Saturday, 11 February 2023 21:34

“የአጭር መንገድ…ረጅም ጉዞ”

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(2 votes)

ብዙ የተወራለት-የተነገረለት ምሁር ነው፡፡ በህይወት የኖረው ግን ለ33 ዓመት ብቻ ነው፡፡ ስለ ህይወቱ ታሪክ ያለን መረጃም ሲበዛ የሳሳ ነው፡፡ ሀሳቦቹንና ልምዶቹን የያዘች አንዲት መፅሐፉ ግን ከብዙ ትበልጣለች፡፡ በዚህም ሳቢያ ከተዋጣላቸው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ደራሲያን ተርታ የክብር ቦታ ይዞ ታሪክ ዘወትር ያስታውሰዋል፣ ያወሳዋል፡፡
የህይወት ዘመኑ  ይጠር እንጂ አያሌ ተግባራት በአጭር እድሜው  ከውኖ አልፏል፡፡ እውቁ የታሪክ  ተመራማሪ ባህሩ ዘውዴ “pioners of change in Ethiopia; the reformist intellectuals of the century” በሚል ጥናታቸው ውስጥ የዚህን ምሁር ሕይወት ቃኝተዋል፡፡ የለውጥ ሃሳቦቹን ተንትነዋል። በኢትዮጵያ  ህብረተሰብ ላይ ያሳደረውን ተፅእኖ፣ የተወውን አሻራ ገምግመዋል።
ፋጊ ወጊ የለውጥ  ፈር ቀዳጆች  የሚል ማዕረግ ከተሰጠው ከመደቧቸው ምሁራን ውስጥ “ነጋድራስ  ገብረ ህይወት ባይከዳኝ” ግንባር ቀደም ሆኖ ይገኝበታል፡፡ የህይወት ታሪኩንም  ባልተለመደ ሁኔታ በዝርዝርና  ሰፋ ባለ መልኩ አጣፍጠው ከትበውለታል፡፡ “ፋና ወጊ የለውጥ አቀንቃኞች በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በአማርኛ ጭምር አቅርበውታል፡፡
ሻለቃ ባይከዳኝ፣ የአፄ ዮሐንስ ባለሟል ናቸው፡፡ የገብሬ ደግሞ ወላጅ አባት፡፡ የሞቱት  በመተማ ጦርነት ነው፡፡ ያኔ ገብረ ህይወት…ገና ሦስት አመት እንኳን አልሞላውም፡፡ በጦርነቱ ከአባቱ ጋር አብረው ሰለባ የሆኑት ንጉሱ አፄ ዮሐንስ…ሞታቸው ያስከተለው የፖለቲካ ክፍፍልና ስነ ልቦናዊ ቀውስ ቀላል አልነበረም፡፡
ከዚህ ባሻገር ለአራት ዓመት የዘለቀው “ክፉ ቀን” እየተባለ በታሪክ  የሚወሳው ረሃብ ሀገሪቱን  እያመሳት ነበር፡፡
አዲሱ ንጉሠ  ነገስት አፄ ሚኒልክ ስልጣናቸውን ለማደላደል ያደረጉት ዘመቻም  ብዙ ጉዳት  አድርሶ ነበር፡፡
 በዚህ ሁኔታ  ነበር እንግዲህ ገብረ ህይወት ከጥቂት ጓደኞቹ ጋር፣ ገና በሰባት አመቱ ወደ ኤርትራ የኮበለለው፡፡ ከዚያ  ምፅዋ አቅራቢያ ከሚገኘው የስዊድን ሚሲዮን ተጠጋ፡፡
 አንድ ቀን የምጽዋን  ወደብ ለመጎብኘት  ከጓደኞቹ ጋር ያደረገው  ጉዞ የህይወቱን አቅጣጫ  ላንዴና ለሁሌም ቀየረው። በወቅቱ በወደቡ መልሕቁን ጥሎ የቆመ የአንድ መርከብ እነ ገብሬን ማረካቸው፡፡ ጀርመናዊ የመርከቡ ካፒቴን ፈቅዶላቸው ገብረ ህይወትና ጓደኞቹ  የመርከቡ  የተለያየ  ክፍል እየዞሩ መጎብኘት ጀመሩ፡፡
 መርከቡ የጉዞ ጊዜው ሲደርስም ገብረ ህይወት እዚያው መርከብ ውስጥ ተሸሽጎ አብሮ ተጓዘ፡፡ መሃል መንገድ ላይ ካፒቴኑ የተደበቀውን ጉብል ቢያገኘውም ሩቅ ስለተጓዙ ወደ አገሩ መልሶ ሊያባርረው አይችልም፡፡ ጉዞውን ከማስጨረስ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረውም፡፡ መርከቡ ኦስትሪያ  ሲደርስም ጉብሉን ለአንድ  ሀብታም ቤተሰብ በማደጎነት ሰጠው፡፡ የዚህ መልካም ቤተሰብ እንክብካቤ ሳይለየው፣ ገብሬ  የጀርመንኛ ቋንቋን ከማጥናቱም በላይ በበርሊን ዩኒቨስርቲ የህክምና ትምህርት እንደተከታተለ ይነገራል፡፡
ገብሬ አማርኛ ቋንቋን ያጠናውና ያወቀው ከአውሮፓ ትምህርቱን ጨርሶ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ነው፡፡ ደጃዝማች ይገዙ የተባሉ የአጤ ሚኒልክ ባለሟል አቅርበውት አስተማሪ በመመደብና በተለየ ትጋት እንዲማር አግዘውታል፡፡ ከአጤ ሚኒልክ ጋርም አስተዋወቁት፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ የንጉሰ ነገስቱ ልዩ ጸሐፊና አስተርጓሚ ለመሆንም በቃ፡፡ በዚሁ ባስተርጓሚነት ሚናው እ.ኤ.አ በ1907 በራሱ መሪነት ወደ ጀርመን የተጓዘውን የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ይዞ ሄዷል፡፡  
የንጉሰ ነገስቱ መታመም ግን ብዙ ነገሮችን አበላሸ፡፡ ለአውሮፓ ሌጋሲዮኖች ሐኪም በመመደብ ዲፕሎማሲያዊ ትርፍ ለማግኘት በር ከፍቶላቸዋል፡፡ ሀኪም ወርቅነህ ንጉሱን ለማከም እንደተመደቡ ሁሉ፤ ገብረ ህይወትም የጀርመኑን ሐኪም ሽታይንኩለር ረዳት ሆኖ ተመደበ፡፡ ይሁን እንጂ ወርቅነህም ሆነ ገብረህይወት የእቴጌይቱን በጎ አመለካከት ለማግኘት አልታደሉም ነበር፤ እንዲያውም እነ ገብረ ህይወት ንጉሱ አጠገብ ድርሽ እንዳይሉ ተከልክለው ነበር፡፡ በዚህም አላበቃም፡፡
 ሽታይንኩለር ታማሚውን ንጉስ ለመመረዝ ሙከራ ተደርጓል በማለቱ የተነሳው ውዝግብ ጣጣው ለገብረ ህይወትም ተርፏል። በዚህ ሁኔታ ነው ገብረ ህይወት ወደ ጎረቤት አገር ወደ ሱዳን በ1902 መጀመሪያ ላይ ለመሰደድ የወሰነው፡፡
ከሱዳን ሲመለስ በጠና ታሞ ምፅዋ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል መታከም ነበረበት፡፡…“አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” የተሰኘውን መጣጥፍ እዚያው ምፅዋ ከህመሙ እያገገመ ነው የፃፈው። በመጣጥፉ ረዥም መቅድም ላይ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ህይወቱን የታደገውን የእድሜ ልክ ጓደኛውን ጳውሎስ መናመኖን አወድሷል፡፡ ጳውሎስ የኋላ ኋላ፣… ገብረ ህይወት ከሞተ ከጥቂት ዓመታት በኃላ “መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” የሚለውን መፅሐፍ አሳትሞለታል፡፡
ገብሬ በመንግስትና የህዝብ አስተዳደር ውስጥ ያሳየውን የአጻጻፍ ምጥቀት ባህሩ ዘውዴ ተንትነው ያስቀመጡት እንደሚከተለው ነበር፡፡…
አካዳሚያዊና የዘለቄታ ጉዳዮችን የሚያነሳ ነው፡፡ በዘነብ ዜና መዋዕል ውስጥ የምናገኘውን ውብ አማርኛ የሚያስታውስ፣ በኋላም በብርሃኑ ዘሪሁን ድርሰቶች ጫፍ የደረሰውን በአጫጭር ዐረፍተ ነገሮች ሐሳብን አሳምሮ የመግለጽ ክህሎት የሚፈነጥቅ ነው፡፡ ይህን ፀጋ ሐሳባቸውን በጠጣር ቃላትና በውስብስብ ዐረፍተ ነገሮች የመግለጽ ዝንባሌ የነበራቸው አፈወርቅ እንኳ አልታደሉትም ማለት ይቻላል፡፡(ገጽ 226)
ገብሬ በሱዳንና በኤርትራ ቆይታው  ነፃይቱ ሀገሩ በቅኝ ግዛት ቀንበር  ስር ከነበሩ አገሮች ጋር ሲያነፃጽራት ምን ያህል ወደ ኋላ የቀረች ሆና ባገኛት ጊዜ፣ ሁኔታውን በሚከተለው መንገድ ገልጾት ነበር፡፡…
“በዙሪያችን ያሉትን አገሮች ብንመለከት አእምሮ ያላቸው ሕዝቦች በብዙ ትጋት ሲያለምዋቸው እናያለን፡፡ ይልቁንም በደርቡሾች ጠፍቶ የነበረውን የሱዳንን መሬት ብናይ እንግሊዞችን የሚመስል ያእምሮ ህዝብ ሲገዛው ምድረ በዳም ቢሆን የደስታ ገነት እንዲሆን ይመሰክርልናል፡፡ አእምሮም በአእምሮ ካልሆነ በቀር በሌላ አትታገድም፡፡ ስለዚህ ወዮለት በድንቁርናው ለሚቀመጥ ሕዝብ ውሎ አድሮ ይደመሰሳልና!”
በሁሉም ምሁራን ዘንድ ማለት ይቻላል ጎልቶ ይታይ የነበረው የያኔ ስሜት፣ ተመሳሳይ ነው፡፡ በተለያየ አጋጣሚ  ከጎበኟቸው ምዕራባውያን አገራት ጋር ስትነፃፀር አገራቸው ምን ያህል ኋላ ቀር እንደነበረች እያሰቡ ይብሰለሰሉ ነበር፡፡ ይህ ስሜት በተለይ ገኖ የወጣው በገብረ ህይወት ዘንድ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ ገብሬ ከሌሎች አቻዎቹ የሚለይበት መንገድ አለ፡፡ ይሄውም የምዕራቡን የሥልጣኔ መንገድ ከመቅዳት ይልቅ ኢትዮጵያ የራሷን የእድገት ጎዳና መቀየስ አለባት የሚል አመለካከት ነበረው፡፡
ሁሉን ቁሳቁስ፣… ማረሻ እንኳን ሳይቀር በገፍ ከአውሮጳ በማስመጣት የአገሪቱን የጎጆ ኢንዱስትሪ የማቀጨጩ ሂደት ይቆጨው ነበር፡፡አገሪቱ በምዕራባውያን የፋብሪካ ውጤቶች ስትጥለቀለቅ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የመጡ አገር በቀል ጥበቦች እየከሰሙ መሄዳቸው ያስተክዘው ነበር፡፡ ይሄን ቁጭት ከህሊና በማይጠፋ ቃላት  መንግስትና የህዝብ አስተዳደር ውስጥ አስፍሮታል፡፡…
“እስቲ አሁን እኛ የኢትዮጵያ ህዝብ አርነት አለን ሊባል ነውን? አርነት ያለው ሕዝብ ማለት እውነተኛ ትርጉሙ ለብቻው መንግስት ያለው ህዝብ ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ራሱንም የቻለ ህዝብ ማለት ነው እንጂ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከ ዛሬ ድረስ ገና ራሱን አልቻለም፡፡ (ገጽ 79)
የአንዳንድ ሰው እድሜ፣… ቁጥር ብቻ አይደለም፡፡ እልፍ ታሪኮችን በውስጡ አቅፎ የያዘ ነው፡፡ የገብሬ ታሪክ፣በእድሜ ከተቆጠረ የትልቅ ሰው ታሪክ አይደለም፡፡ ይሁንና በአንድ ወጣት ሽራፊ እድሜም ቢሆን እልፍ የህይወት ሰበዞች በውስጡ ይፈራረቁበታል፡፡ ከባህሩ ዘውዴ ምርምርም የምንገነዘበው ይህንኑ ነው፡፡
በርግጥ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ስሙ የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ገብቷል፡፡ ስራው ግን እንዲህ በዝርዝር ተቆፍሮ የቀረበበት ሰነድ ይህ የመጀመሪያው ይመስለኛል፡፡ የገብሬ ብቻ አይደለም የአብዛኞቹ ፋና ወጊ የለውጥ አቀንቃኞች የአላማ ጽናትና ታላቅ ስብዕና ያላቸው ምሁራን ሃሳቦቻቸው ቅርሶቻቸው ድንቅ መሆኑን መመስከር ይቻላል፡፡
ሀገራችን በታሪኳ የተከሰቱ አቢይ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጦች የቱን ያህል  ገብሬንና ሌሎች ሃሳበኞችና የሀሳብ አመንጪዎች ውጤት ስለመሆኗ በኔ መጠነኛ የታሪክ ንባብና ግንዛቤ እንኳን ለመረዳት ችዬአለሁ፡፡

Read 378 times