Saturday, 18 February 2023 19:38

በወልቂጤ ከተማ የሟቾች ቁጥር 6 ደርሷል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

- ከ30 ሰዎች በላይ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል
     - ግድያው ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው እርምጃ ነው - ኢሰመኮ
           
       የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ወልቂጤ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች የቧንቧ ውሃ አቅርቦት ለረዥም ጊዜ መቋረጡን ተከትሎ፣ መንግስት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ባለፈው ረቡዕ የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ሰልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ በመንግስት ታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት የሞቱ ነዋሪዎች ቁጥር 6 መድረሱን ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ ተናገሩ፡፡
ከግጭቱ ጋር በተያያዘም፣ ከትላንት ጀምሮ ትራንስፖርትን ጨምሮ ሁሉም አይነት አገልግሎቶች መቋረጣቸውን፤ የመንግስትም ሆነ የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግ መሆናቸውን ነዋሪዎች ጠቁመዋል።
በወልቂጤ ከተማ የውሃ ችግር ከሰባት ዓመት በላይ የዘለቀና ነዋሪውን ሲያሰቃይ የነበረ ጉዳይ  ቢሆንም በተለይ ባለፉት  አምስት ወራት ግን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ዉሃ መጥፋቱንና ህዝቡ ለከፍተኛ ስቃይ መዳረጉን ነው ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ የተናገሩት።
በከተማው ውስጥ ቀደም ባለው ጊዜ የነበረው የውሃ አገልግሎት በማስተላለፊያ መስመሮች እድሳት እጦት፣ በከተማው ነዋሪ ቁጥር ማደግ እንዲሁም በፍላጎት መጨመር ሳቢያ ፍላጎትና አቅርቦት ሊመጣጠን አለመቻሉን የገለፁት ነዋሪዎቹ፤ ከዚህ በተጨማሪም ውሃው ባለበት በቋሚነት አገልግሎት መስጠቱን እንዳይቀጥል ሌላም እንቅፋት እንደገጠመው አስረድተዋል።
ወልቂጤ ከተማ ውሃ የምታገኝበትና በቸሃ ወረዳ የሚገኘው ”ቡዠባር” የውሃ ሳይት ቀቤና ወረዳና ቸሀ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ 10 ያህል ቀበሌዎች ውሃውን ለመስኖና ለሽያጭ በማዋላቸው ወደ ወልቂጤ የሚፈሰውን ውሃ እንዲቀንስ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ እንዲጠፉ ማድረጋቸውን የገለፁት ነዋሪዎች፤ ይህ ችግር በተለይ ላለፉት አምስት ወራት በቋሚነት በመቀጠሉ ህዝቡን በብሶት ወደ አደባባይ እንዳስወጣው ተናግረዋል።
የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የአይን እማኝ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፣ የከተማዋ የውሃ ችግር እየተባባሰ የመጣው ከአራት አመት ወዲህ ቢሆንም፣ ከዚያም በፊት ባለው ጊዜ ህዝቡ ውሃ የሚያገኘው በፈረቃና በሳምንት አንድ ጊዜ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ከአምስት ወር በፊት ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ውሃ መቋረጡንና በወር ከ15 ቀን (በ45 ቀናት) አንድ ጊዜ እሱም ሰው በተኛበት ሌሊት በአሳቻ ሰዓት እንደሚለቀቅ የጠቆሙት የአይን እማኙ፤ ይህ በ45 ቀን በለሊት የሚለቀቅ ውሃ አብዛኛው ነዋሪ በተኛበት ለሁለት ሰዓታት መጥቶ ስለሚጠፋ፣ ሰው ውሃ ለማግኘት ሌላ 45 ቀናት ለመጠበቅ እንደሚገደድ ተናግረዋል።
የወልቂጤ ህዝብ ይህን የውሃ ችግርና ስቃይ መቋቋም ስላልቻለ ወደ ወልቂጤ የሚመጣውን ውሃ ጠልፈው ለሽያጭ ከሚያውሉ ቀበሌዎች ለመግዛትና ህይወቱን ለማቆየት በባጃጅ በጋሪና በተለያየ አማራጮች ሩቅ መንገድ እየተጓዘ፣ አንድ ጀሪካን ውሃ በ20 ብር እየገዛ ችግሩን ለመቋቋም ሲታገል መቆየቱን ነው የአይን እማኙ የተናገሩት፡፡
በአሁን ወቅት የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ ከ150 ሺህ በላይ መድረሱን የገለፁት የአይን እማኙ፤  ይህ የውሃ እጦት ስቃይ  የጥቂቶች ብቻ ሳይሆን የ150 ሺህ ህዝብ ስቃይ መሆኑንም በምሬት ተናግረዋል፡፡ ህዝቡ ይህ ብሶቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ ባለፈው ረቡዕ የውሃ መቅጃ ጀሪካኑን እየያዘ ወደ ከተማዋ የውሃ ልማት መስሪያ ቤት በማቅናት ችግሩን ገልፆ ሀላፊዎች መልስ እንዲሰጡ ቢጠባበቅም፣ ከመስሪያ ቤቱ ሀላፊዎች አንድም ጉዳዩን ነገሬ ብሎ ለህዝቡ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ በመጥፋቱና ጥያቄና ጩኸት እየጨመረ በመምጣቱ፣ የወልቂጤ ከተማ ፖሊስ ወደ ቦታው መድረሱን  ነዋሪው ተናግረዋል፡፡
የከተማው ፖሊሶች ጉዳዩ የውሃ ችግር ጥያቄና ሰላማዊ መሆኑን ካዩ በኋላ፣ ፖሊሶችም የችግሩ ተጠቂ በመሆናቸውና የህዝቡ ጥያቄ ተገቢ ነው ብለው በማመናቸው ወደ መጡበት መመለሳቸውን ማየታቸውን ነዋሪው  ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል።
“በተለይ ባለፉት አምስት ወራት ህዝቡ እንዲህ አይነት የውሃ እጥረት ችግር ውስጥ ሲገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር፣ የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ ፅ/ቤት፤ የዞኑና የከተማው የውሃ ልማት መስሪያ ቤት ሀላፊዎች ችግሩን ለመቅረፍ ለምን ጥረት አላደረጉም” በሚል የተጠየቁት ነዋሪው ሲመልሱ፤ “እስካሁን ለአንድ ክፍለ ከተማ በቂ ነው በሚል ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ጀምረው ነበር፤ ይህ በጣጢሳ ቀበሌ የተጀመረው “ጣጢሳ የውሃ ሳይት” በሁለት ወር ውስጥ ተመርቆ አገልግሎት እንደሚጀምር ሀላፊዎች ቃል ቢገቡም፤ ቆፋሮው ከተጀመረ ሰባት ወራት አልፎት ለከተማው ነዋሪ ጠብ ያለለት ውሃ እንደሌለ ነው በምሬት የገለጹት፡፡
“የከተማው ሀላፊዎች በማህበራዊ ሚድያ ችግሩ ሲነገርና ህዝቡ ሲማረር የተለመደ ግን መፍትሄ የማያመጣ መግለጫ ያወጣሉ “ያሉት ነዋሪው፤ “መፍትሄ ሊመጣ ነው፣ ችግሩን ለመፍታት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ርብርብ ላይ ነን፤ እንዲህ እያደረግን ነው፤ እንዲያ እየሰራን ነው ከማለት ውጪ በተጨባጭ የሰሩት ነገር የለም። ይህንንም የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ኮሚኒኬሽን የፌስቡክ ገፅ ላይ ገብቶ ከመቼና መቼ ጀምሮ ይህንን መግለጫ ያወጡ እንደነበር መመልከት ይቻላል ብለዋል፡፡
ህዝቡ ለከተማ አስተዳደሩ ሀላፊዎች እንደምክረ ሃሳብ ሲያቀርብ የነበረው “ሩቅ ቦታ አትሂዱ፤ ወልቂጤ ከተማ ሰፊ የውሃ ክምችት አላት፤ 3 ሜትር ተቆፍሮ ውሃ ማግኘት የሚቻልባትና በክልሉም በውሃ ሀብቷ ቀዳሚ ናት፤ ለምን እሩቅ ቦታ ትሄዳላችሁ” በማለት ነበር ያሉት ነዋሪው፤ ሰሚ በማጣት አሁን ግን ችግሩ ብሶበት በሰላም ችግሩን ለመግለፅ አደባባይ የወጣ ነዋሪ በጥይት እየተመታና እየቆሰለ ነው ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡
በሰላማዊ ሰልፉ ዕለት የተፈጠረውን ነገር ባይናቸው እንዳዩ የተናገሩት የአይን እማኝ፤ ሰልፉ ሆን ተብሎ፣ አስተባባሪ ኖሮት የተጠራ ሳይሆን ሰው ውሃ ልማት በር ላይ ሄዶ የሚያናግረው ሲያጣ ቁጥሩ እየጨመረ መጥቶ፣ ወደ ሰላማዊ ሰልፍ መቀየሩን አስታውሰው፤ ምንም ሌላ አላማ የሌለውና፣ ህዝቡ ከውሃ መቅጃ ጄሪካን ውጪ የያዘው ነገር እንዳልነበረ ጠቁመዋል።
ይህን የተመለከቱት የከተማው  የፀጥታ ዘርፍ ሀላፊና የልዩ ሀይል ሀላፊው በህዝቡና በፀጥታ ሰራዊቱ መካከል በመቆም “እናንተ ኮሚቴ መርጣችሁ ስጡንና ወደየቤታችሁ ግቡ፤ እኛ ከመረጣችኋቸው ኮሚቴዎች ጋር ተነጋግረን ለችግራችሁ አፋጣኝ መፍትሄ እንሰጣለን “በማለት ህዝቡን ለመበተን ቢሞክሩም፣ ህዝቡ ደግሞ “እስከዛሬ ኮሚቴ እየመረጥን እየላክን ብንቆይም እነዚያ ኮሚቴዎች በሚያስፈራሯቸው አካላት እየፈሩና እየተደለሉ የህዝብን ጥያቄ እየረሱ ለዚህ ችግር በቅተናል፤ እኛ የምንፈልገው የሚመለከታቸው የዞኑ አስተዳዳሪ፣ የውሃ ልማት ሃላፊውም ሆነ ከንቲባው እዚህ መጥተው፣ በዚህ በዚህ ቀን ችግራችሁ ይፈታል፤ በዚህ ችግር ምክንያት ነው እስካሁን የተቸገራችሁት ብለው እንዲያስረዱን ነው” ሲሉ መግለጻቸውን ነው የአይን እማኙ የተናገሩት።
ከዚያ በኋላ ወደ ቤት ግቡ አንገባም በሚል ጭቅጭቅ፣ “ውሃ እንፈልጋለን፣ ውሃ ተጠምተናል፣ ሃላፊዎቹ ቀርበው ምላሽ ይስጡን” በሚል ህዝቡ ድምፁን ሲያሰማ የከተማው ጻጥታ ዘርፍ ሃላፊና የልዩ ሃይል አዛዡ ወደ ህዝቡ አስለቃሽ ጭስና መሳሪያ እንዲተኮስ ትዕዛዝ  መተላለፉን በቦታው ሆነው መስማታቸውንና ማየታቸውን የአይን እማኙ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል።
ተኩሱን ተከትሎም፤ ግንባራቸውን፣ ደረታቸውን፣ ሆዳቸውን ተመትተው የሞቱ፣ አጥንታቸው የተሰበረና የተጎዱ ሰዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ነዋሪው፤ ከሞቱት 6 ሰዎች አራቱን እንደሚያውቋቸው ተናግረዋል።
ሆስፒታል ውስጥ አንድ አስጊ ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው እንዳለ፣ አንዱ በቀዶ ህክምና ጥይት እንደወጣለት፣ የአጥንት ስብራት ደርሶባቸው በህክምና ላይ ያሉና ታክመው የተመለሱ መኖራቸውንም አክለው ገልፀዋል- እማኙ።
“ከጉራጌ  ክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሰልፎች ተደረጉ ቢሆንም፤ አሁን የተከሰተው ግን ከቀድሞው ጋር ፈጽሞ እንደማይገናኝ ነው የአይን እማኙ ያስረዱት።
ወደ ወልቂጤ ሪፈራል ሆስፒታል ደውለን ከሀኪሞች እንዳረጋገጥነው ከሆነ፤ ረቡዕ የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም በተከሰተው በዚሁ ግጭት ወደ ሆስፒታሉ 17 ተጎጂዎች  ገብተው የነበረ ሲሆን፣ ሁለቱ ወጣቶች በእጅጉ ተጎድተው ሆስፒታል ሲደርሱ ወዲያው ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል። “ከ17ቱ መካከል 3ቱ በጠና ታመዋል” ያሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሆስፒታሉ ሃኪም፤ አንዱ ዕድሜው ወደ 60 የሚጠጋና መንገደኛ የነበረ ሲሆን ጭንቅላቱን በልዩ ሃይል ተመትቶ፤ ግማሹ የፊቱ ክፍል፣ ጥርሱና የመተንፈሻ አካሉ በእጅጉ መጎዳቱንና ብዙ ደም የፈሰሰው መሆኑን አስረድተዋል። “ሌላው ወጣት ደግሞ ደረቱ ላይ ተመትቶ መተንፈስ ሁሉ የከበደውና በኦክስጅን ሀይል ያለ ሲሆን ደም በብዛት ፈስሶት አስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛል” ያሉት የህክምና ባለሙያው፤ ሌላው ወጣት ሆዱ ላይ ተመትቶ በርካታ ደም የፈሰሰው መሆኑንና የህክምና ክትትል እየተደረገለት እንደሚገኝ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል።
“እንዴት አገርንና ህዝብን ለመጠበቅ የሰለጠነ ዘመናዊ የጸጥታ ሃይል፣ በሰለጠነ ዘመን ወንድሞቹ ላይ አልሞ ይተኩሳል” ያሉት ሃኪሙ፤ “ወደ ሆስፒታል የመጡት ተጎጂዎች በሙሉ ግንባራቸውን፣ ሆዳቸውን፣ ደረታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ሌሎች የአጥንት ክፍሎቻቸውን በኢላማ የተመቱ ናቸው። ይህ በጣም አሳዝኖኛል” ብለዋል።
እንደ ሃኪሙ ገለጻም፤ በጠና ከታመሙት ውጪ ያሉት 12ቱ ታካሚዎች፤ ቀዶ ጥገና የተደረገላቸውም በተለያየ መልኩ እየታከሙና የጤና መሻሻል እያሳዩ ነው።
“ከሆስፒታላችን ውጪ ሦስት ሰዎች በቦታው ላይ መሞታቸውን አውቃለሁ። አንዱ ከወላይታ፣ አንዱ ከጎንደር ለስራ የመጡ ወጣቶች  ሲሆኑ አንደኛው የከተማው ነዋሪ ነው” ያሉት የህክምና ባለሙያው፤ በተጨባጭ አምስት ሰዎች መሞታቸውን እንደሚያውቁና ገና ቤተሰባቸው ያልተገኙ፣ በደንብ ያልታወቁ ሟቾች ሊኖሩ እንደሚችሉ ግምታቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል፤ በከተማው በሚገኙ ሁለት የጤና ጣቢያዎች እንደዚሁ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ተጎጂዎች እንዳሉና ጤና ጣቢያዎቹ ማከም በሚችሉት ደረጃ የሚሰፋውን ሰፍተው የሚፈስ ደም አስቁመው እያከሟቸው ያሉ ተጎጂዎችም እንዳሉ፣ ሃኪሙ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል።
የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ አሰፋና የከተማው የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ትዕግስቱ ፉጂን በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን ደጋግመን በእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ምላሽ ባለማግኘታችን ሃሳባቸውን ማካተት አልቻልንም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትላንት ባወጣው መግለጫ፤ የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በውሃ ችግር ምክንያት መንግስት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ለማቅረብ ሰልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ በፀጥታ ሃይሎች በተወሰደ የሃይል እርምጃ፤ በነዋሪዎች ላይ ሞትና የአካል ጉዳት መድረሱን ጠቁሞ፤ የአይን እማኞችን፣ ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችንና የጤና ባለሙያዎችን በማነጋገር ባሰባሰበው መረጃና ማስረጃ፣ ሶስት ሰዎች ጭንቅላታቸውንና ደረታቸውን በጥይት ተመትተው መገደላቸውን ማረጋገጡን ያመለከተ ሲሆን፤ ቢያንስ ከ30 ሰዎች በላይ የተለያየ መጠን ያለው የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፤ የተወሰደው የሃይል እርምጃ ከነገሩ መነሻና ሁኔታ አንጻር ሲታይ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ገልጸው፣ “አንገብጋቢ በሆነው የውሃ አቅርቦት ጥያቄ ሰልፍ ወጥተው ድንጋይ በወረወሩና መንገድ በዘጉ ሰዎች ላይ ህይወት የሚያጠፋ መሳሪያ ተጠቅሞና ጥይት ተኩሶ ነዋሪዎችን መግደል ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እርምጃ ነው” ብለዋል።
አክለውም፤ መንግስት አስቸኳይ ማጣራት አድርጎ በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥና ለተጎጂዎች  ተገቢውን ካሳ ሊከፍል እንደሚገባ አሳስበዋል።  ለወደፊትም ተመሳሳይ የመብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ለጸጥታ ሀይሎች ግልጽ አመራር እንዲተላለፍ አሳስበዋል-ኮሚሽነሩ።

Read 2681 times