Saturday, 11 February 2023 21:31

እሽሩሩ መዉደድ እሽሩሩ ፍቅር “እኔ ሳባ፣ እባብም እርግብም ነኝ”

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(6 votes)

  ሳባ እባላለሁ፡፡ ሮማን ቡና ቤት ተቀጥረዉ ከሚሠሩ ጋለሞቶች አንዷ ነኝ፡፡ እነሆ ሕይወት ፈፅሞ ባልተለምኩት ጎዳናዉ አካልቦ እዚኸኛዉ የዕድል ፈንታዬ ምዕራፍ ላይ ጥሎኛል፡፡ የልጅነት ትልሜና የአሁኑ ኑሮዬ፣… ፍፁም የተጣረሰ ነዉ፡፡ ሕይወት በተለሙት መንገድ አይነጉድም፡፡
እንደተለመደዉ አጭር ቀሚሴን ለብሼ ከባልኮኒዉ ራቅ ብሎ ከሚገኝ ወንበር ላይ እግሬን አነባብሬ ተቀምጫለሁ። ማርቦሮ ሲጋራዬን እያቦነንኩ፡፡ ጥቁር ጨርቅ የጠይም ገላዬን ዉበት እንደሚያጎላዉ አዉቃለሁ። ከሁለት ቀን በፊት ብቅ ብሎ የነበረዉ ረጅም ሪዛም ሸበላ (ቀልቤን ሰርቆ የሄደዉ ሸበላ) ዐይኑን እንዲሁ ገላዬ ላይ ሲያንከራት አመሸ። ቤቱን ያ ሁሉ ቆንጆ ሴት ሞልቶት ሳለ፡፡
ሸበላዉ ምናልባት ዛሬም ይመጣ ይሆናል።
አዜብ ከእኔ በተቃራኒ ካለዉ ወንበር ላይ ተቀምጣ ከቦርሳዋ ትንሽዬ የፊት መስታወት አውጥታለች። ፊቷን በማስዋብ ላይ ተጠምዳለች፡፡
ባልኮኒዉን ከበዉ ቢራ የሚጨልጡት ሴቶች (ጋለሞታ የሥራ ባልደረቦቼ) ሳቅና ንትርክ እኔ አለሁበት ድረስ ይሰማል። ማኅበራዊ መስተጋብሬ ሰፊ ቢሆንም አንደበተ ቁጥብ ነኝ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ጋግርታም ናት ይሉኛል፡፡
ዝምታዬ ማንነቴን የጋረድኩበት ጭንብል ነዉ፡፡ ምስጢሬን በልቤ እቀብራለሁ እንጂ ለሌሎች አልነዛም። ወዳጆቼ እንኳ ልቤን አያዉቁትም፡፡ ጭንብሌ ቢገፈፍ የሚገለጠዉ ግብዝነቴ፣ ቂመኛነቴ፣ ከሀዲነቴ፣ ራስ ወዳድነቴ፣ ቅናቴ፣ ምቀኛነቴ፣ ጨካኝነቴ እና ሴሰኛነቴ ነው፡፡
አንደበተ ቁጥብነቴ ስሜ በሌሎች እንዳይጠለሽ የጋረደ ግምጃዬ ነው፤ በሐሜት ከመብጠልጠል የሚተርፍ ሰዉ ባይኖርም፡፡
ክፉም ሆንክ ደግ በሌለህበት እንደ ሙዳ ሥጋ ትቦጨቃለህ። እንደ ቋንጣ ትዘለዘላለህ። ቢሆንም ግን ቁጥብነትን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ወዳጅ አገኘሁ ብሎ ለባዕድ ገመናን ገልጦ መንዛት አይገባም፡፡
ቀንደኛ ጠላቶቻችን፣ ትናንት አብረዉን የበሉ አይደሉምን?
መቃብራችንን ለመማስ የሚማስኑት የአሟሟታችንን መንገድ ስለሚያዉቁት አይደለምን? የዉድቀታችንን ፈለግ?
የዛሬ ወዳጅህ ነገ ሲክድህ ጠልፎ የሚጥልህ በሽንቁርህ ገብቶ ነዉ፣ በደካማ ጎንህ፡፡        
ቡና ቤቱ ዉስጥ ከሚሠሩ ሴቶች በዉድድር ያልጠለሸ ስም ያለኝ እኔ ብቻ ነኝ፣ ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ቢሆንም፡፡ ላይላዩን ሐሜትን የምፀየፍ ልምሰል እንጂ የሰዎችን ጀርባ መበርበር እወዳለሁ፡፡ አንዱ የሌላዉን ምስጢር እንዲዘከዝክልኝ ማድረጉም ለእኔ ተራ ተክህኖ ነዉ፡፡ የሌሎችን ጀርባ የማወቅ ጉጉት የሌለኝ ዳተኛ መስዬ ብታይም፣ ማን ምን እንደሆነ፣ ምን እንዳደረገ፣ ምን እንደሚፈልግ ልቅም አድርጌ አዉቃለሁ፡፡ ለምሳሌ…
ሄለን ለጋስ ብትሆንም በካና ናት፡፡ ቂልነቷም የበዛ ነው።
ወርቅ ላበደረ ወርቅ የምትል ናት፡፡
ማሕሌት የታወቀች ሐሜተኛ ናት፡፡
መክሊት የረባ ያልረባዉ ነገር ቶሎ የሚያስከፋት ነውጠኛ ናት፡፡ የመከዳት ታሪኳን ምሬት ጆሮ ለሰጣት ሁሉ በመዘክዘክ የምታሰለች ችኮ ናት፡፡ ባመነዉ ያልተከዳ ማን ነዉ?
አዜብ ለነዋይ ሟች ናት።
ወዳጅነትን የምትሰፍረዉ በጥቅም ሚዛን ነው፡፡ ሃሳቧ የተገነባዉ “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ” በሚለዉ ብሂል ነዉ፡፡ ለእሷ አዱኛ ብላሽ ታላቅ ለግጥ ነዉ፡፡
ምሽት ላይ የቡና ቤታችን ቋሚ ደንበኞች መጥተዉ ደመቅመቅ ማለት ሲጀምር፣ ሪዛሙ ቀይ ሸበላ ከች አለ፡፡ የቀይ ፊቱን ሰፊ ወሰን የሸፈነዉ ሪዙ መጀመሪያ ቀን መጥቶ ካየሁት ጥቂት በመጎፈሩ ሳይሆን አይቀርም ግርማዉን አግንኖታል፡፡ የተቀመጠዉ ከባልኮኒዉ ጥቂት ራቅ ብሎ ካለዉ ቦታ ነዉ፡፡
የሆነ ገፅታዉ ከቀድሞ ፍቅረኛዬ ጋር ይመሳሰላል። አፍንጫዉ፣ የትከሻዉ ስፋት፣ የከናፍሩ ስስነት ምናምን፡፡ በዐይኖቹ የቡና ቤቱን ትዕይንት በትኩረት እየሰለለ ሳለ ዐይን ለዐይን ተጋጨን። ቀድሜ ያፈርኩ አይነት ዐይኖቼን ሰበርኩ፡፡ እንደገና ባልኮኒዉ ዙሪያ የጦፈዉን ሁካታ የምከታተል መስዬ በስላቺ ልገረምመው ስሰልለው፤ አሁንም ዐይኖቹን እኔ ላይ እንደሰካ ነው፡፡
ሴት አዉል ይመስላል፡፡ የባልኮኒዉን ሁካታ መታዘብ ትቼ ወደ ሸበላዉ ሳማትር ከእኔ እኩል እዚህ ቡና ቤት ሥራ የጀመረችዉ ሊሊ ስትጠጋው አየሁ። (የመዝገብ ስሟ ማህሌት ነዉ፡፡ ሁላችንም፣ እኛ ብቻ የምንጠራራበት፣ ደንበኞቻችን የማያወቁት የሥራ ቦታ ቅፅል ስም አለን) አሁን ፊቱ ተገትራለች። እንደ ኮርማ በሬ ቀንድ ከርቀት የሚታዩትን ጡቶቿን ወድራ (እነዚህ ጡቶቿ ወንድ የምትስብባቸዉ ብቸኛ የመግነጢስ ምትሃቶቹ ናቸዉ) ተጠጋችው ምትሃቶቿ ቀስራ። ያለ ወትሮዋ ደርሳ አስተናጋጅ መሆኗ (አስተናጋጆቹ ድዳቸዉን አስጥተዉ ሳለ) ደንቆኛል፡፡   
ሸበላዉን እየሰረቅኩ መመልከቴን አልተዉኩም፡፡ የቢራ ብርጭቆዉን አንስቶ ወገቡ ድረስ ተጎንጭቶ ሲጋራ ለኮሰ፡፡ ማሕሌት ቢራ ካቀረበችለት በኋላ እንኳ ከሦስቴ በላይ ወደ እሱ ተመላለሰች፡፡ ቀልቡ ሳይጠላት አልቀረም። እንጂማ ወንበር እንድትጋራዉ ጠይቆ ቢራ ይጋብዛት ነበር፡፡
ሙሉቀን መለሰ በእዚያ መረዋ ድምፁ አካል ገላን ማንቆርቆሩን ቀጥሏል፡፡
ሸበላዉ ስልኩን ከኮቱ ኪስ አዉጥቶ ተነጋገሮ እንዳበቃ ከመቀመጫዬ ተነስቼ ወደ እሱ አመራሁ፡፡               
“ምን ይጨመር?” አልኩት በፈገግታ ተጠግቼዉ፡፡ ሽቶዉ ከቡና ቤቱ የሲጋራና የመጠጥ ጠረን በላይ ነግሶ በአፍንጫዬ መሰረገ።
“ሁሉ ሙሉ ነዉ፡፡ ቢራ ይምጣልሽ ተቀመጪ?” አለ በፈገግታ ተሞልቶ በእጁ ፊት ለፊቱ ያለዉን ወንበር እያመለከተ፡፡
“አመሰግናለሁ፡፡” ወንበር ስቤ ፊት ለፊቱ ተቀመጥኩ፡፡
“እንኳን ደህና መጣህ፡፡ ጁሊ እባላለሁ፡፡”     
“ሀኒባል እባላለሁ፡፡” አለ በፈገግታ፡፡ ወዲያዉ የቡና ቤቱ ተወዳጅ አስተናጋጅ በእዚያ የማይነጥፍ ደማቅ ፈገግታዋ ታጅባ ትዕዛዝ ልትቀበለኝ መጣች፡፡ ቢራ አዘዝኩ፡፡
የእዚያ እለት ሀኒባል ጥሩ ገንዘብ ከፍሎኝ እዚያዉ ካዛንቺስ ይዞኝ አደረ፡፡                     
***
የሸበላዉን፣ የሀኒባል ወርቁን ቀልብ ማርኬ ደጋግሞ ቋምጦኝ እንዲመጣ ለማድረግ የቀደመችኝ ሴት አልነበረችም፡፡ ሮማን ቡና ቤት የመጣ ሰሞን እሱን በፍቅር አንበርክኮ ለማግባት ያልተራኮተች፣ ያልተሽቀዳደመች ሴት አልነበረችም፡፡
በተለይ ሄለን (እጅግ የምጠላት ወደረኛዬ ነበረች፣ እሷ ግን ይህን አታዉቅም) ሸበላውን እሱን ስታይ የሚያደርጋትን ነበር የሚያሳጣት፡፡ የልቧን መከጀል ከገጿ ታዝቤ ነበር፡፡ ሄለን ተወዳዳሪ የሌላት ቆንጆ ብትሆንም ጮሌነት ይጎድላታል። ወንድን የማጥመድ ጥበቡን አልተካነችም፡፡ በዉድ ሽቶ መታጠብ፣ ፋሽን ጨርቅ መደረት ብቻዉን የወንድን ቀልብ አይስብም፣ ለትዳር አያሳጭም፡፡
ታዲያ እኔ ሳባ ቆነጃጅቱን ተገዳድሬ ሸበላዉን የግሌ አደረኩ። ወንድን የመሳቢያ መግነጢሱን አውቀዋለኋ፡፡ በሸርሙጥና ያካበትኩት ጥበብ ይህ ነዉ፡፡                     
ሀኒባል ልቡናዉ ዉስጥ የሸሸገዉን ገመና እኔን ተጠልሎ ለመርሳት የሚጥር ምስጢራዊ  ሰዉ ነዉ፡፡ ሳያውቅብኝ ልበረብረዉ ብጥርም የታሪኩን ዝርዝር ማወቅ አልቻልኩም። የፍቅር ሕይወቱን እንዲያወጋኝ በጥበብ ስነካካው፣ ዉስኪና አሰልቺ የፖለቲካ ሐሜት ሲግተኝ አመሸ፡፡
ይህም ሆኖ፣ ሽንቁሩን ገልቤ ጎዶሎዉን መታዘብ አልተሳነኝም፣ ፍቅር ጎድሎታል። ይኸን ጉድለቱን አስልቼ ነበር በወጥመዴ ተብትቤ የጣልኩት፤ አፍቃሪ ሴት ሆኜ። ምሁርነቱ በወጥመዴ ከመዉደቅ አላስጣለዉም፡፡
አፍቃሪ መስሎ ሌሎች ልብ ዉስጥ መጎዝጎዝ የተለየ ተክህኖ ይጠይቃል፡፡ ወንድ ልጅ እንደ እናቱ የምታባብለዉን ሴት ያመልካል፡፡ ሀኒባልን ከእኔ ጋር እንደ አለቅት ምን አጣበቀዉና!
የሁሉም ሴት ገላ እንደሁ ተመሳሳይ ነዉ።
ብልሀቱ ሌላ ነዉ፡፡
ወንድን በፍቅር ለመጣል ከመነሳት በፊት የልብ ትርታዉን ማወቅ ያስፈልጋል፤ ጥረታችን ከሽፎ ገሸሽ እንዳያደርገን፡፡
ሀኒባል የሚያመልከኝ በእሹሩሩዬ ነዉ፤ ለፍቅሬ እጅ ሲሰጥ ሸርሙጣነቴ እንኳ ቁብ አልሰጠሙም፡፡
ወንድ ‘እሹሩሩ ፍቅሬን’ እንዲዘፍኑለት ይፈልጋል፣ ሥጋጃ ሆነዉ እንዲጎዘጎዙለት ይሻል፡፡ እሹሩሩ፡፡
ወንድን እሹሩሩ እያሉ ለመኖር ያን ሰዉ ማፍቅር አያስፈልግም ወይ ትሉ ይሆናል፡፡
ወንድን እንደ ባሪያ ገዝቶ ለመኖር ፍቅር ብቸኛዉ መንገድ አይደለም፡፡ ዋናዉ ነገር ኩሸትን መካን ግብዝነትን መላበስ ነዉ፡፡
ሳይወዱ የወደዱ መምሰል፣ ሳያዝኑ ያዘኑ መምሰል፣ የዉሸት ማንባት፣ የዉሸት ጥርስን ማሳየት፡፡
ንፉግ ሳሉ ቸር መምሰል፡፡
እባብ ሆኖ ርግብ መምሰል፡፡
 እኔ ሳባ እባብም እርግብ ነኝ፡፡  Read 1305 times