Saturday, 11 February 2023 21:25

ግን ደግሞ ይህም ያልፋል!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 ፈጣሪ ሆይ፣ በርህን እያንኳኳን ነው፣ አለሁላችሁ በለን!
አምላክ ብጠራህ ዝም አልህ
ምነው እያለህ እንደሌለህ፣…
እንዲህ የሚል ዜጋ ሲበዛ፣ የሆነ ነገር በእጅጉ እንደሳተ አትጠራጠሩ። ከዚህ የተሻለ መግለጫ ሊኖር አይችለም። አሁን ብዙ ነገሮች በአስደንጋጭ፣ በአስፈሪና በአሳሳቢ ሁኔታ እንደሳቱት ማለት ነው።
የሚገርመው ነገር፣ ምንም እንኳን በርካታ አስከፊ ነገሮች እየተፈፀመቡት እየሆኑባት የከረመች ሀገር ብትሆንም፣…
ምንም እንኳን፣ ምክንያትና መልስ ያልተገኘላቸው፣… ምናልባትም ምክንያትና መልስ ሊገኝላቸው የማይችሉ ድርጊቶች ሲደረጉባት የነበረችና እየተደረጉባት ያለች ሀገር ብትሆንም፣…
ህዝባችን፣ ጥሎ የማይጥለውን አምላኩን እየተማመነ... “ግዴለም፣ መከራ ለእኛ አዲስ አይደለም። ነገም ሌላ ቀን ነው!” እያለ ቀናቱን፣ ወራቱንና ዓመታቱን እያለፈ እዚህ ደርሷል።
“ግዴለም፣ ሊነጋ ሲል ይጨልማል!” እያለ ኑሮው ድቅድቅ ጨለማ ሆኖበትም፣ እየተንገዳገደም ጊዜዎችን እየገፋ እዚህ ደርሷል።
መጠነኛም ብትሆን የተስፋ ጭላንጭል ስትታይ፣ ‘ሊነጋ ነው’ በሚል ተስፋ ልቡ በትንሹም ወከክ እያለች፤ ወዲያው ደግሞ ሁሉም ነገር ድርግም ሲልበት ወከክ ያለችው ልቡ መልሳ እየጠየመችበት እዚህ ደርሷል።
ምናልባትም፣ “የመከራው መንገድ ነገና ከነገ ወዲያ አብቅቶልኝ ትንሽ እፎይ እላለሁ፣” ከሚያስብሉት ነገሮች ይልቅ፣ ጭንቀቱንና ስጋቱን ብሎም ሰቆቃውን የሚያባብሱ ነገሮች በየጊዜው መፈጠራቸው እየቀጠለ በመሆኑ፣ በዛው ልክ ምክንያትና መልስ የሌላቸው ነገሮች መበራከታቸው አይቀርም። ግን ለምን!
መቼ፣ መቼ፣ መቼስ ነው “ካለፈው መማር” የሚባለው ነገር ዘልቆ ሊገባን የሚችለው! ለምንድነው ቀድመውን ያለፉት የተደናቀፉበት ቋጥኝና የተንሸራተቱበት ተዳፋት መልሰው እኛን? እንዴት ካለፈው ለመማር እድሉ ያለንን መልሰው የሚያደናቅፉንና የሚያንሸራርትቱን!
ቋጥኙን ማንሳትና ተዳፋቱን ደግሞ ሜዳ ማድረግ ቢያቅተን እንኳ፣ ዘወር ብለን ማለፍ ያቃተን ስለማንፈልግ ነው? ወይስ ብልሀቱ አልገለጥልን ብሎን!
ይኸው ከመደናቀፍና ከመንሸራተት አልፈን፣ እጅግ ከባድ፣ እጅግ አደገኛ፣ የነገውን ለመተንበይ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ገብተናል።
ጥሎ የማይጥለን ፈጣሪ አስቀይመነው ከሆነም ምህረቱን ይላክልን።
መፍትሄውን ያምጣልን።
መከራዋ በበዛባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሀይማኖቶች ውስጥ ያሉ የሀገር አባቶች እያለቀሱ ነው። የሀገር እናቶች እያለቀሱ ነው። ልጆችም እያለቀሱ ነው። ምክንያቱም ስድሳ ሚሊዮን የሚሆኑ አማኞች ያሏት፣ ሀገር ከማቆም አልፋ ራሷ ሀገር የሆነች ቤተክርስትያን፣ በዚህ ዘመን የማይጠበቅ በእንዲህ አይነት መከራ ውስጥ ስትገባ የሚነካው ሁሉም ነውና።
ከሀገር አልፎ የሌሎች ሀገራት ቤተ እምነቶች፣ አባቶችና አማኞች በማህበራዊ ሚዲያ መልካም ምኞታቸውን እየገለጹና፣ ለቤተክርስቲያኗ፣ ለአማኞቿና ለመላው ህዝባችን ጸሎት ላይ መሆናቸውን እየገለጹ ያሉት እኮ ለዚህ ነው።
...ግን ደግሞ ይህም ያልፋል!
እየሆኑ ስላሉትና በየስፍራው ስለሚታዩ ነገሮች ደጋግመን እንጠይቃለን። ለምን? በምንስ ምክንያት? እንላለን።
ህዝብስ ምን አድርጎ፣ ሀገርስ ምን አድርጋ! “ይሄ አይገባትም፤ አገር ለሠራቸው፣ አገር ላቆመችው፣” እንዲል ዘማሪው።
እንዴት እዚህ ደረጃ ላይ ሊደረስ ቻለ! በዚህስ ትርፍና ኪሳራ የምናሰላው እነማን ነን? ከፖለቲካው ትንቅንቅና ከሌሎች ሌሎች መቆራቆሻ አጅንዳዎች ባለፈ፣ ትርፍና ኪሳራ ሊሰላ የማይቻልበት አንድ ጉዳይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ላይ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ሃይማኖት ላይ የሚመጣ ይህን መሰል መከራ ነው። ምክንያቱም ብልጭ ብሎ ድርግም የሚል ሳይሆን፣ ብዙ ነገሮችን ተሸክሞና ትቶ የሚልፍ ነውና።
በበቂ ተመግቦ መጥገብ አይደለም፣ ረሀቡን ማስታገስ እንኳን እየከበደው ለመጣ ህዝብ፣ ከምኑም ከምናምኑም ነገር አልሞላ ብሎት ሁሉም ለጎደለበት ህዝብ፣ ወደ ተስፋ መቁረጡ በፍጥነት እየተንሸራተተ ላለ ህዝብ...ለምን ይሄ ሁሉ!
እዚህ ላይ ግድ ሊጤቁ የሚገባቸው ጥያቄዎች አሉ። በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚታዩ ነገሮች ሁሉ የሚታመኑ ናቸው ባይባሉም፣ በርካታ እውነተኛ ነገሮች በቀጥታ ጭምር ሲተላለፉ እያየን ነው። እያየንም ልባችን እየተሰበረ ነው። ልባችን እየተሰበረም ሙሉ ለሙሉ ተስፋ ለመቁረጥ ወደ አፋፉ እየተገፋን ነው።
እውን ጥቁር ጨርቅ ጣል ማድረግ ፣ይህን ሁሉ ሊያስከትል ይችላል? ያሳዝናል።
ደጋግመን እንደምንለው እዚች ሀገር፣ “አይሆኑም” ሊባሉ የሚችሉ ነገሮች ለማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ቢመጣም፣ አሁን በምናየው ደረጃ ይደርሳል ብሎ ያሰበ አለ ለማለት ግን ያስቸግራል።
ግራ እያጋባን ያለውም ነገር፣ እነዚህ እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለም እያያቸው ያሉ ድርጊቶች፣ የግለሰቦች፣ ወይም ራሳቸው ወሳኝና አስፈጻሚ የሆኑ ቡድኖች የሚያደርጉት ነው? ወይስ በየደረጃው ያሉ የበላይ አካላት መመሪያዎች ናቸው? ጥያቄያችንን የሚያጠነክረውም፣ እነኚህን ድርጊቶች “ተዉ እንደዚህ አይደረግም!” የሚሉና ነገሮችን መልክ ለማስያዝ የሚሞከሩ ኦፊሴላዊ የሚባሉ ድምጾች አለመስማታችን ነው።
ህዝብማ ምን ጉልበት አለው?
ግን እኮ ደግሞ፣ ፈጣሪ አለ! ግን እኮ ደግሞ፣ እግዚአብሔር አለ! ግን እኮ ደግሞ፣ እስራኤሎችን “የእስራኤል ልጆች ሆይ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን?” ያላቸው ይህችን ሀገር ጥሎ የማይጥላትና ይህን ህዝብ ጥሎ የማይጥለው እግዚአብሔር አለ።
...ግን ደግሞ ይህም ያልፋል!
ፖለቲካ ሌላ ጉዳይ ነው። የወንበር ፍትጊያ ሌላ ጉዳይ ነው። ሃይማኖት ሌላ ጉዳይ ነው።
እውነት እንነገጋርና በየትኛውም የዓለም ክፍል የተለያዩ ሀይማኖቶችና የእምነቶች ተከታዮች እርስ በርስ ተቻችለው ብቻ ሳይሆን አንድ ግድግዳ ብቻ እየለያቸው ተጋጋዘውና ተካለው የሚኖሩባቸው ሌሎች ሀገራት ማግኘት እጅግ ከባድ ነው።
ይህ ጉርብትና፡ ይህ የራስን እምነት ይዞ የሌላውን አክብሮ በጉርብትና መኖር የትኛውም የፖለቲካ ስርአት ያመጣው ሳይሆን ለዘመናት ጨዋ ሆኖ የዘለቀው የኢትዮጵያ ህዝቡ ራሱ ያዳበረው ነው። ለዚህም ነው ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና አማኞቿን በገጠማቸው ችግር “አብረናችሁ ጥቁር ለብሰናል!” “አብረናችሁ እየጸለይን ነው!” የሚሉ የሙስሊምና የፕሮቴስታንት እምነቶች አባላት ማህበራዊ ሚዲያውን ያጨናነቁት።
በሎሬት ጸጋዬ ብዕር አቡነ ጴጥሮስ “እኔ በኢትዮጵያ ስለማምን፣ እኔ እስካመንኩ እሷ አትሞትም፣” እንዳሉት በማንኛውም ሃይማኖት ውስጥ፣ በማንኛውም እምነት ውስጥ ያለን እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች ነን የምንል እስካመንንባት ድረስ ኢትዮጵያ አትሞትም!
በዚህ ጉዳይ የህሊና ጥያቄ የሚነሳባቸው ባለስልጣናት ቢኖሩና ነገሩ እየከበዳቸው ስልጣናቸውን ቢለቅቁ፣ “በእኔ ዘመን ይህንን ስላየሁ መፈጠሬን ጠልቼዋለሁ!” ቢሉ፣ የብዙዎችን ስሜት የሚገልጽ ነው።
ባስብ ብሠራ ብመኝ
መቼም ዘንድሮ አልሆነኝ፣
አዘነ ሆዴ ተናደደ
ምነው ይዞኝ በሄደ፣
የሚሉ የብሶት ድምጾች እየበዙ ሲሄድ መልካም አይደለም።
ይሀች ሀገር እኮ አዛውንቶችንና የማንኛውንም ሃይማኖት መንፈሳዊ አባቶችንና እናቶችን ብሎም አገልጋዮችን የሚያከብር ህዝብ ሀገር ናት እኮ!
በዚህ ፖለቲካ እንደ መኪና ፋብሪካና እንደ ኢንተርፕራይዝ በሆነበት፣ ጨዋታው ሁሉ ትርፍና ኪሳራ በሆነበት፤ መሪ ፍልስፍናው “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው!” በሆነበት፣…
“ለእኛ ትርፍ የሚያስገኝ እስከሆነ ድረስ ማንኛውም ነገር ትክክል ነው፣” በሆነበት፣…
ክንፍ ሊኖረን የምንችለውን ጭራ የወሸቅነውን መለየት አስቸጋሪ ነው። ፈጣሪ በጥበቡ ለይቶ በቦታ ቦታችን ያስቀምጠን አንጂ!
ሀገራችን እዚህ ደረጃ መድረሷ ያሳዝናል፣ ያማልም። አንዱ መከራ ሄደ ወይም ቀነስ ስንል ሌላው እየመጣ፣ አንዱን ክፉ ነገር ነፋስ ወሰድልን ስንል ሌላኛው የባሰ ክፉ ነገር እየመጣ መከራችን አላልቅ ቢልም፣ አሁንም ትልቅ ነገር ብልህነት ነው፣ ምንም ያህል ጊዜ ቢወሰድ ነገሮች ሊለዋወጡ በስተኋላ ሊጸጽቱን የሚችሉና ችግርን ለመፍታት ምንም አይነት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የማይችሉ ስህተቶች ውስጥ ላለመግባት መጠንቀቅ ግድ ይላል። ምክንያቱም አሁን ሁሉም መፍትሄ ያለው በፈጣሪ እጅ ነውና።
...ግን ደግሞ ይህም ያልፋል!
ፈጣሪ ሆይ፣ በርህን እያንኳኳን ነው፣ አለሁላችሁ በለን!



Read 1884 times