርስቶስ በሞቱ ያላስታረቀው የለም። አንድ በየቀኑ በአባታችን ሆይ ጸሎቱ “ይቅር በለን... እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል” እያለ የሚጸልይ ሰው እንዴት እና ከመቼው፣ የሀጢአት ማወራረድ ውስጥ ይገባል?
በክርስቶስ ስም የተመሠረተች ቤተ ክርስቲያንን ለመከራ አዲስ አይደለችም። የመከራ ዘመናት አሏት። ነገር ግን ክርስትና ሥር የሚሰደው ደግሞ በመከራ ውስጥ ነው። ሊቁ ጠርጡለስ “The blood of the Martyrs is  the  seed of  the church” ይላል።  ሰማዕታት የቤተ ክርስቲያን ምርጥ ዘር ናቸው። በዚህ ሁሉ መሃል ግን ቤተ ክርስቲያንን የነኳት ኔሮን እና ማርከስ ኦሬሊየስ የት ናቸው?
ቤተ ክርስቲያን ግን ይኸው አለች። ትኖራለችም። ይኽች ቤተ ክርስቲያን በየሆስፒታሉ ለወደቁ ሕሙማን፣ በየወኅኒው ለታሰሩ፣ አርሰው ዝናምን ለሚጠብቁ፣ በስደት በሰው ሀገር ላሉ፣  ለአእዋፋትና ለአራዊት፣ ይልቁንም ደግሞ ስለአገር ሰላም ሌሊት ተቀን የምትጸልይና የምትማልድ  እመቤት ናት። 
በደመራ ዕለት እና በጥምቀት ዕለት  ብቻ ሳይሆን በመከራዋ ቀን የሚመጡላት እልፍ ልጆች አሏት።  ኖረው ብቻ ሳይሆን ሞተው የሚያከብሯት አዕላፍ ልጆች አሏት። የድረሱልኝ ጥሪዋን ሰምተው ልጅ የእናቱን ድምፅ ሰምቶ እንደሚገሰግስ  ድምጿን ሰምተው በቅጥር ግቢዋ ይሰበሰባሉ። በክንፎቿ ይጋረዳሉ፤ ይጋርዱሟታል።
ቤተ ክርስቲያን ሆይ፣ እንደ አንድ ዜጋ በአንቺ ወቅታዊ ጉዳይ ከመጨነቅ የሚይዘኝ ነገር የለም። እናም ስለሰላምሽ እጸልያለሁ!
አገሬ ሆይ፣ እንደ አንድ ከምድርሽ እንደ በቀለ ዜጋ፣ በአንቺ ወቅታዊ ጉዳይ ከመተከዝ የሚይዘኝ ነገር የለም። እናም ስለሰላምሽ አጥብቄ አነባለሁ!
          ዮናስ ዘውዴ ከበደ
_____________________________________________________

                         “ፓትርያርክ ለመሆን አልመጥንም” የተባለበት ታሪክ አለ


        ፕትርክና አይገባኝም ስላሉ ብቻ መንበራቸውን ጥለው እንዳይሄዱ በወታደር ይጠበቁ የነበረት ከወላይታ የተገኙት ወላይተኛ ተናጋሪው ቅዱስ ፓትርያሪክ
የቀደመው ስማቸው አባ መልአኩ ይባላሉ። ምንም እንኳን ውልደታቸው በጎንደር ጋዢን በምትባል ስፍራ ቢሆንም ረጅም ዕድሜያቸውን ያሳለፉት እና አብረው የኖሩት ማህበራዊ ስነልቦናቸው ያገኙት ወላይታ  በሚባል ደቡባዊ ምድር ላይ ነው።
ከሀገሬው በላይ ወላይተኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ። ከውልደት ስፍራቸው በቀር አኗኗር እና አዋዋላቸው ሙሉ በሙሉ ከአንድ የወላይታ ገበሬ የተለየ አልነበረም።
የመጽሐፍት ትርጓሜ በእዚሁ በወላይታ ምድር ባሉ ጉባኤ ቤቶች አጠኑ። ስርዓተ ገዳም ከተማሩ በኃላ በእዚያው ወላይታ በሚገኘው ደብረ መንክራት አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም መነኮሱ። የብህትና ህይወታቸውን በወላይታ ምድር ጀመሩ።
ከ1926-1968 ለ42 ዓመታት ወላይታ ላይ በወላይተኛ  ቋንቋ  ሐዋርያዊ አገልግሎት ፈጽመው ከ300,000 በላይ ኢ- አማንያንን አስጠምቀዋል እና ከ65 በላይ አብያተክርስቲያናትን አሳንጸዋል።
በእዛ ዘመን አስበኅዋል ወዳጄ?
የደርግ መምጣትን ተከትሎ የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን 2ኛው ቅዱስ ፓትርያሪክ የነበሩት ብጽዕአቡነ ቴዎፍሎስ ተገደሉ።
በመሆኑም ቅድስት ቤተክርስቲያን 3ኛው ቅዱስ ፓትርያሪክ ለመምረጥ 909 አከባቢያቸውን የሚወክሉ አባቶች በአዋጅ ሰበሰበች።
ከ565 ወረዳዎች ለማዕረገ ፕትርክና መንፈስ ቅዱስ የሚመርጠውን አባት ይገኝ ዘንድ ሁለት ሁለት ተወካይ ይላክ ዘንድ ታዘዘ።
ገና ማዕረግ ጵጵስናን ያልተቀበሉት በቁምስና ያሉት መነኩሴው የወላይታው አባት የሆኑት አባ መላእኩ ከወላይታ “ተወካይ ሆኜ አልሄድም” ብለው እንቢ ማለትን ከጅምሩ ቢያሳውቁም በገዳሙ አባቶች ትዕዛዝ እና ቃለ ውግዘት  የወላይታ አውራጃን ወክለው ተላኩ።
ገና ማዕረግ ጵጵስና ሳይቀበሉ በቁምስና ማዕረግ መሆናቸው ደግሞ ለዬት ያደርገዋል። በስተመጨረሻም የመጨረሻው 5 ዕጩ ውስጥ ስማቸው ተካተተ። ከአንድ ቆሞስ እና ከሶስት ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ለ3ተኛው የፕትርክና የአገልግሎት ሥልጣን ለውድድር ተቀመጡ። ከየወረዳው ለመጡት ለመራጩ ተወካዮችም ግን እንቢታቸውን እና ከውድድሩ እንዲያስወጧቸው እንዲህ ብለው ተናገሩ
 “እኔ ባህታዊ ነኝ ..ጥዬው የመጣሁት ህዝብ አለኝ ፣ ኑሮዬ በጫካ ነው እና የከተማውን ህይወት ለምጄ መምራት አይቻለኝም ።የበቁ አባቶች አሉ እና እኔን በእዚህ ምርጫ ውስጥ አወዳድራችሁ መንፈስ ቅዱስን አታሳዝኑ፣ እኔን ከምርጫው ሰርዙኝ“ ብለው ለጉባኤው በተደጋጋሚ እየጮኹ ቢነግሩም ሰሚ አጡ።
በስተመጨረሻም ከሊቃነ ጳጳሳት ጋር ተወዳድረው በአብላጫ ድምጽ መነኩሴው መናኝ የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን 3ኛው ቅዱስ ፓትርያሪክ ሆነው ተመረጡ። በ1968 ሐምሌ ወር ላይ መዓረገ ጽጽስና ተቀብለው ከወር በኃላ በጉባኤው ምርጫ መሰረት
“አባ ተክለሃይማኖት ሣልሳዊ የኢትዮጽያ ፓትርያሪክ” ተብለው ተሾሙ።
ከተሾሙ በኃላም በብህትህና ወደ ወላይታ ተመልሰው በገዳማቸው በዓት ለመዝጋት መንበራቸው ጥለው ሊሸሹ በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም የደርግ ወታደሮች እየያዟቸው ይመልሷቸው ነበር።
በስተመጨረሻም መንበራቸውን ጥለው እንዳይሄዱ በመኖርያ ቤታቸው ጥበቃ ተመደበ። መውጫ መግቢያቸው ከደርግ ወታደሮች እውቅና ውጪ እንዳይሆን ተደረገ።
ወዳጄ... መንፈስቅዱስ ሲመርጥ እንዲህ ነው።
ዳዊትን ከእረኝነት ንጉስ ያደረገ አምላክ፣ሳሙኤልን ከመካኒቷ ማህጸን አውጥቶ ነብይ ብሎ የሾመ ጌታ፣ሙሴን ከውሐ ላይ ታድጎ ነጻ አውጭ አድርጎ የቀባ እግዚአብሔር ....ምርጫው ኮታ ሳይሆን ጸጋ ነው።
ለኚህ አባት ለጸጋ ፕርትርክና የሚገቡ አባት መሆናቸውን ባገለገሉበት 12 የፕትርክና አገልግሎት ዓመታት ገለጡ።
ጫማን ለመንግስት ፕሮግራሞች ብቻ ይጫሙ እንደነበር ይነገራቸዋል። ከፆም ጸሎት በቀር ቅርባቸው የሚሆን ሰው አልነበረም።
ደምወዛቸውን ለነድያን እና ለወላይታ ደብረ መንክራት አቡነ ተክለሃይማኖት መነኮሳት ቀለብ በቋሚነት ይልኩ ነበር።
ለቁመተ ሥጋ ብቻ ተመጋቢ የሆኑት እኝህ አባት በስተመጨረሻ በሥጋ ድካም ሲያርፉ የከበረች ሥጋቸው 25 ኪግ ብቻ ትመዝን እንደነበር ይታወቃል።
እኚህን አባት ዛሬም ድረስ የወላይታ ኦርቶዶክሳውያን ያለስስት በዓለ ረፍታቸውን አስበው በገዳማቸው ይዘክራሉ።
የቅዱስነታቸው የከበረች በረከታቸው ትደርብን!!!
እግዚአብሔር ይመስገን !!!
_________________________________________________


                        የቤተክርስቲያን ሕመም ሕመማችን!


         “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕመም ሕመማችን ክብሯ ክብራችን ነው::” የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን
የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና ለሲኖዶስ ድጋፉን በመግለጽ የአጋርነት ደብዳቤ  ላከች::
“በተፈጠረው ችግር እና ሁኔታ ጥልቅ ሐዘን የተሰማን ሲሆን፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያለንን አጋርነት በመግለጽ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመጠበቅ የሚደረግ ጥረትን በሙሉ እንደግፋለን” ብለዋል የቤተክርስቲያኗ አባት::
በመልእክታቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንጦስ በላከው የመጀመሪያ መልእክት “አንድም ብልት ቢሰቃይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።” 1ኛ ቆሮንጦስ 12፥26 ያለውን ጠቅሰው ሕመሟ ሕመማችን ክብሯ ክብራችን ነው ሲሉ በአጽንዖት ገልጸዋል።
በመጨረሻም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ እና የቤተ ክርስቲያን አንድነት እናት በምልጃዋ እጅግ የተከበረች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድነቷና ደህንነቷ እንዲጠበቅ ታድርግልን ብለዋል።


Read 1976 times