Print this page
Saturday, 18 February 2023 19:31

ኢትዮጵያ የመርማሪ ኮሚሽኑ የሥራ ውል እንዲቋረጥ ያቀረበችውን ጥያቄ የአፍሪካ የሰብአዊና ሕዝቦች መብት ኮሚሽን ውድቅ አደረገው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

የስራ ውል የማቋረጡ ጥያቄ በቅርቡ ለሚካሔደው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ይቀርባል ተብሎ ነበር
               
       የፌደራሉ መንግስት ከህውኃት ኃይሎች ጋር ባደረገው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት  የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲመረምር የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የባለሞያዎች ኮሚሽን የሥራ ውል እንዲቋረጥ  በኢትዮጵያ   የቀረበውን ጥያቄ፤ የአፍሪካ የሰብአዊና ሕዝቦች መብት ኮሚሽን  ውድቅ አደረገው። የስራ ውል  እንዲቋረጥ የቀረበው  ጥያቄ በቅርቡ ለሚካሄሔደው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባኤ እንደሚቀርብ ተገልጾ ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገው ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ለመመርመር መነሳቱና መርማሪ ኮሚሽን ማቋቋሙ ተገቢ አለመሆኑን የገለጸችው ኢትዮጵያ ፤ ድርጊቱ ባለፈው ጥቅምት  ወር ከተፈረመው የሰላም ሥምምነት ወዲህ የታዩ መሻሻሎችን እንደሚያስተጓጉል አስታውቃለች።
ከትላት በስቲያ የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም  በተጀመረው የአፍሪካ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ንግግር  ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ጥያቄው  በቅርቡ ለሚካሔደው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እንደሚቀርብም ተናግረዋል፡፡
“በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የተደረሰው የሰላም ሥምምነት ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ማምጣት የሚለውን መርሃ ያንጸባረቀ ነው” ያሉት አቶ ደመቀ፤
“በኢትዮጵያ  ለተፈጠረው ችግር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት  መፍትሄ ለመፈለግ የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን፣ አይዘነጋም። በአፍሪካ ኅብረት የተመራውን የሠላም ሂደትና በፕሪቶሪያ የተፈጸመውን የሠላም ሥምምነት በመርዛማ ትርክት የሚበክልና  በአገሪቱ ተቋማት እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያዳክም ነው “  ሲሉ መናገራቸው ይታወሣል።
ይህንኑም ተከትሎ የአፍሪካ የሰብአዊና ሕዝቦች መብት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሬሚ ንጎይ ሉምቡ፤   ኮሚሽኑ እያከናወነ የሚገኘው   የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የማጣራት ሥራውን እንደሚቀጥልና   ምርምራውንም እያጠናቀቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በተመድ የተቋቋመው ኮሚሽን ባለፈው መስከረም ባወጣው የመጀመሪያ ሪፖርት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመፈጸማቸው ማስረጃ እንዳገኘ  ያስታወቀ ሲሆን፤  መንግሥት የኮሚሽኑን ሪፖርት ተአማኒነት የሌለው ነው ሲል  ውድቅ አድርጎታል፡፡
ሦስት አባላት ያሉት በተባበሩት መንግስታት  ድርጅት    በሰሜኑ ጦርነት የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን እንዲመረምር የተቋቋመው አለም አቀፍ የባለሙያዎች ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያ  ኤርትራና ህወሓት  የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር  ጥሰት ፈጻሚዎቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቁ ይታወሳል፡፡

Read 2417 times Last modified on Saturday, 18 February 2023 21:08